Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ከደስታው በስተጀርባ  –ይገረም አለሙ

$
0
0

 

justiceበቅድሚያ እንኳን ደስ አለን፡፡ የሌት ቅዥቱ የቀን ስቅይቱ ሥልጣንና ሥልጣን ብቻ የሆነው ወያኔ ያለ ስማቸው ስም ሰጥቶ ያለ ግብራቸው ወንጀል ለጥፎ ህሊናቸውን ለሆዳቸው አሳልፈው የሰጡ አቃቤ መንግስትና ዳኞች ሰይሞ  በውህኒ ያኖራቸው እህት ወንደሞቻችን ከእስር ተፈተዋል፡፡ እነዚህ ወጣቶች ወንጀላቸው አንድና አንድ ነው፤ እናት ሀገር ኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ጸሀይ ልትሞቅ የምትበቃበትን፣ልጆቿ በፍቅር በሰላም በእኩልነትና በአንድነት መኖር የሚችሉበትን ሥርዓት መፍጠሪያውን መንገድ ማመላከታቸው፡ አገዛዝ በቃን ማለታቸው፣ የወያኔን ማንነትና የአገዛዝ እንዴትነት ማጋለጣቸው ሀሳባቸውን መግለጻቸው ወዘተ ነው ወንጀላቸው፡፡

ወያኔ አምስት ዓመት እየጠበቀ ምርጫ ያካሂድ እንጂ መጀመሪያም ለሥልጣን የበቃው ሀያ አራት አመትም በሥልጣን የቆየው በምንና እንዴት እንደሆነ ያውቀዋል፡፡ የሚኖረው በጠመንጃ ቀስፎ፤ በአንድ ለአምስት ጠርንፎ ጆሮ ጠቢ አሰማርቶ ብዙ ሆድ አደሮችን ገዝቶ ቢሆንም ሕዝቡ አጋጣሚ ጠብቆ ከተነሳ ምን ሊያደርገው አንደሚችል በምርጫ 97 አይቷልና ኮሽ ባለ ቁጥር እየደነበረ ትንሽ ነገር ባየ በሰማ ቁጥር ይቺ ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም እያለ ያስራል ይገላል ያሰድዳል፡፡የረጋውን ማዕበል ይቀስቅሱታል ብሎ የሚፈራቸውን በአይነ ቁራኛ ይጠብቃል አስፈራቶ ላንበርከክ ወይንም ደልሎ ጸጥ ማሰኘት ይሞክራል፡፡ ይህ አልሰራ ሲል ወንጀል ፈብርኮ የሀሰት ምስክር አሰልጥኖ በህግ ካባ ስውር ደባ ይፈጽማል፡፡

ህገ ወጥ ተግባሩ  ተቃውሞ አስነስቶ ከዛም ከዚህም ጥያቄ ሲበዛበትና ይህም ለሥልጣኑ አስጊ መስሎ ሲታየው እንዲህ እንደ ሰሞኑ ክስ አቋረጥኩ ምህረት አደረኩ ወዘተ ይልና ያልፈጠረበትን ቅዱስ ለመምሰል ይሞክራል፡፡ስለሆነም በእህት ወንድሞቻችን ከእስር መፈታት የመደሰታችንን ያህል ከዚህ ደስታችን በስተጀርባ ይህ የሆነበትን ምክንያት መመርመር ማወቅና መዘጋጀት ብሎም የተጀመረው ትግል ይበልጥ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን፡፡

ርእዮት አለሙ ለጋዜጠኞች ስትናገር ከእስር ቤት ውጪ ሲሉኝ አመክሮ አልሞላሁ ይቅርታ አልጠየቅሁ በምን መንገድና ምክንያት ነው ውጪ የምትሉኝ ተመልሼ የምመጣ ከሆነ አልወጣም አልኳቸው ያለችው ወያኔን በደንብ በማወቋ ነው፡፡ ሁላችንም እንዲህ አውቀን ከደስታችን በስተጀርባ ይህ ለምን ሆነ፣ወያኔ ምን ገጥሞት ምንስ አስቦ ነው ይህን ያደረገው ብለን ማሰብ መምከር ይኖርብናል፡፡ይህ ካልሆነ ግን የወያኔ የማስቀየሻ ስልቱ ሰራለት ማለት ነው፡፡ ስለ ወያኔ ሳስብ፣

