ከአዳማ ከተማ ወደ ወንጂ በሚወስደው መንገድ ላይ በሚገኘው ወታደራዊ የልብስ ስፌት ፋብሪካ ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ በፋብሪካው ላይ ከፍተኛ የንብረት ጉዳት መድረሱን የዘገበው ራድዮው በ18 ሚሊዮን ብር ወጪ በቅርቡ የተገነባው ፋብሪካው የተለያዩ ወታደራዊ ዩኒፎርሞችን ለሀገር ውስጥና ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ሲሆን የደረሰው አደጋ መንስኤ ሊታወቅ አልቻለም ብሏል።
እንደ ራድዮው ዘገባ ከሆነ በፋብሪካው ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ለማጥፋት ከአዳማ ከተማ የእሳት ማጥፊያ ባለመኖሩ ደብረ ዘይት ከሚገኘው አየር ሀይል እሳት ማጥፊያ እስከሚደርስ ድረስ የተነሳውን እሳት ማጥፋት አለመቻሉን የአይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ሰዓት ያህል በቆየው የእሳት አደጋ ግምታቸው ከፍተኛ የሆነ ማሽኖች ላይ ጉዳት እንደደረሰ የታወቀ ሲሆን ከአራት ቀናት በፊት መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የገዛቸው ማሽኖች በፋብሪካው ገብተው እንደነበረ ታውቋል ሲል ኢሳት ራድዮ ዘገባውን አጠናቋል።
ከአደጋው በስተጀርባ ሊደበቅ የተፈለገ የሙስና ወንጀል ይኖር ይሆን?