Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

በሄኖክ ሰማእግዜር ላይ ለተፃፈ አስተያየቴ ፤ ይድረስ ለስርጉተ ስላሴና  ለቢላል አበጋዝ

$
0
0

ከጋዜጠኛ ደምስ በለጠ  

 

Voa-amharic-የተከበርሽው ወድ እህቴ  ሰርጉተ ስላሴ አንቺስ እንዴት ሰንብተሽልኛል ።   አዎ !በጋራ መድረካችን ዘ-ሃበሻ የሚወጡትን ፅሁፎችሽን እከታተላለሁ ። ይገርምሻል የጋራ ወዳጃችን ስላንቺ በጥቂቱም ቢሆን አውግተውኝ ስለነበር በተወሰነ ደረጃ የማውቀው ነገር አለ ። እህቴ ስርጉተ ስላሴ፤ እንደዛሬ ግን ውስጥሽን ለማየት አልቻልኩም ነበር። የሰዎችን ሰብአዊ መብት መከበር በተለይ ደግሞ እዚህ አሜሪካን እየኖርን ለምን እንደፈጥጣለን በሚል መሰረት ላይ ያጠነጠነውን ፅሁፌን አንብበሽ ለሰጠሽው የራስሽ አስተያየት፤ አክብሮቴን ልገልፅልሽ እወዳለሁ። አክብሮቴን እንድቸርሽ አቢይ ምክንያት የሆነኝ ደግሞ ከፅሁፍሽ “ውስጤ” መጀመሪያ እስከመጨርሻ ድረስ፤ እኔ በሄኖክ ሰማ እግዜር ላይ ካቀርብኩት የፅሁፉ መሰረታዊ ሃሳብ ሳትወጪ ወይም ሌላ ትርጉም ሳትሰጪ ወይም ሃሳቡን ወደምትፈልጊው አቅጣጫ ሳጥጠመዝዢ  መልስ በመስጠትሽ ነው ። ምን ለማለት እንደፈለግሁ ይገባሻል ብየ እጠብቃለሁ።

 

አንዳንድ ለፅሁፌ የሚሰጡ መልሶች እንደ አለሽበት አገር እንደ ስዊስ ቺዝ የተቀዳደዱ ስለሚሆኑ የትኛው ሐሳብ ላይ ላይ ቆመሽ በየትኛው ቀዳዳ ሾልከሽ የትኛውን እንደምትመልሺ ይቸግራል ። እህት አለም ተመልከቺ ስለሄኖክ ሰማእግዜር ስናገር እዚህ አሜሪካን ሃገር ስለተፈፀም ጉዳይ ብቻ ነው የተናገርኩት ። ኢትዮጵያ ውስጥ ወያኔ ጋዜጠኞች አላሰረም ፤አላሳደደም፤ የሙስሊም አማኞችን የእምነት ነፃነት አልተጋፋም፤ ሰላማዊ ታጋዮችን አላሳነቀም የሚል ክርክር ውስጥ አልገባሁም ። ስለአንድ ነጥብ ስናገር የምናገረው ስለዚያ ነጥብ ብቻ ነው ። የማሰብና የመናገር ነጻነት ስል  ሌላ ትርጉም ሳይኖረው አንድና አንድ የማሰብና የመናገር ነጻነት ማለት ብቻ ነው ።

 

በምሳሌ ላስረዳ ። ስቴት ኦፍ አሪዞና ውስጥ አንድ ሰው ሌላውን ሰው በስለት ገደለና ለፍርድ ቀረበ ። ሟችን ለሞት የበቃው ሁለቴ መወጋቱ ነው ። ገዳይ ደግሞ ጠበቃ ቆሞሎት ጥፋተኛ አይደለሁም እያለ እየተከራከረ ነው ። “ጥፋተኛ ያልሆንክበትን ምክንያት አቅርብ” ሲባል፤

“ኢንዶኔዥያ ውስጥ በአንዲት ደሴት ላይ የሚኖሩ ጎሳዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ጎሽ የሚመስለውን በሬያቸውን  በገመድ ዘርጥጠው ከጣሉት በኋላ  ሃምሳ የሚሆኑ ሰዎች ከየአቅጣጫው በአምሳ ጩቤ ወግተው ይገድሉታል ። ሰውነቱን ዘነጣጥለው ስጋውን እየቀቀሉ ይበሉታል ። እኔ የገደልኩትን ሰው በአንዲት አነስተኛ ጩቤ ሁለቴ ብቻ ነው የወጋሁት ። በገመድ አልዘረጠጥኩት፤ በአምሳ ጩቤ ወርሬ አላሰቃየሁት ፤ ስጋውንም ዘልዝየ አልበላሁት በምን ምክንያት ነው እነዚህ በጭካኔ የተሞሉ የኢንዶኔዥያ ሰዎች ሳይከሰሱና ጥፋተኛ ሳይባሉ እኔ ጥፋተኛ ተብየ የምከሰሰው?”

