ከሥረጉተ – ሥላሴ 01.07.2015 /ሲዊዘርላንድ – ዙሪክ/
ክብረቶቼ – እንዴት ናችሁ? ዛሬ ሰፋ ባሉ ሀተታዎች ስላከርምኳችሁ፤ ዬቋንቋዎች ከፍተኛ ባለሙያ አለቃም ከሆነው ሥነ – ግጥም ጋር ትንሽ ቆይታ እናደርግ ዘንድ – ወደድኩኝ። ዛሬም አርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ የነፃነት ትግሉ ልዩ አቅም፣ ጥሪት – ጠሪ ጥርኝም ናቸው። የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ አርነት ያቀዳጀቻቸው ያቺ የአፓርታይድ ዬስቃይ ፋብሪካ ጉሮኖ – ነበረች። ካልታወቀው የወያኔ ሃርነት ትግራይ አፓርታይዳዊ የአሳር ፋብሪካ ጉርኖ ያለው አርበኛ መንፈስም፤ – ሙቀቱ – ግለቱ – ጧፍነቱ – ብርታቱ – ጥገነቱ ተርጓሚው ካለካስማ የቆመው የሰማይ ሚስጥር ብቻ ነው። ያ ያልታወቀው ቦታም ዝክረ የነፃነት አንባችን ቅርሳችን – ነው። ኮቴው ሳይቀር የሚጠቀምባቸው መገልገያዎች ሁሉ የዛሬም ነገ የነፃነት አንባ ትንፋሽ ናቸው።
ሩኽ – ብሩኽ
እንደዋዛ
ቀንሲባዛ
አመርቅዞ – ሲያወረዛ —
እንዲህ – ነቅዞ ሲንዛዛ —
የቀማኛ አይደል – ድንገተኛ
አልነበረም – ሰሞነኛ።
የታለመ – በቀመር
የተሰላ – ለመሰርሰር
አትንኩኝን – ለመመንጠር፤
በትብብር፤
አቅምን – ለማሰር፤
የቁርሾ – ድርድር
ታሪክን አጠቆረ – ሳይግደረደር።
ዬባንዳ በር –
ለቅኝ ግዛት መሆን በደንገጡር
ሃርም – ነውር!
*****
ያ … አርበኛ
የአፍሪካ ቀንድ – ልበኛ።
ሁነኛ።
እሩቅ አሳቢ … ድ — ጎኛ
ቆመስ – ሆኖ የእኛ
ያ … አርበኛ —- ።
ዛሬም ሩቅ አሳቢ — ቂምገደል
ይኽው ነው፤ ይኼው ነው የእሱ መክሊት – በቀልቀበር – ልቅና – በልዕልና
ተንኮል ሰበር – ቅ ————————-ነኛ
ቁጥብ፤ ቅ ——ንተኛ።
ስቃይ ታጋሽ – የመቻቻል ዘበኛ
ያ – አርበኛ ……።
ነገን ለማሳደር – ዛሬን ታግሶ፤
የፈተናውን ቱቦ
ሴራማውን ቦንዳ ሰርዞ
እንደከደነው – ጠቅልሎ፣
በዝምታ – ወልውሎ፣
ውሉን አደሰ – በቃሉ
መሆን ነውና – ደንበሩ ስለቃሉ፤
ሐገሩ።
ያ አርበኛ —
ጥሩኛ – የእኛ።
እሱን የሰጠን – ለእኛ
መንፈሱን ሸለመን በፍቅረኛ – ዘዬኛ።
ነገ ውሎ – እንዲያድር
ዛሬም፤ ን ————-ቃቃት፤ እንዳያቅር።
ካቴና ላይ ሆኖ
ደህንነቱን ተናገረ – በቋሳ የታሸውን ሃሳሩን — አትንኖ።
እንደ ድንግሉ ሰማዕት ቅዱስ – ሐዋርያ
„ወደ አንተ እመጣ ዘንድ ወደድኩኝ – አለ ጥራኝ
ይሄው አለሁ – አለ ምራኝ።“
ዛሬም – ዛሬም – ዛሬም – ዛሬም – ዛሬም – ዛሬም
መልካምነት – በዳግም፤
ቁልፉ –
ያ አርበኛ – ዘርፉ።
ውብአለም። የቡቃያ ፍሬ – የራዕይ ደማም፤
የተሰፋ ሚስጢር፤ ቅኔ ሰገድ – ሰንደቅ
የብርታት ግማድ – ዝልቅ።
ሩኽ – ብሩኽ
ህብርኽ።
ሥጦታ … ለአርበኛ አንዳርጋቸው ጽጌ ይሁንልኝ። 30.06.2015 ሲዊዘርላንድ።
