Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ኣሃዳውያን ፖለቲከኞች ሆይ! ፕሮፌሰር መሳይ ከበደን ወይ ደግፏቸው ወይ ኣውግዟቸው! (ቦሩ በራቃ)

$
0
0

 

mesay

ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ

የማከብራቸው ምሁር ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ከኣንድ ሳምንት ገደማ በፊት በእንሊዝኛ Then and Now: A Rejoinder to my Critics በሚል ርእስ ለንባብ ያበቁትን ፅሁፍ በተመስጦ ነበር ያነበብኩት። በርግጥ ቀደም ሲል ፕሮፌሰሩ ሲያስነብቡን ለቆዩት በርካታ ፅሁፎች ኣልፎ ኣልፎ እንግዳ ባልሆንም ይህኛው ግን ከሁሉም የተለየ ሆኖ ኣገኘሁት። እናም ወዲያው ኣንድ ነገር ልልበት ቸኩዬ ነበር። ሆኖም ሌላ ሃሳብ ድንገት መጣብኝና እጄን ለጊዜው ገታሁት። ይህን የፕሮፌሰር መሳይ ከበደን ፅሁፍ ያነበቡ በተለይም የኣሃዳዊነት ፖለቲካ ባለ ራእይ ምሁራን የሚያንጸባርቁትን ስሜት ለመገንዘብ ቅድሚያ መስጠቱን መረጥሁኝ። ለወትሮው ኣንድ ኮሽታ በተሰማ ማግስት ኣቡዋራ በማስነሳት የሚታወቀው የኣሃዳውያኑ ፖለቲከኛ ጎራ በዚህ ላይ እስካሁን የድጋፍም ሆነ የውግዘት ድምፅ ኣለማሰማቱ ሳይገርመኝ ኣልቀረም።

በፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ፅሁፍ ውስጥ ገና ከጅምሩ ትኩረቴን የሳበው የሚከተለው ኣንቀፅ ነው።

The most important complaint of the Oromo is that the Ethiopian discourse has always marginalized their contribution and identity in favor of a unilateral assimilation that favored Amhara and Tigreans. The demand that Oromo protesters turn their issues into a national or Ethiopian cause seems to repeat the past practice. Following the inescapable reality of the political fragmentation of the country, the Oromo rose up for their own cause, sacrificed their life, and now they are told that they should transfer their heroic deeds to the larger Ethiopian entity even though that entity remained aloof!

በግርድፉ ሲተረጎም – ዋናው የኦሮሞዎች ቅሬታ ወይም እሮሮ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ሁልጊዜም የነርሱን ኣስተዋፅኦና ማንነት ወደ ዳር በመግፋት ለኣማራውና ለትግሬው ውህድ ማንነቶች ቦታ የሚሰጥ መሆኑ ነው። የኦሮሞ ተቃውሞ ኣራማጆች ጉዳያቸውን ከኦሮሞ ኣጀንዳ ወደ ኢትዮጵያዊ ወይም ብሄራዊ ኣጀንዳ እንዲቀይሩ መጠየቅ ያለፈውን ልምድ መድገም ነው የሚመስለው። ከማይካደው የኣገሪቷ የፖለቲካ መሰነጣጠቅ እውነታ ተከትሎ ኦሮሞዎች ለራሳቸው ኣላማ ተነስተዋል። ህይወታቸውን ለዚህ ኣላማ ገብረዋል። ኣሁን ደግሞ ይህንን በጀግንነት ተነስተው መስዋእትነት የከፈሉለትን ኣላማ በዚህ ህዝባዊ ንቅናቄ ውስጥ ሚና ላላበረከተውና ዝምታን ለመረጠው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ስብስብ ኣሳልፈው እንዲሰጡ እየተጠየቁ ነው።