የሚል ክርክር አቀረበ ። ሳሙና ሌላ እንዶድ ሌላ !

 

እኔም እንዳቺው የራሴ ባህሪ አለኝ ። ምን መሰለሽ እመቤት!  አንድ ሰው ከፃፍኩት ርእስ ውጪ መሰረተ-ሃሳቡን ሳይሆን ቃሉን ብቻ ጎትቶ የራሱን ትርጉም ሰጥቶ ሊሞግተኝ ቢሻ መልስ ለመስጠት ይቸግረኛል ። መነሻው የራሱ ትርጉም እንጂ  የእኔ አይደለምና !

 

ሰው! ሰው! ሰው! እያልሽ የሰጠሽው ትንታኔ ለኔም ተመችቶኛል። የምንም ነገር መሰረቱ ሰው ነውና ። ሄኖክም ሰው ነው ። ሰዋዊ መብቱ ይከበርለት ነው ሙግቴ ። የጠላነውን የሄኖክን መብት  ስናከብር የኛንም መብት እያከበርን እንደሆነ መዘንጋት አያስፈልግም ።

 

በፅሁፍሽ ላይ “አያቶቼ የቤተ ክህንት ዓራት ዓይናማ ሊቃናት ነበሩና እናቴ ስትነግረኝ ሲያድጉ መሬትን ሲረገጡ መሬት የታመመች ያህል ወይንም የቆሰለች ያህል እንዲጠነቀቁላት ይቆጣጠሯቸው ነበር። መሬት ላይ መዝለል አይፈቅድላቸውም ነበር።” ብለሻልና በነገረ መለኮት ጥበብ ዘልቋቸው ፤ እውቀትን ተነክረውበት በፍልስፍናው ረቅቀውበት፤ አራት አይን የበራላቸው ፤ ለግኡዟ መሬት ህመም የሚጠነቀቁ ሰዎች የልጅ ልጅ የሆንሺው ስርጉተ-ስላሴ ፅሁፍሽ ላይ “እኛም ስናድግ ጠረኑ እንዲኖር ተደርጎ ቢሆንም፤ አሁን የሚገርምህ ነገር የበለጠ በላቀ ሁኔታ ተፈጥሮን እማይበት መንፈስ ያ የአያት ቅድመ አያቶቼ መንፈስ አፅመ ቅዱስ ቅርስ የላክልኝ – ይመስለኛል። መሬትን ስረግጥም – የበለጠ ከልጅነቴ ጊዜ ተጠንቅቄ ነው።” ያልሺው ድንቅ ነውና በአርአያ ስላሴ ለተፈጠረው ምንኛውም አይነት ለምትወጂውም ሆነ ለማትወጂው ሰው መብት መጠንቀቅ ይጠፋሽል ብዬ አልገምትም ።

 

ሔኖክ ጋዜጠኛ አይደለም ካድሬ ነው ብለሽዋል ።  ለመግባባት እንዲመቸን እኔም ካንቺ ጋር ልስማማና እንደገና ከፅሁፍሽ ልዋስ ። እንዲህ ይጠቀሳል፦ “የኢሠፓ ፓርቲ አባል ሆኜ በካድሬነት ስሠራ በነበረበት ጊዜ እማስበው የፓርቲዬን ፕሮግራም ዓላማና ግብ ተፈጻሚነት ብቻ ነበር። ጉዞዬ አንድ አቅጣጫ ግቤም አንድ ብቻ ነበር። ጋሬ – ዓይነት።”  እንግዲህ ሄኖክም ዛሬ ከዚህ በላይ እንደጠቀሽው አንቺ እህቴ ያኔ የነበርሽበት ደረጃ ላይ ያለ ቢሆንስ? አንቺ ያለፍሽበትን ደረጃና መብት ሊነፈገው ይገባል ? ሌላ ምንም አይነት ትርጉም ሳይሰጠው ማለቴ ነው ። እኔ ሳደርገው ልክ ነው እሱ ሲያደርገው ግን ስህተት ነው እንደማትይኝ ተስፋ አደርጋለሁ ።

