Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሌሊሴ ተፈታች!

$
0
0

lelissie
ላለፉት 5 ዓመታት ያህል ከልጆቿና ባለቤቷ ተለይታ በእስር ስትማቅቅ የነበረችው ሌሊሴ ወዳጆ መፈታቷ በርካታ ኢትዮጵያውያንን ማስደሰቱ ተጠቆመ፡፡
የጋዜጠኛ ሌሊሴን መፈታት አስመልክቶ Ayyaantuu News Online ለንባብ ባበቃው ዜና እንዳመለከተው በስደት አውስትራሊያ ከሚኖረው ከባለቤቷና ከልጆቿ ጋር ተቀላቅላለች፤ ድረገጹ ዜናውን በምስል በማስደገፍም አቅርቦታል፡፡
በጋዜጠኝነት ሲያገለግል የነበረው ባለቤቷ ዳቢሣ ዋቅጂራ አገር ጥሎ መሰደዱን ተከትሎ በማታውቀው ምክንያት የኦነግ አባል ነሽ በማለት ኢህአዴግ 10ዓመት ያለ አመክሮ ፈርዶ ወኽኒ እንዳወረዳት ይታወሳል፡፡ ይህንን ህዝብን ያበሳጨና ያስቆጣ ጉዳይ ሌሊሴ ከታሰረችበት ጊዜ ጀምሮ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና ዓለምአቀፉ የጋዜጠኞች መብት ጥበቃ ድርጅት (CPJ) ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሲያወግዙትና እንድትፈታ ሲሟገቱ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
“በኢትዮጵያ የፖለቲካ እስረኛ የለም” በማለት ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ደሳለኝ የተናገሩትን ተከትሎ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ታህሳስ 24፤2005ዓም (January 2, 2013) በዘገበበት ወቅት፤ ጋዜጠኛ ሌሊሴ ወዳጆን የሰው ልጆችን ኅሊና ከሚፈታተኑት የማኅበራዊ ጉዳዮች ጋር በማያያዝ የግምባር ዜና አድርጓት እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከአብራኳ የወጡትን ልጆቿን የማሳደግ ወግ የተነፈገችው እናት ከ3 ልጆቿ ጋር ሆና የሚያሳየውን ምስሏ አስደግፎ ጎልጉል በወቅቱ ሲዘግብ ጠ/ሚ/ር ሃይለማርያም ለተናገሩት ቅጥፈት ማጣፊያ በማድረግ ነበር፡፡
በእስር ቤት ታጉረው ከሚገኙት በርካታ የኢትዮጵያ ውድ ልጆች መካከል አንዷ ስለሆነችውና ስለአጠቃላይ የግፍ ቀንበር የተጫነባቸው ወገኖች በወቅቱ ለጎልጉል አስተያየት የሰጡት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ የአቶ ሃይለማርያምን ንግግር “በእውነቱ ይህ ፍጹም ቅጥፈት የተሞላበትና አጸያፊ ነው፤ እነዚህ እስረኞች እኮ በቁጥር የሚታወቁ ብቻ ሳይሆኑ ስም፣ ቤተሰብ፣ ልጅ፣ ዘመድ፣ ወዘተ አላቸው፡፡ እናውቃቸዋለን፤ ዓለም ያውቃቸዋል፤ እንግዲህ ጠ/ሚ/ሩ ለእነዚህ ልጆችና ቤተዘመዶች ነው አባታችሁ/እናታችሁ/ዘመዳችሁ ወንጀለኛ አሸባሪ ነው እንጂ የፖለቲካ እስረኛ አይደለም እያሉ ነው ያሉት፤ … ይህ ሥነምግባር የጎደለው ንግግር ነው” በማለት ዕርቃኑን አስቀርተውት ነበር፡፡
“ሌሊሴ ከዚህ ቀጥሎስ?” በሚል በህይወት የተፈተነችበትን የእስርቤት ቆይታዋና በተመሳሳይ ሁኔታ በእስር የሚማቅቁትን ኢትዮጵያዊ ወገኖቿን አስመልክቶ የሚደርስባቸውን ከአንደበቷ ለመስማት የሚጠብቁ ወገኖች እንደሚሉት ከሆነ “ሌሊሴ ጭንቀቷን ለተጨነቀላት የኢትዮጵያ ህዝብ የመፈታቷን ዜናና የእስር ቤት ቆይታዋን ከራሷ አንደበት እንሰማለን” ብለው እንደሚጠብቁ ይናገራሉ፡፡
ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለባለቤቷ፣ ለልጆቿ፣ ለቤተሰቦቿና ከእስር እንድትፈታ እንደየእምነታቸው ለጸለዩና ለተጨነቁ በሙሉ በጋዜጠኛ ሌሊሴ ወዳጆ መፈታት እንኳን ደስ አላችሁ ይላል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ በየእስርቤቱ የሚማቅቁትን የቤተሰብ አውራና የአገር ተረካቢዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የድምጻችን ይሰማ አስተባባሪዎች እና ሌሎች ንጹሃን ዜጎች መንግሥት እስርቤት አጉሮ ዕርምና ቂም ራሱ ላይ ከሚከምር ተመሳሳይ እርምጃ በመውሰድ ችግሩን ቢያስተነፍስና ወደ ዕርቅ ቢመጣ የተሻለ እንደሆነ የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸው የመብት ተሟጋቾች ምክራቸው ይሰጣሉ፡፡ (ፎቶዎቹ የተወሰዱተ ከ Ayyaantuu News Online)

ምንጭ ጎልጉል ድረገጽ


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>