ይህ ጽሁፍ በዘ-ሐበሻ ጋዜጣ የጁን ዕትም ላይ ታትሞ ወጥቷል::
የህክምና ባለሙያዎቹ ‹‹ሃሊቶሲስ›› ይሉታል፡፡ ቃሉ ‹‹ትንፋሽ›› የሚል ትርጉም ካለው ሃልተስ ከተባለው የላቲን ቃልና መጥፎ ሁኔታን ከሚያመለክተው ኦሲስ ከተባለው ባዕድ መድረሻ ነው፡፡ ብዙው የህብረተሰብ ክፍል መጥፎ የአፍ ጠረን በሚል ያውቀዋል፡፡ መጥፎ የአፍ ጠረን አለዎት? ሌሎች ሰዎች መጥፎ የአፍ ጠረን እንዳላቸው ለማወቅ አስቸጋሪ ባይሆንም የራስዎን ሁኔታ ማወቅ ግን ሊያዳግትዎ ይችላል፡፡ የአሜሪካ የጥርስ ህክምና ማህበር መጽሔት ከራሳችን መጥፎ የአፍ ጠረን ጋር እንደምንለማመድና ‹‹አፋቸው በጣም የሚሸት ሰዎች እንኳ ችግራቸውን ላያውቁት እንደሚችሉ›› ገልጿል፡፡ ስለዚህ አብዛኞቻችን መጥፎ የአፍ ጠረን ያለን መሆኑን የምናውቀው አንድ ሰው ስለሁኔታው ሲነግረን ነው፡፡ ምንኛ ያሳፍራል፡፡
መጥፎ የአፍ ጠረን የብዙ ሰዎች ችግር መሆኑ ብቻ መጽናኛ የአፍ ጠረን አስነዋሪና ተቀባይነት የሌለው ነገር ተደርጎ ይታሰባል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከባድ የስሜት መቃወስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ በእስራኤል የቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ፣ የአፍ ማይክሮባዮሎጂ ላቦራቶሪ ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ሜል ሮዘንበርግ እንዲህ በማለት ገልፀዋል፡፡ ‹‹መጥፎ የአፍ ጠረን ግምታዊም ሆነ እውነተኛ ከህብረተሰቡ ለመገለል፣ ከትዳር ጓደኛ ለመፋታትና ራስን ለመግደል ምክንያት ሊሆን ይችላል›› ታዲያ ዛሬ ዛሬ በአዲስ አበባ በርካታ ፋርማሲዎችና ሱፐር ማርኬቶች፣ ‹‹መጥፎ የአፍ ጠረን መድሃኒት እንሸጣለን›› የሚል ማስታወቂያ ማንበብ አዲስ አይደለም፡፡ መድሃኒቶቹ ካለሐኪም ትዕዛዝ የሚሸጡ ከመሆኑ ጋር አይነትና አጠቃቀማቸው ሁሉ፣ ለራሳቸው ለሻጮቹና ሸማቾቹ ጭምር ደናገር ሲፈጥሩ ይታያል፡፡ ባለሙያዎቹ ግን ድርጊቱ ተራ የገበያ ሥራ ሲሉ ያጣጥሉታል፡፡ አንድ የጥርስና አፍ ህክምና ስፔሻሊስት ስለዚሁ ጉዳይ የሚሉት አላቸው፡፡
ጥያቄ፡- የአፍ ውስጥ ህክምና ሲባል ምን ማለት ነው?
ዶ/ር፡- ጥሩ፤ ብዙው የህብረተሰብ ክፍል የአፍ ውስጥ ህክምና ሲባል የጥርስ ሐኪም ወይም ዴንቲስት በሚል ነው የሚረዳው፡፡ ነገር ግን ዴንቲስት ከአፍ ውስጥ ህክምና አንዱ እንጂ ሁሉንም አይወክልም፡፡ ስለዚህ አፍ እና በአጠቃላይ ከአንገት በላይ ያለው የሰውነታችን ክፍል በተመለከተው ‹‹ከአንገት በላይ ህክምና›› የሚባለው አጠራር ትክክል ሳይሆን አይቀርም፡፡ በእንግሊዝኛውም ENT በሚባል አህጽሮተ ቃል ይታወቃል፡፡ E- ear N- nose T- throut የሚባለው መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ በቀር ግን ኢፍታሞሎጂስት (ዓይን)ን እንዲሁም በህክምናው ዓለም ጠጣሩ የአዕምሮ /ኒውሮሎጂስት/ ሳይንስ፣ ራሳቸውን የቻሉ የአንገት በላይ ህክምና ክፍሎች መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም፡፡ የእኛ ስፔሻሊቲ ግን አፍ ውስጥ እና የፊት አካባቢ አጥንቶች ናቸው፡፡
ጥያቄ፡- የአፍ ውስጥ በሽታ መንስኤን ቢነግሩን?
