Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የእኛ “መንግስት” –ከተመስገን ደሳለኝ (ጋዜጠኛ)

$
0
0

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ

ከተመስገን ደሳለኝ
“በእያንዳንዱም መንግስት የሚያድሩ ብዙ ልዩ ልዩ ነገዶች ይኖሩ ይሆናል፡፡ ስለ ሆነ መንግስት አንዱን ነገድ አጥቅቶ ሌላውን ነገድ ለመጥቀም ሥራው አይደለም፡፡ አስተካክለን ካሰብን ዘንድ መንግስት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡ ጥረቱም ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ያልሆነ መንግስት ሊቆም አይችልም፡፡ ለአንዱ ነገድ ወይም ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት ለመንግስት የሚገባ ሥራው አይደለም”  ይህንን መግቢያ የወሰድኩት በልዑል የኢትዮጵያ መንግስት አልጋ ወራሽ ተፈሪመኮንን ማተሚያ ቤት የካቲት 1 ቀን 1917 ዓ.ም ከታተመው የነጋ ድራስ ገብረ ሕይወት ባይከዳኝ‹‹መንግስትና የሕዝብ አስተዳደር›› መፅሀፍ ነው፤ ዛሬም ያለንበትን ዘመን ይዋጃልና፤ በተለይ ስለ‹‹ነገድ›› የተጠቀሰውን አርቀን ሰቅለን፣ ‹‹ለጥቂት ሰዎች ብቻ ማድላት›› የምትለዋን ሀረግ በወጉ ካጤንናት ለጊዜያችን በልክ የተሰፋች መሆኗን ለመረዳት አስቸጋሪ አይደለም፡፡
እናም የስርዓቱን የአስተዳደር ዘይቤ ያለፍርሃት አደባባይ ካዋልነው የቀድሞ ገዥዎቻችን የተጓዙበትን ጎዳና እየተከተለ መሆኑን ለመተንተን የምሁራንን ጥናት መጠበቅ ግድ አይለም፤ ምክንያቱም ለዓመታት የተመለከትነው እውነታ የሚነግረን የአመራሩን እና በዙሪያው የሠፈሩ የጥቅም ተጋሪ ግለሰቦችን ብልፅግና ታሳቢ ያደረገ፣ ከታግሎ መጣል ህግ የተቀዳ፣ የራስ ሀገርንና የራስ ሕዝብን በምርኮ ያስገበረ ፖለቲካ መንበሩን ነው፤ ገብር፣ ገብር፣ ገብር…!!
ዛሬ መንገድ ዳር ረሀብ አዙሮ የጣለው ወንድምህ ስቃይ እንደ ጥላ የሚከተልህ፤ ህፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ በጠኔ ተሸንፈው መመልከቱ የሰርክ አሳዛኝ ክስተት የሆነብህ ከሰው ሰራሽ ችጋር፣ ከሰው ሰራሽ የቀዬ ፍንቀላ፣ ከሰው ሰራሽ እርዛት… የመነጨ መርገምት እንጂ የሰማይ ቁጣ አይምሰልህ፤ እመነኝ መለስም ሆነ ተተኪዎቹ ስኬት አድርገው የሚሰብኩትም ይህንን ነው፤ ‹ሀገር አቀናን!› የሚሉትም ይህንን ነው፤ ሰሞኑን የሚያሰለቹህ ተረኛ ምሁራንም ‹‹ትምህርትና ጤናን በተመለከተ መለስ ‹እልል› የሚያስብል ሥራ ሰርቷል›› የሚሉህ ጣራና ግድግዳ እየቆጠሩ ነው፤ ይህ አይነቱ መደዴ ሙገሳም ለፕሮፓጋንዳ የሚሆን ሪፖርት ለማዘጋጀት ከሚረዳ ቁጥር የዘለለ አበርክቶ አንደማይኖረው አትዘንጋ፡፡