ከኣሃዳዊነት ፖለቲካ ደጋፊዎች መካከል ኣንዱ ኣንደነበሩ የሚታወቁት ፕሮፌሰር መሳይ በተባ ብእራቸው ይህንን ሃቅ መመስከራቸው ያስመሰግናቸዋል። ሌሎቹ የዚህ ጎራ ፖለቲከኞች ብሄሮችን ኣንደ ብሄር መጥራት እንኩዋ ተጠይፈው በፖለቲካ ግራ መጋባት ደዌ በሚሰቃዩበት በዚህ ወቅት ፕሮፌሰር መሳይ ጭራሽ ለኦሮሞ ህዝብ ትግል ያላቸውን ኣክብሮትና ህዝቡ እየከፈለ ላለው መራራ መስዋእትነት የሰጡትን ተገቢ ዋጋና ያመኑበትን የባለቤትነት መብት ሳላደንቅ ኣላልፍም። በርግጥ ይህንን ኣቁዋማቸውን የማይደግፉና በየጉራንጉሩ የሚያጉረመርሙ ኣያሌ ወገኖች እንዳሉም ኣላጡትም። እናም ለነዚህ ወገኖች እንዲህ ይሏቸዋል።

You join the fight and only then can you make the issue of unity a common cause. Those who simply watch cannot present conditions to people being beaten, killed, and imprisoned. To make your support conditional is to forget that you are also chained, beaten, killed, and imprisoned by the same oppressor.

ግርድፍ ትርጉሙ – ትግሉን ስትቀላቀል ነው የኣንድነቱን ጉዳይ የጋራ ኣላማ ማድረግ የምትችለው። ከዳር ቆመው የሚመለከቱት በትግሉ ውስጥ እየተገረፉ፣ እየተገደሉና እየታሰሩ ለሚገኙት ወገኖች ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ኣይችሉም። ድጋፍህን በቅድመ ሁኔታ መወሰን ማለት ኣንተ ራስህ ተመሳሳይ በሆነ ጨቁዋኝ ስርኣት ስር በሰንሰለት እየተጠፈርክ፣ እየተገረፍክ፣ እየተገደልክና እየታሰርክ መሆኑን መዘንጋት ነው።

ዶክተር መሳይ በመጨረሻው የፅሁፋቸው ኣንቀፅ ያሰፈሩትን ተያያዥ ሃሳብ ኣስከትዬ ካስታወስኩ በሁዋላ ወደተነሳሁለት ፍሬ ጉዳይ ኣመራለሁ።

To present condition is also to endorse the divided-and-rule police of the TPLF. Indeed, in being bystanders in this trying and crucial moment for the Oromo, what message are we sending to them? Are we not telling them that their cause and their atrocious mistreatment are not of our concern? How would they feel Ethiopian when those who claim to be Ethiopian turn their back on them? This is to say that the Oromo uprising gives us the unique opportunity both to defeat the TPLF and forge a new unity by our struggle against the common oppressor.

ሲተረጎም – ድጋፍ ለመስጠት ቅድመ ሁኔታ የምታስቀምጥ ከሆነ የህወሃትን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ከመደገፍ ተለይቶ ኣይታይም። በዚህ ለኦሮሞው ህዝብ ወሳኝ በሆነ ወቅት ከዳር ቆሞ መመልከት ለኦሮሞዎች ምን ኣይነት መልእክት ማስተላለፍ ነው? የነርሱ የትግል ኣላማና እየደረሰባቸው ያለው ሰቆቃ የኛ ጉዳይ ኣለመሆኑን እየነገርናቸው ይሆን? ኢትዮጵያውያን ነን ባይ ወገኖች ጀርባቸውን ሲሰጧቸው ኦሮሞዎቹ እንዴት ብለው ነው ኢትዮጵያዊነት ሊሰማቸው የሚችለው? ይህ የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞ የወያኔን ስርኣት ለማሸነፍም ሆነ የጋራችን ጨቁዋኝ ጠላት ላይ ትግሉን ኣፋፍመን ኣዲስ ኣንድነት እንድንገነባ ልዩ እድል ይሰጠናል ለማለት ያህል ነው።

 

