(በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ ቁጥር 53 ታትሞ የወጣ)
ሮማን አብራሞቪች ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ ከመጡ 10 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡ ራሺያዊው ቢሊየነር ቼልሲን በእጃቸው ካስገቡ ወዲህ ወደ ታላቅነት አሸጋግረውታል፡፡ ሰውዬው የእንግሊዝን እግርኳስም መቀየር ችለዋል፡፡ አብራሞቪች በቼልሲ ባለቤትነት ቆይታቸው የፈፀሟቸውን አብይ ኩነቶች እንመልከት፡፡
በእግርኳስ ፍቅር መውደቅ
በ2003 ነበር፡፡ በቻምፒየንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድ በአስደናቂ መልኩ ማንቸስተር ዩናይትድን 4-3 ማሸነፍ ቻለ፡፡ በኦልድትራፎርድ ጨዋታውን ለመመልከት ከታደሙት መካከል ብዙም የማይታወቁ ራሺያዊ ቢሊየነር አንዱ ነበሩ፡፡ በምሽቱ ግጥሚያ በመመሰጣቸው ቀጣይ ጉዟቸው የእግርኳስ ክለብ መግዛት እንደሆነ ወሰኑ፡፡ ከበርቴው ጊዜያቸውን ሳያጠፉ ቼልሲን የግላቸው አደረጉ፡፡
ቼልሲ በለንደን የሚገኝ መሆኑና የአክሲዮን መዋቅሩ ክለቡን በቀላሉ እንዲያገኙት አድርጓቸዋል፡፡ ክለቡን ለመግዛት በአብራሞቪችና በወቅቱ የቼልሲ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ትሬቨር ቢርች መካከል ውይይት ተደረገ፡፡ ‹‹አብራሞቪች ክለቡ ሊገዛ መፈለጉን ሙሉ ለሙሉ ለማመን ተቸግሬ ነበር›› ይላል ቢርች፡፡ አብራሞቪች ክለቡን ለመጠቅለል የተጠየቁትን ገንዘብ ለመክፈል ተስማሙ፡፡ ከቢርች ጋር ያደረጉት ድርድርም 20 ደቂቃ ብቻ የፈጀ ነበር፡፡ ቢርች በወቅቱ የቼልሲ ባለቤት የነበሩት ኬን ቤትስን ካነጋገሩ በኋላ በቀጣዩ ቀን በዶርቼስተር ሆቴል ለመገናኘት ቀጠሮ ያዙ፡፡ አብራሞቪች ቼልሲን ለመግዛት 140 ሚሊዮን ለመክፈልና እዳውን ለመሸፈን በመስማማት ድርድሩ ተቋጨ፡፡ ከዚያም ሮማን በሁለት ወራት ውስጥ ለተጨዋቾች ግዢ ከ100 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ አውጥተዋል፡፡ በሁለት ዓመታት ጊዜ ደግሞ ጆን ቴሪ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ ማንሳት ችሏል፡፡ የእንግሊዝ እግርኳስም በለውጥ ጎዳና መጓዙን ጀመረ፡፡
የአሽሊ ኮል ውዝግብ
አቭራሞቪች ያለገደብ ገንዘባቸውን እንደሚያፈሱ ግልፅ የሆነው ወዲያው ነበር፡፡ በገንዘብ ጡንቻቸው የሚፈልጉትን መግዛት እንደሚችሉ አሳዩ፡፡ የወቅቱ የማንቸስተር ዩናይትድ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ፒተር ኬንየንን ወደ ስታምፎርድ ብሪጅ በማምጣት ሽግግሩን በፍጥነት መከወን ጀምረዋል፡፡ አብራሞቪች ካግሊያሪን ለመግዛት ሙከራ አድርገው እንደነበርም ተዘግቧል፡፡ ለዚህ ምክንያታቸው የሰማያዊዎቹ ኮከብ የነበረው ጂያን ፍራኮ ዞላ የጣልያንን ክለብ ለመቀላቀል በመፈለጉ ተጨዋቹን በስታምፎርድ ብሪጅ ለማቆየት ሲሉ ነበር፡፡
የቼልሲው ባለቤት በወቅቱ በግዢ ሪከርድነት ሊያዝ የሚችል 50 ሚሊዮን ፓውንድ ለአርሰናል በማቅረብ ቲዮሪ ሆንሪን ለማስፈረም ሞክረው ነበር፡፡ ሮማን ዕድሜው ለገፋው አንድሬ ሼቭቼንኮ ግዢ 30 ሚሊዮን ፓውንድ ማውጣታቸው ስህተት ከፈፀሙባቸው ዝውውሮች አንዱ ሆኗል፡፡ የሚፈልጓቸውን ተጨዋቾች ለማምጣት አብራሞቪች እጃቸውን ወደ ኪሳቸው ከማስገባት ወደኋላ አይሉም፡፡
