Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሚካኤል ዲኖ ገጹ ላይ ካሰፈረው… –ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

$
0
0

“አቧራውን ስለማጥራት” ወይስ እውነታውን ስለማድፋፋት!?

Dr Dagnachewእንደአንዳንድ ምሁራን ሁሉ ዶክተር ዳኛቸውም ሀሳቡን በፅሁፍ የመግለፅ ክህሎት ስለሌለው፣ መሐመድ ሀሰን በተባለው ጋዜጠኛ አሰናኝነት፤ ለህትመት እንዲበቃ እየሰራ መሆኑን ከሰማው ከርሜያለሁ። የዶክተር መረራን ስህተት ላለመድገም መጠንቀቁንም አድንቄያለሁ።
በመፅሃፉ መውጣት ዋዜማ፦ ‘በነገው ቀን ይጠብቋት’ አይነት ፖስት ተመልክቼ፤ ‘ሞቱበት እኮ!’ ብዬ አሽማጥጬ ሳልጨርስ፤ የዘራፊ እና ተዘራፊ፣ የውስጥ አዋቂ አባሪ እና የአቧራ አጥሪ ውዝግቦች ተከታተሉብኝ።
በቅደም-ተከተል ከተቀመጡ የመጀመሪያ የሚሆነው ዶክተር ዳኛቸው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጉዳዩን ይፋ ማድረጉ ነው። ዶክተር በድሉ የትራጀዲውን ሌላ ተዋናይ ጨምሮ የተከሰተበት ሁለተኛው ሲሆን፣ ሶስተኛው እና የዚህ ፅሁፍ መንስኤ የሆነው ደግሞ በአቶ አስራት የቀረበው አቧራማ ማስተባበያ ነው።

አስራት፣ እራሱን በቅጡ በመከላከል ፈንታ በመግቢያ ትረታው፣ በእግረ-መንገድ የተጠቀሰውን ተወቃሽ ስም (ሰለሞን ስዩም) በማጎን፤ ለጉዳዩ ሌላ መልክ ለመስጠት ሲጣጣር ትዝብታችን ሀ… ብሎ ይጀምራል።
በመደናገጥ ወደኋላ ተመልሶ የጠቃቀሳቸው ተጋድሎዎቹም ሆኑ አበርክቶዎቹም ቢሆኑ፤ አሁን ላይ እየተወቀሰበት ካለው ጉዳይ ጋ አንዳች ቀጥተኛ ግንኙነት እንደሌላቸው ስናጤን አግራሞታችን መጨመሩ አይቀርም።

በዶክተር በድሉ ላይ በ’አጋለጥከኝ’ መግፍኤ ከተርከፈከፉት፣ የአቶ አስራት ዓውድ-ዘለል ጥይቶች ብስጭት- ወለዶች ናቸውና በቸልታ ልለፋቸው። በእርግጥም በአስራት አብርሀም የፖለቲካ ተክለ-ሰውነት እና ማንነት ደረጃ ላይ የሚገኝ ሰው፣ ሰብእናው በውስልትና እና በንፅህና መካከል ለሙግት ቀርባ ሳለ፣ በመጠሪያ ስም የፊደል ግድፈት ላይ ለማተኮር መሞከሩ የሚይዝ የሚወረውረውን እንዳጣ ያሳያል።
አስራት፤ ዶክተር ዳኛቸው እንደተናደደበት ሲናዘዝልን፣ በትይዩ የክሱን እውነተኛነት እያስረገጠልን እንደሆነ ልብ ማለቱን እጠራጠራለሁ።
የዳኛቸውን ንዴት ሲዘረዝርልንም… አንድም ከመፅሀፉ ጀርባ በሰጠው የተጋነነ አስተያየት (ብለርቡ ላይ የፀሀፊው አስራት ሳይሆን፣ የአከፋፋዩ አስራት መንፈስ እንደሚገን መገመት ይቻላል)፣ አንድም መፅሀፉን በማከፋፈሉ ሳቢያ እንደነበር በመግለፅ ነው።
በተማሪው እና ከስሩ በማይጠፋ “ወዳጁ” የተከዳው ምሁር፣ መናደዱን ከመግለፅ በላይ ምን ሊያደርግ ይችላል?!!!

አስራት ሆይ… ታዲያ ስለግለሰብ ክህደት፣ ብረት አንስቶ ጫካ ይግባ ወይስ ማቅ ለብሶ በሩን ዘግቶ ‘ ወዮ ወዳጅነት’ እያለ ይማቅቅ????? የወዳጅህን መከፋት አቃለህ ማቅረብህስ ምን ማለት ነው?
እስከአሁን ስለጉዳዩ በይፋ ሲናገር ያልሰማነው መሀመድ ሀሰን የተባለውን ፀሀፊ፤ በህግ ለመፋረድ መወሰኑን የተናገረው ዳኛቸው፤ አስራትን ያልጠቀሰው ምናልባት የወዳጅነት ይሉኝታ ይዞት እንደሁ እንጂ አንድነታቸውን ጠፍቶት አይመስለኝም።
አስራት ዝቅ እያለ ሲሄድ ሀፍረቱን መከለል በማይችሉ ብጥቅጣቂ ምክንያቶች እና ህፃን በማይረታላቸው ሽንገላዎች፣ ጉዳዩን ለመሸፋፈን ሲወራጭ በግልፅ መመልከት ይቻላል።
‘ተራ ያልሆነ ወዳጅነት፣ ከአባት እና ልጅ ፍቅር የሚገዳደር ቀረቤታ..’ እያለ የገለፀውን የግንኙነት መደላደል ተጠቅሞ በምንተፋው መተባበሩ ሳያንስ፤ ምንተፋው ዶክተሩን በማስተዋወቅ ረገድ ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ በልበ’ሙሉነት ለማብራራት ሲሞክር እጅግ ያስደነግጣል!!!
የአስራት ካፈርኩ አይመልሰኝ ሰለባውን ከመምከር እስከ እስከመሸንገል ብሎም ዋነኛው ሌባ ድርጊቱን የፈፀመው በቅን መንፈስ ተነሳስቶ መሆኑን እስከመመስከር ይበረታል። አቶ አስራት፣ ዶክተር ዳኛቸው ሰብስቦ ከማሳተም ይልቅ ወጥ ስራ መስራት እንዳለበት መክሮ ሲያበቃ፤ ‘ወደፊት የተሻለ ስራ የመስራት ብቃት እንዳለህ አውቃለሁና ይሄኛውን ዝርፊያ እርሳው’ እስከማለት ይደፍራል።
እውነቱን ለመናገር ” አቧራውን ስለማጥራት” በሚለው ርእሱ ተታልዬ አይኔን ከፍቼ በገባሁበት ፅሁፍ፣ አስራት እራሱን በዘላቂው በጥራት ማየት እንዳልችል በሚያደርግ ሁኔታ አቧራ ሞጅሮብኝ እየተጨናበስኩ ተመልሻለሁ።

በመጨረሻም ግን….
ከእንግዲህ ያለው ደባሪ ታሪክ በኋላ ማንሳት የሚቻለው ነገር…. በተቃዋሚ ፓርቲ፣ በነፃው ሚዲያ፣ በሲቪል ማህበራት… ወዘተ የነፃነት ትግሉን በምናዘምት ፊት-አውራሪዎች ልብ ውስጥ ሳይቀር፤ ይገለጥበት አምባ ያላገኘ.. አምባገነንነት፣ ጥቅመኝነት፣ አድር-ባይነት፣ ይስሙለኝነት፣ ይሉኝታ-ቢስነት እና ጨካኝነት አድፍጧል።
በመላው ኢትዮጵያ ጓዳ ከሚገኘው ማድጋ የተመረዘውን ውሀ እያጠጣን አይደል ዛሬ እነዚህን የመሰሉ አረሞች ያበቀልነው? እንደማህበረሰብ፣፣ ችግሩ እኛም ዘንድ መሆኑ አይካድም።
ቢያንስ ግን የነፃነት ታጋዮች፣ እንዲህ ካለው የሰብዕና እድፍ ራሳችንን ባላፀዳንበት ሁኔታ፣ ምናልባት የወያኔን አገዛዝ ማስወገድ ብንችል እንኳ፣ በአዲስ አቁማዳ ነባሩን ብጥብጥ አገላብጠን እሱኑ እየቀዳን ሕዝቡን ከማሳከር የተሻለ አንዳች ተግባር አንከውንም።

The post ሚካኤል ዲኖ ገጹ ላይ ካሰፈረው… – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>