ዶ/ር፡- የአፍ ውስጥ በሽታ /ፓረንዶንታል ዲዚስ/ የምንለው ጥርስ አቃፊ አካባቢ ያለው ህመም ነው፡፡ የሰው ልጅ ከተወለደ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ጀምሮ ከ300 ባክቴሪያዎች በላይ ሰውነታችን ውስጥ ገብተዋል፡፡ እነዚህ ባክቴሪያዎች በተለያዩ የሰውነት ክፍሎችን ከመሰራጨታቸው ጋር በአፍ ውስጥም ቦታ አላቸው፡፡ ስኳር ነክ የሆኑ ምግቦችን ስንመገብ ቶክሲክ የሆኑ ባክቴሪያዎች ወደ አሲድነት ይለውጡታል፡፡ ለጥርስ መቦርቦርም እነዚህ አሲዶች ዋና ድርሻ አላቸው፡፡ ስለዚህ ምግብ ተመግቦ ሳያፀዳ የተኛ ማንም ሰው በዚህ አሲድ ምክንያት ጥርሱ ሊቦረቦር ይችላል ማለት ነው፡፡
ሁለተኛውና ትልቁ ደግሞ ሌሊት ስንተኛ የምራቅ መጠናችን ስለሚያንስ ካልሲየምና ፎስፈረስ በየጥርስ ዙሪያችን ይከመራሉ፡፡ እነዚህም በተገቢው ሁኔታ ከቁርስ በኋላ ካልፀዱ የጥርስ በሽታን አምጪ ናቸው፡፡ ስለዚህ ማንም ሰው በ24 ሰዓት ውስጥ ሁለት ጊዜ ጥርሱን እንዲያፀዳ ይመከራል፡፡ በመሀሉ ምንም አይነት ምግብ ከተመገብን በኋላ አፋችንን በውሃ መጉመጥመጥ አለብን፡፡ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ጥርሱን ያላፀዳ ሰው በአራተኛው ቀን ማጽዳት ቢሞክር ቆሻሻው ስለሚለጠፍ ብሩሹም ሊያስወጣለት አይችልም፡፡ ስለዚህ ከግል እንክብካቤ ባሻገር በየስድስት ወሩ ደግሞ ሐኪም ዘንድ ቀርቦ ስኬሊንግ /ማጽዳት/ የአፍ ውስጥ ጤንነትን ማረጋገጥ ይችላል፡፡
ጥያቄ፡- የአፍ ውስጥ ህክምና ከጥርስ ህክምና ይለያል ማለት ነው?
ዶ/ር፡- አዎ! ይሄንንም በቅጡ መረዳት ይገባል፡፡ አንድ ካርዲዮሎጂስት ጋ የሚሄድ ታካሚ ልቤን ስላመመኝ መድሃኒት ጻፍልኝ፣ እኛ ጋ የሚመጠውም ጥርሴን ሙላልኝ ማለት የለበትም፡፡ ጥርስ መሙላት ማለት ህክምና ማለት አይደለምና፡፡ ለሁሉም በሽታዎች የየራሱ ሐኪም ስላለ ምን ያስፈልጋል አያስፈልግም ለሙያተኛው ቢተው ነው የሚሻለው፡፡
ጥያቄ፡- ለጥርስና ለአፍ ውስጥ በሽታዎች ምክንያት የሆኑትን ምግቦች ማወቅ እንችላለን?
