አጠቃቀምና የቃላት አሰካክን የተከተለ ነው፡፡ አልፎ-አልፎ የቀበልኛ ቃላትን ቢጠቀምም እንኳ፣ በግርጌ ማስታወሻ አማካይነት “ፍቻቸው” ተቀምጧል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ጉድለት በዋናነት አንድ ነው፡፡ እርሱም፣ በአረንጓዳ ሳሎን ውስጥ በነገርሜ የተገደሉባቸው የራስ አበበ አረጋይ፣ የራስ ስዩም፣ የሜ/ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ፣ የአቶ መኮንን ሀብተ ወልድና የሌሎችንም ባለሥልጣመናት ቤተሰቦች አለማናገራቸው ነው፡፡ ከዓመታት በኋላ፣ እነዚህ የሟቾቹ ቤተሰቦች ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ያላቸውን ስሜትና እውቀት ሊያካትቱት ቢችሉ ምንኛ ዕጹብ-ድንቅ ይሆን ነበር፡፡ ከአቶ ብርሃኑ አስረስ አልገፉበትም እንጂ፣ ትልቅ ሙከራ አድርገው እንደነበር አያጠራጥርም፡፡ በ1953 ዓ.ም የፍትሕ ሚ/ር የነበሩትን ደጃ/ች ዘውዴ ገ/ሥላሴንና ብ/ጄኔራል መኮንን ደነቀን ለማነጋገር ያደረጉት ጥረት መልካም ነው፡፡ እጅግም የሚደነቅ ነው፡፡ በሰማኒያ ሦስት ዓመታቸው የተለያዩ ጫናዎችን ተቋቁመው ይኼንን የመሰለ ድርሳን ስላቀረቡልን ለአቶ ብርሃኑ አስረስ ያለኝን ምስጋናና ልባዊ አክብሮት በአንባቢያን ስም ይድረሳቸው እላለሁ፡፡ አንባቢያንም፣ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ዋጋው ተፋፍቆ በእጥፍ ከምትገዙት፣ ዛሬውኑ መጽሐፉን በትክክለኛው ዋጋ “የግላችሁ አድርጉት!” በማለት ወንድማዊ ምክሬን አስተላልፋለሁ፡፡ ለአቶ ብርሃኑም መልካም ጤንነትና ሰላምን እመኛለሁ፡፡ (በተረፈ፣ በቸር እንሰንብት!)
Email: solomontessemag@gmail.com
ዕድል አጋጣሚ፣ ለሰው ልጅ ስትመጣ፣
መልካምና ክፉ፣ አላት ሁለት ጣጣ !!!
(ከበደ ሚካኤል፣ “የዕውቀት ብልጭታ”፤)
የታኅሣሥ 1953ቱን (ዓ.ም) “ሥዒረ-መንግሥት” ዋዜማ፣ መባቻና ማግስት ያካተተ መጽሐፍ ታትሟል፡፡ የመጽሐፉ ደራሲ፣ አቶ ብርሃኑ አስረስ ሲሆኑ፣ አሳታሚው ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ነው፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ፣ “ማን ይናገር የነበረ…..፣ የታኅሣሡ ግርግር እና መዘዙ” የሚሰኝ ሲሆን፣በ2005 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ አዲስ አበባ ላይ ታትሟል፡፡ ይኼንን የሚያህል ቁምነገረኛ መጽሐፍ በ144.00 (አንድ መቶ አርባ አራት) ብር ገዝቶ ቁምነገር መዝረፍ ያጓጓል፡፡ ገጽ በገጽ ሲገልጡት ከ እሰከም ስለሌለው ነፍስን በሃሴት ያጭራል፡፡ አንድ ጊዜ ብቻ አንበውት የማያልቅ ሃተታ የያዘ ድንቅ ድርሳን (Masterpiece) ነው፡፡ ድርሳኑን ደጋግሞ ማንበብ እውነትን የበለጠ ማወቅ ነው፡፡ “ድንቅ የሆነ ድርሳን” ነው ያልኩት ለማጋነን አይደለም፡፡ በእርግጥም፣ ውብ ነው! እጹብ ድንቅ ነው!….
