Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ወያኔን የትግሬ ነጻ አውጪ ማለት ያለ ግብሩ ስም መስጠት –ይገረም አለሙ

$
0
0

tplf-rotten-appleአቶ አንዱአለም ተፈራ ከገዢው መደብ የምንለይበት በሚል ርእስ ባስነበቡን ጽሁፍ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር መንግሥት የሚለውን አጠራር ለምን እንደመረጡ ያስረዳሉ፡፡ መጠሪያው ለወያኔ የማይገባው በመሆኑና  አቶ አንዱዓለም  መጠሪያውን ለመጠቀም ያአስቻለኝ ብለው  ያቀረቡት ምክንያት   በቂና ተገቢ ሆኖ ስላልተሰማኝ ይህችን አስተያየት ጻፍሁ፡

ትግሬ ስንል የኢትዮጵያ አንድ ክፍል በሆነው ትግራይ የተወለዱና ትግረኛ ቋንቋ የሚናገሩ ወይንም የወላጆቻቸው ስር ከዛ ሆኖ የትም ይሁን የት የተወለዱና ቋንቋውን ሊናገሩም ላይናገሩም የሚችሉትን ሁሉ የሚያጠቃልል ነው፡፡ ስለሆነም የትግሬ ነጻ አውጪ ስንል ወያኔ ትናንትም የታገለው ዛሬም ሥልጣን ላይ ሆኖ የሚሰራው እነዚህን ነጻ ለማውጣት ነው፣ እነርሱም ነጻ አውጪነቱን አውቀውና አምነው የተቀበሉት ነው ወደሚል አንደምታ ይወስዳል፡፡ይህ ደግሞ ወያኔ የሚፈልገው ነው፡፡

እሱ የሚለውን ተቀብሎ ትግሬና ወያኔን አንድ አድርጎ የመመልከቱ  አደገኛነት የታያቸው ኢትዮጵያውያን ገና ከጅምሩ ወያኔንና  ትግረኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንን ለይቶ ማየት እንደሚገባ፣ ሁለቱን መቀላቀል ትግሉን የሚጎዳና ወያኔን የሚጠቅም ብሎም በወደፊት የኢትዮጵያ አንድነት ላይ መጥፎ  ደንቃራ የሚያስቀምጥ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፣ጽፈዋል፡፡ ይህም ሙሉ በሙሉ ባይሆንም በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ተቀባይነት በማግኘቱ ወያያኔ ባሰበውና በተመኘው መጠን ትግረኛ ተናጋሪውን ከቀሪው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ነጥሎ የርሱ ብቸኛ መከታ ማድረግ አልቻለም፡፡

ወያኔዎች ትናንትም ሆነ ዛሬ አላማ ፍላጎታቸው ስልጣን ነው፡፡ ትግል ሲጀምሩ መላ ኢትዮጵያን መያዝ አንችልም ብለው ስላመኑ ትግራይን ይዘው  የሥልጣን ፍልጎታቸውን ለማርካት ስማቸውን ተሀህት፣ማገብት ህውሀት እያሉ ለትግረኛ ተናጋሪው ወገን የሚታገሉ መስለው ተጓዙ እንጂ ከራስ ጥቅም ያለፈ አላማም አጀንዳም ያላቸው አይደሉም፡፡ ይህን ደግሞ በሀያ አራት አመታት አገዛዛቸው በሚገባ የተገነዘብን ይመስለኛል፡፡ በዓላማም በግብርም የማይመስሉትን የቀዳማይ ወያኔን ስም የያዙትም በእምነት ሳይሆን ድጋፍ ለማግኘት ካልሆነም ተቃውሞን ለመቀነስ እንደሆነ የትግራይ አባቶችን ጠጋ ብሎ ጠይቆ መረዳት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያዊ እምነትና ስሜታቸው ጥያቄ የማይነሳባቸው ዶ/ር ኃይሉ አርዓያ በአንድ ጽሁፋቸው  እነዚህ ሰዎች ከቀዳማይ ወያኔ ጋር በዓላማም በተግባርም ስለማይመሳሰሉ ወያኔ ተብለው መጠራት የለባቸውም አስመሳይ ወያኔዎች ናቸው ማለታቸውን አስታውሳለሁ፡፡ ስለሆነም የትግሬ ነጻ አውጪ ማለት ለግብራቸው የማይመጥን  ስም ነው፤ ይበዛባቸዋል፡፡ እንደውም ለእነርሱ ፍላጎት መሳካት የሚበጃቸው ነው፡፡

አቶ አንዱአለም  በጽሁፋቸው እኔ ራሳቸውን እንዲጠሩበት በመረጡት ስም ነው የጠራኋቸው ይላሉ፡፡ ሰይጣን ለተንኮሉ ከመጽሀፍ ቅዱስ ይጠቅሳል እንዲሉ ወያኔ ትክክለኛ ማንነቱን የሚከልልለትንና ትግረኛ ተናጋሪውን ኢትዮጵያዊ ወገን ጋሻ ማድረግ ያስችለኛል ብሎ የመረጠውን ግብሩን የማይገልጽ  ስም ለራሱ ስለሰጠ   እኛ ተቀብለን ማስተጋባት የለብንም፡፡ ይህን አደረግን ማለት በተዘዋዋሪ የወያኔን ፍልጎት ማሳካት ነው የሚሆነው፡፡ የወያኔ ስብከትና ማስፈራራያ ያልበገራቸው በርካታ ትግረኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን በተቃውሞው ጎራ ጥንቃቄ የጎደለው ተግባር ያለፍላጎታቸው ወያኔን ለመደገፍ  መገደዳቸው የአደባባይ ምስጢር ይመስለኛል፡፡ የሚወዱትን ሲያጡ እንደሚባለው ሆኖባቸው፡፡

