አምነስቲ ኢንተርናሽናል ትናንት ሰኔ 24/2007 ዓ.ም ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አክብረውም የሰማያዊ ፓርቲ አባላትን በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቋቸው አሳስቧል፡፡ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ወይንሸት ሞላን፣ ኤርሚያስ ፀጋዬን፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄለም አካለ ወርቅን ፍርድ ቤት በአስር ቀናት ውስጥ ለሶስተኛ ጊዜ እንዲለቀቁ ቢያዝም አራቱ ግለሰቦች አሁንም እስር ቤት ውስጥ ስቃይ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጾአል፡፡
አይ ኤስን ለመቃወም በተጠራው ሰልፍ ላይ ፖሊስ የሀገሪቱንና የዓለም አቀፍ ህግን በመጣስ በሰልፉ ላይ የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር ጥሯል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል በወቅቱ በርካታ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች መታሰራቸውን አስታውሷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባላት የሆኑት ብሌን መስፍን፣ ተዋቸው ዳምጤ፣ ማቲያስ መኩሪያ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቴዎድሮስ አስፋው፣ ሜሮን አለማየሁና ንግስት ወንዲፍራው በሰልፉ ሰበብ መታሰራቸውን በአብነት የጠቀሰው ሪፖርቱ ከሰማያዊ ፓርቲ አባላት በተጨማሪ የሌሎች ታሳሪዎች ፍርድም በሂደት ላይ መሆኑን ጠቅሷል፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አባል የሆነው ናትናኤል ያለም ዘውድና የፓርቲ አባል ያልሆኑ አራት ግለሰቦችም በሰልፉ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰድበዋል፣ መንግስትን የሚቃወም መዝሙር አሰምተዋል በሚል ሰበብ ሶስት አመት እንደተፈረደባቸው ሪፖርቱ አውስቷል፡፡
ወይንሸት ሞላ፣ ኤርሚያስ ፀጋዬ፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄሌም አካለወርቅ ሁለት ወር ተፈርዶባቸው ለሁለት ወር ያህል እስር ቤት በመቆየታቸው እንዲፈቱ ቢታዘዝም ፖሊስ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ በመጣስ ወደ እስር ቤት እንደመለሳቸውም የአምነስቲ ሪፖርት አስታውሷል፡፡ በእነ ወይንሸት ላይ አዲስ ክስና ይግባኝ እንደተጠየቀባቸው የገለፀው የሰብአዊ መብት ተሟች ድርጅቱ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ወይንሸት ሞላን፣ ኤርሚያስ ፀጋዬን፣ ዳንኤል ተስፋዬንና ቤትሄሌም አካለ ወርቅን እስር ቤት ውስጥ በማጎር የፍርድ ቤቱን ቅቡልነትና የህግ የበላይነትን እየሸተሸሩ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ የሚያደርሱትን ስቃይ ማቆምና በነፃ የመዳኘት መብታቸውን ሊያከብሩላቸው እንደሚገባም አሳስቧል፡፡
The post አምነስቲ ኢንተርናሽናል የሰማያዊ ፓርቲ አባላት በአስቸኳይ ከእስር እንዲለቀቁ አሳሰበ appeared first on Zehabesha Amharic.