Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Sport: የጎደለው ሊቨርፑል

$
0
0

ብሬንዳን ሮጀርስ በሊቨርፑል ባሳለፉት የመጀመሪያው ዓመታት ደጋግመው የሚሰነዝሩት አስተያየት ነበር፡፡ ‹‹እንደ ቡድን በመከላከል ረገድ መሻሻል ይገባናል›› ይሉ ነበር፡፡ ‹‹እንደ ቡድን›› የሚለው ቃል መላው ቡድኑን የሚወክል አይደለም፡፡ የተከላካዩን መስመር ብቻ ለመጥቀስ ፈልገው ነው፡፡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን ሮጀርስ ሊቨርፑል ከኋላ ኳስ እየመሰረተ እንዲጫወት ለማድረግ ጥረዋል፡፡ አሰልጣኙ ማየት የሚፈልጉትን የጨዋታ ዘይቤ ቡድኑ የመጫወቱ ነገር ሙሉ ለሙሉ ባይባልም ምልክቶችን አሳይቷል፡፡ እያደርም መሻሻል ተስተውሎበታል፡፡ የመከላከል ስህተቶች የቡድኑን መልካም ስራ አፈር ሲያለብስ ታይቷል፡፡ ከሁሉም በላይ ማርቲን ስከርትል ጥያቄ ውስጥ ገብቷል፡፡
suarez
ስሎቫኪያዊው የመሀል ተከላካይ በ2011/12 የሊቨርፑል ኮከብ ተጨዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር፡፡ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በሊቨርፑል ሁለተኛ ጨዋታ ላይ ወደኋላ ያቀበላት ኳስ ያስከፈላቸው ዋጋ የዓመቱ ችግሩ መነሻ ሆናለች፡፡ ሮጀርስ ኳስ ከኋላ ጀምሮ እንዲመሰረት መፈለጋቸው ለስከርትል መልካም አልሆነም፡፡ የአስቶንቪላው ክሪስቲያን ቤንቴኬ በአንፊልድ በሊቨርፑል ተከላካይ መስመር ላይ ሲረማመድ ግን የማስጠንቀቂያው ደውል ይበልጥ ጮኸ፡፡
ሮጀርስ ቡድኑ የበለጠ እስኪጎዳ ድረስ መጠበቅ አልነበረባቸውም፡፡ ችግሩን ለማቃለል በወሰዱት እርምጃ ስከርትልን ወደ ተጠባባቂነት አወረዱት፡፡ በምትኩም አንጋፋውን ጄሚ ካራገርን ወደ ቋሚው አሰላለፍ መለሱት፡፡ ከውሳኔው በኋላ ስከርትል የቋሚነት ዕድል ያገኘው ከትንሹ አልድሃም ጋር ባደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡ በማንኛውም ሰዓት ከባድ ስህተት ሊፈፀም የሚችል የመሰለው የተከላካይ መስመር በካራገር መመለስ ቢያንስ በመሪነት ችሎታው ተጠቀመ፡፡ ሆኖም ካራ ፍጥነት ያለው ተጨዋች ባለመሆኑ ሮጀርስ ለሚፈልጉት ወደፊት መጥቶ የመከላከል ዘዴ አይሆንም፡፡ ከበስተኋላው ሰፊ ክፍተት ትቶ ወደ ፊት የሚገፋ ተከላካይ መስመር ከተጣሰ የመሀል ተከላካዩ ፈጣን ካልሆነ ጉዳቱ ብዙ ነው፡፡ እናም የሮጀርስ ወጥቶ የመከላከል ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ሆነ፡፡ ከአዲሱ ዓመት መግባት በኋላ ግን ሊቨርፑል በመልሶ ማጥቃት ወደ ሚጫወት ጠንካራ ቡድንነት ተቀየረ፡፡ በዚያው ጊዜ በአንፊልድ ምርጥ ጨዋታዎችን ማሳየት ጀመረ፡፡ ሆኖም ካራገር በውድድሩ ዘመን ማብቂያ ላይ ከተጫዋችነት ለመገለል መወሰኑ ለሮጀርስ ራስ ምታት ይዞ መጣ፡፡ አሰልጣኙም የኋላ መስመራቸውን ሙሉ ለሙሉ ለመቀየር ግዴታ ውስጥ ገቡ፡፡
የሊቨርፑል ተከላካይ ድክመት በመሀል ብቻ አልነበረም፡፡ የሆዜ ኤንሪኬ ብቃት ቀባይነት ይጎድለዋል፡፡ ብቃቱ ሲመጣለት አስደናቂ ጨዋታን ያሳያል፡፡ ሆኖም የተመልካቹን ቆሽት የሚያሳርርባቸውን ጨዋታዎች ጥቂት አልነበሩም፡፡ በማጥቃቱ ደጋፊውን ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ በራሪ የክንፍ ተጨዋቾች በተቃራኒው ሲገጥሙት ደግሞ በመከላከሉ ረገድ ተብረክርኮ ይቀራል፡፡
በተቃራኒው መስመር ብንመለከት እንደግሌን ጆንሰን የሚያጠቁ ፉልባኮች ብዙ አይደሉም፡፡ ሲከላከል ካለፉት ጊዜያት የበለጠ ብቃት ነበረው፡፡ ሆኖም ስቴዋርት ዳውኒንግን በግራ መስመር ተከላካይነት በማሰለፍ አሮን ሌነንን ማጋፈጥ ከባድ ስህተት ይሆናል፡፡
በ2012/13 ሊቨርፑል 43 ጎሎች ተቆጥረውበታል፡፡ ቀደም ባለው ዓመት ደግሞ 40 ጊዜ መረቡ ተደፍሯል፡፡ የቻምፒየንስ ሊግ ቦታን እንዳያገኝ ዋነኛ እንቅፋት የፈጠረበት ተከላካዮች በግል የሚፈፅሟቸው ስህተቶች ናቸው፡፡
የዳንኤል አገር እና የስከርትል ጥምረት በውድድር ዘመኑ የመጀመሪያ ጫዋዎች ላይ ሊመለስ ይችላል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ኳስን መጫወት ከሚችሉ የመሀል ተከላካዮች ግንባር ቀደሙ ዳንኤል አገር ነው፡፡ ባለፈው ውድድር ዘመን ከአገር የበለጠ ጨዋታ የተጫወቱት የሊቨርፑል ተጨዋቾች ስቲቭን ዤራርድ እና ግሌን ጆንሰን ብቻ ናቸውው፡ አገር ምን ያህል የማይዋዥቅ ብቃት እንደነበረው ይህ መረጃ ጠቋሚ ነው፡፡ በ2011 ስከርትል ከዚህ ዴንማርካዊ ጋር ልዩ ጥምረትን በመፍጠር ከፍ ሲልም ለተከላካይ መስመር እንደ ቡድን መዋሃድ ምክንያት ሆነው ነበር፡፡ ስከርትል ኳስን በእግሩ ይዞ የአገር ያህል ችሎታ ባይኖረውም ሰፋ ያለ ርቀት መሸፈን የሚችልና ተንቀሳቃሽ ነው፡፡ ጠንካራ ጎኑን ለመጠቀም መቻሉ በራሱ ልዩ ችሎታ ነው፡፡ ሆኖም የማት ስሚዝ መጫወቻ ሲሆን ማየት ደጋፊውን የሚያስደስት አይደለም፡፡ ድክመቱ በራስ መተማመን ችግር ይምጣ ወይም በችሎታ ማነስ ይከሰት መልሱ ያከራክራል፡፡ ይሁን እንጂ በሊቨርፑል ከቆየ በሮጀርስ የብቃት ትንሳኤ ማግኘቱ የማይቀር ይመስላል፡፡
ኮሎ ቱሬ የመጪው የውድድር ዘመን አማራጭ የመሀል ተከላካይ ይሆናል፡፡ ቱሬ ከአገር ጋር ሊጣመር ይችላል፡፡ ኮሎ ከሁለት የተለያዩ ክለቦች ጋር ሊጉን ማሸነፍ ከቻሉ ጥቂት ተጨዋቾች አንዱ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ እንዲሁም የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ከሆኑ በኋላ ለሊቨርፑል ከተጫወቱ እጅግ ጥቂት ተጨዋቾች አንዱ ነው፡፡ ሮጀርስ የሚፈልጉትን ‹‹የማሸነፍ ስነ ልቦና›› ከራሱ ጋር ይዞ ወደ ቡድኑ መጥቷል፡፡ ከአገር የአየር ላይ የመከላከል ብቃት ጋር የተሟላ ጥምረት ለመፍጠር ያስችላል፡፡ ቱሬ አርሰናል አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ ሻምፒዮን ከሆነበት ዘመን የነበረው ፍጥነት እምብዛም አልቀነሰም፡፡ ባለፉት ሁለት የውድድር ዘመናት በሮቤርቶ ማንቺኒ ተጠባባቂ መደረጉ አሁን ራሱን ብቁ መሆኑን ለማሳየት እንዲነሳሳ ያደርገዋል፡፡
በቀኝ ፉልባክ ቦታ ያሉት አማራጭ ተጨዋቾች ሊቨርፑል ተለዋዋጭ ብቃት እንዲኖረው ያስችሉታል፡፡ ጆንሰን የክለቡ ተቀዳሚ የቀኝ መስመር ተከላካይ ነው፡፡ በሁለቱም እግሮቹ የመጫወት ችሎታው ባስፈለገ ጊዜ የሆዜ ኤንሪኬ ተለዋጭ እንዲሆን ተጨማሪ ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ሆኖም የቀኝ መስመሩን ይዞ መቀጠሉ የማይቀር ይመስላል፡፡ በስተግራ የሚዋዥቅ ብቃት ቢኖረው እንኳን ሆዜ ኤንሪኬ ባለፈው የውድድር ዘመን በቂ አገልግሎት በመስጠቱ ቦታውን ጠብቆ ይቀጥላል የሚለው ግምት ሰፊ ነው፡፡
ከክለቡ አካዳሚ ያደገው አንድሬ ዊዝደም በመነሻው የመሀል ተከላካይ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንደ ብዙሃኑ ወጣት ተከላካዮች ሁሉ በ2013 የግሌን ጆንሰን ተቀያሪ ተደርጎ በሁሉም ውድድሮች በ19 ጨዋታዎች በቋሚነት ተሰልፏል፡፡ በአየር ላይ ጠንካራ ነው፡፡ ፍጥነቱም የሚደነቅ ነው፡፡ ማርቲን ኬሊም የመሀል ተከላካይ ሲሆን አብዛናውን የሊቨርፑል ተጨዋችነት ሕይወቱን በቀኝ መስመር ተከላካይነት አሳልፏል፡፡ በፉልባክነት በተጫወተባቸው በእነዚህ ጊዜት የጠቀማቸው አብይ ጉዳይ ከኳስ ጋር ያላቸው ችሎታ ነው፡፡ በማጥቃቱ ረገድ የግሌን ጆንሰን ያህል ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ አሰልጣን ሮጀርስ እንደሚፈልጉት ኳስን በመጫወት የማይታሙ ተከላካዮች መሆናቸው ግን ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
በቀኝ ፉልባክነት እንዲጫወቱ በተጠሩ ቁጥር የሮጀርስን አንጀት የሚያርሱበት ሌላ ብቃትም አላቸው፡፡ የቡድኑ ተከላካይ ወደ መሀል ሜዳ ተጠግቶ ሲጫወት መስመሩን በመጠበቅ አይታሙም፡፡ ዊዝደምና ኬሊ የሊቨርፑል የነገዎቹ ተከላካዮች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ይሁን እንጂ ብቃታቸውን የበለጠ እንዲያጎለብቱ የበለጠ የጨዋታ ዕድል ማግኘት አለባቸው፡፡ በመጪው የውድድር ዘመን ሊቨርፑል ዩሮፓ ሊግ ላይ አይሳተፍም፡፡ ስሊሊህ ሮጀርስ ወጣቶቹን በካፒታል ዋን ዋንጫ እና በኤፍ.ኤ.ካፕ ላይ ሊያጫውቷቸው ይችላሉ፡፡ ከመደበኛው የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ይልቅ ተቀያሪዎችን ለማጫወት የሚመጥኑ ሌሎች ውድድሮች የሉምና፡፡
የቡድን ለውጥ
ሰባስቲያን ኮአቴስ በ2011 ኮፓ አሜሪካ ላይ ያሳየውን ብቃት በሊቨርፑል መድገም አልቻልም፡፡ በ2011/12 የአገር ስከርትል ጥምረት ውጤታማነት የቦአቴስን የጨዋታ ዕድል ገድቦበት ነበር፡፡ የመጫወት ዕድል ሲያገኝ ደግሞ ይርበተበታል፡፡ አይረጋጋም፡፡ 1.96 ሜትር የሚረዝመው ቁመቱ በአየር ላይ ጥቅም ቢሰጠውም በኦልድሃሙ ማት ስሚዝ ሲፈነጭበት ያሳየው ድክመት ደጋፊዎችን የሚያስጨንቅ ነው፡፡ ኮአቴስ ኳስን ሲይዝ መጥፎ ተጨዋች አይደለም፡፡ ነገር ግን ፍጥነት ይጎድለዋል፡፡ ኬሊ ወይም ዊዝደም አብረውት ከተሰለፉ ፍጥነቱን ከእነርሱ ጋር ለማስተካከል ይቸገራል፡፡ ቦታውን ጠብቆ የመጫወት ችሎታው ጥንካሬው ነው፡፡ በስፔን ወይም በጣልያን ክለቦች በውሰት ሲሰጥ በጠንካራ ጎኑ የበለጠ ማገልገል በቻለ ነበር፡፡ መጪው ዓመት የዓለም ዋንጫ የሚደረግበት እንደመሆኑ የዑራጓዩ ኢንተርናሽናል የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል ካገኘ ለመመረጥ ይጠቅመዋል፡፡
ሊቨርፑል ማርቲን ስከርትልን በውሰት ለመስጠት ሀሳብ እንዳለው ተወርቷል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ ላይ አራት የውድድር ዘመናት ያሳለፈው ስሎቫኪያዊ ግን በውሰቱ ይጠቀማል ተብሎ አይገመትም፡፡ በእነዚህ ጊዜያት ከቋሚ ተሰላፊነት ይልቅ በተጠባባቂነትና ከዚያም በታች የሆነባቸው አጋጣሚዎች ይበዛሉ፡፡ ቢሆንም በጥሩ ያሳለፋቸው የውድድር ዘመናትም አሉ፡፡ በዕድሜው ለጋ ወጣት ባለመሆኑ ሊቨርፑልን የሚለቅ ከሆነ በቋሚ ዝውውር እንጂ በውሰት አይሆንም፡፡ በራስ መተማመኑን መልሶ ካገኘ ደግሞ ሊቨርፑል የስከርትል- አገርን ጠንካራ ጥምረት በድጋሚ ሊያገነው ይችላል፡፡ ሁለት የመሀል ተከላካዮች (ስከርትል እና ኮአቴስ) ሊቨርፑልን ሊለቁ የሚችሉበት ዕድል ካለ በያዝነው ክረምት ሮጀርስ የመሀል ተከላካይ የማስፈረም ከባድ የቤት ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሊቨርፑል ረጅሙን የግሪክ ተከላካይ ኪሪያኮስ ፓፓዶፓሎስ ለማስፈረም ሙከራ አድርገዋል፡፡ከረጅም ጊዜ የጉልበት ጉዳት በኋላ በቅርቡ ጤንነቱን ማግኘቱ ተነግሯል፡፡ ከኳስ ጋር ባለተሰጥኦ ተከላካይ ሲሆን ተጋጣሚዎችን ይዞ ለማስቀረት የሚያስችል አካላዊ ጥንካሬ ባለቤትም ነው፡፡ ወደ አንፊልድ መምጣቱ እውን ከሆነ በቶሎ ወደ ቋሚ ተሰላፊነት የመግባት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡ ገና የ21 ዓመት ወጣት ሲሆን የእርሱ መኖር የማርቲን ኬሊን እና አንድሬ ዊዝደምን ዕድገት ያቀጭጫል፡፡ ዊዝደም በውሰት ካልተሰጠ በስተቀር፡፡