ይኼው ልንገመግመው የመረጥነው መጽሐፍ እጅግ ከፍ ያለ የዋጋ የሚሰጠው፤ የነገረ-መረጃ (Intelegenece)፣ የወታደራዊ፣ የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የታሪክ፣ የንግድ፣ የማህበራዊ ሳይንስና የግብረ-ሠናይ ይዘት ያለው ሥራ ነው፡፡ እንደሚታወቀው፣ በሀገራችን የነገረ-መረጃ (የስለላ-ነክነት) ያላቸው መጽሐፍት ቁጥር እጅግ በጣም አናሳ ነው፡፡ ያሉትም ትቂት መጽሐፍት ቢሆኑ የትርጉም ሥራዎች ናቸው፡፡ ለዚያውም ደግሞ የአቶ ማሞ ውድነህ ጥረቶች ናቸው፡፡ ይህም የሆነው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡
አንደኛ፣ የደኅንነት (የመረጃ) መሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎቹ በተከታታይ ሕይወታቸው በምስጢራዊ አኳኋን በማለፉና የሚያውቁትን ምስጢራዊ መረጃ ሊዘግቡት ባለመቻላቸው ነው፡፡ በጃንሆይ ዘመን የነበሩት የደኅንነት መሥሪያ ቤት ሃላፊዎች በሙሉ በሰው እጅ አልፈዋል፡፡ አቶ መኮንን ሀብተ ወልድ ዋናው ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሌ/ኮለኔል ወርቅነህ ገበየሁም ቢሆን ተታኩሶ ነው የሞተው፡፡ ኮ/ል ዳንኤል ደግሞ በሻለቃ ዮሐንስ አራት ኪሎ ቤተ-መንግሥት ውስጥ (ከነሰናይ ልኬ ጋር አንድ ቀን ነው) የተገደለው፡፡ የደርግ ዘመን፣ ለረጅም ጊዜያት የደኅንነትና የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር የነበረው ኮ/ል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴም ቢሆን፣ ከ21 ዓመታት እስር በኋላ ሊለቀቅ ቀናት ሲቀሩት መሞቱ ተሰማ፡፡ ከርሱም ቀጥሎ ኃላፊነቱን የተቆናጠጠው “ተጋዳላይ” ክንፈ ገ/መድኅን በግንቦት 4/1993 ዓ.ም በጎልፍ ክለብ ተገደለ፡፡ እነዚህ ሁሉ ክስተቶች ተደማምረው፣ የኢትዮጵያን የደህንነት መሥሪያ ቤት የሚመለከቱ መረጃዎች ከኃላፊዎቹ ጋር ተቀበሩ፡፡ የኃላፊዎቹንም ፍጻሜ ያዩት የመረጃ መሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች “ጎመን በጤና” ብለው እንዲታቀቡ ጥላውን አጠላባቸው፡፡
ሁለተኛውም ምክንያት ከባህላችን ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በብዙዎቹ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰቦች አኗኗር ውስጥ “አይተኻልን?-አላየኹም!” ሰምተኻልን?