ጁን 25 ቀን 2015
ዋሽንተን ዲ ሲ ፡
ቱሪናፋ የሚለውን ቃል ሐበሻ የተባለው መዝገበ ቃላት: ወሬኛ።ጉረኛ።ወሬ የሚያበዛ ይለዋል።ይህ ጽሁፍ ለዘለፋ ሳይሆን በፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ላይ ለመወያየት ነው።እኒህን ነጥቦች እዩልኝ።
ኦባማ ለምርጫ ሲቀርቡ “ይቻላል ፡አዎን ይቻላል” ብለው እኛንም አስብለውን ነበር።ለአሃጉራችንም በጎ ያደርጋሉ ብለንም ተመኝተን ነበርን።መመረጣቸውንም ኮርተንበትም ነበር።የኢትዮጵያ ጉብኝታቸው የአገዛዝ ዘመናቸውን ጥላሸት የሚቀባው ነው።ይህ ደግሞ ለሳቸው ክፉ ነው። ወደ ስልጣን ሲመጡ የአፍጋኒስታንና የኢራቅን የውጭ ጉዳይ ችግሮችን ተረክበዋል።በስልጣን እያሉ ሶሪያ እና የመን ተጨምረዋል። እድላቸው ሆኖ የቋጠሩት ሁሉ የሚፈታባቸው ናቸው። ተቀናቃኞቻቸው ውሳኔ ላይ ቆራጥነት የለህም ይሏቸዋል።ስተተኛና ዳተኛ ያደርጓቸዋል። ይህ ጽሁፍም አፍቅሮ ህወሃት ተግባርዎ ስተት ነው ለማለት ነው። ከኢትዮጵያውያን በተረፈም ዓለም እየታዘበዎት ነው።የኢትዮጵያ ህዝብ እምነቱ በኢትዮጵያ አምላክ ላይ ሲሆን የህወሃት እምነት በስዎ ላይ ነው። ለኢትዮጵያ ሁሌም መጨረሻው ላይ ይፈርድላታል።ህወሃት እንደ ጃፓን ሲኒ መሰባበሩ ግድግዳ ላይ ተጽፏል።
የኦባማ ወደ ኢትዮጵያ መሄድ ለማንም ግድ አይሰጥም። ስለ ኢትዮጵያ ካሰብን እውነቱ ይህ ነው። የእስልምና ሃይማኖት ኢትዮጵያን አትንኩ ሲል መጽሃፍ ቅዱስ እጆችዋን ወደፈጣሪዋ ትዘረጋለች ይላል።ዛሬ ደግሞ ደካማ በጸሎቱ፡ብርቱው በጉልበቱ፡ በንብረቱ እግዜርን አለኝታ አድርጎ ኢትዮጵያን ከህወሃት መንጋጋ ሊያወጣት የቆረጠበት ስለሆነ “ኦባማ አላወቁበትም” ከማለት ሌላ፡ አምባገነኖች ጋር ጓይላ ቢጨፍሩ “እንታይ ገድሸኒ” እንላቸዋለን።
ካስተዋልነው ዛሬ የአፍሪካ አሀጉር ከነዚያ የመንግስት ግልበጣ የዞትር ወግ ከነበረባቸው ዘመናት አልፎ ይገኛል።ስለዴሞክራሲ መስፋፋት የሚጽፉት አውራ ምሁራን ፍራንሲስ ፉኪያማ እና አማርትየ ሳን እንደሚሉት ጭቆና እየተገረሰሰ ነጻነት እያበበ ነው ባጠቃላዩ ሲታይ።በአሃጉራችን ናይጄሪያ፡ ጋና፡ ላይቤሪያ፡ ደቡብ አፍሪካ ፡ቦስዋና ለምሳሌ ያህል ይጠቀሳሉ። የዚህ ሂደት ተቃራኒው ክሚታይባቸው አገራት አንድዋ ኢትዮጵያ ናት።
ኢትዮጵያ ከህዝብዋ ብዛት መልክአ ምድርን ይዞ የዓለም ፖለቲካ ሽኩቻ ላይ ያለችበቱ አቀማመጥዋ ዋና ቦታ እዲኖራት የግድ ነው።የምንወዳት ስለሆነ ልንክባት ሳይሆን እውነታው ይህ ነው።ሀያላን ከደጇ እማይጠፉትም ለዚሁ ነው።ሁሉም ለጥቅሙ።ታዲያ ሁለት አሳዛኝ ጉዳዮች አሉ።አንደኛውና ዋነኛው የገዛ ጥቅሟን የሚጻረር ፍጹም አምባገነን መንግስት ተንሰራፍቶባት ይሄው ዘመናት ፈጅቷል።ሁለተኛው ያለውን አደገኛ መንግስት በግዜ እንዳይተካው የተቃዋሚው ሀይል በህብረት ሆኖ ዛሬ አለመጎልበቱ ነው።ትልቅ መሻሻል እያየን መሆኑ የማይካድ ቢሆንም።
