Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የመድረክ መስቀለኛ መንገድ

0
0

ተጻፈ በ  የማነ ናግሽ
Medrek Meeting in Addis
መድረክ በዘገምተኛ ሒደትም ቢሆን በጥናት ላይ የተመሠረተ የአደረጃጀት ሥልቱን ጀምሮ የጋራ አስተሳሰብ የያዘ ማኒፌስቶ በማውጣት ምናልባት በአገሪቱ ግንባር ቀደም ተቃዋሚ ድርጅት እየሆነ ይመስላል፡፡

ቀደም ሲል ይፋ ያደረገውን የፖለቲካ ፕሮግራሙን  አሻሽሎና ከጊዜ ጋር አጣጥሞ አሁን በድጋሚ ለሕዝብ ይፋ ባደረገው ማኒፌስቶው፣ በአብዛኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በስፋት የሚተቹበትንና በኢሕአዴግ ላይ ብዙ ጊዜ የሚያጠፉትን ጣት ቅሰራ ለጊዜውም ቢሆን በመተው ካለፈው የተማረ ይመስላል፡፡ ግንባሩ የመፍትሔ ሐሳብ የሚላቸውን አማራጭ የፖለቲካ እሳቤዎች ይዞ መጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) ‹‹ተረኛ›› ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው፣ የግንባሩ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና የግንባሩ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና በጋራ ሰሞኑን በሜክሲኮ የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን አዳራሽ ባለፈው እሑድ ያቀረቡት ማኒፌስቶ፣ ወቅቱን ያገናዘበ የፖለቲካ ዳሰሳ ከመሆኑም በላይ በተለይ መንግሥትን የሚያሳስብ ነው፡፡ በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በርካታ ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን፣ በውይይቱ ላይ የነቃ ተሳትፎም ነበራቸው፡፡

‹‹በሌሎች አገሮች የሆነው በእኛ የማይሆንበት ሁኔታ የለም››
‹‹የኢትዮጵያ ወቅታዊና መሠረታዊ ችግሮች የመፍቻ አቅጣጫዎች ማኒፌስቶ›› በሚል የቀረበው ይኼው ማኒፌስቶ አገሪቱ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ አገሪቱ ፍፁም አምባገነናዊ የአገዛዝ ባህሪያት ይታዩባታል ይላል፡፡ በተለይ በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ማግስት መድረክን፣ ኢዴፓንና መኢአድን ጨምሮ በሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲቀርቡ የነበሩትን አቤቱታዎች አንድ በአንድ ይዟል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎችም ከፋፍሎ አቅርቧቸዋል፡፡ በፖለቲካ ዘርፍ አብዮታዊ ዲሞክራሲ የተባለው የኢሕአዴግ የፖለቲካ ፕሮግራም የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲጠፋ ማድረጉን፣ የሕግ የበላይነትንና ገለልተኝነትን መጣሱን፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ጨርሶ እያጠፋ መሆኑን፣ ‹‹ሀቀኛ›› ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚደግፉ የሚደርስባቸው ሁሉን አቀፍ ማግለልና ጭቆና፣ እንዲሁም መንግሥት በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ለመደራደር ፈቃደኛ አለመሆን በስፋት ተንትኗል፡፡

ግንባሩ በመፍትሔነት ካስቀመጣቸው መካከል፣ አዘቅት ውስጥ ገባ ያለውን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ለመታደግ ይቻል ዘንድ፣ ‹‹ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ የምክክርና የውይይት መድረክ›› መፍጠር አስፈላጊነት በማስቀደም፣ የሚመለከታቸው የአገሪቱ ኃይሎች በሙሉ የመድረኩ ተሳታፊ እንዲሆኑ ይጠይቃል፡፡ ቀጥሎም ነፃ ዳኝነት እንዲኖር፣ ገለልተኛ ተቋማት እንዲፈጠሩና በነፃ ሚዲያ ላይ እየደረሰ ያለው አፈና እንዲቆም ይጠይቃል፡፡ በአገሪቱ እየተከሰቱ ያሉት የብሔርና የሃይማኖት ግጭቶች በሕገ መንግሥቱ አግባብ ገለልተኛ መፍትሔ ይሻሻሉ ይላል፡፡ የአገሪቱን የፖለቲካ ምህዳር እንዳያላውስ አድርገውታል ያላቸው ሕጎችም እንዲከለሱ ማኒፌስቶው ይጠይቃል፡፡