-አልሰማኹም!” በል የሚል የመረጃና የደኅንነት መግቻ ጥብቅ ሕገ-ድንብ አለ፡፡ ይህ ሕገ-ደንብ ከማንም በላይ የሚጠብቀው የተጠያቂውን ግለሰብ ደኅንነት ነው፡፡ “ሰውን ማመን ቀብሮ ነው!” ያለችውን ቀበሮ ኢትዮጵያዊት ሳትሆን አትቀርም፡፡ “…ልቡ ዘጠኝ፣ ሰምንቱን ሸሽጎ አንዱን አጫወተኝ!” የተባለው ተረት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ሳይሠራ አይቀርም፡፡ ያም ባይሆን፣ ብዙዎቹ “ምስጢር፣ የባቄላ ወፍጮ አይደለም” ብለውም የሚያምኑ በመሆናቸው፣ “አይተው-ላለማየትና ሰምተውም-ላለመስማት” ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ በዚህም የተነሣ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለበርካታ ዘመናት ያህል፣ ምስጢር-ጠባቂነት የግለሰቦች ባህሪ ከመሆንም አልፎ የወል ባህልም ለመሆን ችሏል፡፡
ወደዋናው ትኩረታችን እንመልስ፡፡….“ማን ይናገር የነበረ…..የታኅሣሡ ግርግር እና መዘዙ”፣ የተሰኘው መጽሐፍ ደራሲ ዋናው የትምህርት ጥናታቸው ኤኮኖሚክስ ነው፡፡ በ1951 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ የኤኮኖሚክስ ዲግሪያቸውን በኦክስቴንሽን እያጠኑ ሳለ ከሻለቃ ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ተዋወቁ፡፡ ሁኔታውን እንዲህ ያስታውሱታል፣ “በወቅቱ የምሰራው በአሜሪካን የማስታወቂያ ክፍል (USIS) ነበር፡፡ ደቡብ የመን ደርሶ የመጣውን ጓደኛዬን አዲስ መጽሐፍ ገዝቶ አምጥቶልኝ ነበር፡፡ በሥራ ቦታዬ ላይ ፋታ ሳገኝ ለማንበብ ከጽሕፈት ጠረንጴዛዬ ላይ አስቀምጠው ነበር፡፡….የመሥሪያ ቤቱ ዳይሬክተር… በአንባቢነቴ ይደነቅ ነበርና ጠጋ ብሎ አርእስቱን ቢመለከት “ዳስ ካፒታል” የሚል ሆኖ ያገኘዋል፡፡” በዚህም ሳቢያ አቶ ብርሃኑ በኮሚኒስትነት ተጠርጥረው ወደሕዝብ ፀጥታ ጥበቃ መሥሪያ ቤት ይወሰዳሉ፤ ሻለቃ ወርቅነህም ዘንድ ይቀርባሉ (ገጽ-18)፡፡ (መግቢያችን ላይ የተጠቀምናት፣ “እድል አጋጣሚ፣ ለሰው ልጅ ስትመጣ” የምትለው የከበደ ሚካኤል ስንኝ በትክክል ደርሶባቸዋል፡፡) ደራሲው ከተጠረጠሩበትም የኮሚኒዝም ስርፀት ጣጣ ነፃ ቢወጡም ቅሉ፤ ወደUSIS ተመልሰው እንዳይሠሩ ይደረጋሉ፡፡ ከዚህም ጊዜ ጀምሮ፣ ከኤኮኖሚክስ ጥናታቸው ልቆ የነገረ-መረጃ ሥራቸው ጨምሯል (ገጽ-19)፡፡
“መረጃ አይናቅም፤ አይደነቅም!” በሚለው መሠረታዊ የነገረ-መረጃ ንድፈ-ሃሳብ የሚያምኑት ደራሲ ብርሃኑ አስረስ፣ ሴራውን (መፈንቅለ-መንግሥቱን)ና በሀገሪቱ ውስጥ የነበሩትን የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የአስተዳደራዊ ኩነቶች በገለልተኛነት ለመተንተን ያደረጉት ጥረት የሚደነቅ ነው፡፡ የስዒረ-መንግሥቱ ጠንሳሾች፣ “በህዝቡ ላይ የመታየውን የፍርድ ጉድለት፣ የአስተዳደር በደልና የኤኮኖሚ ድቀት እያስጨነቃቸውና ሰላም እየነሳቸው ስለሄደ፣ አማራጭ መፈለግ ግድ እየሆነባቸው መጣ” ይላሉ(ገጽ፣ 151)፡፡ ነገር ግን፣ በኅዳር 29/1953 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ በኩል የላኳት ቴሌግራም ያለጊዜው እሳት መጫሯን ያትታሉ (ገጽ-151/2)፡፡
