ከ ይርጋ አበበ
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር የካቲት 5/ 1985 ዓ.ም በፖርቹጋሏ ገጠራማ ከተማ ሳንቶ አንቶኒዮ የተወለደው ክርስቲያኖ ሮናልዶ ዶሳንቶስ አቬሮ የዛሬ የእዚህ ገጽ እንግዳችን ነው።
የእግር ኳስ ሕይወቱን ገና በ8 ዓመቱ ነው የጀመረው። አንዶሪና ለሚባለው የአካባቢው አማተር ክለብ በእዚህ ዕድሜው መጫወት ጀምሮ በሲ.ዲ ናሽናል ጎለበተ። በሲ. ዲ ናሽናል ክለብ ለሁለት ዓመታት ቆይታ ካደረገ በኋላ የፖርቹጋሉን ኃያል ስፖርቲንግ ሊዝበን የግሉ አደረገው። 28 ቁጥር ማሊያ ለብሶ በፖርቹጋል ሊግ መታየት የጀመረው የዛሬው የ28 ዓመት ኮከብ በስፖርቲንግ ሊዝበን የአንድ ዓመት ቆይታው አርሰን ቬንገርንና አሌክስ ፈርጉሰንን ጨምሮ የታላላቅ ክለብ አሠልጣኞች ዓይን ያርፍበት ጀመር። በውድድሩ በለስ የቀናው ግን የላንክቫየሩ ክለብ ማንዩናይትድ ነበር በ12 ነጥብ 24 ሚሊዮን ፓውንድ የግሉ አደረገው።
ምንም እንኳ በእንግሊዙ ታላቅ ክለብ በርካታ ሥራዎችን የሠራ ቢሆንም በእዚህ ጽሑፍ ለአንባቢያን ለማቅረብ የሞከርነው ግን በሪያል ማድሪድ ክለብ ውስጥ ያከናወናቸውን አብይ ክንዋኔዎች ለይተን 28ቱን ብቻ ነው። በእዚህ ጽሑፍ ውስጥ የምንጠቀመው የአውሮፓውያን አቆጣጠር መሆኑንም እንገልጻለን።
ክፍል 1
ሐምሌ 1/ 2009
በወላጅ እናቱ ጎትጓችነት የሚወደውን የሰር አሌክስ ፈርጉሰንን ቡድን ለቅቆ ወደሚወዱት ሪያል ማድሪድ ክለብ የተዘዋወረበት ቀን ነው። 80 ሚሊዮን ፓውንድ ወይም 131 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ማሬንጌዎቹን ያስወጣው ፖርቹጋላዊ በእዚህች ቀን የ6 ዓመት ኮንትራቱን ሲፈራረም ከ80 ሺ በላይ ደጋፊዎች በደማቅ ሥነ ሥርዓት ነበር የተቀበሉት። ይህ የደጋፊዎች ቁጥር ደግሞ ዲያጎ ማራዶና ከባርሴሎና ወደ ናፖሊ ሲዘዋወር ከተቀበሉት 75,000 ደጋፊዎች የላቀ ሆኖ ተመዝግቧል።
ነሐሴ 29 ቀን 2009 የስፔኗ ዋና ከተማ ክለብ በሜዳው ዲፖርቲቮ ላኮሮኛን 3ለ2 ሲያሸንፍ ግብ የማግባት ሥራውን አንድ ብሎ የጀመረበት እለት ነው። በሪያል ማድሪድ እግር ኳስ ክለብ ታሪክ ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የአልፍሬድ ዲስቲፋኖን 9 ቁጥር ማሊያ ለብሶ መጫወት የጀመረው CRገ አሁን ለክለቡ ካስቆጠራቸው 193 ግቦች ሁሉ ቀዳሚዋን ግብ ያስቆጠረው በእዚህ እለት ነበር።
ግንቦት 5/ 2010
በእዚህ ዕለት ደግሞ የቀድሞው የሳሙኤል ኤቶ ክለብ የነበረው ሪያል ማዮርካ የክርስቲያኖ ሮናልዶን ሦስት ግቦች (ሀትሪክ) የተስተናገደበት ክለብ ነው። በማሬንጌዎቹ ቆይታው በድምሩ 15 ሀትሪኮችን ቢሠራም የመጀመሪያውን ሀትሪክ ለማስቆጠር ሪያል ማዮርካዎችን መጠበቅ ግድ ሆኖበት ነበር።
ሐምሌ 3/ 2010
ለነጭ ለባሾቹ የፈረመበትን የመጀመሪያ ዓመት እያከበረ ነው። ይህች እለት ግን ሌላ ዜና ይዛለት መጥታለች። ዜናው ከመስከረም 2005 በ52 ዓመታቸው ሕይወታቸው ያለፈውን ወላጅ አባቱን ማስረሻ የሚሆን ነው። እ.አ.አ ሐምሌ 3/ 2010 ክርስትያኖ ሮናልዶ የልጅ አባት ሆነ። የልጁ እናት ማንነት አወዛጋቢ ቢሆንም ክርስቲያኖ ሮናልዶ ግን ሮናልዶ ጁኒየር የሚል ስም የተሰጠውን ልጅ ያገኘው ከላይ በተጠቀሱት እለት ነበር።
መጋቢት/3/ 2011