ገደልን እንዳይሉ ሞተው አገኙዋቸው

ማረክን አንዳይሉ ሰው የለ በእጃቸው

ምን አሉ አንግሊዞች ሲገቡ ሀገራቸው

ለወሬ አይመቹም ተንኮለኞች ናቸው

የሚለው በአጼ ቲዎድሮስ ሞት  የተገጠመውና በተለያየ መጻህፍት የተገለጸው የለቅሶ ስንኝ ይታወሰኛል፡፡ ወያኔዎች ሥልጣናችንን ለማቆየት ይጠቅመናል ካሉ ምንም ነገር ከማድረግ ወደ ኋላ አይሉም፡፡ የተናገሩትን መካድ የሰሩትን አይኔን ግንባር ያድርገው ማለት የገቡትን ቃል ማፍረስ ለእነርሱ ተራ ነገር ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ሥልጣን ነውና፡፡

ቅንጅቶችን አስረው በገጠማቸው ተቃውሞና ተአቅቦ ከገቡበት ማጥ ለመውጣት አቶ መለስ ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅን አማልደኝ ሲሉ ከርመው እስረኞቹ ሲፈቱ 18 ወራት በፈጀ የሀገር ባህል ወግ መሰረት በሽምግልና አንደተፈቱ በመንግስት መገናኛ በብዙሀን ቀኑን ሙሉ ሲነገረን ውሎ በእሰረኞቹ መፈታት የፖለቲካው ትኩሳት በርዶ ወያኔዎች ሲረጋጉ የተፈቱት በሽምግልና ሳይሆን በህግና በህግ ነው ማለታቸውን የምንረሳ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አልፈውም አቶ መለስ ነብሳቸውን ፈጣሪ እንደፍላጎቱ ያድርጋትና ሽምግልና ብሎ ነገር አልነበረም ብለው በአደባባይ መካዳቸውን የማያወቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ለብርቱካን ሚደቅሳ ዳግም መታሰር ምክንያት የሆነውም ይሄው ነው፡፡

ወያኔዎች ለሥልጣናቸው ሲሉ ርኩስ ተግባራቸውን  በራሳቸው ሰዎችም ላይ ከመፈጸም ወደ ኋላ እንደማይሉ አይተናል፡፡አቶ ታምራት ላይኔን ስኳር አታሎኝ የከተማ ኑሮ አማልሎኝ የጓደኞቼን ምክር አልሰማ ብዬ አጥፍቼአለሁ ካልክ አንተም ሆነ ቤተሰብህ ምንም አትደረጉም ብለው ቃል ገብተው ለህዝብ በቀጥታ በተላለፈ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ካስለፈለፉዋቸው በኋላ እንደ አሰሩዋቸውና የራሳቸውን ንግግር እንደ ማስረጃ እየቆጠሩ ሲያብጠለጥሉ ሲወነጅሉዋቸው አይተናል ሰምተናል፡፡ወያኔ ስልጣኔን ያቆይልኛል ብሎ ካመነ መላእክትን ርኩስ ዲያቢሎስን ቅዱስ ከማለት የማይመለስ ለመሆኑ ብዙ ማስረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል፡፡

ወያኔ ማናቸውን ነገር ሲያደርግ ከሥልጣኑ አንጻር ነው፡የመንግሥትነት ስሜት ተሰምቶት፤ለህግ የበላይነት ለመገዛት ዳድቶት ፈሪሀ እግዚአብሄር አድሮበት ለሀገር ደህንነትና ለሕዝብ ጥቅም ተጨንቆ ወዘተ የሚፈጽመው አንዳችም ነገር አለመኖሩን በሀያ አራ አመታት አገዛዙ አሳይቶናል፡፡ ስለሆነም ጥሩ ሲያደርግ ከደስታችን መጥፎ ሲያደርግ ከሀዘን ቁጣና ጩኸታችን በስተጀርባ ረጋ ብለን ነገሮችን መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ይህን ማድረግ ባለመቻላቻን ነው ወያኔ በስልት በእብሪትና በማን አለብኝነት በሥልጣን ለመቆየት ያስችሉኛል በማለት  የሚወስዳቸው እኩይና ሰይጣናዊ ተግባሮች ሁሌ አዲስ የሚሆኑብን፡፡

እስረኛን መፍታት መልካምና የተቀደሰ ተግባር ቢሆንም ወደዚህ ደረጃ የተደረሰው  በእምነት ሳይሆን በግፊት ድርጊቱ የተፈጸመው በሰይጣናዊ አስተሳሰብ በመሆኑ እህት ወንድሞቻችን ከአውሬዎች እጅ በመውጣታቸው እየተደሰትን ደስታችን የወያኔን ተንኮል ከማየት አንዳይጋርደን መጠንቅ ይኖርብናል፤ ወያኔዎች ለወሬ የማይመቹ ተንኮለኞች ናቸውና፡፡

 

 

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>