አቡ ዘኪያ
ከምድረ አናቶሊያ
ኧረ ደሴ ደሴ …ደሴ ላኮመልዛ
ምን አንልህ አንድዬ መከራችን በዛ
የመቶ ሃያ ሰባት ዓመት እድሜ ባለጸጋዋ…በዉበት መፍለቂያ አምባዎች ስር የተሸጎጠችው የደሴ ከተማ ዛሬም እንደ ትናንቱ ታነባለች…መስከረም 17 ቀን 1909 የመስቀል እለት ነው አሉ ደሴን መናገሻቸው ላደረጉት የሰሜኑ ንጉሥ ሚካኤል “ልጅዎ ልጅ ኢያሱ ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተደርጓል::እርሱም የት እንደደረሰ አይታወቅም::”የሚል አንድ ቤትና ጨርቅ አስጥል የስልክ መልእክት ከወደ አዲስ አበባ የደረሳቸው::ደዋይዋ የወቅቱ የውጭ ሥራና የንግድ ሚኒስትር ቢትወደድ ኃይለ ጊዮርጊስ ወልደ ሚካኤል ባለቤትና የንጉሥ ሚካኤል ልጅ ወይዘሮ ስኅን ነበሩ::Water shortage in Desse, Ethiopia
አዛውንቱ ንጉሥም ብዙም ሳይመክሩ “ወላድ ፍረደኝ የጠፋ ልጄን አፋልገኝ” በሚል አንጀት-በላ ዲፕሎማሲያዊ የክተት አዋጅ የደሴና አካባቢዋን ጎበዛዝት አስከትተው በደመ ነፍስ ወደ ሸዋ ገሰገሱ::በለስ ቀናቸውና ጥቅምት 7 ቀን 1909 በራስ ሉልሰገድ የተመራውን የሸዋ ጦር ቶራ መስክ ላይ ድባቅ መቱት::”ሲያልቅ አያምር” እንዲሉ ከአስር ቀን በኋላ ድል እድል ነሳቻቸውና ሰገሌ ላይ በሸዋ ጦር ድል ተነስተው ተማረኩ::አየ የቀን ክፉ …አዛውንቱ ንጉሥ ሚካኤል…የአድዋው ጀግና ንጉሥ ሚካኤል ልክ እንደ ልጃቸው ካልጋ ላይ ወደቁና አረፉት ::ለይህም እኮ ነው የደሴ አዝማሪ እንዲህ ሲል ያንጎራጎረው:-
ወይ እነሱ አያውቁ
ወይ ሰው አይጠይቁ
አባትና ልጁ ካልጋ ላይ ወደቁ
ንጉሡ ቢማረኩም ሰራዊታቸው እጅ አልሰጠም::በልጅ ኢያሱ ይደገፉ የነበሩ የንጉሥ ሚካኤል የጦር አበጋዞች ደሴ ላይ መሽገው ለወራት የሸዋን ጦር ቁም ስቅሉን አሳዩት::የኋላ የኋላ መዳከም መጣና ደሴ በሸዋ ጦር እጅ ወደቀች::,የሸዋም ጦር አንድ ሐበሻ በሌላ ሐበሻ ላይ ይፈጽመዋል ተብሎ የማይጠበቅ ጭፍጨፋ በደሴ ሕዝብ ላይ ፈጸመ::ደሴ እንደ ችቦ ነደደች…አምርራም አነባች…የሕዝባቸውን መከራ ዝዋይ ደሴት እስር ላይ ሆነው የሰሙት አዛውንቱ ንጉሥ ሚካኤልም እንዲህ ብለው ስንኝ ቋጠሩ አሉ:-
ደግ ነገር ሳለ ክፉ ተናግሬ
ያገር ልጅ እያለ ከባሪያ መክሬ
አቃጠሉት መሰል ሸተተኝ ሀገሬ
የደሴ መከራ መች እንዲህ በዋዛ ሊያበቃ…በወርኅ መስከረም 1928 ጣሊያን ሀገራችንን ዳግም ወረረ::ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም ክተት ሰራዊት ምታ ነጋሪት ብለው ወደ ሰሜን አመሩ::የጦር ሰፈራቸውንም ደሴ በሚገኘው ቪላ ኢታሊያ ወይም መርሆ ግቢ በሚሰኘው የአልጋ ወራሽ አስፋ ወሰን ኃይለ ሥላሴ ቤተመንግሥት ዉስጥ አደረጉ::በመሆኑም ደሴ የፋሽስት ጣሊያን የጦር አውሮፕላኖች ዋና ኢላማ ሆነች::