በገጽ 81 እና 82 ላይ እንደገለጹት ሁሉ፣ ሻለቃ ወርቅነህን ለለውጥና ለመሻሻል ያነሳሱትን አምስት ምክንያቶች ዘርዝረዋል፡፡ እነርሱም በኮሪያ ዘመቻና በቶኪዮና ሴኡል የህክምና ጉብኝቱ እንዲሁም በሲዊድን ቆይታው ወቅት በገሃድ ያያቸው መሆናቸውን ያብራራሉ፡፡ ከግርማዊነታቸውም ጋር በተለያዩ አገሮች ሲሄድ ባወቃቸው ኩነቶች ተገፋፍቶ እንደሆነም ያወሳሉ፡፡ የኢትዮጵያንና የሕዝቧንም እድገትና ብልጽግና ያጫጨው “የመሬት ስሪት/ፖሊሲው” ጉዳይ መሆኑን ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህን ዋቢ አድርገው ያትታሉ (ገጽ-91/2)፡፡ ኮ/ል ወርቅነህ ባቀረበው የመሬት ስሪት/ፖሊሲው ጥናታዊ ማስታወሻ እንደጠቀሰው፣ “የመሬት ይዞታው ጉዳይ አንደጋንግሪን እየገዘፈ መጥቶ መንግሥትን የሚያናውጥ ሕዝብንም የሚያፋጅ ቀውስ እንደሚያመጣ” ማስረዳቱን ያስታውሳሉ፡፡ በአሁኑም ጊዜ፣ “በዓለም ላይ ርስት የለሽ ሕዝብ ያለባት ብቸኛ አገር (ከኮሚኒስት አገሮች በቀር) ኢትዮጵያ ሳትሆን አትቀርም፤” ይላሉ(ገጽ-92)፡፡ አያይዘውም፣ “ሰው በሰውነቱ እኩል ሆኖ የተፈጠረ ስለሆነ፣ የአገሩ የተፈጥሮ ሀብት ከሆነው መሬት ድርሻ ሊኖራ ይገባል፤….” የሚል አቋም የነበራቸውን አፄ ኢያሱ አድያምሰገድን የመሬት ስሪት ደንብ ያቀርባሉ (ገጽ-121)፡፡ አፄ ምሊልክም አዲስ አበባን ሲቆረቁሩ ይዘውት የነበረውን ፍትሀዊ የመሬት ስሪት ደንብ ያወሱና፣ የምኒልክ ሹማምንት ግን “ከሕዝብ ተለይተው መሬት ለነርሱ ብቻ እንደተፈጠረ ወደ ማድረጉ አዘነበሉና ራሳቸውን ብቻ በማበልፀግ የማኅበራዊና የኤኮኖሚያዊ ኑሮውን ደረጃ ልዩነት አሰፉት፤” ሲሉ ይወቅሳሉ (ገጽ-125)::
በመጨረሻም፣ ከበድ ያለና ጥንቃቄን የሚሻ ትንታኔ ለአንባቢያኑ ያቀርባሉ፡፡ “የኢትዮጵያን የመሬት ስሪት ድልድል እንዳጠና ሌ/ኮሎኔል ወርቅነህና አቶ ገርማሜ ንዋይ አዘዙኝ” ይላሉ (ገጽ-119)፡፡ ገርማሜ የኢትዮጵያን የመሬት ወረራ ያመሳሰለው ለመጀመሪያ ዲግሪው መመረቂያ ጽሑፉ ሲያዘጋጅ ካጠናው ከኬንያው የ“ማው ማው” ንቅናቄ ጋር ነበር፡፡ ሆኖም፣ ከላይ የተገለጹትን የአፄ ኢያሱንና የአፄ ምኒልክን የመሬት ስሪት ድልድል ሲረዳ፣ “ድሮ ከነበረው ስሜቱ መለስ” ብሎ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ሆኖም፣ “ገርማሜ ነዋይ፣ እነዚህ ከመሬት ባገኙት ኤኮኖሚ ተጠቃሚ የሆኑ ጥቂቶች፣ የፖለቲካ ስልጣኑንም በመጨበጣቸው በሕዝቡ ላይ ይደርስ ለነበረው የአስተዳደር በደልና የፍትሕ መጓደል በዋናነት ተጠያቂ አድርጎ ያቀርባቸው” እንደነበርም አትተዋል (ገጽ-126ና 139)፡፡ በተመሳሳይ ኹኔታም፣ በገርማሜ ታላቅ ወንድም በብ/ጄኔራል መንግሥቱ ነዋይ ይመራ የነበረውንም የክብር ዘበኛ አምርሮ ይጠላው እንደነበር በገጽ-266 ላይ ዘግበዋል፡፡ ገርማሜ እንዲህ አለ፤ “የክብር ዘበኛ… በመፍረሱ ደስ ብሎኛል፡፡…. ያ ሠራዊት ጀግና ነው፡፡ የታወቀ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የፈለገውን ነገር ማድረግም ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን፣ በንጉሠ ነገሥቱ ላይ ያለው ታማኝነት ከፍ ያለ ስለሆነ ሳይዋጋ ቀረ፡፡…. ሠራዊቱ አንድ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተነሳ ሲባል ሄዶ ያፍናል፡፡ ስለዚህ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሆኑ ማንኛውም ሰው (ድርጅት) በተቃውሞ መንቀሳቀስ ወይም የልቡን ተናግሮ ሀሳቡን መግለጽ ስላልቻለ፣ ይህ ሠራዊት ከተበተነ በኋላ ለተቃውሞ እንቅስቃሴ ይነሣሣል፡፡ ዓላማውም ውጤት እንዲያገኝ ይረዳል….፡፡” ከአራት ዓመታትም በኋላ ገርማሜ ነዋይም እንደተነበየው ሆነ፡፡ በ1957 ዓ.ም ጀምሮ የተማሪዎች አመጽ እየበረታ ሄደ፡፡
አቶ ብርሃኑ፣ ለመጽሐፋቸው ዋና መነሻ የሆኗቸውን ሃሳቦች ያገኙት በድርጊቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆናቸው ነው፡፡ ደራሲው፣ እዚህም-እዚያም ተሰባጥረው የሚገኙትን የ1953ቱን ስዒረ-መንግሥት መነሻና መድረሻ “ማን ይናገር?…የነበረ!” እና “የታኅሣሡ ግርግር”ባሉት ሃይለ-ሃሳብ አደላዳይነት በፈርጅ-በፈርጁ ሊደለድሉት ጥረዋል፡፡ ሙከራቸውም ፈሩን ያለቀቀ ነበር፡፡…. በአስተሳሰባቸውና በአቀራረባቸውም የገለልተኛነት ስፍራን ለመውሰድ ተግተዋል፡፡ በመፈንቅለ-መንግሥቱ ሴራ ተሳትፏቸው የተነሣ ለአምስት ዓመታት ያህል ቢታሰሩም፣ የእልህና የስሜታዊነት ጥገኛ ለመሆን አልፈለጉም፡፡ ከዚህም ከዚያም ብለው ጠቃሚ የሆኑትን ሃሳቦችና ነጥቦች ተፈላልገው በማጠናቀር የዐይን እማኞችን ሃቲት ለማካተት ተግተዋል፡፡ ይሁንና፣ ምንም የገለልተኛነት መንገድን ለመውሰድ ቢሞከሩ እንኳን፣ በአለቃቸው/በወዳጃቸው በሌ/ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ተጽእኖ ስር ከመውደቅ አላመለጡም፡፡ “የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪዎች” የሚለው ምዕራፍ ሥር “ወርቅነህ ገበየሁ (?