ስላለፈውም ስለመጭውም የፖለቲካ ጉዞ በልበ ሙሉነት ትንታኔ ለመስጠት ድፍረት አግኝቻለሁ !!!
ትችት ከብንያም ሰለሞን
እንደ አ.አ. በ2014 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ በኤሶፕ አሳታሚ የታተመው ባለ 444 ገጽ አዲስ መጽሃፍ በእኔ ግምት በአገራችን ዘመናዊ የ40 ዓመታት የፖለቲካ ሂደት ለበርካታ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ መጽሃፍ ነው፡፡ በማንኛውም የእድሜ፣ የእውቀትና የስራ ልምድ ክምችት ላለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ስለሃገሩ ጠለቅ ያለ እውቀት እንዲኖረው በእጅጉ ይረዳዋል፡፡ እኔ ይችን አጭር አስተያየት የጻፍኩት ስለ መጽሃፍ ግምገማ ሙያና ብቃት ኖሮኝ አይደለም፡፡ አስተያየት መስጠት መመስከር ነውና ከመጽሃፉ ያገኘኋቸው በርካታ ቁም ነገሮች ለረጅም ጊዜ በውስጤ መልስ ሳያገኙ ለኖሩ ጥያቄዎች ያልጠበኳቸውን አጥጋቢ መልሶች እንዳገኝ ስለረዳኝ ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው ? ከመልሴ በፊት መንደርደሪያ ላስቀምጥ፡፡
ከአጼ ኃይለ ስላሴ ንጉሳዊ ስርአትና በደርግ ዘመነ መንግሥት አሁን ደግሞ በትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር አገዛዝ ውስጥ አልፌአለሁ፡፡ ወጣቱን ለለውጥ ፍላጎት አነሳስቶ ሳይደራጅ በስሜት ተነሳስቶ የህዝብ ጥያቄዎችን አንግቦ ሊነሳበት የቻለው ምክንያት ምንድን ነው? አብዮት ብሎ አመጽ ከየት መጣ? ለግብታዊ እንቅስቃሴ ያነሳሳውና የገፋፋው የሃገር ውስጥና ዓለም አቀፋዊ የፖለቲካ ካምፖች ሚና በኢትዮጵያ አብዮት ላይ የነበራቸው ተጽእኖ ምን ነበር? የአጴው ስርአት ተገርስሶ ከወደቀ በኋላ ወታደራዊው ጁንታ ሊተካ የቻለበት ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ነበሩ? በደርግ ዘመን ውስጥስ ምን ችግሮች ተከሰቱ? የአስራ ሰባት አመቱስ ጦርነት ምን አስከተለ? ኤርትራ እንዴት ልትገነጠል በቃች? የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባርን ለመፍጠር የረዳው ሁኔታ ምን ነበር? ከአንዱ ስርአት ወደሚቀጥለው ስርአት ስንሸጋገር በጎና ክፉ ነበሩ ወይም ናቸው የምንላቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው? የወያኔን ነጻ አውጭ ግንባር ለስልጣን ያበቁት የውስጥና የውጭ ችግሮችና አመቺ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? የወያኔ መሪዎች የግላቸው የህይዎት መዋዕል አሁን ለሚከተሉት የአምባገነንነት አመራር ምን አስተዋጽኦ ይኖረው ይሆን?
ለእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎች ጥርት ባለ ቋንቋና ቀላል አገላለጽ የዶክተር ነገደ ጎበዜ መጽሃፍ አጥጋቢ መልሶችን ይዞ ቀርቧል፡፡ በሌሎች መጽሃፍት ውስጥ ያልተዳሰሱና ብዙ ልፋትን የጠየቁ ሥራዎች መሆናቸው ለመጽሃፉ ልዩ ዋጋ ይሰጡታል፡፡
መጽሃፉ ከመግቢያው ሌላ በአራት አበይት ምእራፎች የተከፈለና ዋናውን ትኩረት በኢትዮጵያ ውስጥ የተደረጉ የለውጥ ሙከራዎች ላይ አድርጎ ዘመናዊ ሥልጣኔ ከጀመረበትን ወቅት በመነሳት ብዙ ጊዜ የማናገናዝበውን የወቅቱን ዓለማዊ ሁኔታ ማለትም ከጣልያን ወረራ በፊት የነበረውን የጃፓናይዘርስን የለውጥ ሙከራ እንደ መንደርደሪያ በመጥቀስ የታሪኩን ቅደም ተከተል በዘመን ሂደት ጠብቆ ይተነትናል፡፡