ቼልሲ የትኛውንም ተጨዋች ለማስፈረም ከአቅሙ በላይ እንደማይሆን ማመን ጀመረ፡፡ ለተጫዋች ዝውውር ከፍተኛ ሂሳብ ለመክፈል ፍቃደኛ መሆኑ በበርካቶች ዘንድ አነጋጋሪ ሆነ፡፡ የአሽሊ ኮል ዝውውር ውዝግብ በጥሩ ምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆ ከአርሰናሉ የግራ መስመር ተጨዋች ጋር በለንደን አንድ ሬስቶራንት በመገናኘት በመወያየታቸው ቼልሲ ያለ አርሰናል ፍቃድ ኮልን በማነጋገሩ ጥፋተኛ ተብሎ ነበር፡፡ አርሰን ቬንገርም በወቅቱ የቼልሲን አቀራረብ ህገወጥ የፋይናንስ ስራ ብለውት ነበር፡፡ በመጨረሻ አብራሞቪች የሚፈልጉትን ተጨዋች አግኝተዋል፡፡ ኮል ወደ ቼልሲ ከመጣ ወዲህ ክለቡ ስምንት ታላላቅ ዋንጫዎችን ማሸነፍ ችሏል፡፡
አዲስ የልምምድ ማዕከል
የአብራሞቪች ረብጣ በተጨዋቾች ዝውውር ላይ ብቻ አልፈሰሰም፡፡ በቼልሲ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መሰረተ ልማት በማካሄድ ላይም ውሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት ቼልሲ በፋይናንስ አቅሙ በዓለም ላይ ከሚገኙ ታላላቅ ክለቦች ጎራ የሚቀላቀልበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ዴሎይቴ ባወጣው መረጃ ቼልሲ አርሰናል፣ ኤሲሚላን፣ ሊቨርፑልና ጁቬንቱስን በመብለጥ ከዓለም ታላላቅ ክለቦች ዝርዝር ላይ በአምስተኛነት ተቀምጧል፡፡ በአብራሞቪች ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ ክለቡ ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ከ700 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ የሆነው ብድር ወደ ወለድ የማይከፈልበት ብድር ተሸጋግሯል፡፡ ክለቡ አሁን ከእዳ ነፃ ነኝ ሊል ይችላል፡፡
ሮማን ቼልሲን በሁሉም ዘርፍ በፍጥነት እንዲያድግ ያደረጉት ጥረት በግልፅ ይንፀባረቃል፡፡ ከሀርሊንግተን የልምምድ ማዕከል በ2007 ወደ ተከፈተው ኮብሃም መዛወር ችለዋል፡፡ አብራሞቪች በወጣት አካዳሚው ላይ ያፈሰሱት ገንዘብ አሰልጣኞች ለወጣቶች እድል ለመስጠት በቂ ጊዜ ስለማያገኙ ስኬታማ ለመሆን አልቻለም፡፡ ቼልሲ ወጣቶችን እንዲያፈራ ያላቸው ፅኑ ፍላጎት ግን አነስተኛ ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡
የአቭራም ግራንት ሹመት
አብራሞቪች በቼልሲ በቆዩባቸው ያለፉት 10 ዓመታት ከፈፀሟቸው ተግባራት የሚጎላው የአሰልጣኞች ሹም ሽራቸው ነው፡፡ ጆዜ ሞውሪንሆን እንዲያሰናብቷቸው የገፋፋቸው በኮሪደር ላይ ፖርቹጋላዊው ሊያብራሯቸው እንደማይችሉ በመግለፃቸው ምክንያት እንደሆነ ዘገባዎች ይጠቁማሉ፡፡ በእርግጥ ሮማን ቁልፍ በሆኑ አማካሪዎቻቸው ያልተቋረጠ ድጋፍ ያገኛሉ፡፡ ከሊቀመንበሩ ብሩስ ባክ እስከ ዳይሬክተሮቹ ዩጂን ቴኔንባውምና ማሪና ግራኖቭስካይ ድረስ በዙሪያቸው አሉ፡፡ በባለሀብቱ ወሳኝ ሰዎች ተርታ በተለያዩ ጊዜ የገቡ ሌሎች ሰዎችም አሉ፡፡
ከእነዚህ መካከል የራሺያዊው ጥሩ የሆኑት አብራም ግራንት ይጠቀሳሉ፡፡ ግሪ በእስራኤል የሰሩት ስራ በቼልሲ የፉትቦል ዳይሬክተር መሆን እንደሚያስችላቸው አብራሞቪችን በማሳመን በ2007 ኃላፊነቱን ተረከቡ፡፡ በኋላም ጆን በመተካት የአሰልጣኝነቱን ወንበር ተቆናጠጡ፡፡ ግራንት ቼልሲን በቻምፒየንስ ሊጉ ፍፃሜ ቢያደርሱትም በማንቸስተር ዩናይትድ ተረትተው ዋንጫውን ሳያነሱ ቀሩ፡፡ የግራንት ስኬታማ ጉዞ አሰልጣኝ መቀያየር ውጤት እንደማይኖረው ለሮማን የቀረበ ማስረጃ ነበር፡፡ በኋላም አብራሞቪ ሉዊዝ ፌሊፔ ስኮላሪ፣ ጉስ ሂዲንክ፣ ካሮል አንቼሎቲ፣ አንድሬ ቪያስ-ቦአስ፣ ሮቤርቶ ዲ ማቲዎ እና ራፋ ቤኒቴዝን ቀያይረዋል፡፡ ወቅቱ የተጨዋቾች ተሰሚነት ይበልጥ የጎለበተ ነበር፡፡ ‹‹የአሰልጣኝነት እድሉን ለመጠቀም ካሰብክ ምናልባት ራስህን መጀመሪያ ማሰናበት አለበህ›› በማለት ፍራንክ ላምፓርድ ስለሚፋጀው ወንበር ተናግሮ ነበር፡፡
