ምሥጢረ ኃይለ ሥላሴ – ዙሪክ/ስዊዘርላንድ
በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የባሕልና የስፖርት ፌደሬሽን አስተባባሪነት ለ13ኛ ጊዜ ያዘጋጀው የእግር ኳስ ውድድር እ.አ.አ. ከሐምሌ 15-18 በፍራንክፈርት ከተማ ተካሂዷል። በ1ኛ ዲቪዚዮን 18 ቡድኖች፣ በ2ተኛ ዲቪዚዮን 12 ቡድኖች ተመድበው፣ በወጣቶችም ከ7-10 እና ከ11-14 ዕድሜ ክልል ውስጥ ባሉ ወጣቶች መካከል በተደረገ ፉክክር አሸናፊዎቹ የተዘጋጀላቸውን ሽልማት ተቀብለዋል። በዚህም መሠረት ከ1ኛ ዲቪዚዮን እንደ አምናው ኢትዮ ኖርዌ ከኢት ሎንዶን ገጥመው ባልተጠበቀ ሁኔታ ሎንዶን በፍፁም ቅጣት ምት አሸንፎ ድጋሚ ዋንጫውን አንስቷል። ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ከአዲስ አበባ የመጣው የአበበ ቢቂላ ቡድንና የጣልያኑ ኢትዮ ኢሚይልያ ተጋጥመው ኢሚይልያ አሸንፎ ዋንጫ አግኝቷል። በወጣቶች ከ7-10 በፍጹም ቅጣት ምት 5 ለ4 ፣ ጀርመን ኢትዮ ስዊስን ሲያሸንፍ ከ11-14 ኢትዮ ዙሪክ ኢትዮ ስዊስን 4-1 አሸንፎ ባለዋንጫ ሆኗል። የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ዮሐንስ የወጣቶቹ ውድድር እንዲሳካ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ለወጣቶቹ አሸናፊዎች ሽልማቶቹ ተመልካች በበዛብት በሚኖርበት ጊዜ ከትልልቆቹ ጋር፣ አለመሆኑ ምክንያቱ ግልጽ አልሆነም። ቢሆን ኖሮ ለወጣቶቹ ከፍ ያለ የሞራል እገዛ ይሆን ነበር።
ዘንድሮ በዳኝነት በኩል መልካም መሻሻል ታይቷል ቢባልም ሠዐት ያስከብራሉ ተብለው አደራ የተጣለባቸው ዳኞች በዚያ ጠራራ ፀሐይ ተጨዋቾቹን ሜዳ ላይ እያንቃንቁ በአንድ ወቅት ሊመገቡ ሄደዋል ሲባል በሌላ በኩል ያሉበት አልታወቀም ተብሎ ሲፈለጉ እንደነበረ እንዲህ በቶሎ አይረሳም። ጥላ በረድ እስኪል ተጠልለው ነው ያሉ ባይታጡም ቢያማክሩን ተጨዋቹቹም ሆነ ተመልካቹ መላ ይፈልግ ነበርና መጠነኛ ቅሬታና ማጉረመረመም እንደነበረ መጥቀሱ አስፈላጊ ይመስለኛል። በነገራችን ላይ የቅዳሜው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርትም ይጀመራል ከተባለው 4 ሰዓት ከ30 ያህል ዘግይቶ መጀመሩጊዜና አዘጋጂዎቹ እንዳልተጣጣሙ ያመላክታል። እንዲያው የሚመለከታቸው ወገኖች መሻሻል ይኖርባቸዋል ከሚለው ዝርዝር ውስጥ እንዲያስገቡትና ለወደፊቱ ቢታረም አይከፋም ተብሎ እንጂ ስንቱ ጉድለት ተዘርዝሮ ያልቃል?
