ከመሐመድ
ፖሊስ የኛ አይደለም ሊሆንም አይገባውም፡፡ “ፖሊስ” ለዚህ ጽሁፍ ሲባል “ኢህአዴግ” የተባለ የማፊያዎች ስብስብን ለመጠበቅ ህዝብን በአደባባይ ሊያሸብር ህጋዊ ፈቃድ የተሰጠው የደደቦች ስብስብ ነው፡፡ ፖሊስ ደደብ ነው፡፡ ማገናዘቢያውን በኢህአዴግ የሽብር ቡድን የተቀማ ህጻናት ፣ ሃረጋውያን ፣ ነብሰ ጡር ፣ ሴት ፣ ሰላማዊ ሰዎችን ፣ መንገደኛ መለየት የተሳነው እንሰሳ ነው፡፡ ፖሊስ ክብሪት ነው፡፡ አምጣ የወለደችውን እናቱን ለመደብደብ የማያቅማማ ቅል ራስ፡፡
ጉዞ በጦር ቀጠና….
ከብሔራዊ …በአዋሽ ወደ ኮሜርስ….. ቱርርር ድጋሚ ወደ አዋሽ ባንክ ፣ በአርቲስቲክ ወደ ብሔራዊ ባንክ ሆም መዘክር ፣ ታጥሯል መንገዱ ቱርርር ወደ ተገኘው ቅያስ ሰዎች ተደብድበዋል ፣ መስገጃ ፣ ጫማዎች ፣ አማይማ ፣ ኮፊያ ፣ የተፈነከቱ ሰዎች ፣ የተያዙ ወጣቶች ፣ ረጃጅም አጠና የያዙ የባንዳው ውሾች ፣ በፋራረሱት መንደሮች አቆራርጠን እዚያችው ትንሽ ፈቀቅ ብለን…
…አትሩጡ …አትሩጡ… ጥግህን ያዝ!! ጥግጥጉን ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር … የተለያዩ የመንግስት መስሪያቤቶች የሙስሊሙ እስር ቤት ሆነዋል፡፡ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ በብዙ ውሾች መሃል የተያዙ ወንድሞቼን ተመለከትኩኝ….አንዱ ውሻ ጋረደኝ ሁሉንም ለመቁጠር አልቻልኩም ……..አንድ ..እእ….ሁለት ተነጥለው ሌላ …ሁለት…. ወዲ…ያ ….ሌሎች የታሰሩ ግን በስንቱ መስሪያ ቤቶች ስንቱ ሙስሊም ታስሯል…! መስሪያ ቤቶች ባጠቃላይ (ያሲን ኑሩ በሆነው ሲዲው ላይ አጀልህ ከደረሰ ሁሉም ነገር አንተን ለመግደል ሰበቢያ መሆን ይችላል ብሎን ነበር) ሙስሊሙን ለማሰር አፋቸውን ከፍተው ሲጠብቁን አስተዋልኩ…ናሽናል ጂዎግራፊ ቲቪ ላይ በብዙ ነብሮች የተከበበችውን ሚዳቋ ትዝ አለችኝ… ከመንጋዋ የተነጠለችውን አንዷን ሚዳቋ ጥቂት የነብር መንጋ ከበው ሲበሏት ለመን መንጋው አይታደጋትም ስል ጠየኩ…..ዛሬም ከጀምአው እየነጠሉ የሚደበደቡትን ወንድሞቼን ለመርዳት ሳይሞክሩ ነብስን ለማዳን የሚራወጡት ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ከሚናዝኑት ከብዙው የህዝን መንጋ ጥቂቱን ብቻ አስተዋልኩ…ጥቂት ናቸውና የባንዳው ሰራዊት በቀላሉ አጠቃቸው….
አንድም ባስ አልተሰበረም ፣ አንድም ድንጋይ ሲወረውር የተመለከትኩት ሰው አልነበረም፡፡ በእርግጥ …..መብትን መጠየቅ ሽብር አይደለም ፣ እራሱ ገዳይ እራሱ ከሳሽ ፣ በሃገራችን ሰላም አጣን ፣ መንግስት የለም ወይ ፣ እንትን የህዝብ ነው (ይሄን እኔ አላልኩም) ፣ ኢቴቪ ፣ዛሚ ፣ ፋና ፣ መንግስት ፣ ወዘተረፈዎች ሌባ ናቸው ብለናል፡፡ የህዝብን አደራ የበሉ ፣ ከህዝብ አብራክ ወጥተው ህዝብ ላይ ቁልቁል የሚተፋ ወሽካታ አድርባይነታቸውን ነግረናቸዋል፡፡ ጥፋታችን በግፍ የታሰሩብንን መሪዎቻችንን እንዲፈቱልን መጠየቃችን ነበር፡፡ በሃይማኖት ጣልቃ አትግቡብን ፣ ህገ መንግስቱ ካልተተገበረ የወረቀት ነብር ነው ብለን ብሶታችንን ማሰማታችን …….
