ኢሳት ከሳምንት በፊት ያወራውን ወሬ ፋና ትኩስ ወሬ አስመስላና ቆራርጣ አቅርባዋለች።
ዜናው “መቼ ነው ይህ የሆነው?” የሚለውን መጠይቅ በዚህ በዚህ ቀን ብሎ በትክክል አይመልስም። እንዲሁ ወደ መጨረሻው ላይ “ሰሞኑን” ብሎ ነው ያለፈው። “የት?” የሚለውንም እንዲሁ በደፈናው “ከኤርትራ በሚዋሰን ድንበር” ብሎ ነው ያለፈው። በየት አካባቢ በሚዋሰነው ድንበር? ምንም ዝርዝር የለውም። እንኳን ወታደራዊ ዜና፤ አንድ ተራ ዘገባ እነኚህን የዜና አበይት መጠይቆች ሊያሟላ ግድ ነው።
ምነው ፋናዎች! ግልጽነትን ሌላው ቢቀር ከወዳጃችሁ ከሪፖርተር ተማሩ እንጂ!
-ደግሞ ሪፖርተር ምን አለ?
ዘይቱ ድንጋይ ሆነ አለ።
-ከየት የመጣው ዘይት?
ከወዳጅ ቻይና!
-መቼ?
ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም
-ኣሀ ኣሀ…ኣሀ…ለዚህ ነዋ አያቴ እንደዛ ያለችኝ?
ምን አሉሽ?
“አረ አያቴ ሆዴ ጥጥር ብሏል፤ድንጋይ ሆኖብኛል፤ ምን ሆኜ ይሆን?” ስላት ፦” እኔ ምናቅልሻለሁ የቻይና ዘይት በልተሽ ይሆናላ!” አለችኝ።
ህምም…
መንግስት ያመነበት ዜና የሚከተለው ነው
ከኤርትራ ጋር በሚዋሰን ምእራብ ትግራይ ድንበር አካባቢ ሰርጎ ለመግባት የሞከሩ ከ30 የማይልቁ የሻዕቢያ ተላላኪዎች መደምሰሳቸውን የፌደራል ፖሊስ ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 3፣ 2007 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ከኤርትራ ጋር በሚዋሰን ምእራብ ትግራይ ድንበር አካባቢ ሰርጎ ለመግባት የሞከሩ ከ30 የማይልቁ የሻዕቢያ ተላላኪዎች መደምሰሳቸውን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄነራል አሰፋ አብዩ ተናገሩ።
በሻዕቢያ ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ትንኮሳ ለመፈጸም ከሞከሩት ጸረ ሰላም ሃይሎች መካከል አብዛኞቹ ሲደመሰሱ ጥቂቶቹ በቁጥጥር ስር ውለዋል።
እንደ ኮሚሽነር ጄነራሉ ገለጻ ከተንኳሾቹ አንድም ወደ ኋላ ያፈገፈገ ሳይኖር የትንኮሳ ዕቅዳቸው ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የሻዕቢያ ተላላኪዎች አልፎ አልፎ የትንኮሳ ድርጊት የሚያካሂዱ መሆኑን ገልፀው፥ ሰሞኑን የተደረገው ከዚህ ቀደም ከነበረው የተለየ አይደለም ብለዋል።
እነዚህ ሃይሎች ያደረጉት ትንኮሳ አነስተኛ እና በቀላሉ በቁጥጥር ስር ለመዋል የቻለ ነው ያሉት ኮሚሽነር ጄነራሉ፥ ፀረ ሰላም ሃይሎቹ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር ውግያ ለመግጠም የሚያስችል አቅምም ብቃትም የላቸውም ብለዋል።
የኤርትራ መንግስት ኢትዮዽያ እና ሌሎች ሃገሮችን ለማተራመስ የያዘውን አቋም የማይቀይር ከሆነ ኢትዮዽያ ተመጣጣኝ እርምጃ እንደምትወስድ ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ሰሞኑን መናገራቸው ይታወቃል።
Source: FBC