ሊቨርፑል በቦታው ሊገዛው ይችላል ተብሎ የሚጠበቀው ሌላው ተከላካይ ቲያጎ ሱሪስ ይባላል፡፡ ፍጥነቱና ከኳስ ጋር ያለው ችሎታ ጥሩ ይመስላል፡፡ አሰልጣኝ ሮጀርስ የሊቨርፑል ተከላካይ ግራ ክፍል የማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው በይፋ ተናግረው ነበር፡፡ ጃክ ሮቢንሰን መጪውን የውድድር ዘመን በብላክፑል እንዲያሳልፍ በውሰት ተሰጥቷል፡፡ ከአርሰናል ጋር ሲጫወቱ ቲዮ ዋልኮትን በመጋፈጥ ተስፋ ሰጪ ብቃት አሳይቶ ነበር፡፡ ሆኖም ብላክፑል ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ለመመለስ በሚያደርገው ትግል ላይ ለአንድ የውድድር ዘመን ከተሳተፈ የተሻለ ተጨዋች ይሆናል የሚል ግምት አለ፡፡ የቤንፊካው ሎሬንዞ ሜልጋሬዮ የጆዜ ኤንሪኬ ተጠባባቂ ይሆን ዘንድ ወደ ሊቨርፑል ሊመጣ ይችላል፡፡ የቫሌንሲያው ዓሊ ሲሶኮም በቀዮቹ ለዝውውሩ ከታጩት የግራ መስመር ተከላካዮች አንዱ ነው፡፡ የ25 ዓመቱ ፈረንሳዊ ባለው የቦታ አያያዝና አጠባበቅ ብቃትና የመከላከል ጥንካሬ የተሻለ ተመራጭ ይመስላል፡፡
በግዢ ከማምጣት ይልቅ ወጣቶችን ማሳደግ ካስፈለገ የሊቨርፑል አካዳሚ አሰልጣኝ ከዋናው ቡድን ጋር አልፎ አልፎ የሚጫወት ተከላካይን እንዲጠቀሙ ሊደረግ ይችላል፡፡ የ17 ዓመት ሰሜን ዌልሳዊ ሎይድ ጆንሰን ሰሜን አየርላንዳዊው የቀኝ መስመር ተከላካይ ሪያን ማክላፍሰን ከአካዳሚው ሰልጣኞች አይን ውስጥ ይገባሉ፡፡ ማክላፍሰን ከአንድ ዓመት በፊት በዝግጅት ጨዋታ ላይ በአሜሪካ ከፍሪንቼስካ ቶቲ ጋር ተጋፍጦ ነበር፡፡ በመጪው የውድድር ዘመን በፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ጨዋታውን መጫወቱ የማይቀር ነው፡፡ የ19 ዓመቱ ብራድ ስሚዝ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን መጨረሻ ላይ በሊቨርፑል ዋናው ቡድን ውስጥ ለተጠባባቂነት የበቃ ቢሆንም ጉዳት ህልሙን እውን እንዲያደርግ አግዶታል፡፡
ሊቨርፑል ረጅም ጊዜ ያገለገለውን ካራገርን ቢያጣም የአካዳሚው ተስፋዎችን ጨምሮ አማራጭ ተስፋዎች አሉትት፡ አሰልጣኝ ሮጀርስ የሚወስዱት እርምጃ ሁሉ ተከላካይ መስመሩን ለረጅም ጊዜ ከመገንባት አንፃር እንደሚሆን እርግጥ ነው፡፡ ሩቁን ማሰብ ብቻ አላማ አይሆንም፡፡ በቅርቡም ሊቨርፑልን ወደ ቻምፒየንስ ሊግ መመለስ የሚችል ተከላካይ መስመርም እንደሚያስፈልጋቸው ይረዳሉ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>