ከ11-14 የዕድሜ ክልል ውስጥ ተሳትፎና የዋንጫውን የመጨረሻ ጨዋታ ኢትዮ ስዊስን 4 ለ1 ያሸነፈው የኢትዮ ዙሪክ ታዳጊዎች ቡድን፤
ይኽ ፌደሬሽን የተጣመመውን እያቃና እንዲሄድ ሲያስተካክል አበጀህ እያልን ሲወላገድና መስመሩን ሲለቅ እየጠቆምን መቆየታችን በተለይ የፌደሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ አካላት በሚገባ ይገነዘቡታል የሚል እምነት አለኝ። በዚህ ረገድ ቅንጅት ስዊዘርላንድ ፓልቶክ ክፍል ከፌደሬሽኑ ሰዎችና ከተመልካችም ሆነ የቡድን መሪዎች አስተያየቶችን እያሰባሰበ ይኽ ፌደሬሽን ስህተቶችን እያረመ ከስፖርትና ኢትዮጵያዊነት ውጪ ያሉትን ነገሮች ሁሉ ሳይደበላላቅ በስፖርቱ፤ ከተቻለም ባሕልን ማስተዋወቁና ማስጠበቁ ላይ እንዲተኮር አሳስበናል። በዓመት አንድ ጊዜ ለተወሰኑ ቀናት ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚገናኙበት፣ በተለይ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገሮች ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ሕፃናትና ወጣቶች ሲገናኙ የሚፈጥረውን ሰሜት ስንመለከት በፌደሬሽኑ መጎልበት ሁላችንም ተጠቃሚዎች መሆናችን ግልጽ ነው። ግን ለመሆኑ ፌደሬሽኑ አድጓል፤ቀጭጯል ወይንስ ባለህበት ሂድ ነው? ማደግ ማለትስ ምንድነው? እንዴትስ ይለካል? እስቲ በስሱ እንፈትሸው፤ አንድ ልጅ ከተወለደ በሁዋላ በየዓመቱ የሚያሳያቸው ለውጦች ከኣቅፍ ወደ ዳዴ ማለት ከዚያም እየተውተረተሩ መራመድና እራሱን ችሎ እስከ መሮጥ መድረሱ ከጤናማ እድገት ጋር የሚመጡ የእድገት መለኪያዎች ሲሆኑ በአዕሞሮ ማደግም እንዲሁ ጊዜውን ጠብቆ ሲመጣ በ13 ዓመት ዕድሜው ምን ያህል አድጓል?ይኽ ፌደሬሽን የዛሬ 13 ዓመት ሲመሠረት የተወለዱ ልጆች እዚህ ፍራንከፈርቱ ውድድር ላይ ከ11-14 ዕድሜ ክልል ውስጥ ተካተው ተጫውተዋል፤ ትልቅ እድገት፣ ትልቅ ለውጥ ነው። እንግዲህ የፌደሬሽኑን እድገት እንዲህ ስንለካው ጤናማ እድገት አሳይቷል? በሀላፊነት ላይ የተቀመጡትስ አብረው ማደግ ችለዋል? ዛሬ በበዐሉ ላይ የሚገኘው ሕዝብ ብዛት በአውሮፓ ነዋሪ ከሆነው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር በውን አድጓል? ሕዝቡ እርስ በርሱ ተጠራርቶና ተገባብዞ ስለተገናኘ ፌደሬሽኑ ያመጣው እድገት ነው ማለት ይቻላልን? እስቲ የፍራንክፈርቱን ዝግጅት ጠለቅ ብለን እንየው። ምንም እንኳን የፌደርሽኑ ስም እንደሚጠቁመው የ“ስፖርት እና የባሕል“ ቢባልም ከእግር ኳስ ሌላ ምንም አይነት የስፖርት እንቅስቃሴ አልታየም። ሩጫ የተባለውን አላየንም፣ የሴቶች የመረብ ኳስ (ቮሊ ቦል) አልነበረም። ከወትሮው ለየት ያለ እንቅስቃሴ ነበር ከተባለም ከአርብ ጀምሮ በሁለቱ ዋና ዋና መግቢያዎች ላይ የመግቢያ ዋጋ እናስከፍላለን ብለው የፌደሬሽኑ ተወካዮች ክፈል አልከፍልም የሚል ግብ ግብ እንደ ስፖርት እንቅስቃሴ ካልተቆጠረ በስተቀር ማለቴ ነው።
