በልጅነቱ ከቤተሰቡ ተደብቆ ጀብሎ ሆኖ ሰርቷል፤ ሲጋራ እና ማስቲካ ሻጭ ማለት ነው፡፡ በሰፈሩ የታወቀ የብይ ተጨዋችም ነበር፡፡ ‹‹አሁንም እንደ ከረንቦላ ቆሞ መጫወት ቢቻል ብይ ብጫወት ደስ ይለኛል ነበር›› ባይ ነው፡፡ ዛሬም ድረስ የልብስ ስፌት መኪና ‹‹ሾፌር›› የሆኑት አባቱ ሰይፉ ማሩ ጉንጆ አጠገብ ቁጭ ብሎ እየተከፈለው ልብስ ይዘመዝም ነበር፡፡ [አቶ ሰይፉ ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ እና ከዶ/ር ብርሃኑ ጋር በአንድ ቡድን ውስጥ አብረው ኳስ ተጫውተዋል፡፡] ጨዋታ አዋቂ እና ታታሪዋ እናቱ አይናለም ሲማ የእሱም ሆነ የቤተሰቡ ተምሳሌት የሆኑ ዛሬ እሱ ለደረሰበት ደረጃ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ጠንካራ ሴት ናቸው፡፡ መፍጠር ይሻ የነበረውን የቢዝነስ ኢምፓየር የመንግሥት ፖሊሲዎች እና የአፈጻፀም ችግሮች ተግዳሮት ሲሆኑበት ፖለቲከኛ በመሆን ለመታገል በፓርቲ ፖለቲካ ስር ተጠቃለለ፤ የቅንጅት ውህድ አንድ አካል በነበረው ኢዴሊ፡፡ ከምርጫ 97 በኋላ በተፈጠረው ጦስ ቃሊቲ የተላኩት አመራሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ በተፈጠረው አንድነት ፓርቲ ውስጥ የፖለቲካ ትከሻው እየጎላ መጣ፡፡ ይህ ሰው በምርጫ 2002 ብቸኛው የመድረክ ዕጩ በመሆን ፓርላማ የሚገኘው አማራጭ ድምጽ አቶ ግርማ ሰይፉ ነው፡፡
ከጥላቻ ፖለቲካ የነጻው ግርማ ዛሬ (ሐምሌ 3/2005 ዓ.ም) ልደቱ ነው፤ 47 ዓመቱን ጭጭ ያደረገበት፡፡ ታዲያ ዛሬ ልደቱን የሚያከብረው ኬክ ቆርሶ ሳይሆን ‹‹የነጻነት ዋጋ ስንት ነው?›› የሚል ባለ 235 ገጽ መጽሐፉን በ10፡30 – 22 ማዞሪያ አካባቢ በሚገኘው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አዳራሽ በማስመረቅ ነው፡፡ በአምስት ክፍል፣ በ19 ምዕራፍ የተከፈለው ይህ መጽሐፍ ስለ ፖለቲካ አጀማመሩ፣ በኢዴሊ፣ በቅንጅትና በአንድት ስላሳለፈው የፖለቲካ ጉዞው የተመለከታቸውን መጻፍ አለባቸው ያላቸውን ጉዳዮች የዳሰሰበት ሲሆን እንዴት የምርጫ 2002 ክስተት እንደሆነም በስፋት የሚነግረን አለው፡፡ የግል ታሪኩም ተካቶበታል፡፡ [የግል ታሪኩን ለመሰብሰብ አብሬው በእናት እና አባቱ ቤት ተገኝቼ ከላይ የጠቀስኳቸውንም ሆነ ሌሎች አስገራሚ ሁኔታዎችን ማዳመጥ ችያለሁ፡፡] እንደነገረኝ ከሆነ ከሆነ አነጋጋሪ ሊሆኑ የሚችሉ፣ በድፍረት የተጻፉ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን መጽሐፉ ይዟል፡፡ ዋጋው 50.70 ብር ነው፡፡ ከነገ ጀምሮ ገበያ ላይ ይውላል፡፡ የምርቃቱ አካል ትሆኑ ዘንድ በአዳራሹ እንድትገኙ ግርማ ጋብዟችኋል፡፡ ፖለቲከኞቻችን መጽሐፍ እየጻፉ መሆናቸው በራሱ መልካም ነገር ነውና እናበረታታ፡፡
የሚገርመው በቅርቡ በለቀቅነው ‹‹ኢትዮጵያን ማን ይታደጋት?›› በሚለው መጽሐፋችን ላይ የውይይቱ አካል ካደረግናቸው ውስጥ በቀጣይ ጊዜያት ብዙዎቹን እንደ ግርማ ሁሉ በመጽሐፍ ታገኟቸዋላችሁ፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ መጽሐፍ ጀምረዋል፡፡ የሌ/ኮሎኔል ደበላ ዲንሳ ቤተሰቦች ደበላ ጀምረውት ሳይጨርሱት የሄዱትን መጽሐፍ ለማጠናቀቅ ተፍ ተፍ እያሉ ነው፡፡ የፕሮፍ ብዕር እንደምታውቁት አይሰንፍም፡፡ ሙሼ ሰሙ በቀጣዩ ዓመት አነጋጋሪ መጽሐፍ ይዞ እንደሚመጣ ነግሮኛል፡፡ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የአንድ ሲዝን የሥራ ዘመናቸው እንዳበቃ የመጀመሪያ ተግባራቸው መጽሐፍ መጻፍ ነው፡፡ ዶ/ር ወሮታው ሁሌም ለአዲስ ሥራ በተጠንቀቅ የቆሙ ሰው ናቸው፡፡ ሁለቱም የሃይማኖት ልሂቃን እየጻፉ ነው፡፡ አሁን ላይ ያለውን ሀሳባቸውን ባላውቅም ተመስገን ሁለተኛውን፣ ዳዊት የመጀመሪያውን መጽሐፋውን ጨረሱ ከተባለ ቆይቷል፡፡ ለሁሉም መልካሙን ተመኝቻለሁ፡፡