ይህንን በተመለከተ ለተሰበሰቡት የመድረክ ደጋፊዎች ያቀረቡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ የፖለቲካ እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፣ ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ታች ያሉ ካድሬዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በጋራ ተጠያቂ እንዲሆኑና ነፃ የሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ እንዲቁቋም ጠይቀዋል፡፡ ነፃ ሚዲያን በተመለከተ ጫና የሌለባቸው ነፃ የግል ሚዲያዎች እንዲፈጠሩ ጠይቀው፣ ‹‹ስለምርጫ ብዙ የምናወራው ዓለማችን ሕዝቡን የሥልጣን ባለቤት ለማድረግ ስለሆነ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሐሳባቸውን ሲያጠቃልሉም፣ ‹‹ባለፉት ጥቂት ዓመታት በሌሎች አገሮች አይቻልም ሲባል የነበረው ተችሏል፡፡ በእኛ የማይቻልበት ሁኔታ የለም፤›› ሲሉ በከፍተኛ ጭብጨባ ታጅበዋል፡፡

‹‹ኢሕአዴግ መሪም ነጋዴም ነው››
የማኒፌስቶው ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ክፍል ኢሕአዴግ የአገሪቱ ኢኮኖሚ አድጓል የሚል የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ መሆኑን፣ አብዛኛው ሕዝብ በከፍተኛ ኑሮ ውድነትና በሰቆቃ እንደሚገኝ ከፍተኛ የፖለቲካ አድልኦ የሰፈነበት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መኖሩን ያትታል፡፡ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ጥራት እንደሚጎድልባቸው፣ የፋይናንስ ሴክተሩን ወጥሮ በመያዝ የባንኮችና የኢንሹራንስ ድርጅቶች ሚና ገድቦ የያዘው የፋይናንስ ሥርዓት እንዲከለስ፣ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ በመጣስ በአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ መዛባትን ይፈጥራሉ ያሉዋቸውን የገዥው ፓርቲ የኢንቨስትመንት ድርጅቶች ወደ ገበያ ኢኮኖሚ አካልነት የሚዘዋወሩበት ሁኔታ ላይ መነጋገር ይገኝባቸዋል፡፡

በማኅበራዊ ጉዳዮችም የሥራ ዕድል አጥተው ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉ ያሉት ወጣቶች መታደግ፣ የሥራ ዕድል ከፖለቲካ ወገንተኝነት ለሁሉም ዜጎች ነፃ እንዲሆን፣ የትምህርት ፖሊሲው ብቃት ያላቸው ዜጎች እንዲያፈራ መከለስ፣ እንዲሁም የትምህርትና የሥልጠና ዕድሎች ከፖለቲካ ወገንተኝነት ለሁሉም ዜጎች በብቃትና ተወዳድረው የሚገቡበት እንደሆን በመፍትሔነት ያስቀምጣል፡፡

ይህንን ክፍል ለደጋፊዎቻቸው እያዋዙ ያቀረቡት ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ‹‹ዶ/ር ነጋሶ የኢሕአዴግን ሥራ ከእኔ በተሻለ ሁኔታ ስለሚያውቅ›› በማለት ተሰብሳቢዎቹን ፈገግ ያሰኙ ሲሆን፣ ‹‹የተቃዋሚዎች አንዱ ድላችን አቶ ስዬ አብርሃ፣ አቶ ገብሩ አስራትና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ወደተቃውሞ መድረክ ማምጣት መቻላችን ነው፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹የኢሕአዴግ ሃይማኖት›› ያሉት አብዮታዊ ዲሞክራሲ መሪነት የአገሪቱ የኢኮኖሚ መድረክ ከካድሬዎች ቁጥጥር ውጪ የሚሆንበት ሥርዓተ እንፈጥራለን ይላሉ፡፡ አገሪቱ እጅግ አሳሳቢ ሙስና መዘፈቋን ገልጸው፣ ‹‹ኢሕአዴግ መሪም፣ ነጋዴም ነው፤›› በማለት የድርጅቱ የቢዝነስ ኢምፓየር መሰበር አለበት ብለዋል፡፡