ዋቢ መዛግብቶች እንደሚያወሱት ከኅዳር እስከ የካቲት 1928 ባሉት ሦስት ወራት ዉስጥ ብቻ ደሴና ሕዝቧ ስምንት ከባድ የአየር ድብደባዎችን አስተናግደዋል::ደሴ ላይ የወረደውን የቦምብ ዶፍ አስመልክተው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ “ሕይወቴና የኢትዮጵያ እርምጃ” በተሰኘው ግለ-ታሪክ ድርሳናቸው ላይ “ህዳር 26 አርብ ጧት 1928 ሃያ አንድ አውሮፕላኖች መጥተው ቦምብ ያዘንብቡን ነበር…እንደሚጥሉት ቦምብ ትልቅነትና ብዛት በደሴ ከተማ የሰው ዘር የሚተርፍ አይመስልም ነበር::”በማለት ነበር የደሴን አበሳ የገለጹት::በወቅቱ ጦርነቱን ለዓለም ሕዝብ ለመዘገብ ደሴ ከትመው ከነበሩት የውጭ ጋዜጠኞች አንዱ የነበረው ጆርጅ ስቲር Caesar in Abyssinia በተሰኘው በዚያው ሰሞን በታተመው መጽሐፉ የኅዳር ሃያ ስድስቱን ድብደባ አስመልቶ እንዲህ ይለናል “The casualities were heavy,for the bombardment was quite unexpected.Fifty three were killed,many by burning in their huts,and about two-hundred killed in crowded Desseye.The people of Desseye were crazy with fear and rage:as the planes circled round,the town seethed as a furious hive.” አየ አለመታዴል ዴሴ ነዴዴች…
እ.አ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን 1936 ከፈታኝ ዉጊያ በኋላ ስትራቴጂካዊዋ የብሶት ከተማ ደሴ ፋሽስቶች እጅ ላይ ወደቀች::የፋሽስቱ ጦር የሰሜን ግንባር አዛዥ ፊልድ ማርሻል ባዶሊዮም The War in Abyssinia በተሰኘው መጽሐፉ ላይ እንዲህ ሲል ጻፈ “the last and bloodiest of all the battles came to an end at Dessie” አዎ ደሴ እንደ ወትሮው በደም ታጠበች…አምርራም አነባች…
በብርሃን ፍጥነት ወደ 1965….
1960 ልክ እንደ ዛሬው የዓረቦች ጸደይ ወጣት አብዮተኞች አውራ ጎዳናዎችን የተቆጣጠሩበት ዓመት ነበር::ፓሪስ ቶኪዮ ፕራግና መሰል ከተሞች በወጣት አብዮተኞች ተናወጡ::የኛዋ አዲስ አበባም በግራ ዘመሞቹ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪነት የአብዮታዊ ሰልፎች መዲና ሆነች::ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ ከፍተኛ አብዮታዊ እንቅስቃሴ በማካሄድ የሚታወቀው የደሴው ወ/ሮ ስኅን ት/ቤት ነበር::በእለተ ዓርብ ግንቦት 10 ቀን 1965 በወ/ሮ ስኅን ተማሪዎች መሪነት የደሴ ተማሪዎች ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ::እንዳለመታደል ሆነና ያ ታሪካዊ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ በደም ተጠናቀቀ::በጠቅላይ ግዛቱ እንደራሴ ደጃዝማች ሰለሞን ኣብርሃ(የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አጎት)አዛዥነት የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ አዛዥ በነበሩት ጄኔራል ዮሐንስ አስፈጻሚነት የንጉሠ ነገሥቱ ፈጥኖ ደራሽ ጦር ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በመተኮስ 15 ተማሪዎችን በግፍ ሲገድል አያሌዎችን አቆሰለ::የደሴዋ ፒያሳ በደም ታጠበች…ደሴም ስለ ልጆቿ ምርር ብላ አለቀሰች…