 

“ሌላው ያነሳኽው ሰላማዊ ሰልፍን በሚመለከት ነው” ብለሽኛል ። እኔ ያነሳሁት ሰላማዊ ሰልፍን ሳይሆን  የሰላማዊ ሰልፉን አላማ ከሃዲድ መውጣት ወይም መንገዱን መሳቱን ነው ። ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው ።እንደገና ፅሁፌን ተመልከቺው ። እህቴ ስርጉተ  እዚህ ፅሁፍ ላይ ከላይ እንዲህ ብያለሁ እኔም እንዳንቺው ስለባህሪዬ ስገልፅ  ። “አንድ ሰው ከፃፍኩት ርእስ ውጪ መሰረታዊ-ሃሳቡን ሳይሆን ቃሉን ብቻ ጎትቶ የራሱን ትርጉም ሰጥቶ ሊሞግተኝ ቢሻ መልስ ለመስጠት ይቸግረኛል ። መነሻው የራሱ ትርጉም እንጂ  የእኔ አይደለምና !” ፅሁፍሽ ላይ ከዚህ ሌላ ከፅንሰ-ሃሳቡ የወጣ ሃሳብ አላገኘሁም ። ሆኖም ግን አስከትለሽ “ሰላማዊ ሰልፍ የተፈቀደ አመፅ ማለት ነው” ብለሻልና እኔም አንድ ነገር ጥያቄ አለኝ ላንቺ ። ሰላምና አመፅ እንዴት አድርጎ ነው አንድ  የሚሆነው? ሰላማዊ ሰላም ነው ፤ አመፅም አመፅ ነው ።

 

ይገርምሻል እዚህ ዋሽንግቶን ዲሲ ከ50 ሰዎች በላይ ለሰላማዊ ሰልፍ የምትጠብቂ ከሆነ ከዲሲ ገቨርንመንት ፈቃድ ማውጣት ይኖርብሻል ። የተፈቀደ አመፅ ላደርግ ነው የመጣሁት ብለሽ ብትነግሪያቸው እዚያው ነው ለእስር የሚዳርጉሽ ። ጠላትሽ ይታሰር ።

 

ስለአበበ በለው “እንዲህ ዓይነት ሰብዕና ሲያመጣ – አመመኝ።” ብለሻል ። ምን አይነት ሰብዕና ይሆን ያመጣው?  ለኔ ግልፅ አይደለም ።  “ስለ – አዋረደኝ” ያልሺውንም ልገምትና አንቺ ስለመንቶቹ ስትፅፊና በምናብሽ የሳልሺውን በወረቀቱ ላይ ስታወራርጂ አበበን የሳልሺው በራስሽ እይታ ይመስለኛል ። አበበም ፤ “ስርጉተ እባክሽ ስለእኔ ስትፅፊ እንዲህ፡ እንዲህ ብለሽ ፃፊልኝ” እንዳላለሽ እገምታለሁ ። ብሎሽ ከሆነ እውነት ነው አዋርዶሻል ፤ ካላላሽ ደግሞ ውዳሴ ከንቱው የቱጋ እንዳለ ፈልጊው እሱ አላዋረደሽም እላለሁ ። “አንድ ጋዜጠኛ በአድማ መግባት – በፍጹም የለበትም።”  ብለሻል ስለአበበ በለው ። የትኛው አድማ ላይ እንደገባ ግልፅ ስላልሆነልኝ  የምለው ነገር ይቸግረኛል ።

 

በተረፈ ፅሁፌን አንብበሽ የተሰማሽን በጨዋነት በመግለፅሽ አመሰግናለሁ ። በሰነዘርሻቸው ሃስቦች ላይ የምስማማባቸውም ሆኑ የማልስማማባቸው ሃሳቦች ቢኖሩም  የሃሳብ ነፃነትሽን አከብራለሁ ።

ለምወዳቸውም ሆኑ ለማልወዳቸው ሰዎች እኩል መብት እንዲኖራቸው ነውና ጥረቴ በዚህ እንደምንተጋገዝ  ተስፍጋ አደርጋለሁ ።

 

ደሕና ሁኝልኝ እህት አለም።

 

\\\\\\

 

 