‹‹ኪራይ ሰብሳቢ ይለናል፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ ራሱ ኢሕአዴግ ነው፤›› ሲሉ በደጋፊዎቻቸው ከፍተኛ ጭብጨባ ታጅበው ነበር፡፡ እንደ መጨረሻ የመፍትሔ ሐሳብ ‹‹ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት በጥምረት ማቋቋም›› የግንባሩ እምነት ሲሆን፣ ይኼም ነፃና ፍትሐዊ ምርጫ ተደርጎ የፓርላማ ወንበር ካገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ነው፡፡ ሁሉም ‹‹ሀቀኛ›› የሚላቸው ተቃዋሚዎች እንዲተባበሩ የሚጠይቀው የመድረክ ማኒፌስቶ፣ የታሰበው የጥምረቱ መንግሥት ዋነኛ ሥራም አገሪቱ ገባችበት ከሚለው ሁለንተናዊ አዘቅት ለማውጣት በጋራ መረባረብ ነው፡፡ ዶ/ር መረራ መድረክና ሌሎች ‹‹ሀቀኛ›› እያሉ የሚጠሩዋቸው ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ሕዝቡም ከየትኛውም ጊዜ በላይ በላዩ ላይ የተጫነው አምባገነናዊ አገዛዝ ሥርዓት ለመላቀቅ ከጎኑ እንዲሰለፍ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

‹‹የመድረክ የትከሻ ስፋት ምን ያህል ነው?››
በርካታ የስብሰባው ታዳሚዎች አስተያየቶች ሲሰጡ አንዳንድ ጥያቄዎችም አንስተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል፣ ‹‹ከዘረዘራችሁት ሁሉ ችግር የምንወጣበት የነፃነት መንገድ ምንድን ነው? ወደዚህ ነፃነት ለመምራት የመድረክ ትከሻ ስፋት ምን ያህል ነው?›› በሚል ለቀረቡት ጥያቄዎች ዶ/ር ነጋሶ ሲመልሱ፣ ‹‹ሕዝቡ ነፃ መውጣት የሚችለው በራሱ ነው፡፡ እኛ የማታገያ ስልትና ስትራቴጂ ብቻ ነው መቅረፅ የምንችለው፤›› ሲሉ፣ ዶ/ር መረራ በበኩላቸው፣ ‹‹የመድረክ ትከሻ ስፋት የኢትዮጵያ ሕዝብን ትከሻ ያህል ነው፤›› በማለት አገር አቀፍ ውክልና ያለው ስብስብ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መድረክ የተለያዩ አደረጃጀቶች ያላቸውና ከአራቱ የአገሪቱ ክፍሎች የሚወከሉ ፓርቲዎች የመጀመርያ ስብስብ ነው ብለዋል፡፡

ሰላማዊ ሠልፍን በተመለከተም ጥያቄ የቀረበ ሲሆን፣ ‹‹ቁፋሮ እስኪያልቅ በሚል የቀረበውን ሰበብ ለምን ትታገሳላችሁ? ቁርጠኛ ከሆናችሁ እስረኞቻችንን ለማስፈታት እስከ ቃሊቲ እስር ቤት ወስዳችሁ አሠልፉን፡፡ ሕዝቡን ከሚያሰቃየው ኢሕአዴግ ጋርም ጥምረት ትፈጥራላችሁ ወይ?›› የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበዋል፡፡ ዶ/ር መረራ ‹‹ብሔራዊ እርቅን›› አስመልክተው ለጥያቄውን ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹እርግጠኛ ነኝ የኢሕአዴግ ጆሮ አንድ ቀን መስማት ይጀምራል፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴም የደርግም ጆሮዎች በመጨረሻ ሰዓታት መስማት ጀምረው ነበር አልተሳካላቸውም እንጂ፤›› ብለዋል፡፡ ‹‹ያለትብብር የሚሠራ ሥራ የትም አያደርስም፡፡ አንድ ቡድን የትም አገር ብቻውን መግዛት አይችልም፡፡ ማሸነፍ ይቻል ይሆናል መግዛት ግን አስቸጋሪ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የግንባሩ ሊቀመንበር አቶ ጥላሁን እንደሻው ነፃነትን በተመለከተ፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱ ጭቆና በቃኝ ማለት ሲችል ነው፤›› ብለው በጎሳ የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መድረክ ውስጥ አሉ ለተባለው በስሜት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ብሔሮች ‹‹በጎሳ›› መፈረጃቸው ያልጣማቸው አቶ ጥላሁን፣ ‹‹በብሔርና በኅብረ ብሔር እንጂ በጎሳ የተደራጀ ድርጅት የለም፡፡ አልነበረምም፡፡ ዋናው ጥያቄ የጋራ ራዕይ አለን ወይ ነው? በኢትዮጵያ ብሔርተኝነትም አንዳችን ከሌላችን የምንበላለጥ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