ባንድ ወቅት ተማሪዎቹ የነበሩት የወ/ሮ ስኅን ተማሪዎች በግፍ መጨፍጨፋቸውን የሰማው ገጣሚና ቀያኒ ዮሐንስ አድማሱ በወርኃ ጥቅምት 1966 በጻፋት “ዕንባሽ”የተሰኘች ግጥሙ የእናት ዓለም ደሴን ሰቆቃና እንባ ከመጽሐፍ ቅዱሷ ራሔል እንባ ጋር በማነጻጸር እንዲህ ሲል ሰነኘ:-
በዕንባሽ ውስጥ አልፌ በዕንባሽ ተንሳፍፌ
ገና ዳር ሳልወጣ ዕንባሽን ቀዝፌ
ራሄልን በዕንባሽ አየሁዋት በራማ
በዕንባሽ ተቀስቅሳ ታነባለች ቁማ ::
ዘመን ቢያርቃችሁ
ሥፍራ ቢለያችሁ
ዕንባ አጋጠማችሁ
ዋይታ ተሰምቶ ጆሮዬ ተጠማ
ያንች ካለሁበት የራሄል ከራማ
የዋይታ ክብሩ የሙሾውም ቃና
የእሷ የእናትነት ያንች የድንግልና ::
ዘመን ቢያርቃችሁ
ሥፍራ ቢለያችሁ
ዕንባ አጋጠማችሁ
እድሜ ለዚያ ትውልድ አንበሶችና አናብስቶች በየካቲት 1966 ሕዝባዊ አብዮት ፈነዳና የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስርዓት ተገረሰሰ::ምን ዋጋ አለው?!…አብዮታችንን ስልጣንና ደም በጠማቸው ወጥቶ አደሮች ተነጠቅን::ሀገራችንም ከድጡ ወደ ማጡ ዘቀጠች::የኢትዮጵያ ከተሞች የሞት አምባ ሆኑ::ወጣትነት ወንጀል ሆነ::ቀይ ሽብር ታወጀ:: የቀይ ሽብር ግንባር ቀደም ሰለባ ከሆኑት ከተሞች አንዷ ሰርክ-አንቢዋ ደሴ ነበረች::በ1969 መባቻ ላይ በወሎ ክፍለ ሀገር ዋና አስተዳዳሪ ኮሎኔል ጌታሁን እጅጉና በደህንነት ሹሙ ሻለቃ ንጉሤ ቱጂ መሪነት የሕዝብ ድርጅት አባላት በቀበሌና ከፍተኛ የአብዮታዊ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ ነፍሰ ገዳዮች በመታገዝ በደሴ ወጣቶች ላይ “መንጥር” የተሰኘ ዘመቻ አወጁ::
ዘመቻ መንጥር አያሌ የደሴ ልጆችን ለእስርና እንግልት ዳረገ::ይህ በንዲህ እንዳለ ቅዳሜ የካቲት 26 ቀን 1969 ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ የወሎ ክፍለ ሀገር የደህንነት ሹምና የዘመቻ መንጥር ጠቅላይ አዛዥ የነበሩት ሻለቃ ንጉሤ ቱጂ በኢሕአፓ አባላት መኪናቸው ላይ በተጠመደ ፈንጂ ሸዋ በር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከነአጃቢያቸው ተገደሉ::የደሴ አዝማሪም እንዲህ ሲል አንጎራጎረ:-
ጨካኝ ነበር እርሱ ጨካኝ አዘዘበት
እንደ ቡሄ ዳቦ እሳት ነደደበት
የሻለቃ ንጉሤን ሞት ተከትሎ ሞት ደሴ ላይ ነገሠ::የከተማዋ ጎዳናዎች በደም ታጠቡ…ደም-ምሷ ፒያሳም ሬሣ በሬሣ ሆነች…ደሴም ስለ ልጆቿ ምርር ብላ አለቀሰች…ይህን ግፍ ያየ አዝማሪም እንዲህ ሲል በማሲንቆው አለቀሰ:-
ኧረ ደሴ ደሴ ገራዶ ገራዶ
አለቀልሽ ልጅሽ እንደ በሬ ታርዶ
ግንቦት 10 ቀን 1983…