ይችን ዴሞክራሲና ፍትህ ቧልት የሆኑባትን ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ኦባማ ለምን ለጉብኝት መረጥዋት ? በመጀመሪያ የአስተዳደር ዘመናቸው “አምባገነኖች ወዮላችሁ !”ሲሉ ቆይተው የአምባ ገነኖች የንብ ቀፎን ያስመረጣቸውን ምክኛት መመርመር ድንቅ ነው።ዛሬ ኢትዮጵያ ትልቅ እስር ቤት ናት።የታሰረ ልጠይቅ ብለው ይሆን ? ዘር ማጥፋት የተካሄደባቸውን ስፍራዎች በዓይናቸው በብረቱ ለማየት? ሻል ያሉ ምክንያቶች እናስብ እንጂ! ጎበዝ! የአባታቸውን አገር የደፈረውን አል ሸባብን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ?እግረ መንገዳቸው ደቡብ አፍሪካ ከመያዝ ያመለጠውን የሱዳኑን አል በሺር ጎራ ብለው ጋማውን ይዘው ዋንታናሞ ኩባ ሊሰዱት? ይህስ እንዴት ይረሳል። የአፍሪካ አምባ ገነኖችን አንድ ጋ አዲሳባ ሲማግጡ ሲያገኟቸው አንዱን በካልቾ! ሌላውን በኩርኩም! የቀረውን በቴስታ።ጉድ ሊያፈሉ ነው ለምርጫ ጊዜ እንደፎከሩት። ላቶ መለስ ለቅሶ ሊደርሱ? ይበቃል:: እኒህ የአስቂኙ ጓደኛዬ ወጎች ናቸው። አንድ ነገር እውነት ነው።ዋይት ሀውስ ከኦባማ ቤት በር ፊት ለፊት “ሚስተር ኦባማ! እረ ሚስተር ኦባማ ! አይሰሙም እንዴ ?” እያለን እንጮህ ለነበርነው ልጅነታችንን አስጨርሰውናል።በፖለቲካ ትግል ይህ አቢይ ጉዳይ ነው።ካባቶቻችን አልማር ያልነውን እንድንማር አድርገዋል።ትግሉ ባገር ቤት ባሉ ኢትዮጵያውያንና፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ባንድ ወገን ወያኔ በተቃራኒ መካከል ነው። ኦባማ ላሻቸው ወገን ቲፎዞ ይሁኑ።ባሻቸው በመሰላቸው ጊዜ። የመን የሆነው ይህ ነው። አሊ አብደላ ሳሊህ የኪሳቸው መሀረብ ነበር። የዛሬውን ሳይሆን።እኛ ኢትዮጵውያን ከሚገድለን የበለጠ የናቀን ላይ ቂም እንይዛለን። አንረሳም።ዴሞክራሲ ሲሉ ወያኔ ያረገው ምርጫ ይበቃችኋል ነው። በዚህ እንተወውና ሌሎች ምክንያቶችን እናቋጥር።እኛ ምን ቸገረን ሲሻቸው ሰሜን ኮሪያም ሄደው ከዚያ ድንቡሼ የአገሩ መሪ ጋር ቅርጫት ኳስ ይጫወቱ።ያችን አፈነዳታለሁ የሚላትን ነገርም ቢቀሙት ለዚያ አካባቢ ሰላም ነው።ከዚህ የተረፈውን ያገራችን ሙያተኛ ቀልደኞች ይቀጥሉበት።ዋና ጭብጥ ነገሮችን ከፌዙ በተረፈ ከዚህ በታች እንወያይ:: አካባቢያችንን በተመለከተ።
ከአመታት በፊት አሜሪካ በሶማሊያ የማይታረም ስተት ሰርታለች።እንዲያው ከኢራቅም ከሌሎቹም የቀበሌው ችግሮች በፊት የሶማሊያ ይቀድማል።ከዚያ ወዲያ ዘሎ መግባት በኢራቅ።ዘሎ መግባት በየመን።ጎረቤት ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ ነው።በዚህ በኩል ሲያስቡት ይዘገንናል::ህወሃት ልትጨምረን የምትፈልገው ገደል የመንን ይመስላል። ቶሎ ህብረት ፈጥረን ጊዜ ሳንወስድ ወያኔን እናስወግድ የሚለው ዓላማ በተጨባጭ ከዚህ ምክንያት ይነሳል። አገር የማዳን ትግል ሲባል ይሄው ነው።ኢትዮጵያ ሌላዋ ስተት አንዳትሆን::