******
ክብረቶቼ – ከመሰናበቴ በፊት ላልፈው የማልሻው ጉዳይ „የጓጎሉ ጉሞች“ በሚለው ጹሑፌ ላይ ከአንድ ዓመት በላይ ያስቆጠረ የተለመደ አስተያዬት – አንብቤያለሁ። በተቀያዬረ ሥም ከዘወትር ደምበኛዬ ከተከበሩ አቶ ወንዱ June 27, 2015 – 8:11 pm „እህታቺን አቅዋም ያዥ:: ተሚታቶቢሃል„ የዘወትር የጹሑፌ ታዳሚና ሃያሲዬ በመሆኑዎት ከልብ አብዝቼ – አመሰግነወታለሁ። እግዚአብሄር – ይስጥልኝ። የቀረበዎትን ነገር ለማሟላት አለመቻሌን ፈቅጄው በመሆኑ መቀበል ግድ – ይለዎታል። እኔ „እኔ“ እንጂ እኔ እርስዎ አይደለሁምና። በእኔ ውስጥ ያለሁት እኔ ብቻ ነኝ። የትውስት „እኔነት“ የተጸዬፈ ስብዕና ነው ያለኝ። በሰው ያልተጠፈጠፈ ፈጣሪ የሰራው ልብ – አለኝ፤ የሌላ ሰደተኛ መንፈስ ልብ እንዳይገጠምለት ሆኖ – የተቆለፈ።
ምርቃት …. ለማላውቀዎት – ወንድሜ፤
ሁለት ዘርፍ አለው ዕይታዎት አንደኛው ሥርጉተ የማን ናት? ነው። ሥርጉተ – የዕንባ ናት። ሥርጉተ ዬኢትዮጵያ ናት። ፓል እሳተፍ በነበርኩበት ጊዜም ሥሜም ‚ሥርጉት ለኢትዮጵያ‘ ይል ነበር። እኔነቴ በሚያልቅ አጀንዳ ውስጥ አይደለም የተፈጠረው እዬሸተ በሚሄድ ሥነ – ማንነት እንጂ። ያ ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው። ሁለተኛው በግልጽ የቀረበውን ደግሞ እንዲህ – ይመለስለዎት። ነፍስ ካወቅኩበት ጊዜ ጀምሮ ለአቋሜ ቋሚ አቋሙ እኔው ነኝ። ማለት እኔ እራሴ አቋሙም ተቋሙሙ ነኝ – ለእኔ። የትጥቅ ትግል፤ የሰላማዊ ትግል በተጨማሪም የዲፕሎማሲ ትግል በሁለንትናዊነት አስፈላጊነቱን – አምንበታለሁ። ጹሑፌም የሚለው ይህን ነበር። ስካር ላይ እያለሁ በሞቅታ ፈረስ አልነበረም – የጻፍኩት፤ ይልቁንም በተደመጠ የተደሞ ሥነ ህይወት – እንጂ። የትግል ስልቶቹ እንደ አዳምና ሂዋን፤ ወይንም እንደ ሥጋ እና ደም ተነጣጥለው ሊታዩ ቀርቶ ሊታሰብም አይገባም ባይ ነኝ። ቀይ የደም ሴል፣ ነጭ የደም ሴል ፕላዝማ ናቸው። ቬን እና ሴልም።
አንድ የነፃነት ትግል ዬእኔ የሚለው ዕንባ አባሽ የመከላከያ ኃይል ሊኖረው – ይገባል – ማገር። አንድ የነፃነት ትግል ሠራዊት ደግሞ የእኔ የሚለው ደጀን ያስፈልገዋል። መንግሥታትም የተደራጁት በዚህ መርህ ነው ሀገር የሚመሩት። ገላ ከፈን – ያስፈልገዋል፤ አካልም – ምግብ፤ ለዕጽዋት የጸሐይ ብርሃን ምግባቸውን እንዲያዘጋጁ ይረዳቸዋል —- ለእነሱ የተቃጠለው ለእኛ ህይወት ነው። የእኛ የተቃጠለው ካርቦንዳይኦክሳይድ ደግሞ ለእነሱ ዬልምላሜ – መሰረት ነው። ሰጥቶ – መቀበል። ተቀብሎ – መስጠት። ፊኖሚናል አምክንዮው ይኸው ነው። በመኖር።
