ገብረመድህን አረአያ
ከፐርዝ፣ አውስትራሊያ
ስብሃት ነጋ ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ በሚታተመው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ አነበብኩት:: ስብሃት ነጋ “ኢህዴግን የመሰለ ፓርቲ በአፍሪካ የለም” እና ሌላም ብዙ ፣ ብዙ ይላል:: ይዘብታል ፣ ይፎክራል፣ ይሸመጥጣል፣ ያቀረሻል፣ በህዝብ ሞራል ላይም ያላግጣል:: ብዙም አልደነቀኝም:: ስብሃትም ሆኑ የዚህ ፋሺስታዊ ስርዓት አንቀሳቃሾች በብዙሃን ደም ላለፉት አርባ አመታት ታጥበዋል ፣ ታሪክ አውድመዋል ፣ እጅግ ከፍተኛ ዘረፋ ፈጽመዋል ፣ አገር ቆርሰው ሸጠዋል:: በጣም ከፍተኛ ወንጀል የሰሩ ሰዎች እንደመሆናቸው በአገሪቷ የፖለቲካ ለውጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ መቀጣጠሉ እንቅልፍ እንደነሳቸው እያየን ነው:: አዎን ስብሃት ገና ፣ ገና ከዚህም በላይ ብዙ ይናገራል ፤ ቁጣው እያየለ በሄደ ቁጥር ብዙ ወንጀሎችም ይሰራል::
ዛሬ ወያኔ ኢህአዴግ ከመቼውም ጊዜ በበዛ ፍጥነት እና ማን አለብኝነት ኢትዮጵያዊ የሆኑ መሰረቶችን የመናዱን ስራ አጠናክሮ እየሰራ ለመሆኑ በየእለቱ የምንሰማቸው ዜናዎች እና ዘገባዎች ያሳያሉ:: እንደ እኔ ፣ እንደ እኔ የወያኔ የጥፋት ስራ ሳይሆን የጨመረው ይልቁንስ ረጅም እድሜ ለኢሳት ይስጠውና የዜና ዘገባ ብዛት እና አይነቱ መጨመሩ ይመስለኛል:: ወያኔ ሲፈጠር ጀምሮ ኢትዮጵያዊ መሰረት ያላቸውን እሴቶችን የማጥቃት ስራን እንደ መጨረሻ ግብ(strategic goal) አስቀምጦ የሚንቀሳቀስ ድርጅት መሆኑን ቀድመን ላወቅን እና ለተረዳን ሰዎች ግን እምብዛም አዲስ ነገር አይደለም:: ዛሬ ላይ ከኢትዮጵያ ከሚወጡ ዜናዎች በብዛት የምንሰማው ብዙዎች ሲያለቅሱ እና ጥቂት ዘረኞች ደግሞ ያለ ይሉኝታ ሲዘርፉ ፣ ሰዎችን አስረው ሲያሰቃዩ፣ እና ኢትዮጵያውያንን ዘር ቆጥረው ከቀያቸው ሲያፈናቅሉ ሆኗል::
የኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ዋይታ በቤኒሻንጉል እና ጉራፈርዳ፣ የባህታውያን ለቅሶ በዋልድባ ፣ የእስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያውያን የፍትህ ጥያቄ በመላ ሃገሪቱ ፣ ሌላም ፣ ሌላም:: ወያኔ ኢህአዴግ በአገር እና በወገን ላይ የሚያደርሰው ጥቃት በግብ ደረጃ የተያዘ በመሆኑ ይብሱን ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል:: ዛሬ ላይ ከዳር ቆመው የሚመለከቱ ሰዎችም ሆነ በስርዓቱ ውስጥ ያሉ ካድሬዎች እና አገልጋዮች ይህንን ሃቅ በደንብ ልብ ብለው ሊመለከቱት ይገባል:: የጥቃት ዱላው በአንድ ወይም በሌላ በኩል አይደርስ የሚመስልበት ቦታ ሁላ ይደርሳል::