አቶ አንዱአለም ትግሬዎችን ነፃ አወጣለሁ ብሎ የተነሳ ግንባር፤ የትግሬዎች ነፃ አውጪ ግንባር ነኝ ሲል፤ ሌላ ምን ብዬ ልጠራው ይላሉ፡፡ ይህን አባባል ከላይ ለመግለጽ በሞከርኩት አስተሳሰብ ስናየው ሶስት ጉድለቶች አሉት የመጀመሪያው ትግሬዎችን ነጻ አወጣለሁ ብሎ የተነሳ የሚለው ሲሆን ይህን ከላይ ለማሳየት ሞክሬአለሁ፤ ሁለተኛው ግንባር የሚለው ነው፡ከመጠሪያው ጋር ሊቀራረብ የሚችለው ህወሀት ነው እሱ ደግሞ ግንባር አይደለም፤ ግንባሩ  ኢህአዴግ ነው፡፡ እሱን በጥቅሉ የትግሬ ነጻ አውጪ ለማለት ተፈልጎ ከሆነ ደግሞ ወያኔ ሀገራዊውን የፖለቲካ ትግል የጎሳ ትግል ለማድረግ ሌት ከቀን የሚማስንበትን ስራ እያሳካንለት ነው ማለት ነውና አደጋ አለው፡፡ ሶስተኛው ነኝ ሲል እኔ ምን ብዬ ልጥራው የሚለው ነው፡፡ እኛ መጠራት ያለብን እሱ ነኝ በሚለው ማንነቱን በማይገልጸው ሳይሆን ለማንነቱ በሚመጥነው ለግብሩ መገለጫ በሚሆን መጠሪያ መሆን አለበት፡፡ አሁን ልማታዊ መንግሥት እያለ ራሱን እየጠራ ነው ታዲያ እኛ በዚህ  እንጠራዋለን?

ነገርን ነገር ያነሳዋል አንዲሉ በዚህ ረገድ ሌሎች ስህተቶችም ስንፈጽም ኖረናል አሁንም እየፈጸምን ነው፤  ብሶት የወለደኝ ሲል ተቀብለን ብሶት የወለደው ብለናል፣ በረሀ የወረድነው አንባገነኑን የደርግ መንግስት ለማስወገድ ነው ሲሉ ሰምተን አሰምተናል ተቀብለን ተናግረናል፡፡

እንደሚነግሩን ጫካ የገቡት የካቲት 1967 ነው፡፡ በዚህ ወቅት ንጉሱን ከሥልጣን ያወረዱት ወታደሮች ይይዙት ይጨብጡት የጠፋባቸው፣ ይሆኑት ያደርጉት ነገር የቸገራቸው ነበሩ፡፡ እናም ወያኔዎቹ ብሶት የወለደን ለማለት የሚያበቃቸው ምክንያት አልነበረም፤ሊሆን የሚችለውን የመተንበይ ችሎታ ነበረን ወይም ጠንቋይ እንቀልብ ነበር ካላሉ በስተቀር  ደርግም በዛን ወቅት አንባገነን የሚባል አልነበረም፡፡

የሀገሬ አርሶ አደር አልጋ ፈርሶ አልጋ እስኪደላደል

ይህን ግዜ ነበር የጠሉትን መግደል

እንደሚለው የንጉሱ ሥርዓት ፈርሶ መጪው ማንና ምን እንደሚሆን በውል ባልታወቀበትና የመንግስት ክፍተት በተፈጠረበት አጋጣሚ ሲያልሙት የኖሩትን ከአጼ ዮሀነስ በምንይልክ ከትግሬ በሸዋ ተነጠቀ ብለው የሚቆጩበትን ስልጣን የሚያገኙበት አጋጣሚ ያገኙ መስሎአቸው  ምኒልክ ቤተ መንግሥት መድረስ ባይችሉም ከዮሀንስ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ሲገቡ እየታያቸው  ተጠራርተው ደደቢት ወረዱ፡፡ ነገር ግን ያሰቡት ያለሙት ሳይሆን ያልጠበቁት ሆነ፡፡ የ17 አመታት ትግልና ምኒልክ ቤተ መንግስት የመግባት ድል፡፡ ታዲያ እነዚህ እንደምን ብሶት የወለዳቸው፤የደርግን አምባገነን ሥርዐት ለመታገል በረሀ የወረዱ ፣የትግሬ ነጻ አውጪ ሊባሉ ይችላል፡፡

The post ወያኔን የትግሬ ነጻ አውጪ ማለት ያለ ግብሩ ስም መስጠት – ይገረም አለሙ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>