የግንቦት 10 ቀን 1965 ሰማዕታት አስራ ስምንተኛ ዓመት በሚታሰብበት እለት ሌላ ታሪካዊ ክስተት ደሴ ላይ ተከሰተ::በስድስት ብርጌዶች የተዋቀረው “ብሶት የወለደው” የጀግናው ኢሕአዴግ ቴዎድሮስ ክፍለ ጦር በቀድሞው የወ/ሮ ስኅን ተማሪ ዋለልኝ መኮንን ስም በተሰየመ ዘመቻ ደሴ ላይ መሽጎ የነበረውን 26ኛውን የመንግሥት ሰራዊት ድባቅ በመምታት ደሴን ከደርግ “ነጻ” አወጣ…እድሜ ለዘመቻ ዋለልኝ ደሴ ሰናይ ዘመን መጣ ብላ ፈገግ አለች::ግና ያፈገግታ ያ ተስፋ ወዲያው በኖ ጠፋ::የአዲሱ ገዥ ኃይል አካሄድ ያላማራቸው የታሪካዊው ወ/ሮ ስኅን ት/ቤት ተማሪዎች ሰኔ 3 ቀን 1983 ፒያሳ ላይ ያደረጉት የተቃውሞ ሰልፍ በወያኔ ወታደሮች የመትረየስ እሩምታ ተበተነ::ደም-ምሷ ፒያሳም በደም ታጠበች…ደሴም ስለ ልጆቿ ምርር ብላ አለቀሰች…
የሰኔ 3 ቀን 1983 ጭፍጨፋ ኢሕአዴግ ፊቱን ያዞረ ደርግ መሆኑን ለደሴ ሕዝብ ያረጋገጠ አሳዛኝ ታሪካዊ ክስተት ነበር::ከዚያች እለት ጀምሮ ኢሕአድጋዊያንና ደሴ ሆድና ጀርባ ሆኑ::የደሴ ሕዝብም ምርጫ በመጣ ቁጥር ድምጹን በመጠቀም በኢሕአዴግ ላይ ድምጽ አልባ መፈንቅለ መንግሥት( Silent Coup d’État)ማድረግን የፖለቲካ ባህሉ አደረገው::አብዮታዊ ዴሞክራቱ ኢሕአዴግም በበኩሉ በየምርጫው ዋዜማና ማግሥት የደሴን ሕዝብ ማዋከብና በውኃና መብራት ማዕቀብ ማሰቃየትን የሙጥኝ ብሎ ተያያዘው::
ታኅሳስ 4 ቀን 2004…
“ድምጻችን ይሰማ” የሚል ጩኸት ከወደ አወሊያ ተሰማ::የደሴ ሙስሊሞችም በብርሃን ፍጥነት “አዎ ድምጻችን ይሰማ” ሲሉ ለአወሊያ ተማሪዎች ጥሪ ምላሽ ሰጡ::ዓመት ከስምንት ወር በሆነው የሙስሊም ሐበሾች የነጻነት ትግል ደሴዎች ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወቱ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው:: ይህ በመሆኑም ነው የኢሕአዴግ ዘረኛና መርዘኛ የግፍ በትር የደሴ ሙስሊሞች ላይ በርታ ያለው::ልክ የዛሬ ወር እውቁ የኃይማኖት መምሕር ሸህ ኑር ኢማም በግፍ ተገደሉ:: የሸህ ኑሩን ግድያ ተከትሎ የደሴ ሙስሊሞች ቁም ስቅላቸውን እያዩ ነው::
በአሁኑ ወቅት ደሴ ዉስጥ ሙስሊም መሆን ወንጀል ነው::ሕዝበ ሙስሊሙ የረመዳን ጾምን ያለመብራትና ዉኃ እንዲጾም ተፈርዶበታል::ዘመነ አፈሳ ወ አበሳ ደሴ ላይ ዳግም ነግሷል::የገዥው ኃይል ቅጥረኞች የዓይኑ/ኗ ቀለም ያላማራቸው ሙስሊም ላይ ነጻ እርምጃ እንዲወስዱ በጌቶቻቸው ታዘዋል::ሙስሊሞች ይታሰራሉ ይገረፋሉ ይደፈራሉ ይዘረፋሉ::ወዴት እየሄድን ነው?የመናገር መብታችሁን አስከበርኩላችሁ የሚለን ልማታዊ መንግሥታችን ከመናገር በኋላ ያለውን መብታችንን መቼ ይሆን የሚያከብርልን?መብቴ ይከበር ብሎ መጮህ በየትኛው አዋጅ ነው ወንጀል ተብሎ የተደነገገው?ግራም ቀኝም ገባን ጃል… …በዘመነ መኳንንቱ(ዘመነ አፄ) በዘመነ ሰራዊቱ(ደርግ)እና በዘመነ ደደቢት(ኢሕአዴግ) መሀል ያለው ልዩነት አልታያችሁ አለን’ኮ…ጎበዝ ልብ ያለው ልብ ይበል ደሴ ላይ የመከራ ደመና አንዣቧል…ደሴ እያነባች ነው…ኧረ ለመሆኑ የእናት ዓለም ደሴ ዋይታ ፍጻሜ መቼ ይሆን?
ያ ያዬሁት ዕንባ ከልብሽ ተልኮ
ባይኔ ላይ ሲያዘግም መንፈሴ ታውኮ
የብቸኝነት ቅኔ ሲቀኝ ሰማሁ ቁሜ
ራማ ነው አለኝ የዋይታሽ ፍጻሜ ::
(ዮሐንስ አድማሱ ጥቅምት 1966)
የእናት ዓለም ደሴ ሙስሊሞች ሆይ በሩቁ ከወዲሁ ዒድ ሙባረክ ወኩሉ ዓም ወአንቱም ቢኸይር ብያለሁ!
ማዓ ሰላማህ!