ኢትዮጵያውያን ከምንም ነገር በላይ ለሃይማኖት እና የእምነት ተቋሟት ታላቅ ክብር ይሰጣሉ:: በዛሬ ጽሁፌ ለማንሳት የፈለግኩት ጉዳይ በአንድ ወቅት በወያኔ ኢህአዴግ ውስጥ ታጋይ በነበርኩበት ወቅት በዘመቻ ከስብሃት ነጋ እና ከሃለቃ ጸጋይ በርሄ ጋር ሌሎች ሁለት ታጋዮችም ተጨምረውበት አንድ ገዳም እንዴት እንደፈርን እና እንደዘረፍን በማሳየት ስብሃትም ሆነ ድርጅቱ እንዴት ለአገራዊ እና ሃይማኖታዊ ተቋማት ያላቸውን ንቀት ለማሳየት ነው:: ጊዜው ሕዳር ወር 1971ዓ.ም. እና የተ.ሓ.ህ.ት. 1ኛ ጉባኤ እየተቃረበ የመጣበት ወቅት ነበር። ድርጅቱ ለጉባኤው ማካሄጃ በሚል ሰበብ የትግራይ ደሃ ገበሬዎችን ንብረት እና ገንዘብ በስፋት መቀማቱን በዘመቻ ተያይዞታል:: ሃብትና ንብረታቸው የተዘረፈ ንጹሃን የትግራይ ገበሬዎችንም ሃለዋ ወያኔ በማስገባት መፍጀቱ ተጧጡፏል፤ በወቅቱ የተ.ሓ.ህ.ት. ቤዝ በለሳ፤ እገላ ወረዳ ውስጥ ይገኛል። ብዙ ክፍሎች፤ ማለትም 02 ወታደራዊ ማሰልጠኛ፤ 03 ህክምና፤ 04 ፖለቲካ ጽ/ቤት፤ 05 ክፍሊ ኢኮኖሚ፤ 09 መሳሪያ ግምጃ ቤትና 06 ሃለዋ ወያነ ተበለው ተከፋፍለው እዚሁ ቦታ ላይ በተለያየ አቀማመጥ ሆነው ይሰራሉ። አቦይ ስብሃት በ04 ፖለቲካ ጽ/ቤት በሚታዘዙ እና በአዲ ጨጓር እና በለሳ ምይ ሃማቶ ላይ በሚገኙ ሁለት ሃለዋ ወያኔዎች(እስር ቤቶች) ንጹሃንን አሳስሮ ያስገርፋል፣ ያስገድላል:: እኔ በወቅቱ የህክምናው ክፍል ሃላፊ ነበርኩኝ:: እና ታዲያ በዚሁ አንድ የህዳር ቀን በስብሃት የተጻፈ ቀጭን ደብዳቤ በምሰራበት የህክምና ክፍል ደረሰኝ:: ደብዳቤው እንዲህ ይላል : ነገ ጠዋት ልክ በ2 ሰዓት መሬቶ እንድትጠብቀኝ፤ ወደ ሽራሮ ለሥራ ጉዳይ አብረን እንሄዳለን:: ለምን ፣ እንዴት ፣ በምን ተብሎ አይጠየቅም፤
በነጋታው እንደታዘዝኩት በተባለው ሰዓት መሬቶ ቁሽት ቀድሜ ደረሼ ቆየሁት። እሱም በሰዓቱ መጣ። ተያይዘን ጉዞአችንን ወደ ጭላ ወረዳ ቀጠልን። ቀኑን ሙሉ ስንጓዝ ውለን በመሃልም ግርማይ ጀብር የሚመራት አንድ ሃይል ተቀብላን አንድ ቦታ አደርን። ከአስመራ ወደ አድዋ የሚወስደውን መንገድ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ላይ አሻገሩን። ይህ መንገድ ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ጦር አይለየውምና ለመሻገር ጥንቃቄ ይሻል::
ጭላ ከጥዋቱ 2 ሰዓት ገባን። እዛ የቆዩን ሃለቃ ፀጋይ በርሄ–የላይ አድያቦ ሕዝብ ግንኙነት፤ አጽብሃ ሀ/ማርያም–የአንከረ ሕዝብ ግንኙነት፤ ቀሺ ታደሰ–የክርቢት ነውጠኛ መሪ ነበሩ። እኔና ስብሃት ተደምረን አምስታችን ጭላ ውለን ስብሃት ቀድሞ ለወጠነውና አስቅድሞ መረጃው ለሌለኝ የዘረፋ ስራ ወደ እንዳማርያም ገዳም ጉዞ ጀመርን:: ሃለቃ ፀጋይ በርሄ በስብሃት በታዘዘው መሰረት አስቀድሞ ጥናቱን ጨርሶ ስለነበር፤ የቤት ክርስትያኑን አቃቤ ግምጃ ቤት ባህታዊ ማን መሆናቸውን እና የት አካባቢ እንደሚኖሩ አውቋል። ሌሎቻችን ታጣፊ ክላሽንኮቭ ስብሃት ነጋ ደፍሞ ሽጉጥ ታጥቋል። ለምን እና ወዴት እንደምንሄድ ቀሺ ታደሰ፤ አጽብሃ ሃይለማርያምም ሆነ እኔ አናውቅም። ኋላም ተጉዘን እንዳማርያም ቤተ ክርስቲያን ገባን። ቤተ ክርስቲያኑ በጥንት ዘመን በአብርሃ ወአፅብሃ ዘመነመንግሥት የተሰራ፤ በጣም ሰፊና ብዙ የአትክልት እና ፍራፍሬ እርሻ የሚለማበት ገዳም ነው:: በመነኮሳት ጉልበት በመስኖ የለማ ሎሚ፤ ሙዝ፤ ብርቱካን፤ ትርንጎ፤ መንደሪን ገዳሙን ከቦታል። መቼም አካባቢው ውብ እና ለመንፈሳዊ ህይወት የተመቸ ነው:: በእድሜ የበለጸጉ ባህታውያን፤ ቀሳውስት፤ መናንያን እና ዲያቆናት በገዳሙ ዙሪያ መንፈሳዊ ህይወታቸውን ይመራሉ። ውስጥ ለውስጥ ብዙ ከሄድን በኋላ ከፊታችን አንድ ዲያቆን አገኘን። ሃለቃ ፀጋይ ዲያቆኑን ለብቻ ነጥሎ አናገረው፤ ምን እንደተነጋገሩ እኔ ካለሁበት ብዙም አይሰማም ብቻ ሁለቱ ተያይዘው ከፊት እየመሩ ወደ አንድ ቤት ውስጥ አስገቡን። ቀጥሎም ስብሃት ነጋ እንዲህ አለ፤ ሌሎቻችሁ እዚሁ ቆዩ:: እኔ ፣ ገ/መድህን እና ሃለቃ ፀጋይ ብቻ የገዳሙን አስተዳዳሪ ለማናገር እንሄዳለን:: ከዚያም ሶስታችንም ተያይዘን ከነትጥቃችን ወደ ገዳሙ አስተዳዳሪ ቤት አቀናን:: የገዳሙንም አስተዳዳሪ ከቤታቸው አገኘናቸው:: ለአፍ ያህል ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ስብሃት ጊዜ ሳያጠፋ “የመጣነው ገንዘብ እንዲሰጡን ስለሆነ ያለዎትን ሁሉ ይስጡን!” አላቸው። ለመነኩሴው ግር የሚል ትዕዛዝ ነበር:: ብዙም ሳያቅማሙ “እኔ አልሰጥም፤ የእመቤቴ ብርሃን ንብረትና ሃብት ላይ የማዘዝ መብት የለኝም:: አልሰጥም::” በማለት እቅጩን በግልጽ አማርኛ ተናገሩ:: ስብሃትም አይኑን እያጉረጠረጠ ድምጹን ከፍ አድርጎ አምጡ ማለቱን ቀጠለ:: ስብሃት በቀላሉ እንደማይመለስ በድምጽም ፊቱን በመቀያየርም እንዲረዱ አደረገ ፣ ምስኪኑ አባትም አማራጭ እንደሌላቸው ተረዱ::ትንሽ አስብ አደረጉና ወደውስጥ ገብተው የተቋጠረ ከረጢት ተሸክመው መጡ።
ባዘነ አንደበት እንዲህም ሲሉ ተናገሩ ፤ “የቤተ ክርስቲያን ሃብት ወድጄ ፈቅጄ ሳይሆን የሰጠኋችሁ አስገድዳችሁ እና አንቃችሁ እንደወሰዳችሁ እወቁት::” ከዚያም ከረጢቱን አልሰጥም በማለት ብር 50,000 የታሰረ ገንዘብ ከፊቱ ዘረገፉለት። ስብሃትም በፍጥነት ይዘነው በመጣነው ‘ሃቨር ሳክ’ በሚባል ወታደራዊ ሻንጣ ሞልተን ተሸክመን እንድንወጣ አዘዘ:: እኛም የተባልነውን አደረግን:: ባህታዊውም በመውጫችን ላይ እንዲህ አሉ፤ “ነገ ጠዋት ለሕዝበ ክርስቲያኑ የሆነውን ሁሉ እናገራለሁ::” የተዘረፈውን ገንዘብ እኔና ስብሃት ተሸክመን ተመልሰን በለሳ ማይሃምቶ ገባን።
የተፈጸመውን የዘረፋ እና የገዳም ደፈራ የአካባቢው ሕዝብ ሁሉ ሰማው፤ በተሰራው ስራም ክፉኛ አዘነ፤ አወገዘውም። ስብሃት ድርጊቱ የየግል ምስጢራችን ሆኖ መጠበቅ እንዳለበት አስጠነቀቀን። ለዘረፋው ስራም ባለን ድርጅታዊ ታማኝነት እንደተመረጥን ገለጸልን። እንግዲህ ይህ አንድ ገጠመኝ ብቻ ነው:: ዘረፋ፣ ማውደም ፣ ታሪክ እና ቅርስ ማጥፋት ፣ የእስላምም ይሁን የክርስቲያን ቤተ እምነቶችን መድፈር እና ማበላሸት ለህወሃት የሰርክ ስራዎች ናቸው::