አንድነት ሰላማዊ ሠልፍ እያካሄደ ነው የመድረክ ሚናስ ምንድን ነው? ለሚለው ጥያቄ አመራሮቹ ቀጥተኛ ምላሽ አልሰጡም፡፡ በባንዲራው ላይ ያለውን ‹‹ዓርማ›› አስመልክቶ ለቀረበው ጥያቄ ግን መድረክ ተቃውሞ እንደሌለው አስታውቋል፡፡ ‹‹ምልክቱ የሃይማኖትና የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነትና አብሮነት አመላካች ከሆነ ምን ችግር አለው? ሕዝቡን ግን ማወያየት ይቻላል፤›› የሚል ምላሽ የሰጡት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹የብሔራዊ አንድነትን ጥምረት›› በተመለከተ ጠንከር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ምርጫ በነፃነት ይካሄድ እንጂ ኢሕአዴግን ለሚመርጥ ትልቅ አክብሮት ይኖረናል፣ ጥምረትም እንፈጥራለን፤›› ካሉ በኋላ፣ ‹‹ከዚህ ውጪ ዛሬም አንድ ብሔር አንድ ቋንቋ አንድ ሃይማኖት የሚል እምነት ያለው ፓርቲ ካለ ይሞክራት!›› በማለት ከዚህ በፊት ከተለመደው ከተቃዋሚዎች ወጣ ያለ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ይኼ አገር የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችና ሃይማኖቶች አገር ነው፡፡ ይህንን የማይቀበል አስተሳሰብ የትም አይደርስም፤›› በማለት ስም ሳይጠቅሱ ሸንቆጥ አድርገዋል፡፡

የመድረክ ረዥሙ መንገድ
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቃውሞ ታሪክ እንደ አገሪቱ ዲሞክራሲ ሁሉ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረ አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ በትረ ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 22 ዓመታት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማቆም ሙከራ አድርጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ውስጥ ከተካተቱ መብቶች ሁሉ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚቋቋምበት መንገድ የሚመለከት ሲሆን፣ እሱም በዲሞክራሲያዊ ምርጫ አግባብ ብቻ መሆኑን ይደነግጋል፡፡

ይህ የበለፀጉ አገሮች (በአብዛኛው ምዕራባዊያን) የሚያቀነቅኑት ሥርዓት አተገባበሩ ከአገር ወደ አገር በመጠኑ ቢለያይም ዋነኛ ማጠንጠኛው ግን አንድና አንድ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ቅድመ ሁኔታም፣ ግብም ነው፡፡ በሊብራል ሥርዓት ኢኮኖሚው በነፃ ገበያ መመራት እንዳለበት ሁሉ ፖለቲካው በነፃ መደራጀት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽና የተደላደለ የፖለቲካ ሜዳ መፍጠር የሚጠይቅ ሲሆን፣ ለዚህም ገለልተኛ የዲሞክራሲ ተቋማት መኖር፣ ነፃ ፕሬስ መበልፀግና የተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰብና ፕሮግራም ያላቸው የፖለቲካ ድርጅቶች መኖርን ይጠይቃል፡፡ መድረክ ያነሳቸው ጥያቄዎችም እዚህ ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡

በ1987 ዓ.ም. በኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት የፀደቀው ሕገ መንግሥት ለእነዚህ ሁሉ መብቶች ከለላ የሚሰጥ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያትም እስካሁን አራት አገራዊ ምርጫዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ ኢሕአዴግ አሸናፊ እየሆነ ሥርዓተ መንግሥቱን ቀላል ለማይባል ጊዜ በቁጥጥሩ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ድርጅቱ በተደጋጋሚ ምርጫ ያሸነፈበት መንገድ ግን አወዛጋቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጠቃቀስናቸው ፖለቲካዊና ሕጋዊ ማዕቀፎች በተግባር እንደሌሉ የሚያምኑ የመድረክ ሰዎች ሜዳው ለሁሉም ተወዳዳሪዎች እኩል አለመሆኑንና የፖለቲካ ጨዋታው ሕጉ ለኢሕአዴግ ያደላ ነው በሚል መከራከርያ ያቀርባሉ፡፡ ኢሕአዴግ በበኩሉ፣ ‹‹ተቃዋሚዎች ከጥላቻና ከቂም በቀል ስላልወጡ፣ አገር የመምራት አቅምም የላቸውም፡፡ ኢሕአዴግን ከመጣል ባሻገር አገር ለመምራት የሚያስችል የፖለቲካ አስተሳሰብና ፕሮግራም የላቸውም፤›› በማለት ይከራከራል፡፡ በተደጋጋሚ የሚሸነፉበት ምክንያትም የሕዝቡን አመኔታ ማግኘት ባለመቻላቸው መሆኑን ያስረዳል፡፡

በአገሪቱ የ20 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ ላይ ዳሰሳ ለማድረግ የሚሞክር ገለልተኛ አካል ግን እውነታውን በሁለቱም ጫፎች አያገኘውም፡፡ ሀቁ ያለው በሁለቱም ጫፎች መካከል ነው፡፡ ኢሕአዴግ የሚመራው የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ለሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች የሚያሠራ የተስተካከለ ሜዳ አለመሆኑን ብዙዎች ያስረዳሉ፡፡ እስካሁን በአገሪቱ የተከሰቱ ተቃዋሚዎችም፣ ከጥላቻና ከቂም በቀል ወጥተው የሕዝቡን አመኔታ የሚያስገኝ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳልነበራቸውም ይገነዘባሉ፡፡ ‹‹በመተባበር ወይም በመሰባበር›› አንድ ላይ የተሰበሰቡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢሕአዴግን የፈተኑ ቅንጅትና ኅብረት ‹‹ኢሕአዴግን ከመጣል›› ባሻገር ይኼ ነው የሚባል ግልጽ አማራጭ ፕሮግራም እንዳልነበራቸው ይወሳል፡፡ ለመተባበር የቸኮሉትን ያህልም ለውድቀት ሲፈጥኑ ለኢሕአዴግ ጣልቃ ገብነትም የተመቹ እንደነበሩ ብዙ ተብሏል፡፡

ቅንጅት ካረቀቀው እዚህ ግባ የማይባል ማኒፌስቶ ይልቅ ዶ/ር ነገደ ጎበዜ ለምርጫ 97 ያበረከቱት ‹‹ሕገ መንግሥት፣ ምርጫና ዲሞክራሲ›› የሚለው መጽሐፍ በተቃዋሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውና እንደ መመርያ የተከተሉት ሥራም ነበር፡፡ መደምደሚያው ባያምርም፡፡ ‹‹ኢሕአዴግን በ97 ዓ.ም. ምርጫ መጣል ምንም አማራጭ የለውም፡፡ ከተቻለ በምርጫ በእሱ ካልተቻለ በአመፅ ፈረንጆች (Election or Otherwise) የሚሉት ‹‹ሲሞቅ በማንኪያ ሲቀዘቅዝ በእጅ›› ዓይነት መንገድ የተከተለ ነበርና መጨረሻም አገሪቱ ወዳልተፈለገ የፖለቲካ አዘቅት ውስጥ የሚከት እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ሁለቱም ተቃራኒ ወገኖች በዚሁ የተሳሳተ መንገድ ያበረከቱትን ድርሻ ከፍና ዝቅ ቢያደርጉም፣ በየፈርጃቸው የፈጸሙትን ስህተት ሙሉ ለሙሉ አይክዱም፡፡ በሕዝቦች መካከል ሊከሰት የነበረው የእርስ በርስ ግጭት ባይሳካም፣ አሁንም ያልበረደ ጠባሳ ትቶ አልፏል፡፡ መድረክ ካለፉት ከእነዚህ ስህተቶች በአግባቡ ተምሮ ይሆን?