ይህን ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የሚሉትን ‘ልዩ እድል’ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ዋጋ የሰጡት ኣይመስልም። የፖለቲካ መሪዎች የሚባሉት የጉዳዩ ባለድርሻ ኣካላት ህዝብ ሰብስበው ስለ ኦሮሞ ፖለቲካ ኣደረጃጀት የውስጥ ጉዳይ ሲያነሱና ሲጥሉ፣ የብሄር ማንነትን ሲያወግዙና ለዴሞክራሲያዊ ስርኣት ግንባታ በእንቅፋትነት ሲፈርጁት እንጂ እኒህ ምሁር በመከሩት መልኩ ሌሎችን በመቀስቀስ ከኦሮሞ ጎን ኣሰልፈው ባማታገል በጋራው ጠላት ላይ በሚያመረቃ ደረጃ ሲያተኩሩ ኣላየናቸውም። ለትግል ትብብር ቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጡ ነው ያየናቸው። የኦሮሞውን የማንነት ፖለቲካ ኣቁዋም ደግፈውና ኣክብረው ሌላውም በራሱ ማንነት ወደ ትግሉ ጎራ እንዲቀላቀል ጥሪ ሲያቀርቡ ኣልሰማናቸውም። ይልቅ የኦሮሞዎቹን ብሄራዊ ኣደረጃጀትና የትግል ቁርጠኝነት ሌሎቹ ወገኖች በጥርጣሬና በስጋት እንዲመለከቱት የሚገፋፋ ኣይነት ቅስቀሳ ሲያደርጉ ስማናቸው።

 

እንደምናውቀው ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ድርጅታቸው በጠራው ስብሰባ ላይ ሲናገሩ የኦሮምያውን ተቃውሞ በተመለከተ ያነሷቸው ኣንዳንድ ፍሬ ጉዳዮች በኦሮሞ ብሄርተኞች ዘንድ ቁጣን ቀስቅሰዋል። እኔ ራሴ በጉዳዩ ላይ በወቅቱ ኣጠር ያለ ፅሁፍ ኣቅርቤ ነበር። የፕሮፈሰር ብርሃኑን ንግግር በማስተጋባትም ሆነ በመቃወም ብዙ የተጻፉ ነገሮችን ኣንብበያለሁ። በርግጥ የፕሮፌሰሩ ኣገላለፆች ቀደም ሲል ከሚታወቁት የኣሃዳዊ ፖለቲካ ኣቁዋሞች የተለዩ ኣልነበሩም። የተለየ ነገር የጠበኩት ምናልባት ኦሮምያ ውስጥ የተቀሰቀሰውንና በመሰረቱ፣ በስፋቱም ሆነ በሂደቱ ቀጣይነት ልዩ ስፍራ የሚሰጠውን የኦሮሞ ህዝብ ተቃውሞን ተከትሎ የፖለቲካ ኣመለካከትን የማሻሻል ኣጋጣሚ ይፈጥር ይሆናል የሚል ነበር።

 

እነ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ዘንድ ጠብቄ ያጣሁትን ያን የኣመለካከት ማሻሻያ ኣጋጣሚ ፕሮፌስር መሳይ ከበደ ዘንድ ኣገኘሁት። ኣሃዳዊያን ፖለቲከኞች ከገቡበት የግራ መጋባት ማጥ እንዲወጡና ነጭን ነጭ ጥቁርን ጥቁር ብለው ኣንዲመሰክሩ ፕሮፌሰር መሳይ ምክር ለግሰዋል። ምክራቸውን ተከትሎ ድጋፍ ወይም ውግዘት መጠበቅ ተፈጥሮኣዊ ነው። ነገር ግን በጎራው ዘንድ እየታዘብን ያለነው ፀጥ ረጭ ያለ ዝምታ ነው። ፕሮፌሰር መሳይ ዝምታውን ሰብረዋል። ቢያንስ የኦሮምያው ተቃውሞ የኦሮሞ ተቃውሞ ተብሎ መጠራቱ ፍትሃዊነት እንዳለው ኣብራርተዋል። የኦሮሞውን ተቃውሞ ወደ ኢትዮጵያ ተቃውሞ ለማሸጋገር እንደ ኦሮሞዎቹ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ነን የሚሉት ወገኖች በቁርጠኝነት መነቃነቅ እንደሚጠበቅባቸውና ያንን ሳያደርጉ የኦሮሞዎችን መስዋእትነት ለመንጠቅ መከጀል የታሪክ ዝርፊያ መሆኑን ኣስምረውበታል።

 