ከሙኒኩ ድል በኋላ ያደረጉት ንግግር
ባለፉት 10 ዓመታት አብራሞቪች ለእግርኳሱ ያላቸው ፍቅር በመቀዝቀዙ ቼልሲን የሚገዛ ባለሀብት ሊፈልጉ እንደሚችሉ ጭምጭምታዎች ይሰሙ ነበር፡፡ አብራሞቪች በዝውውር ላይ ገንዘባቸውን የቆጠቡበት ጊዜ ነበር፡፡ በስታዲየም ተገኝተው የታደሙበት ጨዋታዎች ብዛት አነስተኛ የነበረበት ወቅትም ነበር፡፡ በአንድ ወቅት ትኩረታቸውን ከቼልሲ ውጪ አድርገውም ነበር፡፡ ከራሺያዊው ጎን ያሉ ሰዎች ግን ባለሀብቱ ለእግርኳስ ያላቸው ፍቅር አለመቀዝቀዙን እና ለቼልሲ የሰነቁት ራዕይ እንደ ቀድሞው ጠንካራ መሆኑን በተደጋጋሚ ይገልፁ ነበር፡፡
ቼልሲ በ2011/12 ቻምፒየንስ ሊጉን ካሸነፈ በኋላ በመልበሻ ክፍል አብራሞቪች ያደረጉትን ንግግር ያደመጡ ሰውየው ስለወደፊቱ እያሰቡ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ‹‹ሮማ በመልበሻ ክፍሉ አጭር የምስጋና ንግግር አድርገዋል›› ሲሉ ባክ በወቅቱ የተከሰተውን ተናግረው ነበር፡፡ አብራሞቪች በቴኔንባውም አስተርጓሚነት በተረጋጋ መንፈስ ‹‹አሸንፈናል፡፡ ይህ ግን ገና መጀመሪያችን ነው›› ብለዋል፡፡
ጋርዲዮላ ሲያጡ ፊታቸውን ወደ ሞውሪንሆ መልሰዋል
ዲ ማቲዎ የቻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ ካመጣ ከስድስት ወራት በኋላ ከኃላፊነቱ ሲነሳ ዎል ስትሪት ጆርናል ‹‹የቼልሲ አሰልጣኝ ለመሆን የሚፈልግ ማነው?›› የሚል ርዕስ አውጥቶ ነበር፡፡ በእርግጥ መልሱ በርካታ ሰዎች የሚል ቢሆንም ርዕሱ የአብራሞቪችን አካሄድ በጥሩ ሁኔታ ይገልፃል፡፡ ሮማን አሰልጣኞችን የሚያሰናብቱት ዋንጫዎች ብቻ ፈልገው ሳይሆን ማራ አጨዋወት መመልከት ስለሚፈልጉም ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን በርካታ አሰልጣኞችን መቀያየራቸው አማራጫቸውን ገድቦባቸዋል፡፡
ፔፕ ጋርዲዮላ ከቼልሲ ይልቅ ባየር ሙኒክን የመረጠው የተሻለ ገንዘብ ፍለጋ አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ስፔናዊውን ያጡት አብራሞቪች አማራጭ ስለሌላቸው ሞውሪንሆን በድጋሚ ለማስፈረም ተገደዱ፡፡ የጆዜ ቅጥር በአሰልጣኞች ላይ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች ስህተት እንደነበሩ የመቀበል አይነት ይመስላል፡፡ ምናልባት ስኬታማ የነበሩት ሞውሪንሆን ማሰናበታቸው ስህተት እንደነበር ያመኑበት ሊሆን ይችላል፡፡ አሰልጣኞች ቢቀያየሩም ክለቡ ዋንጫዎቹን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሞውሪንሆን ባለፉት 10 ዓመታት በቼልሲ ቆይተው ቢሆን ቡድኑ ምን ያህል ዋንጫዎችን ሊያሸንፍ ይችል ነበር? የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡ አብራሞቪችና ሞውሪንሆ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ መረጋጋት እንደሚመርጡ እየተዘገበ ይገኛል፡፡ ከዚህ ውጪ በክለቡ ያለው ፍላጎት ማሸነፍ በቻ ሳይሆን በማራኪ አጨዋወት ስኬታማ መሆንም ጭምር ነው፡፡