‹‹መቼም እንዳይደገም››
በ1997 ዓ.ም. ምርጫ ሥልጣን ለመያዝ በተደረገው ትንቅንቅ አላስፈላጊ ድርጊቶች መፈጸማቸው አይረሳም፡፡ ከምርጫው በኋላ የወጡ ሕጎች የፖለቲካ ምኅዳሩን የማያፈናፍን በማድረግ አሉታዊ ሚና መጫወታቸው ብዙ ተብሎለታል፡፡

ከአዲሱ የዲሞክራሲ ጭላንጭል አላግባብ የተጠቀሙትን ጨርሰው ከአገሪቱ የፖለቲካ ተሳትፎ የራቁ አሉ፡፡ የአንዱ ስህተት በሌላ የአፀፋ ስህተት እየተደገመ፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በ20 ዓመት ወደኋላ ተጎትቷል፡፡ ይህ የሚባልበት ምክንያት ሕዝቡ በተቃዋሚዎች ላይ ተስፋ ቆርጦም ይሁን፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር በመታፈኑ፣ ኢሕአዴግ የአገሪቱን የፖለቲካ አስተሳሰብ በሞኖፖል መቆጣጠር የሚያስችል 99 በመቶ የፓርላማ ወንበር ለብቻው መቆጣጠር ችሏል፡፡ ተፃራሪ ሐሳቦች ሲስተናገዱበት የነበረው ፓርላማ የአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሰዎች መሰብሰቢያ ሆኗል፡፡

‹‹አማካይ ስፍራ….››?
ከ2002 ምርጫ አንድ ዓመት ቀደም ብሎ መድረክ የተባለ ስብስብ ለመፍጠር የቀረቡት የእነ አቶ ስዬ አብርሃ፣ የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳና የዶ/ር መረራ ጉዲና ጥናታዊ ዳሰሳዎችም እነዚህን እውነታዎች ያገናዘቡ ነበሩ፡፡ ከዚህም ትምህርት የተወሰደ ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎቹን በሐሳብ ለማሰባሰብ ያስቻለና በብዙዎች ተቀባይነት ያገኘ የሚመስል ‹‹አማካይ ስፍራ›› የመፍጠር ሐሳብ ቀርቦ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በብሔር ላይ የተመሠረቱትን ድርጅቶች የማይቀበሉ ሳይቀሩ ለመጀመርያ ጊዜ በብሔር ላይ ከተመሠረቱት የእነ ዶ/ር መረራ የኦሮሞ ድርጅቶችና የአቶ ገብሩ አሥራት የትግራይ ተቃዋሚ ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት ተስማምተው አንድ አማካይ ስፍራ መድረክን ፈጥረዋል፡፡

በኅብረ ብሔር ላይ የተመሠረቱ የመድረክ ግንባር አባል ድርጅቶች አሁንም በአገሪቱ ፖለቲካ አወዛጋቢ በሆኑ፣ በተለይም በመሬት ባለቤትነትና በፌዴራሊዝም ሥርዓት አወሳሰን ላይ ስምምነት ላይ ደርሰው መድረክ ምን ማለት እንደሆነ የሚያሳዩበት ግልጽ የፖለቲካ አሃዳዊነት ግን አልፈጠሩም፡፡ በተቀሩት ጉዳዮች ላይ ግን ባልተለመደ ሁኔታ ሰፊና ፈርጀ ብዙ ፕሮግራም (ማኒፌስቶ) ይፋ አድርገዋል፡፡

አንድነት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ሰላማዊ ሠልፍ እያካሄደ ሲሆን፣ መድረክ በሌላ በኩል ማኒፌስቶውን እያስተዋወቀ ነው፡፡ መለያየታቸው በግልጽ ይፋ ባይወጣም፣ ግንኙነታቸው ግን ለብዙዎች ግልጽ አይደለም፡፡ አንዱ በሌላው እንቅስቃሴ ጣልቃ ባይገባም፣ አንዱ ከሌላው ጋር በትብብር እየሠራ ስለመሆኑ ማረጋገጫ የለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችም በሁለቱም ወገኖች በኩል መሸፋፈን ይስተዋላል፡፡ የመድረክንና የአንድነትን የወደፊት ግንኙነት የአገሪቱ የፖለቲካ ዕጣ ፈንታ የሚወስነው ይሆናል፡፡ ምናልባትም ኅብረ ብሔር ድርጅቶች ከብሔር ድርጅቶች ጋር አብረው መሥራት እንደማይችሉ ትልቁ የማሳያ ፈተና ይሆናል፡፡ የመድረክ መንገድ ወዴት ይሆን?

Source: <a href=”http://www.ethiopianreporter.com/index.php/politics/

Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles