በሰላሳዎቹ መጀመሪያ የምገኝ ሲሆን ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ወላጆቼና እኔ በአንድ ከተማ ውስጥ የምንኖር ሲሆን፣ እኔ የተከራየሁት ቤት ከቤተሰቦቼ የራቀ ነበር፡፡ እናቴ በተደጋጋሚ እያመማት ስለነበር በቅርበት ለመሆን ብዬ ቤት ተቀይሬ ወላጆቼ ያሉበት አካባ ተከራይተን ለመኖር ከባለቤቴ ጋር ወስነን ቀየርን፡፡ ይህ በሆነ በሁለት ወሩ አካባቢ እናቴ ሞተች፡፡ ከቆይታ በኋላ ባለቤቴ ‹‹እናትህ መሞታቸው ላይቀር የለመድኩትን ሰፈር አስለቅቀህ…›› ምናምን እያለች መጨቃጨቅ ጀመረች፡፡
የእኔ ሁኔታም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መጣ፡፡ አሁን መስሪያ ቤቱ በሰጠኝ የትምህርት ዕድል ተጠቅሜ በከተማችን በሚገኝ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪዬን እየተማርኩ ነኝ፡፡ ነገር ግን ለአለባበሴ ግድ የለኝም፣ ዝም ብዬ ተስፋ እቆርጣለሁ፣ የማልጠቅም ነኝ ብዬ አስባለሁ፣ ምንም ነገር ብሰራ አልደሰትም፣ የሚታየኝ መኝታ ክፍል ገብቼ መተኛት ብቻ ነው (በጣም ረዥም ሰዓት እተኛለሁኝ)፡፡
የቀድሞ ጓደኞቼን በሙሉ ርቄአቸዋለሁ፡፡ ትምህርቴን ላጠና እፈልግና ትኩረቴ አይሰበስብም (ማጥናትም ይደብረኛል)፣ የምግብ ፍላጎትም የለኝም (በቀን አንዴ ከበላሁ ይበቃኛል)፣ ወዘተ፡፡ አሁን ደግሞ በሁኔታዬ እናደዳለሁ፣ ይጨንቀኛል፡፡ ከስነ ልቦና አንፃር ሲታይ ይህንን ለማስወገድና እንደ ቀድሞዬ ለመሆን ምን ትመክሩኛላችሁ? ለምትሰጡኝ ምላሽ ከወዲሁ አመሰግናለሁ፡፡
የሁልጊዜ ተከታታያችሁና አድናቂያችሁ ካለሁበት፡፡
መልስ፡-
ከጽሑፍህ የተገነዘብኩት፣ በእንግሊዝኛው ‹ዲፕረሺን› በአማርኛው ደግሞ ድብት ተብሎ የሚጠራው ችግር ነው፡፡ ድብት ከስሜት ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ ምድብ የሚካተት ሲሆን በምድቡ ከተካተቱ ችግሮች ውስጥ በብዛት የሚከሰተው ድብት ነው፡፡ የድብት ምልክቶች ከሰው ሰው የሚለያዩ ቢሆንም፣ የዘርፉ ጠበብቶች ዋና ዋና ምልክቶች ያሏቸውን ለይተዋል፡፡ ከእነዚህ ዋና ዋና ምልክቶች ውስጥ፣ ሁለቱና ከዛ በላይ የሆኑት ለተከታታይ ሁለት ሳምንትና ከዛ በላይ አንተ ላይ ከተከሰቱ ድብት አለብህ ተብሎ ይወሰዳል፡፡ እነዚህ ምልክቶችም፡-
– ለነገራት የነበረን ፍላጎት መቀነስ ወይም ከዚህ በፊት ያዝናኑን የነበሩ ሁኔታዎች አሁን ደስታ አልሰጡን ማለት፣
– የድካም ስሜት መሰማት (ያለምንም ወይም በጥቂት አካላዊ እንቅስቃሴ)፣
– የማልቀስ ፍላጎት (በተደጋጋሚ ማልቀስ) እና በተደጋጋሚ መበሳጨት፤
– ብቻን የመሆን ከፍተኛ ፍላጎት፣
– የወሲብ ፍላጎት መቀነስ/ማጣት