በአጠና ተነረትን ፣ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ፊት ለፊት ግንቡ ጥግ ስር እራሱን ስቶ የወደቀው በግምት እድሜው ወደ ስልሳዎቹ የሚጠጋው አዛውንት መሃል አናቱ ተበርቅሶ ደሙ እየፈሰሰ ማንም እንዳይረዳው የባንዳው ሰራዊት ከበው ሞቱን ይጠብቃሉ ፣ ጉዞ ወደ ጥቁር አንበሳ!! ብሔራዊ ሜትሪዮሎጂ ፊት ለፊት ያለው የባንዳው ሰራዊት ጣቢያ ፊት ለፊት ባለው ሚዲያን/የአስባልት አካፋይ ተዘርግፈው የወደቁ ሰዎች ይታዩኛል ፣ አንድ አባት ከሁለት (በግምት የአስራ አራት እና ከአስራ ስምንት የማይበልጡ) ልጆቹ ጋር አፈር መስለው ሶስቱም በባዶ እግራቸው የሰውዬው ኮት በጭቃ ጨቅይቶ የሴቶቹ ልብሶች አፈር መስሎና ጸጉራቸው ተንጨባሮ በቢታንያ ክሊኒክ ቅያስ ብቅ አሉ፡፡ የሰራዊቱ ጣብያ በር ላይ ደም ረግጠን በቅያስ ወደ ሞሃ እድገት በስራ ት/ት ቤት ደረስን፡፡ ከጦር አውድማው ወጥተን መስሎን ጫማችንን ሱሪያችንን ልናነጻ ቀልባችንን ልናረጋጋ ሊስትሮ ፍለጋ ስንኳትን ከእናቱ ጋር የተለያየ አንድ ከአስራሁለት አመት የማይበልጥ ልጅ አይኖቹ ወዲያ ወዲህ ሲሉ አይን ለአይን ተገጣጠምን፡፡
እየተቅለሰለሰና እየተርበተበተ “ከእናቴን ጋር ተጠፋፋን ወደ መሳለሚያ 01 መንገዱን አሳዩኝ..” ሲል ልመናውን አቀረበ፡፡
እናቱ ታየችኝ!! ልክ ብሔራዊ ባንክ ጋር ጥጉን ካሰለፏቸው ሰዎች መካከል አንዲት ነብሰ ጡር ሁለት ልጆቿን ይዛ ርህራሄ የማያውቁትን እነዚህን የባንዳውን ሰራዊት ያዝኑላት ዘንድ ስትለምናቸው…ሚጣ በሚሯሯጡት ሰዎች ተረግጣ እሪሪሪ ስትል ከልጇ እኩል የምታነባዋ ብሔራዊ ቲያትር ጋር የየኋት እናት በአይኔ ይዞሩ ጀመር፡፡
“እናትህ ስልክ ይኖራታል..!” የኔ ጥያቄ ነበር ከልጁ ይልቅ የእናቱ ጭንቀት በአይኔ እየዞረ…
“የላትም!”
“ና” በል! ጉዞ በሞሃ ወደ በርበሬ በረንዳ…ከአብነት ፣ ከምራብ ፣ ከተክለሃይማኖትና ከሜክሲኮ ያሚመጡ መንገዶችን የሚያገናኘው መስቀለኛው መንገድ ላይ ሊስትሮ ስንፈልግ ከተክለሃይማኖት ቱርርር እያሉ አናታችን ላይ ሊወጡ … ወደ ጭድ ተራ ቱርር…ሃደሬ ሰፈር ውስጥ ውስጡን ሰዎች ይሯሯጣሉ ዞር ስል ልጁ ከአጠገቤ የለም!! የት ገባ!! በቃ አንድ ሰው ያሳየዋል ብዬ ጥሩውን ጠረጠርኩ!! ከጭድ ተራ ወደ ምናለሽ ተራ ምናለሽ ተራ ጋር የሰላም ቀጠና ነው ብለን እርግት ፣ ቅዝቅዝ ፣ ትክዝ ፣ ፍዝዝ እንዳልን…ከወደ ሰላም ባልትና አካባቢ ቱርርር ወይ ዛሬ!! ምናለሽ ተራ ያላትን ቁሶች ኁላ ቆሽ…ኮሽ…ስብር …ብረታብረቶችን ድስጣድስጦችን ፣ ማንኪያዎችን ምናምኖችን ሽክም ይዞ ቱርርር ….የጭንቅ ቀን አይመሽም!! በሃያሁለት ቀበሌ ወደ ድሬ ህንጻ ሰባተኛ፡፡ አሁን ሰላም ነው፡፡
ስለምን ይሄ ሁላ ውርጅብኝ….አንድም ጠጠር እንኳ ባላነሳ ህዝብ ላይ ግን ለምን!!
የመንግስትን መግለጫ ለማዳመጥ ሞባይሌን አውጥቼ ዛሚን ከፈትኩ …ኤንሶ ኤንሶ…ይላል…ወደ መስተዳድሩ ኤፍ ኤም….አይኬ ..ጫምባላላ ይላል…ወደ 97.1 የእስፖርት ዝውውር ይዘግባል አንዱን ሃገር በቀል ተጫዋች ጋብዘው….98.1 የአምስት ሰዓት ዜና ጀመረ…ጆሮዬን ሰክቼ ቀልቤን ሰብስቤ በትካዜ ማድመጥ ጀመርኩ፡፡
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከንቲባ ጽ/ቤት አቶ እከሌ በአዲስ አበባ እስታዲየም በመገኘት መንግስት ድህነትን ለመቀነስ በሚያደርገው እርብርብ ህዝበ ሙስሊሙ እያደረገ ያለውን አስተዋጽዎ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገነዘቡ፡፡ የኢድ ሶላትም ህዝበ ሙስሊሙ በተገኘበት በአዲስ አበባ እስታዲየም በሰላም ተካሂዶ እንደተጠናቀቀ ከኢዜአ ባገኘነው መረጃ ለማወቅ ተችሏል” ብሎ ኩም አደረገኝ፡፡ አሁን አመመኝ፡፡ አሁን ጆሮዬን ጠዘጠዘኝ፡፡ /…./