ይድረስ ለአቶ ቢላል አበጋዝ በቅድሚያ የከበረ ሰላምታየ ይድረስዎ ። ከርስዎ ጋር በሃሳብ አልተለያየንም። የሄኖክ መብት መከበር እንደነበረበት፤ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ነገሮች ከመስመር መውጣት እንዳልነበረባቸውና ያም ከብስጭት የመጣ እንደሆነ ገልፀው ልምድ ሊያርመው የሚችል ስህተት ነው ብልዋል ። እኔ መኖሪያየን ቀይሬ አሁን ወደምኖርበት ስቴት እስከተዛወርኩ ድረስ ለ15 አመታት ወያኔን በመቃወም በዋሽንግተን ዲሲ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቻለሁ። ያስታውሱ እንደሆነ በ2005 ኖበምበር 14 ቀን 30ሺህ ኢትዮጵያዊ ሰላማዊ ሰልፍ ውጥቶ ከአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት የተነሳው ሰልፍ እስከ ኮንግረሱ ፅህፈት ቤት ድረስ ተጉዟል ። ያን ሰላማዊ ሰልፍ ክጅምሩ እስከ ፍፃሜው ካስተባበሩትም ከመሩትም ሰዎች አንዱ እኔ ነበርኩ ። ለቨርጂኒያ ዲሲና ሜሪላንድን መገናኛ የሆኑት አውራ መንገዶች ሙሉ ለሙሉ ተዘግተው ነበር።  የሰልፉ አላማ ግብ በወያኔ ጥይት የተገደሉ ወገኖቻችንን መከራ ማሳየትና ብሎም እስር ቤት የተወረወሩት የቅንጅት መሪዎችን መስዋእትነት ማሰብ ነበር ። ታዲያ ሰላማዊ ሰልፉ በራሱ ግብ አልነበረም ። ስለዚህ የሚደረጉ ሰልፎች ሁሉ  በመሰረቱ ግቦች አይደሉም ። የአንድ ትልቅ አላማ ተጨማሪ ማሳያ   ብቻ መሆን ይገባቸዋል ።  ፅሁፍዎ ላይ  እንዳሉት ሄኖክ ወጥ እየዛቀ በላ አልበላ ቤቱ ችሎት ስለሚኖር የኔ ጉዳይ አይደለም ።

 

ሌላው አንዱ አረፍተ ነገርዎ ከቀጣዩ ጋር አልያያዝልኝ እያለ ተቸግሬ ነበር። ስሜት አልሰጥ ያሉኝን እያለፍኩ ግንዛቤ በሰጡኝ ላይ ብቻ ነው መልስ ለመስጠት የሞከርኩት ። እኔ እርስዎን ብሆን የሆሊውድን “ሴልማ” ፊልም የታሪክ ማጣቀሻ አድርጌ ላቀርብ አልደፍርም ነበር ፤ ፊልሙንም አላየሁትም ። ታሪኩ ግን በስቴት ኦፍ አላባማ ፤ ወደርዕሰ-ሰከተማይቱ ሞንትጎመርይ በደቡባዊ የአሜሪካ ስቴቶች ለሚኖሩ ጥቁሮች የመምረጥ መብት መከበር ላይ ያነጣጠረ ሰላማዊ ሰልፍ እንደነበር አውቃለሁ ። አቢይ አላማው ከሰልፉ በፊት ቀድሞ የታሰበበት  ለጥቁሮች የመምረጥ መብትን ማጎናፀፍ ሲሆን ለዚህ መብት መከበር ሰላማዊ ሰልፉን እንደማሳያ ተጠቅመውበታል ።  በአላባማ ስቴት ከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛና በባለስልጣናቱ ድጋፍ  መከራ የደረሰባቸውና ይተደበደቡት ጥቅሮቹ ሰላማዊ ሰልፈኞች ፤ የእርስዎን አባባል ከፅሁፍዎ ልዋስና በብሽቀት ፤ እልህና ምሬት፤ ደብዳቢዎቻቸውን ነጮቹን እነሱም መደብደብ ቢጀምሩ ኖሮ ፤ የሰልፉ አላማ መንገዱን ስቶ የዛሬው ታሪክ ሌላ በሆነ ነበር ።

 

አቶ ቢላል አበጋዝ ጨቋኞችን የማውረድ ስልጣን አለኝ አላልኩም ። ይህ እርስዎ ፅሁፌን ሲያነቡ በራስዎ ልምድ የተረጎሙት ነው ። ደሞ አያስጎምጁኝ ፤ ይህማ ስልጣን ቢኖረኝ ኖሮ በአለም ያሉትን የሰው መብት ገፋፊዎች ሁሉ ገንድሼ ገንድሼ እጥላቸው ነበር ። ወይ ነዶ !