በአለቃ ገበረ ሃና ስም የሚነገር አንድ ታሪክ አለ:: ልጅቷ አለቃ ጋር ሄዳ “ጎረምሶቹ ሁሉ ድንቼ ፣ ድንቼ እያሉ ይጠሩኛል:: ለምን ይመስልዎታል::” ብትላቸው አለቃም እንዲህ አሉ:: ” ሊልጡሽ ፈልገው ነዋ!”:: ትናንትና በዘር እና በሃይማኖት እየመረጠ የአንድን አገር ወንድማማቾችን አንዱን ለአንዱ ታሪካዊ ጠላትህ ነው ፤ ላንተ ህልውና ከኔ በላይ ላሳር እያለ ሲመጻድቅባቸው የነበሩ የሃይማኖትም ሆነ የብሄር ቡድኖችን ከነጠለ በኋላ ያለ ሃይ ባይ ሲያጠቃ እያየን ነው:: ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ እስር ቤቶች አስር ሺህ በሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ታጭቀዋል:: በቃሊቲ ፣ በጨለንቆ ፣ በዝዋይ ፣ በሸዋ ሮቢት ፣ እና በሌሎችም በይፋ ባልተመዘገቡ የወያኔ ማጎሪያዎች ውስጥ ዜጎች ያለሃጥያታቸው ታስረው ይሰቃያሉ::
ስርዓቱ ዛሬ ላይ በሰፊው በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ የመጨረሻውን ዱላ ከማንሳቱ በፊት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንን የማጥቃቱን ስራ ሙሉ አቅሙን አሳርፎ ሰርቷል:: ከኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች በቀር በጉዳዩ ብዙም ግድ ያለው አልነበረም:: ነገ ደግሞ ተረኛ የካቶሊካዊት ወይም የሌላ ወንጌላውያን ቤተክርስቲያናት ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አይከብድም:: ይህን ዘረኛ እና ከፋፋይ ስርዓት በመታገስ እና በማስታመም የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል ነገ ጥቃት ተቀባይ ሊሆን አይገባም::
ስለወያኔ ማንነት ይኸው ለአመታት የተናገርኩት አንድ በአንድ ጊዜውን እየጠበቀ ሲፈጸም አየን:: አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምጽ በቃ የሚሉበት ጊዜ ላይ ደርሰናል:: የለውጥ ጊዜ እየቀረበ ነው:: ኢትዮጵያውያን አይን ለአይን ተያይተው ፤ ልብ ለልብ ተግባብተው ይህንን ዘረኛ እና ፋሺስታዊ ስርዓት ከዚያች ቅዱስ አገር የሚያጠፉበት ጊዜ በእውነትም እየቀረበ ነው:: ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲሰሩ ምን ማድረግ እንደሚችሉ እስከ አፍንጫው በታጠቀው የወራሪው የፋሺስት ኢጣልያ ጦር ላይ የተቀዳጁትን የአድዋውን ድል ማስታወሱ ብቻ በቂ ነው::በአዲስ ተስፋ ለህልውናቸው እና ለቀጣይ ትውልድም የምትበቃ አገር እና መንግስት ለማቆም ሊሰሩ የሚገባበት ወቅት እየመጣ ነው:: በመጨረሻም ከሰሜን እስከ ደቡብ ፤ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ:: እስላም እና ክርስቲያን ሳይሉ ፤ ኦሮሞ ፣ አማራ ፣ ትግሬ ፣ ጉራጌ ፣ ወላይታ ፣ አገው ፣ አፋር ፣ ቤኒሻንጉል ፣ ስልጤ ፣ አደሬ ነኝ ብለው ወያኔ በሰፋላቸው የዘረኝነት ወጥመድ ውስጥ ሳይወድቁ እጅ ለእጅ ተያይዘው ለወሳኝ የፖለቲካ ለውጥ እንዲሰሩ ጥሪዬን አስተላልፋለሁኝ::
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ገብረመድህን አርዓያ
ፕርዝ፣ አውስትራሊያ