እውነት እውነት እልሀለሁ፡- ይህ የሆነበት ብቸኛው ምክንያት መንግስት በስልጣን ላይ ስለሚቆይበትመንገድ ብቻ መጨነቅን ግዴታው በማድረጉ ነው፤ ይህንን ለመረዳትም እያገባደድን ባለው ክረምት የመንግስት ትኩረት በምን ላይ አንደሆነ የሚያሳይ ማስረጃን ጨርፌ ላሳይህ፡፡
ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- የእስልምና እምነት ተከታዮች መንግስት በሃይማኖታቸው ጣልቃ መግባቱን በመቃወም እና የታሰሩ ኮሚቴዎቻቸው እንዲፈቱ በመጠየቅ እያደረጉ ያለውን ትግል በሰላማዊ መንገድ አጠንክረው ሲቀጥሉ፤በተቃራኒው ‹‹ፀጥታ አስከባሪዎች›› አንዳንዴ በጥይት፣ አንዳንዴ በአስለቃሽ ጢስ፣ አንዳንዴ በማጋዝ…ምላሽ ሲሰጡ…
በርግጥ መንግስት ከኃይል እርምጃው በተጨማሪ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የሚገኙ ነዋሪዎችን (በምን አግባብቶ ወይም በምን አስፈራርቶ እንደሆነ ባይታወቅም) ወደ አደባባይ በማስወጣት መብት ጠያቂዎቹን ከ‹‹አክራሪ››ነት እና ‹‹ወሃቢዝም››ነት ጋር አያይዘው የውግዘት በረዶ እንዲያዘንቡባቸው እያደረገ ነው፡፡ ኢቲቪም ይህንን ኩነት እየተከታተለ ማራገቡን ቀጥሎበታል፤ ‹‹የቲፒ ከተማ ነዋሪዎች ‹አክራሪዎችን አወገዙ››፤ ‹‹በደቡብ ወሎ ኩታ በር ዞን አንድነት ፓርቲ ህገ-ወጥ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰልፍ ተካሄደ››፤ ‹‹የደሴ ከተማ ነዋሪዎች ‹የሼሁ ግድያ ድራማ አይደለም› አሉ፣ ‹የሼህ ኑሩ ኢልም ነው፣ የአሸባሪዎች ብር ነውም›ብለዋል››፤‹‹የመርሀቤቴ ነዋሪዎች ፅንፈኞችን በመቃወም የአቋም መግለጫ አወጡ››፤…
ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- አንድነት ፓርቲ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የ‹‹ፀረ-ሽብር ሕጉ›› እንዲሰረዝና የህሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ እና የአዳራሽ ስብሰባዎችን እያካሄደ ነው፤ መንግስትም አንዳንዴ የአፀፋ የድጋፍ ሰልፍ ሲያካሄድ፤አንዳንዴ የአዳራሽ ስብሰባዎች ከመካሄዳቸው አስቀድሞ ‹መጋኛ› ሲሆንባቸው፤ አንዳንዴም የአስተባባሪዎቹን መኪና ጎማ ሲያፈነዳ፤ አንዳንዴም አዳራሽ ከልክሎ ሲያደናቅፋቸው… መዋሉ ፋታ የነሳው ይመስላል፤ በወላይታ የተጠራውን የአዳራሽ ስብሰባም ‹በጠቅላይ ሚኒስትሩ የትውልድ ቦታ እንዴት ተደርጎ!›› ያሉ ካድሬዎች የአንድነት ሰዎችን አዋክበው ስብሰባውን አክሽፈዋል፤