-1953)” የሚለው ንዑስ-ርዕስ የደራሲውን የሃሳብ አካሄድና የአስተሳሰብ ፈለግ በይበልጥ የሚመሰክር ነው፡፡ ደራሲው ንጉሠ ነገሥቱንና ሌሎችንም ሰዎች የሚያዩት በእነርሱ ዐይን ነው፡፡ ለአብነትም ያህል ገጽ-85፣ ገጽ-92፣ ገጽ-102፣ ገጽ-111/2፣ ይጠቀሳሉ፡፡ በገጽ-145ና ገጽ-342 ያሉትን አተያዮች ደግሞ በብ/ጄኔራል መኮንን ደነቀና በመቶ አ/ በቀለ አናሲሞስ በኩል ነው ያስተላለፉት፡፡ ይኼንንም ያደረጉት ይሆነኝ ብለው ነው፤ ከስሜታዊነት ለመራቅ፡፡
በተጨማሪም፣ ደራሲው በመፈንቅለ መንግሥቱ ተሳታፊ የነበሩትን ዋና ዋና ተዋንያን እስር ቤት ሳሉና ከወህኒ ቤትም ከወጡ በኋላ ተከታትለው በማናገር የተበታተኑትን ምስጢራዊ መረጃዎች አጠናቅረውና አስፋፍተው በመፃፍ አንድ ጉልህ-ፈር ቀደዋል፡፡ ከእንግዲህ ወዲያም፣ የተለያዩ የታሪክ ተመራማሪዎች፣ የፖለቲካ ሳይንስ አጥኚዎች፣ የሥነ-ጽሑፍና የትውን ጥበባት ቀማሪዎች ስለጉዳዩ በየፊናቸው ለመተርጎም የሚያስችላቸውን ግብዓት አግኝተዋል፡፡ ከዚህም ሌላ፣ ምስጢራዊ ሰነዶችና መረጃዎችም እንደምን ሊገኙ እንደሚችሉ መላና ዘዴውን ገልጠዋል፡፡ ለውጥ እንዴት ያለነውጥ ሊመጣ እንደሚችል ተሞክሯቸውንም አካተዋል፡፡ በምዕራፍ 1ና በምዕራፍ 9 ስርም ያሉት ሁለቱ ሃተታዎች ይኼንን የደራሲውን የሕይወት ተሞክሮና ዕጣ-ፈንታ ይተርካሉ፡፡ የሚደንቀው ነገር፣ ደራሲው “እኔ-በዚህ ወጥቼ፣ እኔ በዚህ ወርጄ!” ከሚለው የንፉግ ትችት የራቁ መሆናቸው ነው፡፡
በታኅሣሥ 1953 ዓ.ም የተደረገውን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተከትሎም፣ በስድስት ኪሎ ገነተ-ልዑል ቤተ-መንግሥት አረንጓዴው ሳሎን ስለተገደሉት አስራ አምስት(15) ባለሥልጣናት አሟሟት ልከኛውን መረጃ ይሠጣሉ፡፡ ግድያውን የመራው ገርማሜ ነዋይ እንደነበረና ዋነኛው ነፍሰ-በላም እጩ መኮንን ነጋሽ ድንበሩ መሆኑን ይገልፃሉ (ገጽ-258 እና 266 ይመልከቱ፡፡) ብ/ጄነራል መንግሥቱ ነዋይ፣ “ኧረ ለመሆኑ ሚኒስትሮቹ እንዴት ሆኑ? ፈታችኋቸው? ልዑል ጌታዬስ? (አልጋ ወራሹስ) ማለታቸው ነው፤” ብለው ሲጠይቁ፣ ገርማሜ “እሳቸው እዛው ናቸው፡፡ ለሚኒስትሮቹ ግን የሞት ቅጣት ሰጥተናል፤” እንዳለ ይተርካሉ፡፡ የመጽሐፉም አንኳር ነጥብ ያለው እዚሁ ላይ ነው፡፡ በኮሚኒዝም ስርፀት ከሁለተኛው የእጩ መኮንንነት ኮርስ የተቀነሰው መርሻ ድንበሩና በኮሚኒስትነት ከወላይታ አውራጃ ገዢነቱ የተነሳው ገርማሜ ነዋይ፣ ዜጎችን ያለፍርድ በመግደል ለነሻለቃ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም አርዓያ ሆኑ፡፡ ለሌሎችም “በዲሞክራሲ ካባ ስር፣ የማርክሲዝምና ሌኒኒዝምን ጃኬት” ለለበሱ ነፍሰ ገዳዮች አጽድቆት ሰጡ፡፡
ማጠቃለያ፤
“ማን ይናገር የነበረ…..የታኅሣሡ ግርግር እና መዘዙ”፣ የተሰኘው መጽሐፍ እጅግ የሚደነቅ የቋንቋ