በደጋፊም መልኩ ይሁን በተቃዋሚ ፤ እኔ ጨቋኝ በኔ ላይ እንዲነግስብኝ አልፈቅድም ነው ያልኩት ። ያ የኔ ምርጫና መብት ነው ።

 

“ለሄኖክ መብት የምከራከረውን ያህል ለኢሳትም እቆማለሁ ።” ብለዋል እኔም ከእርስዎ ጎን እቆማለሁ ። በተለይ የሚዲያ  መብት እንዲከበር ስለምጥር ፡ በነፃነት የመናገሪያና ሃሳብን መግለጫ መድረኮችን ሁሉ እደግፋለሁ ። ሁለት ነገሮች ደግሞ አልወደድኩልዎትም ። በምርጫ ይሁን በግዴታ ዝም በል የሚለኝን ሰው እንቀዋለሁ ። የኔ ትምህርቴም የግል ባህሪየም ዝም እንድል አይፈቅዱልኝም ። ስለዚህ ዝም እንደማልል እንዲያውቁልኝ ፍላጎቴ ነው ። በሰዎች መብት ላይ ስንስማማ ቆይተን  ስናበቃ አበበ በለው ላይ  “በሳምንት መጨረሻ አንድ ቀን ለሚመጣ ቱሪናፋ” ብለውታል ። አዘንኩብዎ በጣም አዘንኩ ። አበበ ላይ ቂም የያዙበት ነገር እንዳለ ተሰማኝ ። አዲስ ድምፅ ራዲዮም በነጻዋ አገረ አሜሪካ ፡ በነጻነት ሃሳብን መግለጫ መድረክ ነውና የእሱም መብት እንዲከበርለት መጣር ይኖርብናል  ።

 

አበበ በለው የጻፈውን ደብዳቤ በተመለከተ የጠቀስኩት አሁንም ከመብት ጋር የተያያዘ እንጂ እርስዎ እንዳሉት አርበኞች ግንቦት 7ን ለመጎሸም እንዳልነበረ ሊያውቁልን እፈልጋለሁ ፤ ይህ የርስዎ ትርጉም ነው ። እዚህ ላይ ፍንትው ብሎ እንዲታይዎ የምፈልገው አንድ ነገር አለ ።እኔ አርበኞቹን እንደቱሪስት መስህብ ለቀናት ብቻ አይደለም ጎብኝቻቸው የመጣሁት ። ወይም በሪሞት ኮንትሮል በቴሌቪዥን መስኮት አይደለም የማውቃቸው ። እኔ አርበኞቹን ደጋግሜ ተመላልሼ ፤ አንዴ እንዳውም ለስድስት ወራት ቆይቼ የሚበሉትን በልቼ የሚጠጡትን ጠጥቼ አብሬያቸው ኖሬ አውቃቸዋለሁ ። በኢሳትም ሆነ በሌሎች ሚዲያዎች የሚቀርቡትን ተዋጊዎች ፎቶዎች በስም እየጠቀስኩ ልነግርዎ እችላለሁ ።  የትኞቹ የድምሕት የትኞቹ ደግሞ የአርበኞች እንደሆኑም እየለየሁ ልነግርዎ እችላለሁ ።  ስለዚህ በኔ በኩል የምጎሻሸምበት ምንም ምክንያት የለም ።

 

እንዲያውም የኤርትራ ልምዴንና ያየኋቸውን ሁኔታዎች ሁሉ ፤ በቅርቡ በተከታታይ ካሉኝ የፎቶና የፊልም ክምችት ጋር እያያያዝኩ  አቀርባቸዋለሁና  እንዲከታተሉ እጋብዛለሁ ።

 

አዎ መብት ማክበርን ልማዳችን እናድርግ ። ሮም ሲሄዱ እንደሮማውያን እንደሚባለው የምንኖርበትንም አገር ህግ ማክበር የተገባ ነውና እናክብር ። አቶ ቢላል አበጋዝ ሆይ ፤ ጌታ ክርስቶስ ጤናዎን እንዲጠብቅልዎ  እፀልያለሁ ። ቸር ይግጠመን ።

 

 

 

ጁላይ 8 2015 ፡

ከላስ ቬጋስ ኒቫዳ ።

 

 

 

 

 

 

 

The post በሄኖክ ሰማእግዜር ላይ ለተፃፈ አስተያየቴ ፤ ይድረስ ለስርጉተ ስላሴና  ለቢላል አበጋዝ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>