“ለማንኛውም የምከፍለው ዋጋ ለለሃገሬና ለነፃነት ነው፡፡ በአካል ብታሰርም ህሊናዬ አይታሰርም፡፡ ከገደሉኝም ትግሌን አደራ!!! አገራችን የወያኔ ዘረኞች ብቻ መፈንጫ መሆን የለባትም! ትግላችን የነፃነት፤ ጉዞአችን ጎርባጣ፤ መድረሻችን ነፃነት፤ ታሪካችን ዘላለማዊ ነው፡፡” ሳሙኤል አወቀ ፊስቡክ ገፅ ላይ የተገኘ ሰኔ 8/2ዐዐ7 ዓ.ም፡፡
ምስራቅ ጎጃም ግንደ ወይን 1978 ዓ/ም ተወልዶ – በህግ የዲፕሎማ እና ዲግሪውን ሰርቷል፡፡ ሣሙኤል አወቀ የሠማያዊ ፓርቲ መስራች አባልና ከዚያም በፊት እንደ ሌሎች ጓደኞቹ ከቅንጅት ጀምሮ በአንድነት ፓርቲ ውስጥ ሲታገል የቆየ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ ነበር፡፡ ሣሙኤል በሙያው የህግ ባለሙያና በጥብቅና ስራ በግል እየሠራ ጎን ለጎን ደግሞ ለአገሩ ከነበረው ፅኑ ፍቅር የተነሣ በሠላማዊ ትግል በማመን ገና በልጅነቱ ትግሉን ተቀላቅሎ በግፍ እስከተገደለ ድረሥ በንቁ የፖለቲካ አመራር ሲታገል ቆይቷል፡፡ ሣሙኤል የሠማያዊ ፓርቲ ከተመሠረተ ጀምሮ በከፍተኛ ኃላፊነት በንቃትና በተደራጀ መልኩ በተወከለበት ቀጠና በምስራቅ ጎጃም ዞን ሲያደራጅና ሲያስተባብር ነበር፡፡
ሳሙኤል አወቀ በአካባቢው ዘንድ የተከበረ እና ምስጉን ወጣት ነበር፡፡ በቅርቡም በተደረገው ሃገራዊ ምርጫ ፓርቲውን ወክሎ የዞኑ የተወካዬች ም/ቤት ጠንካራ ተወዳዳሪ እንደነበር አስመስክሯል፡፡ ሣሙኤል በምሰራቅ ጎጃም አካባቢ እታች አርሦ አደሩ መንደር በመዝለቅ በንቃት ሲያደራጅና ሲያስተባብር የነበረ በየአካባቢው ይደርስ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ አስተዳደራዊ ጭቆናና በደል እየተከታተለ ለሕዝብ መረጃ ሲያቀብል እንደነበረ! በተለይም በፓርቲው ልሣን በነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ላይ አምደኛ በመሆን ተከታታይ መረጃዎችን ሲያቀብል የነበረ ጠንካራ የማይበገር ታጋይ እንደነበር ተገንዝበናል፡፡
በትናትናው ዕለት ማለትም ሰኔ 8 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም የወያኔ ኢህአዴግ የፀጥታ ሃይሎች ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ ከሚኖርበት ቤት አጠገብ ደ/ማርቆስ ከተማ ውስጥ እጅግ አሠቃቂ ድብደባ ተፈጽሞበት በግፍ ለተገደለው የሰማያዊ ፓርቲ አመራር አባል ሣሙኤል አወቀ አለም ሃዘናችን ፅኑ፣ መራርና ፈጽሞ ለአፍታም ያህል የማይረሳ የዘመናችን የነፃነት ትግል አርዓያ ዋና ተምሣሌት፣ እንዲሁም ለኢትዮጵያችን እንደቀደሙት ጀግኖች እንደነ አቡነ ጴጥሮስ የታሪክ ባለአደራ የወቅቱ የትግል ጥሪ ፈር ቀዳጅ ጀግናችን ነው፡፡ ለሣሙኤል አወቀ ቤተሰቦች እግዚአብሔር እንዲያፅናናቸው እየተመኘን ዛሬ ሣሙኤል በአካል ከትግል አጋሮቹ ጋር ባይኖርም የሥራው ተምሣሌት ግን ለነፃነት ትግሉ ጉዞ ህያው ሥንቅ ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ሣሙኤልን በጥቅም ሣይደለል በኃይል በማስፈራራት ወይም በአካሉ ላይ ድብደባ በመፈጸም ትግሉን ለማስቆም ያልቻሉት የወያኔ ኢህአዴግ ቅልብ ወንጀለኞች በአካሉ ላይ ያደረሱት ጉዳት አልበቃ ብሏቸው በትናትናው ዕለት በስለት ፊቱንና አካሉን በመቆራረጥ ማንነቱን መለየት እስከማይቻል ድረስ በጭካኔ ገድለው ጥለውታል፡፡ ይህ ዓይነቱ የመንግስታዊ አሸባሪነት የመጀመሪያ ሣይሆን በተደጋጋሚ የታዬና አገዛዙ ጠንካራ ተቃዋሚ አመራሮችን በተመሣሣይ ጥቃት ሲያደርስ እንደቆየ ሕዝቡ ያውቃል፡፡ በኢትዮጵያ ተንሠራፍቶ ያለው ኢሰብአዊ አምባገነን ዘረኛ መንግስት በሕዝቡ ላይ በተለይም በተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና በነፃው ኘሬስ አባላት ላይ ከፍተኛ በደሎች ማለትም እስራት፣ ድብደባ፣ግድያና ሁለገብ የሆነ የስነ ልቦና፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሃይማኖታዊ ወንጀል እየፈጸመ ይገኛል፡፡ የሣሙኤል አወቀ የግፍ ግድያ ከላይ እነደተጠቀሰው አገዛዙ ሕዝቡን የሚያጠቃበት መለያ ባህረው አንድ አካል መሆኑን አስረጅ ሊሆን የሚችልና አገዛዙ ምን ያህል በጥላቻ እንደተጠመደና እጅግ አሣሣቢ ደረጀ ላይ መድረሱን ያሣያል፡፡ የወንድማችን የሣሙኤል የግፍ አገዳደል አልበቃ ብሏቸው የአገዛዙ ቅልብ ነፍሰ ገዳዬች በሣሙኤል ቀብር ላይ የተገኙትን ሌሎች አመራር አባላት ከቀብሩ ስነስርዓት ሲመለሱ አግተው አስረዋቸዋል፡፡
ውድ የኢትየጵያ ሕዝብ ሆይ፦
ይህ አይነቱ እጅግ ዘግናኝ በደል ሃዘናችንንና ቁጭታችንን ያባብሰዋል እንጅ ለነፃነት የተጀመረውን መራር ትግል ለአፍታም አያስቆመውም፡፡ በአገርቤትም በውጭም የምንኖር የሠላማዊ ትግል ደጋፊዎችና አራማጆች እንዲሁም መላው አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን የአገዛዙን ሰይጣናዊ ስራ በአንድ ድምፅ ማውገዝና መቃወም ይገባናል፡፡ ዛሬ በሣሙኤል ሞት ልባችን እንደቆሰለ ነገ በሌሎች ሣሙኤሎች ተመሣሣይ ግፍ እንዳይፈጸም ሁላችንም በአንድ ላይ እንነሣ! አገዛዙን በጋራ ታግለን ማስወገድ ይኖርብናል፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
እግዚአብሔር የሣሙኤልን ነፍስ በገነት ያኑርልን!
The post የሳሙኤል አወቀ መገደል የነፃነት ትግሉን አያስቆመውም !! appeared first on Zehabesha Amharic.