ክረምቱእንዲህእየተገባደደነው፡-ገዥው ፓርቲ ‹የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አንደኛ ሙት ዓመት አከብራለሁ› በሚል መላ ኢትዮጵያን ችግኝ መትከያ፣ መላ ዜጎቿን ደግሞ ወደ አርሶ አደርነት በአስማት የቀየራቸው አስመስሏቸዋል፤ቴሊቪዥንና ራዲዮንም አስፈላጊነታቸው በየመንደሩ ችግኝ መተከሉን እየተከታተሉ መዘገብ ብቻ እስኪመስል ድረስ እንዲህ ሲሉ ጀምበር ወጥታ ትጠልቃለች፡- ‹‹የላይ አርማጮህ ነዋሪዎች ችግኝ ተከሉ››፣ ‹‹በመቀሌ ከተማ ‹ዘመቻ መለስ› በሚል የችግኝ ተከላ ተካሄደ››፣ ‹‹አቃቂ ኮረብታ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠር ችግኝ በኦሮሚያ ፌደራል ፖሊስ አባላት ተተከለ፤ ቦታውም ‹መለስዜናዊ ኮረብታ› ተብሎ ተሰይሟል››፣ ‹‹በምዕራብ ሀረርጌ አስራ ሰባት ሚሊዮን፣ በወልበራ አስራ አራት ሚሊዮን ችግኝተ ተክሏል››፣ ‹‹በመንዝ ላሎ ወረዳ ተቆጥሮ የማያልቅ ችግኝ ተከላ ተደርጓል››፣ ‹‹የብአዴን አመራርና ካድሬ በባህር ዳር ከተማ በቢሊዮን የሚቆጠር ችግኝ ተከሉ፤ በፕሮግራሙ ላይ ጓድ አዲሱ ለገሰ ‹ችግኝ የምንተክለው አገሪቱ በአረንጓዴው ልማት በአለማችን ማግኘት የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ ለማድረግ ነው› ሲል፣  ጓድ በረከት ስምዖን ደግሞ ‹ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በአለማችን በአንድ ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ችግኝ እየተከሉ ያሉባት ብቸኛ ሀገር ናት› ብሏል››፤‹‹ዝክረ መለስ 1ኛ ዓመት መታሰቢያን ምክንያት በማድረግ ከሐምሌ አስራ አምስት ቀን ጀምሮ ሁሉም ቀበሌዎች በስሙ ‹ፓርክ› ሰይመው ችግኝ ተከላ እያካሄዱ›› መሆኑን ደግሞ የባህር ዳር ከተማ ከንቲባ መግለፁን የአማራ ክልል ብዙሃን መገናኛ ዘግቧል፤ ‹‹በወልቂጤ ከተማ በተደረገው ችግኝ ተከላ ላይም አንዲት ወጣት ‹መለስ ለሴቶች የተለየ አመለካከት ነበረው›› ማለቷም በዘገባው ተጠቅሷል፤ …ማን ነበር የመለስ ራዕይ ‹ችግኝ መትከል ነው› ያለው? …ኢህአዴግ ይሆን?
ከዚሁ ጎን ለጎን (አሁንም ሙት ዓመቱን ለማሰብ) በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች የእግር ጉዞ ተደርጓል፣ የሻማ ማብራት ስነ-ስርዓትም ተካሄዷል፤መነሻውን መቀሌ፣ መድረሻውን አዲስ አበባ ያደረገ ‹‹የመለስ ቱር አረንጓዴ ልማት›› የብስክሌት ውድድርም ሊጠናቀቅ ገና አንድ ሳምንት ይቀረዋል፤ በብሄራዊና ሀይማኖታዊ በዓላት ቀንለሃያ አንድ ጊዜ ይሰማ የነበረው የመድፍ ድምፅም፣ የመለስን አንደኛ ሙት ዓመት ለማብሰር ተተኩሷል፤ …በግድ አልቅሱ፣ በግድ ተዝካር አውጡ፣ በግድ ችግኝ ትከሉ፣ በግድ ተወያዩ፣ በግድ አደባባይ ውጡ፣ በግድ የፎቶ ግራፍ ኤግዚቢሽን ጎብኙ፣ በግድ..  ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ደሳለኝ እና የትምህርት ሚኒስትሩ ሽፈራው ሽጉጤ ከአንድ ሺህ ሰባት መቶ በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርስቲ ከፍተኛ መምህራን ‹የአቅም ግንባታ ስልጠና› እየሰጡ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሁራኖቹን ማሰልጠን ያስፈለገበት ምክንያት ‹‹ብቃት ያለው ምርጥ የተማረ ኃይል ለማፍራት››መሆኑን ቢነግርህ አይግረምህ፤ ይህ ኢትዮጵያ ነውና የዐዋቂነት ማረጋገጫው መማር፣ ማንበብ፣ መመራመር… አይደለም፣ የፖለቲካውን ኃይል መያዝ እንጂ፤ ‹ስልጣን ላለው ሁሉምሚስጥረ-ጥበብይገለፅለታል› እንዲል አብዮታዊ ዲሞክራሲ መለስ ዜናዊም በሁሉም መስክ ‹አስተማሪ› ነበር፤ የህግ ባለሙያዎችን ሰብስቦ የሀገሪቱን ወንጀለኛ መቅጫ ህግ ትርጓሜ ሲተነትን ደጋግመህ ሰምተኸዋል፤ በቀጣዩ ቀን ደግሞ ለግብርና ባለሙያዎች ከውሃ ማቆር እስከ በላብራቶሪ የሚዳቀል ምርጥ ዘር ድረስ ባሉጉዳዮችዙሪያ የሁለት ቀን ማብራሪያ መስጠቱን ታስታውሳለህ፤ እመነኝ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትርም ይህንኑ ነው እያደረገ ያለው፤  የሆነ ሆኖ ኃ/ማርያም ለምሁራኖች ከሙያቸው ጋር ስለተያያዙ ጉዳዮች ጭምር በሰጣቸው ስልጠና ላይ እንዲህ የሚል ጥያቄ ቀርቦለት ነበር ‹‹የኢንዱስትሪዎች በበቂ ሁኔታ አለመኖሩ፣ በክፍል ውስጥ የምናስተምረውን ንድፈ ሃሳብ በተግባር ለማሳየት እንቅፋት ሆኖብናል››፤ በርግጥጠቅላይ ሚንስትሩ‹‹መፍትሄ››ያለውን የተናገረው ብዙም ሳይጨነቅ ‹‹እኔ ኢንዱስትሪን ‹ዲፋይን› የማደርገው ግብርናም ኢንዱስትሪ ነው ብዬ ነው››በማለት ነበር፤…ግና!ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል በተጨባጭ አላብራራም፡፡ለምሳሌ ህክምና የሚያጠና ተማሪ በምን መልኩ በሞፈርና ቀንበር የተግባር ልምምድ ማድረግ እንደሚችል፤ወይም ፖለቲካ ሳይንስ የሚያጠና ተማሪ የተግባር ልምምዱን በግብርና ኢንዱስትሪ እንዴት ሊወጣው እንደሚችል? ማለቴ ነው፡፡
ለዓመታት በርካታ ምሁራን ብቃት አልባ ተማሪዎች እንደ ሰማይ ከዋክብት የመብዛታቸው መንስኤን ከትምህርት ፖለሲው ጋር የሚያነፃፅሩበትን ሀቲት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ ባገኘው የሀገር መሪነት ስልጣን ገልብጦ በዩንቨርስቲ ቆይታው መምህራኖቹ የነበሩትንም ጭምር ‹‹አቅም አንሷችኋልና-እገነባችኋለሁ›› ሲል ከመስማት የከፋ እንደ ሀገር ክሽፈት የለም (በነገራችን ላይ ከወራት በፊት ለኃይለማርያም ደሳለኝ፣ በረከት ስምዖን፣ ቴውድሮስ አዳህኖም፣ ሶፍያን አህመድ በአጠቃላይ ሁሉም የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት አንድ ህንዳዊ ፕሮፌሰር በኢህአዴግ ጽ/ቤት ‹‹ልማታዊ መንግስት›› እንዴት ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ሲተነትንላቸው፣ እነርሱም ደብተርና እስክርቢቶ ይዘው በንቃት ሲከታተሉ የቴሌቪዥ ዋና ዜና ሆኖ የቀረበበትን ምክንያት ዛሬም ድረስ ሊገለፅልኝ አልቻለም፤ በተለይም ፕሮፈሰር እንድርያስ እሸቴ ‹‹በቃሉ የፀና…›› በሚል ርዕስ መለስን አስመልክቶ በተዘጋጀ ዶክመንተሪ ፊልም ላይ ‹‹በዓለማችን ለመጀመሪያ ጊዜ ልማታዊ ስርዓተ መንግስት ‹ዴሞክራሲያዊ ሊሆን ይችላል፤ መሆንም አለበት› ብሎ በአደባባይ የተከራከረው እኔ እስከማውቀው ድረስ መለስ ነበር›› ማለቱን፣ ተተኪዎቹ ፍልስፍናውን ገና እየተማሩት ከመሆኑ አንፃር ስናየውሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ጉዞው ወዴት ነው? ያስብላል፡፡ …ከቶስ በተማሪ ፖለቲከኛ የሚተዳደር ሕዝብ ከኢትዮጵያ በቀር ወዴት ይኖራል?)

ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- የህዳሴውን ግድብ ከዳር ለማድረስ በቂ ገንዘብ ስላልተገኘ ተደጋጋሚ የቦንድ ሽያጭ እየተካሄደ ነው፤ አንዳንድ የመንግስት ሰራተኞችም በካድሬ ባልደረቦቻቸው ጫና በድጋሚ ቦንድ ለመግዛት መወሰናቸው ተሰምቷል፤ በርግጥ ከፍተኛ የኢህአዴግ የአመራር አባላት በአውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ እና በመካከለኛው ምስራቅ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቦንድ እንዲገዙ ለመቀስቀስ የአዘጋጇቸው ስብሰባዎች ‹‹ቅድሚያ የዜጎች መብት ይከበር›› ባሉ የሀገራችን ልጆች መክሸፉም የክረምቱ የመንግስት ዋና ሥራ ነው፤ ክረምቱ እንዲህ እየተገባደደ ነው፡- በነቢብ የኢትዮጵያ፣ በገቢር የገዥው ፓርቲ የግል ንብረት የሆነው ቴሌቪዥን ጣቢያ ባለፉት ሶስት ወር ብቻ ከሃያ በላይ ‹‹ዶክመንተሪ ፊልም›› አሳይቷል (ገና ይቀጥላልም) በርዕሳቸው እንደሚከተለው እንዘርዝራቸው፡- ‹‹ኢፍቲን›› በሶማሊያ ላይ የሚያጠነጥን፣ ‹‹የጥቁር ህዝቦች ልሳን (መለስ በአፍሪካ)››፣ ‹‹ከፓን አፍሪካ እስከ አፍሪካ ህዳሴ›› የጠቅላይ ሚንስትር መለስን ህይወት የሚዳስስ፣ ‹‹ዘመነ አፍሪካ››፣ ‹‹የአፍሪካ ልሳን-መለስ››፣ ‹‹መለስ ማን ነው?