ይኸ ዓመታዊ ዝግጅት በተለያዩ አባል ቡድኖች ባሉባቸው የአውሮፓ ከተማዎች ውስጥ ሲዘጋጅ በአብዛኛው ቡድኖቻቸውን ተከትለው አለበለዝያም ወዳጅ ዘመድ፣ አንዳንድ ጊዜ በድምጽ (በይበልጥ የፓልቶክ ታዳሚዎች) የሚያውቁትን በአካል ለማግኘት የሚመጣው እንደሚበልጥ ያስታውቃል። እስካሁን በነበሩት ዝግጅቶች ሁሉ ማለት ይቻላል በአውሮፓ ቀበሌዎች ካሉት ቁጥር ስፍር ከሌላቸው የስፖርት ማዕከላት ውስጥ ደረጃቸውን የመጠኑ ሜዳዎች ተመርጠው ውድድሮችን አስተናግደዋል። ደረጃቸውን የመጠኑ ሲባል፤ በቂ ማለትም ቢያንስ ሦስት ሳር ወይም ሰው ሠራሽ ሳር ለበስ ሜዳዎች፣ተጨማሪ የመለማመጃ ሜዳዎች፣ ቢያንስ ለዋና ዋና ጨዋታዎች የተዘጋጀ ባለ መቀመጫ (ስታድዮም መሰል ሜዳ/ትሪቡን፤ መብራትና ውሃ፣ በቂ የመጸዳጃ ቤቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። ) የ13ኛው በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የባሕልና የስፖርት የኳስ ውድድር አሸናፊ የሆነው ኢትዮ ሎንዶን ቡድን
ከሁለተኛ ዲቪዚዮን ኢትዮ አበበ ቢቂላን አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት የሆነውና ወደ 1ኛ ዲቪዚዮን የተዘዋወረው የጣልያኑ ኤሚልያ ቡድን
ፍራንከፈርት ከዚህ ለየት በጣም ለየት ያለ ነበር።ለዚህም ምክንያቱ አዘጋጂዎቹ የኢትዮ-አዲስ ፍራንክፈርት ቡድን ሰዎች በመጀመርያ ይዘነዋል ብለው በምስል የተደገፈ|“ማስረጃ“ ከላኩና በቡድን ተወካዮች ካስጎበኙ በሁዋላ ቦታው ስለተከለከለ ተለዋጭ ተብሎ የተያዘ መሆኑን በይፋም ባይሆን ሲነገር ሰማን። ከሚታጎል ተብሎ የተያዘ ነው ማለት ነው።ይሁን እንጂ ከዚህ የተሻለ በፍራንክፈርትና አካባቢዋ አልተገኘም ለማለት በጣም ይከብዳል።የብዙዎቹ ግምት የተሻለ ለማግኘት የበለጠ መከፈል ስለሚኖር የቁጠባ ሥራ ተሠርቷል ነው። ዋናው ሜዳ (ቁጥር 1) የተባለው የተንጣለለና ፊት ለፊት የሚገኝ ላሉት ሁለት!! ሽንት ቤቶች ቅርበት ይኑረው እንጂ መቀመጫ የሌለው በፍጹም ጨዋታ ለመመልከትም የማይመች ሲሆን ከሌሎች ሁለቱ ግን የተሻለው ነው ማለት ይቻላል። ሁለተኛው ሜዳ ወደ ሗላ ሸጎጥ ያለ ሆኖ የተሰመሩት መስመሮች ሁሉ ተረጋግጠው ለመለማመጃ እንጂ ለመጫወቻ የተዘጋጀም አይመስል። ሦስተኛው ሜዳ ሀገራችን „አሸዋ ሜዳ“ የምንለው እዚህ አውሮፓ በዝናብ ወራት ቡድናት ለመሟሟቅያ የሚጠቀሙበት አሸዋ ለበስ ሜዳ እንጂ ለመጫወቻ የተዘጋጀ አይደለም። እዚያ ላይ ወድቆ ሳይገሸላለጥ የተነሳ የለም በብዙ መልክ የተቻላቸውንና አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ሳይታክቱ ሲያደርጉ የነበሩትን አስተናጋጆች እጀ ሰባራ ካደረጉት አንዱ የሜዳዎቹ ጥራት ዝቅተኝነት መሁኑ መነገር ይኖርበታልና በዚህ በኩል አልተሳካም። በዚህ ላይ ፌደሬሽኑ የመግቢያ ማስከፈል ሲጀምር ለምኑ? የሚለው ጥያቄና የሜዳዎቹ ጥራት የለሽነት ጎልቶ ታዬ እንዲያም ክፍያው „የኮቴ“ ነው ያሉ ጥቂቶች አይደሉም።