– ለመተኛት አለመቻል ወይም እንቅልፍ ማብዛት፤
– የምግብ ፍላጎት መቀነስ ወይም በጣም መጨመር፤
– ትኩረትን መሰብሰብ አለመቻል ወይም ውሳኔ ለመስጠት መቸገር፤
– የባዶነት ስሜት መሰማት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት መሰማት፤
– ከፍተኛ የክብደት መቀነስ ወይም መጨመር፤
– የእረፍት ማጣት ስሜት ወይም ከመጠን በታች እየሰሩ እንደሆነ መሰማት፤
እንደ አሮን ቤክ ያሉ ታዋቂ የስነ ልቦና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፣ ራስን ከመጠን በላይ መመርመር፣ የአልጠቅምም ስሜትን ማዳበርና በግንኙነቶች መካከል ያልተፈቱ ችገሮች መኖር የድብት አይነተኛ ምንጮች ናቸው፡፡ እንደ ባለሙያዎቹ ማብራሪያም፣ ድብት መፍትሄ ካልተሰጠው እየተባባሰ የሚሄድና ወደ ዓለምን የመጠራጠር የሰብዕና ችግር እየተባባሰ ይሄዳል፡፡
ለድብርት የሚሰጠው ስነ ልቦናዊ ድጋፍ ዋነኛ አላማ ደግሞ፣ ግለሰቡ ስለራሱ እና ስለ ዓለም ያለውን አተያይ ማስቀየር ነው ይላሉ ጠበብቱ፡፡ በመሆኑም ጠያቂያችን የድብት ችግርህን ለመቅረፍ የሚያግዙ ሶስት በተከታታይ መተግበር ያለባቸው አቅጣጫዎችን እንጠቁምህና ተግብራቸው፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫ 1
አስተሳሰብን መለወጥ
የተወደድክ ጠያቂያችን ሆይ! አንድን ችግር ለመቅረፍ በመጀመሪያ ደረጃ ችግሩን በሚገባ መገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡ ስለሆነም አንተ ላይ እየታዩ ያሉ ምልክቶችን መመርመር የመጀመሪያው ተግባርህ መሆን አለበት፡፡ ይህንንም ለመከወን ወረቀት አውጣና በአንተ ላይ እየታዩ ያሉ ምልክቶችን ዘርዝረህ ፃፋቸው፡፡
ድብት በአምስት የተለያዩ የህይወት ዘርፎቻችን ላይ ምልክቶችን ያሳያል፡፡ አንደኛው በባህሪያችን ላይ ነው (ለምሳሌ ራስን ማግለል፣ ራስን መጣል፣ ወዘተ) ሁለተኛው በተነሳሽነታችን ላይ ነው፡፡ (ለምሳሌ ለነገሮች ያለን ፍላጎት መቀነስ) ሶስተኛ በስሜታችን ላይ ነው (ለምሳሌ መበሳጨት፣ መጨነቅ)፡፡ አራተኛ በአስተሳሰባችን ላይ ነው (ለምሳሌ ትኩረትን ለመሰብሰብ መቸገር)፡፡ አምስተኛ በአካላችን ላይ ነው (ለምሳሌ የድካም ስሜት፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት)፡፡ እናም በእነዚህ አምስት ዘርፎ ላይ አንተ ላይ እየታዩ ያሉ ምልክቶችን በዝርዝር መፃፍ፣ የችግርህን መጠን ለመረዳት ያስችልሃልና የመጀመሪያው ተግባርህ አድርገው፡፡
በመቀጠል የኋልዮሽ በመጓዝ የልጅነት ዕድሜህን መፈተሽ አስፈላጊ ተግባር ነው፡፡ በተለይ ደግሞ አንተን በማሳደግ ሚና ከነበራቸው ሰዎች ውስጥ የስሜት ችግር (ለምሳሌ ድብት፣ የስሜት መቀያየር ችግር ወዘተ) ያለባቸው ሰዎች መኖራቸውን ለይ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንደነዚህ አይነት ችግር ያለባቸው አሳዳጊዎች፣ ልጆችን የማግለል ባህሪ ስለሚታይባቸው ያሳደጓቸው ልጆች የመገለል ስሜትን ከህፃንነት ጊዜያቸው ጀምሮ ስለሚያዳብሩ፣ በጎልማሳነት ዕድሜያቸው ለድብት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ይሆናል፡፡
ልጅነትህን ከቃኘህ በኋላ የችግርህ መነሻ የት እንደሆነ መለየት ትችላለህ፡፡ ችግሩ ከየትም ይነሳ ከየት በመቀጠል መተግበር ያለብህ ጉዳይ፣ አሁን ያሉና ጠቃሚ ያልሆኑ አስተሳሰቦችህን መለየት ነው፡፡
ለምሳሌ ‹‹በሙሉ ትክክለኛነት መስራት ካልቻልኩ መስራቴ ዋጋ የለውም››፣ ‹‹የእኔ ዋጋማነት የሚለካው ሰዎች ስለኔ ባላቸው አመለካከት ነው››፣ ወዘተ የሚሉ አመለካከቶች ካሉህ ነቅሰህ ማውጣት፡፡ አስተሳሰቦችን ነቅሰህ ካወጣህ በኋላ ደግሞ ትክክለኛነታቸውን መፈተሹ ጠቃሚ ተግባር ነው፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ ያን አስተሳሰብ ለመያዝ ያስቻሉህ ምክንያቶችን መፈተሽ ተገቢ ነው፡፡ በምሳሌ ላስረዳህ፣ በጽሑፍህ ላይ ‹‹የማልጠቅም ነኝ ብዬ አስባለሁ›› ብለሃል፡፡ የማልጠቅም ነኝ ብለህ ለማሰብ ምክንያቶችህ ምንድን ናቸው? ምክንያቶችህስ የዚህ አይነት ድምዳሜ ላይ ለመድረስ በቂ ናቸው ወይ? በቂ ከሆኑስ (ከጽሑፍህ በመነሳት እኔ አይመስሉኝም) ጠቃሚ ሰው ለመሆን የተሻለው መንገድ የቱ ነው? መጨነቅ ወይስ የእርምት እርምጃ መውሰዱ? ወዘተ አይነት ጥያቄዎችን በማንሳት እያንዳንዱን አስተሳሰብህን መሞገት የአስተሳሰብ ለውጥ እንድታመጣ ዐብይ ሚና ይጫወታል፡፡
ከዚህ ጋር ተያያዥ የሆነው ሌላው ተግባር ራስህ ለራስህ ኃላፊነት መውሰድ ነው፡፡ በምንም መስፈርት ለአንተ ከአንተ የቀረበ ሰው የለም፡፡ አንተ የቤተሰብ ኃላፊ ነህ፡፡ ይህንን ኃላፊነትህን የምትወጣው በህይወት ስትኖርና ጤነኛ ስትሆን ነው፡፡ ስለሆነም ሌሎች ኃላፊነቶችህን ለመወጣት ከመሞከርህ በፊት በመጀመሪያ፣ አንተን ለራስህ በህይወትና በጤና መኖር የሚያስችሉህ ተግባር መወጣት ይጠበቅብሃል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በመጀመሪያ ለእኔ ተግባራት ኃላፊነት መውሰድ ያለብኝ እኔ ነኝ የሚል አስተሳሰብን መያዙ ወሳኝ ነው፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ካዳበርክ በኋላ ደግሞ ቀጥሎ የምጠቁምህን ተግባራት በመተግበር ሁኔታህን ወደ መለወጥ ትጓዛለህ፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫ 2.
ባህሪን መለወጥ
የተለያዩ የስነ ልቦና ጥናቶች እንዳሳዩት፣ የስሜት ለውጥ የባህሪ ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ ጉዳይ ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት፣ የናፈቀህን ሰው እቅፍ አድርገህ ስትስመው (ባህሪ) ውስጥህን ደስ ይልሃል (ስሜት)፡፡ በመሰረቱ የአንተ ችግር የስሜት ችግሮች ውስጥ የሚካተት ነው፡፡ ችግርህን ለመቅረፍ ደግሞ ባህሪህን በመለወጥ ስሜትህን መለወጥ ወሳኝ ነው፡፡ ባህሪህን ለመለወጥ ስትነሳ ደግሞ ከቀላል ባህሪያት መጀመሩ ተገቢ ነው፡፡ ከባድ ባህሪያትን ለመለወጥ ጀምረህ ባይሳካልህ ችግርህን እንደማያባብሰው ልብ ይሏል፡፡
በመሆኑም የመጀመሪያው ተግባርህ ማተኮር ያለበት ራስህን በመንከባከብ ላይ ነው፡፡ በቀን ውስጥ (ጠዋት ቢሆን ይመረጣል) ራስህን ለመንከባከብ የሚያስችልህ የሆነ ጊዜ መድብ፡፡ ይህን ስታደርግ ከዚህ ሰዓት እስከዚህ ሰዓት ብለህ መገደብ ይጠበቅብሃል፡፡ በዚህ በገደብከው ሰዓት ውስጥ መከወን አለብኝ የምትላቸውን ራስን የመንከባከብ ተግባራት ዘርዝረህ አውጣ (ለምሳሌ ሰውነቴን መታጠብ፣ ልብሴን መቀየር፣ ካልሲዬን ማጠብ፣ ጥሩ ምግብ መብላት፣ የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ፣ የታዘዘልኝን መድሃኒት መውሰድ፣ መጽሐፍ/ጋዜጣ መጽሔት ማንበብ፣ ወዘተ…)፡፡
በአጠቃላይ ለአንተ አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን በሙሉ መዘርዘር አስፈላጊ ነው፡፡ በመቀጠል ከእነዚህ ተግባራት ውስጥ በገደብከው ሰዓት ውስጥ የቻልከውን ለመከወን ጣር፡፡ የገደብከው ሰዓት ካለቀ ትግበራን አቁምና ወደ ሌሎች ተግባራቶችህ አምራ፡፡
በቀጣዩ ቀን ደግሞ ዝርዝርህ ውስጥ ያሉ ተግባራትን በወሰንከው የሰዓት ገደብ ውስጥ ብቻ ለመከወን ሞክር፡፡ እንዲህም እያደረክ ለተወሰኑ ቀናት ሙከራህን ቀጥል፡፡ በዚህ ወቅትም በየቀኑ የወከንካቸውን ተግባራት ቁጥር በመመዝገብ፣ ከቀን ቀን ቁጥራቸውን ለመጨመር ጥረት አድርግ፡፡ በስተመጨረሻው በገደብከው ሰዓት የምትከውናቸው ተግባራት ቁጥር እየጨመረ ሲሄድና የድብት ሁኔታህም በመጠኑ የቀነሰ መስሎ ሲሰማህ ወደ ቀጣይ ተግባራት ታመራለህ፡፡
ቀጣይ ተግባራህ የጊዜ አጠቃቀምህን በተወሰነ መልኩ ማስተካከል ነው፡፡ በአንተ ላይ ከታዩ የድብት ምልክቶች አንዱ የበዛ እንቅልፍ መተኛት ነው፡፡ በመሆኑም በየቀኑ የተኛኸውን ሰዓት በማስላት በአንድ ሳምንት ውስጥ በአማካኝ በቀን ምን ያህል ሰዓት እንደምትተኛ አስላና አግኝ፡፡ በመቀጠልም በስሌት ካገኘኸው ሰዓት ላይ አንድ ሰዓት ያነሰ ለመተኛት ዝግጅት አድርግ፡፡ በአጠቃላይም በሳምንት ሰባት ተጨማሪ ሰዓታት ታገኛለህ፡፡ ድብት የያዛቸው ሰዎች መተኛት የሚያበዙት፣ በነቁበት ሰዓት የሚሰሩት ነገር ማጣታቸው አንደኛው ምክንያት ነው፡፡
ስለሆነም ትርፍ ያገኘኸውን ሰዓት ለሁለት ተግባራት ለማዋል ጣር፡፡ አንደኛው ስታወራቸው የሚያዳምጡህ ሰዎችን ፈልግና (ለምሳሌ ልጆችህን) ከእነሱ ጋር ለማሳለፍ ሞክር፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከዚህ ቀድሞ ስትከውናቸው የሚያዝናኑህ አሁን ግን ብዙም የማይመስጡህ ተግባራት ላይ ለማድረግ ሞክር (እደበረህም ቢሆን)፡፡ እነዚህን ተግባራት መከወንህ የእንቅልፍ መጠንህን ይቀንሳል፣ የእጠቅማለሁ ስሜትህን ያዳብራል፣ ብሎም የተለያዩትን ስሜታዊ ችግሮችህን ይቀንሳል፡፡
የመፍትሄ አቅጣጫ 3
ራስህን መፈተሽ
ቀደም ሲል የጠቆምኩህን አቅጣጫዎች በሚገባ ከውኛቸዋለሁ ብለህ ስታምን ወደዚህኛው አቅጣጫ ፊትህን አዙር፡፡ ጊዜ ውሰድና የእኔ ጠንካራ ጎኖችና ልጠቀምባቸው የምችላቸው ዕድሎች ምን ምን ናቸው ብለህ በዝርዝር ፃፋቸው፡፡ ይህን በፃፍክበት ወረቀት ጀርባ ደግሞ ደካማ ጎኖችና ላሻሽላቸው የሚገቡት የትኞቹ ናቸው ብለህ ዘርዝር፡፡ በተመሳሳይም ነገራትን እንዳልከውን የሚገድቡኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው ብለህ ፃፋቸው፡፡
በመቀጠል ከደካማ ጎኖችህ አንዱን ብቻ በማንሳት፣ እንዴት ማሻሻል እንደምትችል አቅጣጫ ንድፍና ትኩረትህን በእሱ ላይ በማድረግ ለማሻሻል የምትችለውን ሁሉ አድርግ፡፡ ያን ደካማ ጎን በተወሰነ መልኩ አሻሽያለሁ ብለህ ስታምን ወደ ሌላኛው ደካማ ጎንህ ማሻሻል አዝግም፡፡ በተመሳሳይ በእያንዳንዱ ገዳቢ ነገር ትክክል ገዳቢው ሁኔታ ሲመጣ፣ እንዴትስ ልታልፈው እንደምትችል/እንዳለብህ አቅጣጫ አስቀምጥ፡፡ እነዚህን ተግባራት መከወን ህይወትህ ወደተለመደው/የቀድሞው ሁኔታህ እንዲመለስ ያደርጋል፡፡
በስተመጨረሻ አንድ ሶስት የሚሆኑ ማሳሰቢያዎች አሉኝ፡፡ አንደኛውና ዋነኛው እነዚህን አቅጣጫዎች ስትተገብር በቅደም ተከተል መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ለምሳሌ ዘለህ ደካ ጎንህን ለመለወጥ ብትሞክር ችግርህን የመቅረፍ ሁኔታህ አናሳ ይሆናል፡፡ ወይም ደግሞ ችግርህን ታባብሰዋለህ፡፡ ሁለተኛው ማሳሰቢያዬ የተለያዩ ዕፆችን ወይም ያልታዘዙ መድሃኒቶች ወይም መጠጦችን የምትጠቅም ከሆነ ከቻልክ ለሁሌ ካልቻልክ ደግሞ ከችግርህ እስክትወጣ አቁማቸው፡፡
ወደ ሶስተኛውማሳሰቢያዬ ስዘልቅ፣ ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት የድብት ችግር ያለባቸው ወላጆች በቀጣይ ወደ ድብት ያጋልጣቸዋል፡፡ ስለሆነም በተቻለህ አቅም ልጆችን ከማግለልና ከመቆጣት ራስህን ቆጥብ ባይ ነኝ፡፡ እነዚህን ካልኩ በኋላ ደግሞ መልካም የለውጥ ጊዜ እየተመኘሁልህ የዛሬ ምክሬን በዚሁ አጠናቅቃለሁ፡፡
The post Health: ድብት እያንገላታኝ ነው፤ ምን ትመክሩኛላችሁ? – ጥያቄና 3ቱ መፍትሄዎች appeared first on Zehabesha Amharic.