››፣ ‹‹ሀገሬ-ቤቴ››፣ ‹‹ባለራዕዮቹ›› ስራ ፈጠራ ላይ የሚያተኩር፣ ‹‹ደውል›› እና ‹‹ደውል 2›› ህገወጥ-የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ (በተለያያ ጊዜ የተላለፉ)፣ ‹‹የዲያስፖራ የልማት እንቅስቃሴ››፣ የካርታ ስራ ድርጅትን በተመለከተ፣ ‹‹የጥልቅ አስተሳሰብ ባለቤት›› በፕ/ር እንድርያስ እሸቴ ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን፣ ምድር ባቡር ኮርፕሬሽንን በተመለከተ፣ ‹‹ያልተለመደ ጉብኝት›› የአዲስ አበባ አስተዳደር የአምስት ዓመት የመንግስት ግንባታዎችን በተመለከተ፣ ‹‹ሼህ ኑር ለምን ሞቱ?›› የደሴውን ሼህ ኑር ይማምን ግድያ በተመለከተ፣ ‹‹የተስፋ ስንቅ››፣‹‹በቃሉ የፀና›› በድህረ መለስ ላይ የሚያተኩር፣ ‹‹ያልተጠኑ ገፆች›› በመለስ ዜናዊ ህይወት ዙሪያ (በርግጥ በዚህ ፊልም እህቱ ጠላ፣ ወንድሙ አንባሻ በመሸጥ መተዳደራቸውን በምስልም በድምፅም ማቅረቡ ምን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ተፈልጎ እንደሆነ ለማወቅ ግራ ያጋባል፤ …ምናልባት እንዲያ እየዘረፈ ለቤተሰቦቹ ‹ሶልዲን› የማይሰጥ ‹ቆነቋና› ነበር ለማለት ይሆን? ወይስ ለአዜብ መስፍን ‹የወር ቀለባችንን እንቸገራለን› የአንድ ሰሞን ማስተዛዘኛ ምስክር ፍለጋ ነው?

በጥቅሉ ለኢህአዴግ ሕዝብን የማስተዳደር፣ ሀገርን የመምራት መገለጫ ይህ ነው፤ ሌላ አይደለም፤ ግና! ለዘመናት ያልተመለሱ ጥያቄዎቻችን ዛሬም መጮኻቸውን አላቋረጡምና እነሆ እንዲህ ቀጥለዋል፡- ሀገር ማስተዳደር ‹መለስ ጀግና ነበር› እያሉ ማሰልቸት ነውን? የመንግስትስ ስራ (ግዴታ) ምንድር ነው? ሀገሪቱን ‹‹መለስ-ፓርክ›› ወደሚል ስያሜ ከመቀየራችሁ በፊት፣ ለጤፍ ዋጋ አለቅጥ መናር ምክንያቱን ስለምን መመርመር ተሳናቸው? ሀገሪቱን በ‹አራጣ› እንደያዘ ስግብግብ ነጋዴ በሚሊዮኖች ህይወት ላይ የማይሞላ ‹ሳፋ› ደቅኖ አዋጣ፣ ግዛ፣ ክፈል፣ ገብር… እያለ የሚያስጨንቀው ማን ነው? ስለመለስ ‹የሃሳብ ምጡቅነት› መስካሪ ምሁራኖቻችን ለጎዳና ኑሮ የተዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስንት ሚሊዮን እንደደረሱ እና እልፍ አላፍት ታዳጊዎቻችን በሴተኛ አዳሪነት እንደተሰማሩ የምትነግሩን መቼ ነው?እንዲህ የመሆኑ ምክንያትስ በማን ይሆን? ‹የሁለት ዲጂቱ›ዕድገት ሸክምን የማለዘብ አቅም ከሌለውፋይዳው ምንድር ነው? ‹ሳቅ ትዝታ› ስለሆነባቸው ጎጆዎች ለምን አትነግሩንም? መለስ ‹ያለመለማት› ኢትዮጵያ ወዴት ትሆን? ‹ፖለቲካ› ማለትስ ይህ ነውን? …ነጋ ድራስ ገ/ህይወት እንዳሉት ‹‹…መንግስት መቆሙ ለሕዝቡ ሁሉ ጥቅም ነው፡፡ ጥረቱም ህዝቡን ሁሉ በትክክል ለመጥቀም ያልሆነ መንግስት ሊቆም አይችልም፡፡›› የመተራረሚያው ጊዜም በጣም ያለፈ ይመስለኛል፡፡ አገዛዙን ‹እንደ መንግስት› መቀበሉም እንዲሁ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>