ምግብና መጠጥ በተመጣጣኝ ዋጋ ቀርቧል። የሚያስመስግን ዝግጅት ነው። ቅሬታ የፈጠረውና ብዙ ሰዎችን ሲያስመርር የሰማነው ነገር ቢኖር የመጠጡና የምግቡ ቦታ ተራርቆ ትኬቱ ደግሞ የሚሸጠው ሌላ ቦታ መሆኑ በተለይም የጎብኝዎቹ ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ሰልፉ ረጅም ጊዜ የወሰደና አሰልቺ መሆኑ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው ሁለት መጸዳጃ ክፍሎች ለ ብዙ ሽህ ሰዎች እንዴት ተደርጎ ተፈቀደ? ብዙዎቹን ከምር አበሳጭቷል። የትኬት ሽያጭ! ሰልፉን ፈርቶ በርከት አድርጎ የገዛ በዕለቱ ሙሉ በሙሉ ካልተጠቀመበት ይቀልጣል ማለትም ይከስራል። ብዙ ጭቅጭቅም ተፈጥሯል።
ለምን? አዘጋጅዎቹ አላስፈላጊ ውዝግብ ውስጥ ሲዘፈቁ አይተናል።በዚህ ላይ የመግቢያ ዋጋ ፌደሬሽኑ በመጠየቁ ብዙዎቹን አበሳጭቷል፣አነታርኳል። መቀመጫ አንኳን ሳይዘጋጅ ለምንድነው የመግቢያ እንድንከፍል የተጠየቅነው? ያሉ ጥቂት አልነበሩም። እምቢ ብለው አምባጓሮ የፈጠሩም ነበሩ። ክፍያ ለምን? ምን ተደረገና? ብዙ ብዙ ተጠይቋል፤ አሁን ዝም ብለን ከከፈልን ፌደሬሽኑ በቋሚነት ኪራይ ሰብሳቢ ሊሆን ነው እያሉ ስጋታቸውን የገለፁ አያሌ ሰዎች አጋጥሞናል።
ይህ በዚህ እንዳለ ከአሁን ጀምሮ ፌደረሽኑ እራሱ እያዘጋጀ ገንዘቡም ለፌደረሽኑ በፌደረሽኑ የሚወሰንና ዝግጅቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር መወሰኑን ሰማን። እንዴት? ቢያንስ እስከ አሁን ድረስ ለማዘጋጀት እድሉ ያልገጠማችው ክለቦች እንዲያዘጋጁ አይፈቀድላቸውም? ፌደሬሽኑስ ከአገር አገር ተዟዙሮ የማዘገጀቱ አቅሙ አለው? በቅርብ ሰለማውቀውና እስካሁን የማዘጋጀት እድሉ ስላልገጠመው ስለ ኢትዮ ዙሪክ ትንሽ ማለት ፈልግኩ። ከሁለት ዓመታት በፊት (2013) ውድድሩ በኢትዮ ስዊስ አዘግጅነት ስዊዘርላንድ /ኒዮን በተዘጋጀበት ወቅት ሁሉም ነገር ጣራ የነካ ውድነት የታየበት በመሆኑ ሕዝብ ተማሯልና ስዊዘርላንድ ቢዘጋጅ ሰዉ አይመጣም የሚሉ አሉ። እውነት ነው በተጋነነ መልኩ ውድ ነበር። ያ ውድነት ከስግብግብነት የመነጨ አንጂ በምግብም ሆነ በሆቴል በኩል ከዚያን ጊዜው ቢያንስ እስከ 50% በቀነስ ሁኔታ ማዘጋጀት እንደሚቻል በባለሙያዎች የተደረጉት ጥናቶች ያረጋግጣሉ። ኢትዮ ዙሪክ የሚያዘጋጅ ከሆነና የመግቢያ ፌደሬሽኑ ማስከፈል ቢፈልግ እንኳን ለኮቴ ሳይሆን ለምን እንደሚከፍል ከፋዩ እራሱ ያውቀዋል። ከፋዮች ለሚከፍሉት የሚመጥን አገልግሎት ያገኛሉ። አሁን እንደሚሰማው፤ ፌደሬሽኑ በራሱ ላዘጋጅ ካለ፣ የሚዘጋጅበትን ሀገርና አካባቢ ኮሚኒቲ ሳያሳትፍ ምን አይነት ዝግጅት ሊሆን ይችላል? በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋትና በጥልቀት መወያየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል።
ከምድቡ 3ኛ ወጥቶ ከውድድሩ ቀደም ብሎ የተሰናበተው ኢትዮ ዙሪክ ቡድን፤
ከእግር ኳሱ ይልቅ በሊቢያ አይሲስ ለታረዱት ሰማአታት ቤተ ሰቦች ገንዘብ አሰባስቦ ኤርትራም ጭምር የሚገኙትን በማግኘት ባደረገው እርዳታ ታዋቂነትን አግኝቷል።