Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ህወሓት እና የሀውዜኑ ጭፍጨፋ

$
0
0

ከጌታቸው ሽፈራው

በደርግ ዘመን ከተፈፀሙት ጭፍጨፋዎች መካከል ሀውዜን ከተማ ላይ የተደረገው በዘግናኝነቱ ይጠቀሳል፡፡ ይህን ጭፍጨፋ ያከናወነው ደርግ መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም ህወሓት በጭፍጨፋው ላይ እጁ እንዳለበት የሚናገሩ አልጠፉም፡፡ በመሆኑም በዚህ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የጠራ አመለካከት ሳይያዝ ቀጥሏል፡፡

hawzen
የቀድሞው የህወሓት ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ‹‹A Political History of the Tigray People’s Liberation Front (1975-1991): Revolt, Ideology and Mobilization in Ethiopia›› በተሰኘ መጽሃፋቸው እ.ኤ.አ በ1983 ትግራይ ውስጥ ይደረግ የነበረው ትግል የኢትዮጵያ አብዮት አንድ አካል መሆን አለመሆን ላይ አለመግባባቶች እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ እንደ አባይ ጸሃዬና መለስ ዜናዊ የመሳሰሉ አመራሮች አብሮ ለመስራት የሚያስችል ድርጅት ባለመኖሩ ህወሓት የትግራይን ነፃ መንግስት ለመመስረት በተቀረፀው ማንፌስቶው መሰረት መታገል እንዳለበት ውሳኔ ይተላለፋል፡፡ ከዚህ ጊዜ በኋላ አብዛኛው ታጋይ እነ አቶ መለስ ባስቀመጡት አላማ መሰረት ትግሉ ቀጠለ፡፡
ሆኖም የህወሓት ሰራዊት ትግራይን ነጻ ማድረግ ከጀመረ በኋላ አቋሙን ቀይሮ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል በተለይም ወሎና ጎንደር እንዲዘምት ያዛል፡፡ በዚህ ወቅት አብዛኛው እነ አቶ መለስና አባይ ጸሃዬ ባሰረጹት ጥላቻ አዘል ብሄርተኝነት ያታነጸ አብዛኛው የህወሓት ሰራዊት ‹‹በማንፌስቴው መሰረት የራሳችን የትግራይን መንግስት እናቋቁማለን›› በሚል ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል ለመዝመት ፈቃደኛ ሳይሆን ይቀራል፡፡ ስለሆነም እነ አቶ መለስ ደርግ እስካልተደመሰሰ ድረስ የትግራይ ህልውናም አደጋ ላይ መሆኑን በማሳየት ሰራዊቱን ለማንቀሳቀስ የሚያስችል ስልት መንደፍ የግድ ሆነባቸው፡፡ የሀውዜን ጭፍጨፋም ደርግ በትግራይ ልይ የሚፈጥረውን አደጋ በማሳየት ይህን ሰራዊት ለማንቀሳቀስ የተጠነሰሰ የወቅቱ ሴራ መሆኑን ይነገራል፡፡
የገብረመድህን ምስክርነት 

ስለ ሀውዜን ጭፍጨፋና ስለ ሌሎች የህወሓት ሚስጥሮች በቀዳሚነት እየተናገሩ ከሚገኙት መካከል ገብረ መድህን አርዓያ የተባሉ የቀድሞ የህወሓት አመራር ይገኙበታል፡፡ አቶ ገብረ መድህን እንደሚሉት የሀውዜን ጭፍጨፋ ሚስጥር የሚጀምረው የህወሓት ሰራዊት ከትግራይ ውጭ መዋጋት እንደማይፈልግ አቋን በገለፀበት ወቅት ነው፡፡ በወቅቱ የህወሓት አቋም ያልተስማማው 10 ሺህ ያህል ሰራዊት ከጦር ሜዳ አፈግፍጎ ወደ ትውልድ ሰፈሩ ተመልሷል፡፡ ይህ የሰራዊቱ አቋምም የህወሓትን የመጨረሻ አጣብቂኝ ውስጥ ያስገባ ነበር፡፡ በመሆኑም እነ ስብሃት ነጋ፣ መለስ ዜናዊ፣ ገብሩ አስራትና ሌሎቹም ሰራዊቱ ድረስ በመሄድ ለማግባባት ጥረዋል፡፡ አልሆን ሲል ከጦር ሜዳ ያፈገፈጉት የሰራዊቱ አባላትም ታድነው እንዲያዙ ተደርገዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸውም የተመለሱትን የሰራዊቱን አባላት ይዘው እንዲሰጡ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ አብዛኛዎቹም ታስረዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካታ የሰራዊት አባለት ጠፍተው መቅረታቸውን የሚገልጹት አቶ ገብረ መድህን በድሮው የእነ መለስ አስተሳሰብ አምነው ‹‹እኛ ትግራይን ነፃ አውጥተናል›› ብለው በተመለሱ የሰራዊቱ አባላት ላይ ግድያ መፈፀሙንም መስክረዋል፡፡
ይህ የህወሓት እርምጃ ግን ሰራዊቱ ወደ ቀሪው ኢትዮጵያ ክፍል እንዲዘምት ለማሳመን በቂ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ሌላ ስልት መነደፍ ነበረበት፡፡ ሀውዜንን ማስጨፍጨፍ፡፡ አቶ ገብረ መድህን አርዓያ እንደሚሉት ህወሓት የትግራይን ከተሞች በማስደብደብ ህዝብን ማንቀሳቀስ የጀመረው በሀውዜን አይደለም፡፡ ከሀውዜን ቀደም ብሎም በተንቤን፣ አብአዲና ጭብሃ የተባሉ አከባቢዎች ላይም የህወሓት አመራሮችና ሰራዊቱ ከተሞቹ ውስጥ እንዳለ በማስመሰል ከተሞቹን በደርግ አስደብድቦ ህዝብን ለማንቀሳቀስ ጥሯል፡፡
ሀውዜንን በማስደብደብ ሰራዊቱ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እንዲዘምት ያስችላል የተባለለትን ስልት የቀየሱት አቶ መለስና ስብሃት ነጋ መሆናቸውን ገብረ መድህን አርዓያ ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ፡፡ ለዚህም ሲባል ህወሓት ሀውዜን ውስጥ ትልቅ ሰሚናር እንደሚያካሂድ ማስመሰልና ‹‹ሚስጥሩም›› ወደ ደርግ እንዲሾልክ ማድረግ ነበረበት፡፡ ህወሓት ስለሚያደርገው ሰሚናርም አሳማኝ መረጃ በወቅቱ የትግራይ ክፍለ ሀገር ገዥ ለነበረው ለገሰ አስፋው እንዲደርስ ይደረጋል፡፡ ይህ ሚስጥራዊ የተባለ መረጃ መቀሌ ለሚገኘው የክፍለ ሀገሩ ገዥ እንዲደርስ የተደረገውም በወቅቱ የወታደሩ ደህንነት የነበረው ሀይሉ በርሄ የተባለ ሰው አማካኝነት መሆኑን ገብረ መድህን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ጥብቅ የተባለ መረጃም ከለገሰ አስፋው ወደ ማዕከላዊ መንግስቱ ይላካል፡፡ አቶ ገብረ መድህን እንደሚሉት ህወሓት በለገሰ አስፋው የደረሰው መረጃው ትክክል መሆኑን ለደርግ ለማሳየት ሌሎች መንገዶችንም በመጠቀም ሀውዜን ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ አሰቃቂ እንዲሆን በርትቶ ሰርቷል፡፡ ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው ለአካባቢው ህዝብ ሃውዜን ውስጥ የህወሓት ስብሰባ እንዳለ ውስጥ ውስጡን ማስወራት ነበር፡፡ በሁለተኝነት ደግሞ ሰሚናሩ ይካሄድበታል በተባለው ሰሞን የህወሓት ሰራዊትን ሀውዜን ውስጥ ሰፊ እንቅስቃሴ እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡
ድብደባው ቅዳሜ ሊደረግ አረብ ቀን በታደሰ ወረደ የሚመራና ሌላ አንድ ክፍለ ጦር ሀውዜን ውለውን እንዲመለስ ይደረጋል፡፡ በተራውም ሌላ ክፍለ ጦር መጥቶ ለቅዳሜ እንዲያድር ይደረጋል፡፡ ከሀገር ገዥው፣ ከህዝቡና ሽርጉድ ይል ከነበረው የህወሓት ሰራዊት አንጻር ሰሚናር መኖሩን እርግጠኛ የሆነው ደርግም ህወሓትን ለመደምሰስ ዝግጅት አድርጎ መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ሲዘጋጅ የሰነበተው ደርግም ህወሓት በሌለበት በገበያ ቀን ከተማው ውስጥ የነበረውን ከ3000 በላይ ህዝብ ጨፍጭፏል፡፡
አቶ ገብረ መድህን የሀውዜን ጭፍጨፋ የህወሓት እጅ አለበት ሲሉ የሚያቀርቡት ማሳመኛ መካከል በወቅቱ ህወሓት ያደረገው ያልተለመደና አነጋጋሪ ቀረጻ አንዱ ነው፡፡ እንደ ቀድሞው የህወሓት ታጋይ ከሀውዜን በፊት ሀወሓት ህዝብን ለማንቀሳቀስ ሲልም ያስደበደባቸውም ሆነ ደርግ በራሱ ጥቃት ያደረሰባቸው የትግራይ ከተሞች ላይ ድብደባ ሲደረግ ህወሓት በከተሞች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት የመቅረጽ ልምድም ሆነ አቅም አልነበረውም፡፡ የሀውዜን ጭፍጨፋ በዘመናዊ ካሜራ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ህወሓት እንደቀረጸው የሚጠቅሱት ገብረ መድህን ሴራውን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል ባይ ናቸው፡፡ እንደ ገብረ መድህን እነ አቶ መለስ ሀውዜንን ለማስጨፍጨፍ እቅድ እንዳወጡ 12 ያህል ታጋዮችን ወደ ሱዳን ልከው ስለ ካሜራ ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል፡፡ ወደ ሱዳን በመሄድ ስልጠና አግኝተው ደርግ በከተማዋ ላይ የሚያደርገውን ድብደባ ከቀረጹት 12 ታጋዮች መካከል እያሱ በርሄና ሱራፌል የተባሉ የህወሓት ታጋዮች እንደሚገኙበትም አቶ ገብረ መድህን በትውስት ይናገራሉ፡፡ የእነዚህ ስለ ስለ ቀረጻ ስልጠና የወሰዱ ታጋዮችም ቦታ ቦታቸውን ይዘው የደረግን ጥቃት መጠባበቅ የጀመሩት ድብደባው ከሚደረግበት አንድ ቀን ቀደም ብለው ነው፡፡
ደርግ ከተማዋን በበርካታ ሚጎች ሲያወድም ከተለያየ አቅጣጫ ይጠባበቁ የነበሩት ታጋዮች ትዕይንቱን በካሜራቸው ሲያነሱ መዋላቸውን አቶ ገብረ መድህን ይገልጻሉ፡፡ ይህ ሲቀረጽ የዋለው ፊልምም ወደ ሱዳን ተልኮ ጭፍጨፋው በተደረገበት ቀን ማታ በበርካታ ቴሊቪዥኖች መታየት ችሏል፡፡ ደርግ ድብደባውን ባደረገበት ወቅት ምንም አይነት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ጋዜጠኛ ሀውዜን ውስጥ እንዳልነበረ የሚጠቅሱት አቶ ገብረ መድህን በውጭ አገር ቴሊቪዥኞች ይተላለፍ የነበረው ህወሓት ሲያስቀርጸው የዋለው ፊልም መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ህወሓት ለሀውዜኑ ጥቃት ድርግ ብቸኛው ተጠናቂ መሆኑን እየገለጸ ነው፡፡ በተቃራኒው የህወሓት አባላት ደግሞ ህወሓትም ደርግ ያደረገውን ጥቃት አቀነባብሯል በሚል ቀዳሚ ተጠያቂ ያደርጉታል፡፡ በወቅቱ ጭፍጨፋውን በበላይነት አስፈጽመዋል የተባሉት አቶ ለገሰ አስፋውን ጨምሮ በርካታ የደርግ አባላት በዚህ ተጠያቂነታቸው ተፈርዶባቸዋል፡፡ በአንጻሩ በፓርቲው አባል በነበሩ አካላት ሳይቀር የሚወቀሰው ህወሓት እስካሁን ተጠያቂ አልሆነም፡፡ ህወሓት በአባላቱ የሚደርስበትን ወቀሳ እውነት አለመሆኑን ለማሳየትም አጣሪ አካል አለመመደቡም ጉዳዩ እስካሁንም ግራ እንዳጋባ ቀጥሏል፡፡
ህወሓት ይህን ክስ የሚያስተባብልበት አሳማኝ መረጃ ማቅረብ ካልቻለ ህዝብ ሊያምን የሚችለው በእነ ገብረ መድህን ምስክርነት ነው፡፡ በተቃራኒው የደርግ አባላት ፍርዳቸውን ቢጨርሱም የህወሓት አባላት እያወጡት የሚገኘው ሚስጥር ላይ ተጨባጭ መረጃ በማቅረብ ከጭፍጨፋው በስተጀርባ ህወሓት መኖሩን ማረጋገጥ ቢችሉ የተሸከሙትን የህሌና እዳ ማቃለል እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡ በሌላ በኩል በችግሩ ላይ የህወሓት እጅ እንዳልነበረበት ማረጋገጥ ቢችሉም ህዝብ በጉዳዩ ላይ የጠራ አመለካከት እንዲኖረው በማድረግ ግዴታቸውን መወጣት ይችላሉ፡፡

The post ህወሓት እና የሀውዜኑ ጭፍጨፋ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>