የማከብረዎት ወንድሜ — እኔ አቋሜን ተውሼው ወይንም ገብያ ሸምቼው ወይንም ወረፋ ጠብቄ ገዝቼው ሳይሆን ሆኜበት የኖርኩበት ጽኑዑ ጠረኔ ነው፤ ሥሜም ከዚኽው – ይነሳል። እኔን የሚገልጸኝን፤ እኔ የሆንኩትን አምክንዮ ፈርቼው ሳይሆን ደፍሬው መሆን መቻሌ ነው የሚስጢሩ ሥነ – ነፍስ። ማነን ፈርቼ?! እኔ የሥላሴ ባርያ ከፈጣሪዬ በስተቀር በፍላጎቴ፣ በስሜቴና በፖለቲካ አቋሜ እምፈራው ማንምና ምንም እንደሌለ ላረጋግጥለዎት – እወዳለሁ። ወደ ኋላ የሚጎትት የማናቸውም ዓይነት የይሉንታን ሃዲድን የሰበርኩ የራሴ ጌታ እኔው ሥርጉተ ሥላሴ ነኝ። መንፈሴን – ነፃ ያወጣሁ ራሴንም የገዛሁ ሴት ነኝ። በምንም ሁኔታ በመንፈስም፤ በገሃዱ ዓለም ኑሮ ሆነ በማህበራዊ ህይወቴ እኔን እንዳወጣ ገብያ ላይ አውጥቼ ቸርችሬው – ሸቅጨው ወይንም መንዝሬው አላውቅም። ወቅት ዘንበልና ቀና ባለ ቁጥርም የተቀበሉኝ ደጄ ጠኝም – አይደለሁም። ርፍራፊ ወይንም ቅርጥምጣሚ ለማኝም አይደለሁም። እራሴን ለመግለጽ ተጠማኝም አይደለሁም። ወይንም ዬሞፈር ዘመት ድንኳን ሰበርነት – አይነካካኝም። እኔን የገነባኝ እራሴን እምስተዳድርበት የኑሮዬ ህግ አለኝ። ተርፎ ባይናኝም ያለኝ – ይበቃኛል።
በሌላ በኩል የማናቸውም ግንኙነቴ ላዕላይና ታህታይ መዋቅሩ የፖለቲካ አቋሜ መሆኑን በአጽህኖት ልገልጽለዎት – እወዳለሁ። መስፈርቱ ይኼው ብቻ ነው። በተዛነፈ ዝልብልብ – ውልብልቢቱ በሚንጠባጠብ በተስረከረከ አሰር ዘረክራካ ስሜት የሚፈጠር አንዳችም የግንኙነት መስመር ኑሮኝ – አያውቅም። አጋጣሚዎች ቢያስጀምሩት እንኳን ትንፋሹን ሳይሰበሰብ – ይሰናበታል። መወሰን ሕይወቴ ነው። የፅንሰ ሃሳብ ትንተና የሚያስፈልገዎት ከሆነም በነፃነት ፍለጋ ጉዞ የዓይኑን ብረት አብራርቼ ልጽፍለዎት – እችላለሁ፤ ትምክህት ግን አይደለም የተመክሮን ማሳ ተጠዬቅ ለማለት ይለፍ መስጠቴ እንጂ። ሌላው ግን የቀለም ተማሪ ስላልሆንኩኝ እሱን ቢጠይቁኝ አልችልም፤ የተገዛ ዲግሪ ቀርቶ የተገዛ ተራ ስርትፊኬት የለኝምና። በተረፈ ይህችን ዬአማርኛ ቋንቋ ፊደላትን እንክትክት አድርገው ካለርህራሄ አካሏን ውልቅልቅ የሚያደርጓትን ህመም ለመታደግ አንድ ቢሏት መልካም ነው። ተደጋገመች … ይለማመዱት – በትሁት መንፈስ፤ ከዛ አንዲትም ዘለላ ሥንኝ ብትሆንም እንኳን አስተካክለው መጻፍ – ይቻላሉ። ደህናም ይሰንብቱልኝ። ስለ አሉ ነው …. እንዲህ መነጋገር የቻልነው – እና።
ውዶቼ ለሰጣችሁኝ የማይጠገብ ተናፋቂ – አድማጭነት ከልብ አመስግናችሁአለሁ። መሸቢያ – ሰሞናት።
የሥነ ግጥሜ መነሻ https://www.youtube.com/watch?v=lWH1L35ZRNI
https://www.youtube.com/watch?v=O7fknrUAE94
ተጨማሪ —- የውስጥነት መስመር https://www.youtube.com/watch?v=FmeGfeOaM_I
Radio Tasegaye or www.tsegaye.ethio.info Aktuell Sendung
አርበኞቻችን መርሆቻችን፤ መንገዶቻችን ናቸው!
ለእኔስ ሰው መሆኔ ብቻ ይበቃኛል።
እግዚአብሄር ይስጥልኝ።
The post ሩኽ – ብሩኽ። (ሥረጉተ ሥላሴ) appeared first on Zehabesha Amharic.