የሶማሊያን ችግር ለመፍታት አማሪካ ዘወር ማለት አለባት።ሌሎች አውሮፓ፡ቻይና ሩሲያ ህንድ እኒህ ብልሃትና ዘዴው ተቀባይነትም ስለሚኖራቸው የተሻሉ ሽማግሌዎች ይሆናሉ።አልሸባብን ከአልቃይዳ ጉያ ሊያወያወጡ የተሻለ እድል አላቸው። የተቀረው አረብ ገንዘብ ያልቸገረው ቲርኪሚርኪ ነው።ምንአልባት ትናንሾቹ የአረብ ኤሚሪቶች ቦታ ይኖራቸዋል።ከዚህ የሰላም ሙከራ ውጭ ወያኔን ወታደራዊ ሀይል አቅራቢ አድርጎ፤ሰው አልባ አውሮፕላን ይዞ ለመዝመት ከሆነ የፈሪ በትር ይሆናል።የኢትዮጵያ ሰራዊትም ከድንበሩ ተሻግሮ በከንቱ አይሞትም።ስለዚህ ህወሃትም መለስ ዜናዊ አንዴ በልቶበት የነበረውን ዘዴ መቀየር ይገባት ነበር።መለስ ትቶት የሄደው ግምብ ራስ ሁሉ ተመልሶ ከዚያው! አዲስ ብልሃት ከየት ይምጣ ? ከሶማሊያም ሌላ የመን ሄዶ የአገራችን ሰው ለምን ይማገድ?ያውም ድንበር በማያስከብር ከሃዲ ቡድን እየተመራ።ማሃይም የህወሃት ጄኔራሎች ቀድመው ይግቡበት።ገንዘቡ ወደነሱ ኪስ ሞቱ ለተራው ወታደር መሆኑ ፍትሃዊ አይሆንም።
የየመንም ጉዳይ ውሉ ከተፈታ ቆየ። አሁን ተተብትቧል።የአየር ድብደባ አይፈታውም።የአየር ድብደባ ቀድሞ ቬትናም በኋለ አፍጋኒስታን አልፈየደም።በዚህም ግጭት የአውሮፓ፡ቻይና ሩሲያና የህንድ ሚና ካአሜሪካ ይሻላል።ላሁን ፍጥጫው የጥይት ድምጹ ሞቱ ስደቱ መቆሚያው አይታይም።
ቻይና የዛሬ አርባ አምስት ዓመታት፡ እኤአ 1970 መጀመሪያ ታንዛም የባቡር መስመርን በምስራቅ አፍሪካ ዘርግታለች።ይህ የባቡር መስመር ታዛንያን እና ዛምቢያን የሚያገናኝ 1710 ኪሎ ሜትር የሚደርስ በስድስት ዓመት ያለቀ ነው። ይህን ተግባር የምናነሳው የቻይናን አፍሪካን በጇ ማድረግ ስራ ቀደም ያለ እቅድ ያለው እንዳአማሪካ አንዴዚህ አንዴዛ እንዳልሆነ ለማሳየት ነው።ዛሬ ቻይና በአፍሪካ ተንሰራፍታለች።ለአምባ ገነኖች የጡት እናት እየሆነችም ቢሆን። ስለዚህ ኦባማ የአፍሪካን ወዳኝነት ለማግኘት ከሆነ ዉሻ ከሄድ ጅብ ጮኸ ነው።አምባ ገነኖቹንም ብዙ ገንዘብ ስላስለመደቻቸው ክፍያው ይበዛባቸዋል።ቻይናን ካፍሪካ ዘወር በይ የሚል የማን ወንድ፡ ነው?
ታዴያ የዲሞክራሲያዊ እና የሰብአዊ መብት ረገጣው ላይ ከመሳለቅ በተቀረ ከላይ ባነሳናቸው ጭብጦች ተነስተን የኦባማ ጉዞ ምን ይፈይዳል?ኬንያ ዘመድ ጥየቃ ቢያደርጉ መልካም ነው።ናይሮቢ ኤሌትሪክ አለ ስልክ ይሰራል ውሃ አለ። በጠቅላላው ካአዲሳባ ይልቅ ይመቻቸዋል። እዚያ ብቻ ቢሄዱ መልካም ነበር። ቱሪናፋን በስዋሂሊ ብችለው ደስ ይለኝ ነበር።
ኢትዮጵያን አምላክዋ ይጠብቃታል:: እብሪተኞችን ያንበረክካል!
በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞች፡የሀይማኖት መሪዎችን፡ የፖለቲካ መሪዎችን ለማስፈታት እንጩህ! የፍርድ ያለህ ! የነጻነት ያለህ!
ህወሃትን ከምድር ገጽ አጥፍተን ሽብርተኛ ዝር እማይልባትን ኢትዮጵያ እንገነባለን!
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!!!
The post ኦባማን የኢትዮጵያ መንገዳቸው ቱሪናፋ አያደ ርጋቸውም ? – ከቢላል አበጋዝ appeared first on Zehabesha Amharic.