ይህን ፅሁፍ ያነበቡ የኦሮሞ ምሁራንም ለፕሮፌሰር መሳይ ከበደ ኣጨብጭበዋል። በሌላኛው ጫፍ የቆሙት ደግሞ ዝምታን መርጠዋል። ነገር ግን በዚህ ወሳኝ ወቅት ዝምታ መልስ ኣይሆንም። ኣሃዳዊያን ፖለቲከኞች ፕሮፌሰር መሳይ ከበደን ለመደገፍ ወይም ለማውገዝ ድምጻቸውን መሳል እንዴት ተሳናቸው? ‘ኣገር እናድናለን’ እየተባለ እንደዚህ ያለው ምሁራዊ ኣንቂ ደወል ሲደወል ሰምተው እንዳልሰሙ መሆን ምን ሊባል ነው? ስጋት ወይስ ግድየለሽነት? ሃፍረት ወይስ ግራ መጋባት? ፖለቲከኞች ግራ ተጋብተው ህብረተሰባቸውን ግራ ሲያጋቡ ኣደገኛ ውጤት ያስከትላል። በርግጥ ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ የፖለቲካ ድርጅት መሪ ኣይደሉም። ኣንጋፋ ምሁር እንደመሆናቸው መጠን ግን በየጊዜው ብቅ እያሉ የሚያቀርቧቸው ሃሳቦች የፖለቲካ ግንዛቤን ከማዳበር ኣኩዋያ ትልቅ ግምት ይሰጣቸዋል።

 

ፕሮፌሰሩ ባነሷቸው ወሳኝ ፍሬ ጉዳዮች ላይ ሃሳብ ከመለዋወጥ ይልቅ ኦሮምያ የኦሮሞ ነች ኣይደለችም በሚለው ላይ በዚህ ወቅት ኣላስፈላጊ ሰጣገባ መግጠም የፖለቲካ ማሙሽነት ይመስለኛል። ይህ ደግሞ የሚመነጨው የብሄር ማንነት ፖለቲካን በወያኔ ኣመጣሽ በሽታነት ፈርጀው በጭፍን ጥላቻ ለመመልከት ከሚደረገው ጥረት ነው። ኣሃዳውያኑ ፖለቲከኞች ይህን ኣውራ ስህተት ማረም ዛሬም ድረስ ኣልተቻላቸውም። ወያኔ የብሄር ማንነት ፖለቲካን ከመሬት ኣንስቶ ጠፍጥፎ ኣልሰራውም። የብሄር ማንነትን እንደ መሳሪያ ተጠቅሞ ግን ስልጣን ላይ ተደላድሏል። በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲነት ተጠቅሞበታል። ወያኔ መወገዝ ያለበት የብሄሮቹን የስልጣን ባለቤትነት መብት ጨምድዶ በራሱ እጅ በማስገባቱና የራሱን ብሄር የበላይነት ኣረጋግጦ በሌሎቹ ላይ ኣስነዋሪ ዘረፋ በማካሄዱ እንጂ ኦሮሞውን ኦሮሞ፣ ኣማራውን ኣማራ፣ ጉራጌውን ጉራጌ ብሎ ስለጠራና የኣሰፋፈር ጂኦግራፊያቸውን ኣምኖ ስለተቀበለ መሆን የለበትም።

 

ኣሃዳዊያን ፖለቲከኞች 25 ኣመት ሙሉ ይህንን ሃቅ መዋጥ ተስኖኣቸዋል። ይህን ባለመቀበላቸውም በብሄር ማንነት ከሚያምኑት የፖለቲካ ሃይሎች በተለይም ከኦሮሞዎች ጋር ተቀራርቦ የትግል ህብረት መፍጠር ኣልተቻለም። በቃላት ደረጃ ብቻ ስለ ትግል ህብረት መስበክ የትም ኣያደርስም ኣላደረሰምም። ይህንን መሰረታዊ የጋራ ግንዛቤ መፍጠር ለሁሉም ድል መሰረት ነው። ለነገው ሰላምና ኣብሮኣዊነትም ዋስትና ይሰጣል። ይህ ደግሞ የሚጀምረው እነ ፕሮፌሰር መሳይ በከፈቱት መስኮት ኣሻግሮ መመልከት ሲቻል ብቻ ነው። ለዛም ነው ኣሃዳዊያኑ ፖለቲከኞች የፕሮፌሰሩን መሪ ሃሳቦች ወይ በመደገፍ ኣልያም በማውገዝ ኣቁዋማቸውን ግልፅ እንዲያደርጉ የምጠይቀው።

 

 

ለኣስተያየትዎ:

Gulummaa75@gmail.com

 

 

The post ኣሃዳውያን ፖለቲከኞች ሆይ! ፕሮፌሰር መሳይ ከበደን ወይ ደግፏቸው ወይ ኣውግዟቸው! (ቦሩ በራቃ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>