በተለይ በዘመኑ የነበረውን የባእዳን መንግሥታ ስውር ደባና ግልጽ ወረራ፣ እንደዚሁም ለለውጥ የተደረጉ የተለያዩ ሙከራዎች እንዴት እንደተጀመሩና በምን ምክንያት ሊከሽፉ እንደቻሉ ያብራራል፡፡ ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ሃገሪቱን ዘመናዊ የማድረግ ይህ የመጀመሪያው ጥረት በወረራው ሳቢያ ከሸፈ፡፡ በወቅቱ በይፋ ደረጃ መላው አለም የመንግስታት ማህበርን (ሊግ ኦፍ ኔሽንስን) ውሳኔ አክብሮ ይህንን ወረራ ቢያወግዝም የነበረው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ሃያላን የተባሉት በሙሉ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከየራሳቸው ምክንያት እየተነሱ እንግሊዝና ፈረንሳይ ኮሎንያሊስቶች ብቻ ሳይሆኑ ሶቭየቶችም አሜሪካኖችም ከልፈፋቸው ባሻገር በተግባር እንዴት ከወራሪው ጎን ተሰልፈው እንደነበረ፣ በዚህ ሁሉ ትርምስ መሃከል ደግሞ በተጨባጭ መሳሪያ በማቀበል ከሃገራችን ጎን ቆሞ የነበረው አዶልፍ ሂትለር እንደነበረና የነዚህን ሁሉ ምክንያቶች እየዘረዘረ ያስረዳል፡፡
ከዚያም ከወረራው በኋላ የለውጥ ሃሳብ እንደገና እንዴት እንዳንሰራራ፣ የታህሳሳውያን የለውጥ ሙከራ በተለይም በመንግስቱ ነዋይ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ውስጥ ተዋናዮቹ እነማን ነበሩ ? አላማቸውስ ምን ነበረ? ሙከራቸው ለምን ከሸፈ? የሚሉትን መሠረታዊ ጥያቄዎች በጥልቀት ይፈትሻል፡፡
ከሙከራው መክሸፍ በኋላ የተከተለው ጸጸት ምን ትምህርትን ሊያስገኝ እንደቻለና የህዝቡ ንቃተ ህሊና እንዴት እያደገ እንደመጣ ደረጃ በደረጃ ይመረምራል፡፡ ከዚያ በኋላ እስከ የካቲት ወር መጀመሪያ ድረስ የተከሰቱ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም አቅጣጫቸውን እንዴት ስተው እንደተቀለበሱ ቀጥሎም ህዝባዊ እንቅስቃሴ እንዴት ሊነሳ እንደቻለ ያስቀምጣል፡፡ ማን ያውራ የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ እንዲሉ ደራሲው ራሳቸው የነበሩበትን አፍላ ተሳትፎ ያስቃኙናል፡፡ በተለይም በሂደቱ ውስጥ ከመሸነፍ ወደ ማጥቃት የተሸጋገሩ ሃይሎች በአብዮቱ አፍላ ወቅት ሁሉም ብሶቱን እያነገበ፣ ሁሉም ብሶትህ ብሶቴ ብሎ እየተጋገዘና ከዚያም ደግሞ ለዘላቂ መፍትሄ ሲባል ሁሉም ለስርአት ለውጥ በሚል አላማ ትግሉ የተጓዘበትን « ሶስትዮሽ » ብለው የጠሩት አካሄድ እንዴት እንደነበረ ያብራራሉ፡፡
ይልቁንም ከሰኔ 66 ዓ.ም. እስከ የካቲት 67 ባለው ጊዜ ወታደራዊው የደርግ መንግሥት እንዴት አድርጎ ሥልጣኑን እየጨመደደ ለመያዝ እንደቻለና መሬት ላራሹ የሚለውን የአርሶ አደሩን ጥያቄ ለመመለስ ሁኔታዎች እንዴት እንዳስገደዱት፣ ድሃ ገበሬዎችና ዘማቾች በአንድ በኩል፣ « ታማኝ ቀልባሾች » በሌላ በኩል ያካሄዱት ወስብስብ ትግል እንዴት እንደነበረ ፍንትው አድርገው አስቀምጠውታል፡፡ ተራማጅ ሃይሎች ደርግ በሚከተለው አመራር ላይ በነበራቸው አስተያየት ጎራ መለየት፣ ቀጥሎም የህዝባዊ ግንባሮች አውታሮች እንደተመሰረቱና በተለይም ገበሬዎች እንዴት በማህበር መደራጀት እንደሚገባቸው የፖሊሲ አመንጭ የነበረው የምሁራኑ የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዜያዊ ጽ /ቤት እንዲቋቋም የነበረውን ድርድር፣ ስምምነት የተደረሰባቸውን ሰነዶችና አመሰራረቱን የሚመለከት ትንታኔ ቀርቧል፡፡
በተለይ አዲሱ ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ለመመርመር ሲነሳ ከአጴው ሥርአት ቀጥሎ ምን ተፈጠረ ? የተሞከረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ሁሉ ምን አከሸፈው? ለክሽፈቱ አስተዋጽኦ የነበራቸው ኃይሎች ሚና ምን ነበር ? ብሎ ራሱን መጠየቁ እንደማይቀር በመገመት ይህንን መጽሃፍ ማንበቡ ስለ ወደፊቱም የሃገሪቱ የፖለቲካ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችል መተንበይ አያዳግተውም ብየ አስባለሁ፡፡ ስለዚህም ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይልቁንም በአመራር ላይ ያሉ ኃይሎች ሊያነቡት እንደሚገባ አስባለሁ፡፡
