(ዘ-ሐበሻ) ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ በአማርኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን ላይ እየተካሄደ ያለውን የዘር ማጽዳትና ማጥፋት ዘመቻ አስመልክቶ ጥሪ አቀረበ። ቅዱስ ሲኖዶሱ ለዘ-ሐበሻ በላከው መግለጫ ” ሀገራችን ኢትዮጵያ በአምላኳ ጥበቃና በሕዝቧ ፍቅር ነፃነቷንና አንድነቷን ጠብቃ ለብዙ ዘመን ኖራለች። አንድነቷን ከነፃነቷ አስተባብራ የኖረች በመሆኗም ነፃነትን ለሚናፍቁ ሕዝቦች ሁሉ ምልክት ነበረች። በዚህም ምክንያት ለነፃነት የተነሡ ሁሉ ሰንደቅ ዓላማዋን አርማቸው ኢትዮጵያዊነትን አርማቸው አድርገው በነፃነት መንገድ ላይ ተጉዘዋል። እግዚአብሔር አምላክም ለሕዝባችን በሰጠው አርቆ አስተዋይነትም፥ አገሩን የሚከፋፍል ነገር በመካከሉ እንዳይገባና አገራችን በቅኝ ገዢዎች እጅ እንዳትወድቅ ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ኖሮአል። እንግዶችን መቀበል፥ አብሮ መብላት፥ አገር ማልመድ የቆየ ኢትዮጵያዊ ባሕላችን ነው። በዚህ ኢትዮጵያ ባህል ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ባህል ከባህል ጋር ተስማምቶ ኢትዮጵያዊ ውበት ያለው ሕብር ፈጥሮአል።” ካለ በኋላ ” የኢሕአዴግ መንግሥት አገራችንን ኢትዮጵያን በጠመንጃ ኃይል ከተቆጣጠረበት ጊዜ አንሥቶ ግን ይህ የኢትዮጵያ አንድነት ከባድ አደጋ ውስጥ ይገኛል። አገሪቱን በዘርና በጎሣ በመሽንሸን፥ አንዳች ችግር ቢፈጠር በአንድነት አገራዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ እንዲበታተኑ የሚያደርግ የጎሣ ፖለቲካ በሕገ መንግሥቱ ላይ ቀርጾ አስቀምጧል። ይህን ያደረገው የራሱን እድሜ ለማርዘም ነው። በዚሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሰብአዊ መብት ጥሰት፤ የመልካም አስተዳደር እጦት እና የኑሮ ውድነት እየጨመረ መምጣቱ የሚታወቅ ነው። የዘር ማጥፋት ዘመቻውንም መልኩን በመቀያየር በቦረናና በአርባ ጉጉ፥ በጋምቤላና በኦጋዴን፥ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአፋር፣ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በቤኒሻንጉል በሚኖሩት ወገኖቻችን ላይ በማከናወን ላይ ነው። ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ይህ እየተከናወነ ያለው የዘር ማጥፋት ዘመቻ ጥቂቶች በብዙዎች ላይ ነግሠው እንዲኖሩ ለማድረግ የታቀደና የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ በመላው ዓለም ያለን ሕዝቦች የወገኖቻችንን ግፍና ስቃይ ተረድተን ጩኸታችንን በማሰማት ድምጹ ለታፈነበትና በሰቆቃ ላለው ሕዝብ ድምጽ በመሆን በዓለም የተለያዩ መድረኮች ጩኸቱን እንድናደርስለት ጥሪ ታቀርባለች።” ብሏል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ መግለጫውን ቀጥሎ ” በኤርምያስ ዘመን አምባገነን መሪዎች የነበሩ ሲሆን እምነት የሌላቸው እውነት የተለያቸው እግዚአብሔርን የማያከብሩ ሰውን የማይፈሩ ጨካኞች እውነትን የማይወዱ ሥልጣናቸውን ለማቆየት ሲሉ ብቻ እግዚአብሔርን የሚዋሹ ክፉዎች ነበሩ። ከዚህ የተነሳ ሕጻናትን በሥጋና በመንፈስ ይገሉ ነበር። ለዚህ ነበር እግዚአብሔር በኤርምያስ አድሮ ይህን የዋይታ መልዕክት ያስተላለፈው፤ ራሔል የምትወክለው ጠቅላላ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ነበር፣ ዋይታዋ ጩኸቷም በግፍ በጨካኞች ስላለቁት የእግዚአብሔር ሕዝብ ሕጻናት ነበር። ምክንያቱም ሕጻናቱ ከፉዎች ስለ ገደሏቸው አልቀዋል የሉም ሞተዋልና ነው። በክርሰቶስ ጊዜ የነበረው ሄሮድስም በደሉን እንደገና ስለደገመው ማቴዎስ ይህንኑ ቃል ተጠቅሟል፤ እኛም ዛሬ እየተጠቀምንበት ነው። ምክንያቱም በሄሮድስም በኤርምያስም ጊዜ የነበሩ መሪዎች ክፉ መንፈስም አሁን በኢትዮጵያ በአሉ መሪዎች ልብ ስለ አለ ነው፤ በአገሪቱ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው አካል በዚያን ወቅት ከነበሩት ሰዎች ጋር አንድ ዓይነት ስለሆነ ያንኑ ጩኸት እንጮኸለን። የኢትዮጵያ ወላጆች አሁን የራሔልን ጮኸት እየጮሁ ነው።
“ዛሬ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ ከፍ ብለን ከጠቀስነው ጊዜና ሁኔታ ይበልጥ የከፋ ሁኖ እናገኘዋልን። እናቶች እንባቸው ደርቆ የደም እንባ እያነቡ ይገኛሉ። ይሄው ከፋፋይ መንግስት ተከባብሮና ተፋቅሮ አብሮ የኖረውን ህዝባችንን በሃይማኖትና በዘር ማለትም እስላሙን ከክርስቲያኑ፤ ኦሮሞውን ከአማራው፤ ሱማሌዉን ከኦሮሞው፤ ስልጤውን ከጉራጌ፤ ከንባታ ከወላይታ፤ አፋርን ከኢሳ፤ ሲዳማውን ከጌዶ፤ አኚዋክን ከኑር ፤ ትግሬውን ከቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር ለማለያየት ወይም ለመከፋፈል እየሞከረ ነው። ይህ አልበቃ ብሎ አንድ ኢትዮጵያዊ በትውልድ ሀገሩ የመኖርና የዜግነት መብቱ ተነፍጎ አንዱን ዜጋ ከፍ አድረጎ በአንጻሩ ሌላውን ግን እንደ አውሬ በመቁጠር ከሰባዊ ፍጡር አሳንሶ በመመልከት በዜጎች ላይ የሚደረገው የዘር ማጥፋትና ማጥራት ግፍ ሲታይ ከዚህ በላይ ከተጮኸው ጩኸት የበለጠ ያስጮኻል።” ሲል ይቀጥላል።