ለሀገሩ ሲጫወት ከደረሰበት ጉዳት አገግሞ ወደ ሜዳ የገባበት እና በማላጋ መረብ ላይ ሦስት ግቦችን ያሳረፈበት እለት። ለ10 ቀናት ቁምጣና ታኬታ መልበስ ያልቻለው ፈጣኑ ልጅ በእዚህ ዕለት ኳስ ናፍቆት እንደነበር ያሳየበትን ጨዋታ ነበር ያደረገው።
ሚያዝያ 20/2011
ከመጋቢት ሦስት እስከ ሚያዝያ 20 ድረስ ባሉት 6ሳምንታት ውስጥ 6 ግቦችን በማስቆጠር እ.አ.አ በ2007/08 ማንቸስተር ዩናይትድ በነበረበት ጊዜ በዓመቱ ያስቆጠረውን 42 ግብ የማግባት ክብረ ወሰን የተጋራበትን ጀብዱ ፈጽሞ ነበር ለሚያዝያ 20 የኤል ክላስኮ ጨዋታ የደረሰው። 103 ደቂቃዎችን በፈጀው በእዚሁ የኤል ክላሲክ ፍልሚያ ማሬንጌዎቹ ብዎሉ ግራናዎቹን አሸንፈው የኮፓ ዴልሬይ ዋንጫን ሲያነሱ መልከ መለካሙ ሮናልዶ ከኢማኑኤል አዲባየር የተሻገረችለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ከቪክቶር ቫልዴዝ መረብ ውስጥ ጨመራት።
ግንቦት 7/ 2011
የኢንዶኔዢያ ክለብ ሲቪያ በሜዳቸውና በደጋፊያቸው ፊት አንገት የሚያስደፋ ውጤት ሲያስመዘግቡ ግብ አነፍንፊው ፖርቹጋላዊ 4 ግቦችን ለግሉ ሲያስመዝግብ ለቀሪዎቹ ሁለት ግቦች የነበረው ሚናም ከፍተኛ ነበር። እነዚህ ግቦች በዓመቱ ያስቆጠራቸውን ግቦች ድምር ወደ 46 ያሳደጉለት ነበሩ።
ሜይ 15/2011
ከአራት ቀን በፊት በጌታፌዎች መረብ ላይ የዶላቸው ሦስት ግቦች 49ኛ የውድድር ግቦች ሲደርስ ግንቦት 15/2011 ምሽት ደግሞ ሌላ ታሪክ ሠራ። ቀደም በሁጎ ሳንቼዝ እና በቴልሞ ዛኑ ተይዞ የነበረውን 38 የሊግ ግብ የተጋራበትን ግብ ቪላሪያል መረብ ላይ አሳረፈ።
ግንቦት 21/2011
የዓመቱ የመጨረሻ ጨዋታ አልሜሪያ ከሪያል ማድሪድ በሳንቲያጎ ባበርናባው ክለቡ ሪያል ማድረድ በ37 ጨዋታዎች 97 ነጥቦችን ሰብስቦ ከባርሴሎና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት 8 አድርሷል። በአንፃሩ የቀድሞው የማን/ ዩናይትድ ወጣት 38 ግቦችን አስቆጥሮ የፒቺቺ ኮከብ ግብ ማስቆጠሩን አረጋግጧል። የአልሜሪያ ጨዋታው ግን ለልጁም ሆነ ለክለቡ ታሪክ የሚሠራበት ቀን ነበር። ሪያል ማድሪድ ካሸነፈ 100 ነጥቦችን በአንድ የውድድር ዓመት የሰበሰበ ብቸኛው የላሊ ክለብ ይሆናል። በአንፃሩ ሮናልዶ ግብ ማስቆጠር ከቻለ ደግሞ ከፍተኛ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነቱን በሪከርድ መዝገብ ላይ ማስቀመጥ ይችላል። ጨዋታው ከተጀመረ ደቂቃዎች ሄዱ። ሪያል ማድሪድ አልሜሪያን ሲያሸንፍ ኮከባቸው ሮናልዶም ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ በ40 ግቦች የውድድር ዘመኑ ከፍተኛ ግብ አግቢ ሆኖ አጠናቀቀ።
ነሐሴ 17 /2011
የስፓኒሽ ሱፐር ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ የመጀመሪያ ዙር በካምፕኑ ምሽት የምንጊዜም ተቀናቀኞቹ ባርሴሎና ከሪያል ማድሪድ ከዕረፍት በፊት ዴቪድ ቪያ ባስቆጠረው ግብ ባርሴሎና መምሪት ጀመረ። ከደቂቃዎች በኋላ ግን ከራኡል ጎንዛሌዝ ክለቡን መልቀቅ በኋላ «7 ቁጥር» ማሊያ የለበሰው የፖርቺጋል ብሔራዊ ቡድን አምበል ማሪጌዎቹን አቻ አደረገ። ይህች ግብ በሪያል ማድሪድ ማሊያ ያስቆጠራቸውን ጠቅላላ ግቦች ድምር 100 ማድረስ የቻለች ነበረች። መቶኛ ግቡን በካምፕኑ። (ይቀጥላል)
↧
የክርስቲያኖ ሮናልዶ 28 ልዩ ቀናት
↧