ይልቁንም በአሁኑ ጊዜ በመከሰት ላይ ያለው አምባገነናዊ ሥርአት መነሻና አካሄዱ እንዴት ነው? ያለፉት ትንበያዎችስ የቱን ያህል ተጨባጭ ሆነዋል? ብሎ አካሄዱ የት ላይ መስመር እንደሳተ መገንዘብ ይችላል፡፡ ለምሳሌ በ1967 ዓ.ም. ደርግ ስልጣን ለመያዝ ዳር ዳር ሲል ተማሪዎች ከሌሎች ተራማጅ ሃይሎች ጋር በመሆን ወታደራዊ ጁንታ ሊቋቋም ይችላልና ከዚህ ይልቅ መሆን ያለበት ህዝባዊ መንግስት ነው ሲሉ ተሟግተው እንደነበረ ይታወሳል፡፡ የተፈራውም አልቀረም ደረሰ፡፡ ይሁንና ያን ጊዜም ቢሆን ከደርግ አባላት መካከል ተራማጆችን በመያዝ ህዝቡን ማንቃት፣ ማደራጀትና ማስታጠቅ ሊቀድም ይገባል የሚሉ ሃይሎች እንደነበሩ አይዘነጋም፡፡ ሆኖም የተራማጅ ሃይሎች በሁለት ጎራ መከፋፈልና መዋቀር ለደርግ አምባገነን ሥርአት መፈርጠም አመችቶታል ማለት ይቻላል፡፡ በትግሉ ሂደት አያሌ ምሁራንና ወጣቶች ለለውጡ ሲሉ ወድቀዋል፣ ደማቸውንም አፍሰዋል፡፡
በዚህ ጊዜ የውጭ ጠላቶች ወረራ፣ የኤርትራ ነጻ አውጭ ግንባር ፍልሚያና የትግራይ ነጻ አውጭ ግንባር ዙሪያ ገብ ጦርነት የደርግን ስርአት በ17 አመት ትግል ሊቀጨው ችሏል፡፡ ከዚያ በኋላ የተከሰተው ሁኔታ የረጅም ጊዜ ጦርነት ያስከተለው የሰው ሃይል የመንፈስና የመሰልቸት ሁኔታ ከጫካ በሚነዛው የሬድዮ ስብከት ታጅቦ እነሆ አሁን ያለንበት ሁኔታ ደረስን፡፡
እዚህ ላይ ቆም ብለን መጠየቅ ያለብን ጉዳይ እውነት በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ጭቆና ነበርን? ከኮሙኒስቶች ማኒፌስቶ አጉል ጥራዝነት በኮሙኒስትነት በመንገድ ላይ እንዳለና ከዚያም በኋላ ከአልባንያ ቅጂ ወደ አስመሳይ ካፒታሊስትነት የተለወጠው እስከ 5ኛው ምርጫ ድረስ ሊደርስ የቻለውና ሥልጣንን ጨምድዶ የያዘው፣ ዴሞክራሲን እየሰበከ አምባገነን ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ወደፊትስ በዚሁ አይነት እስከመቼ ሊቀጥል ይችላል?
በዶክተር ነገደ ጎበዜ መጽሃፍ ውስጥ የቀረበውን ትንተና በዚች አጭር አስተያየት ማጠቃለል አይቻልም፡፡ ዓላማዬ ግን መነበብ ያለበት መጽሃፍ ነው በሚል መንፈስ ተነሳስቼ ያቀረብኩት አስተያየት መሆኑን አጠንክሬ ለመግለጽ ብቻ ነው፡፡ መጽሃፉን ያላነበበ አይኖርም ብዬ አስባለሁ፡፡ ሆኖም ግን ተደጋግሞ መነበብ ያለበት ሥራ ይመስለኛል፡፡
በእኔ ግምት የዶ/ር ነገደ ጎበዜ መጽሃፍ በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ታሪክ ያሰፈረ ብቻ አይደለም፡፡ ከዓለም አቀፉ ሁኔታዎች ጋር ያገናዘበ፣ በሶሻል በኢኮኖሚና በባህል ላይ የተመሰረተውን የማህበረሰቡን ታሪክ ያናበበ፣ የወደፊቱን አቅጣጫ የሚጠቁም ብዙ ልፋት የተደረገበት የምርምር ስራ ውጤት ይመስለኛል፡፡ በበኩሌ መጽሃፉን ካነበብኩ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ታሪክና ስለ መጭው ጊዜ በልበ ሙሉነት ትንታኔ ለመስጠት ድፍረት አግኝቻለሁ፡፡ እንደዚህ ያለ ሥራ አዘጋጅቶ ማቅረብ ለእናት አገር የተከፈለ መስዋእትነት አድርጌ ነውና የምመለከተው ደራሲውን ከልብ ላመሰግን ይገባኛል፡፡ እግዚአብሄር ይክፈልዎት፡፡
ብንያም ሰለሞን
The post የዶክተር ነገደን ‘ይድረስ ለግንቦት ከየካቲት’ ካነበብኩ ወዲህ……- ትችት ከብንያም ሰለሞን appeared first on Zehabesha Amharic.