ዶ/ር፡- አይ! ይሄ በአጠቃላይ ከህብረተሰባችን የአኗኗርና የአመጋገብ ዘዬ መለወጥ ጋር ተያይዞ መታየት ያለበት ነገር ነው፡፡ እንደሚታወቀው ሁሉ በአሁኑ ወቅት ብዙ የምግብ ግብአቶቻችን የገበያ ወይም የሱፐር ማርኬት ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ የምግብ ግብአቶች ደግሞ ቀጥታ ፕሮቲናቸው የወጣ በመሆኑ ለሰውነት ያላቸው ጠቀሜታም የዚያን ያህል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ቀደም ባለው ዘመን እናቶች በቤት ውስጥ ጋግረው ሲያበሉን የቆየው ኦርጋኒክ ዳቦና አሁን በዳቦ ቤቶች ወይም ሱፐር ማርኬቶች ተዘጋጅተው የምንመገባቸው ዳቦዎ እኩል ጠቀሜታ አላቸው አይባልም፡፡ ሌሎቹንም የምግብ አይነቶች እንዲሁ ማየት ይቻላል፡፡ በጥቅሉ ፕሮሰስድ የሆኑ ምግቦች በቀላሉ ጥርስ ላይ የመጣበቅና የመጠራቀም ባህሪይ እንዳላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ከላይ እንዳልኩት እነዚህን በወቅቱ ካላፀዳን ይለጠፉና ወደ ፓራንዶንታል ዲዚስ /ጥርስ ዙሪያ/ በሽታ ይሸጋገራል ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህን ስል በሽታውን ያመጣው ምግቡ ሳይሆን ምንም ተመገብን ምንም ጽዳት ካደረግን ምንም በሽታ አይኖርም ነው፡፡
ጥያቄ፡- በባህል ሁኔታ ጥርሳችን የምንፍቅባቸው እንጨቶችስ ምን ያህል ጠቀሜታ አላቸው?
ዶ/ር፡- እስካሁን የተናገርኩት ከምግብ በኋላ ጥርስን ማጽዳት ተገቢ መሆኑን ነው፡፡ በዚህ ረገድ ጥርሱን ምንም ከማያፀዳ ባህላዊ ጥርስ መፋቂያዎች የተሻሉ መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ እርግጥ የጥርስ መፋቂያ እንጨቶች ቆሻሻል በመቀነስ አስተዋፅኦ ያላቸው ቢሆንም፣ ጫን ተብለው በተያዙ ቁጥር ድድን በመክፈት ሌላ ችግር ማስከተላቸው አይቀርም፡፡
ጥያቄ፡- የጥርስ ብሩሽ ሳሙና አፍ ያሸታል የሚባለውስ?
ዶ/ር፡- ስህተት ነው፡፡ ብሩሽና ሳሙናውን ያዘጋጁት እኮ በሳይንስ የኖቤል ተሸላሚ የሆኑ ሳይንቲስቶች ናቸው፡፡ በብሩሹ ደረጃ ጠንካራ፣ ለስላሳና መካከለኛ የሆኑ አሉ፤ ይህም እንደ አመራረጡ ነው፡፡ ሳሙናውም በይዘት ያካተተው ፍሎራይድ የመሰለ ለጥርስ ተፈላጊ የሆነ ኤለመንትና ፀረ ባክቴሪያዎች አሉት፡፡
ጥያቄ፡- በአሁኑ ወቅት በብዙ የከተማችን ፋርማሲዎችና ሱፐር ማርኬቶች ‹‹የአፍ ጠረን መድሃኒት እንሸጣለን›› የሚል ማስታወቂያ ጽፈው እያየን ነው፡፡ እስቲ ስለ አፍ ጠረን መድሃኒት ትንሽ ቢያብራሩልን?
ዶ/ር፡- ‹‹የአፍ ጠረን መድሃኒት አስመጥተናል›› ማለት በሌላ አነጋገር የሞተ አይጥ ሽታ የሚያጠፋ መድሃኒት እንሸጣለን ማለት ነውኮ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች የአፍ ሽታ ምክንያቱን አላውቁም፡፡ ባለማወቃቸውም ጉዳዩን ለገበያ ተጠቅመውበታል ማለት ነው፡፡ ባይሆን እንኳ ሐኪሙ የአፍ መጉመጥመጫና ሌሎች የሚያዛቸው አሉ፡፡ አሁን እያየን እንዳለነው አንዳንድ የህብረተሰብ ክፍል ሐኪም ቀርቦ ከመታየት ይልቅ በገበያ ማስታወቂያዎች ተማልሎ በራሱ ላይ ተጨማሪ በሽታ በመሸመት ላይ ይመስላል፡፡ አንዳንድ ፋርማሲስቶችም ከሐኪም ትዕዛዝ ውጭ መሸጥ የሌለባቸውን መድሃኒቶች እንደሚሸጡ ይታወቃል፡፡ አንድ ጊዜ የታዘዘ መድሃኒትን ደጋግመው የሚገዙና የሚጠቀሙ ሰዎች ቁጥርም ቀላል የሚባሉ አይደሉም፡፡ እንደዚሁ ሁሉ የሀገር ውስጥና የውጭ መድሃኒቶች በሚል ተጨማሪ ዋጋ የሚጠይቁ እንዳሉ የማናውቅ አይደለንም፡፡ ለእኔ ግን ይህ ሁሉ ከባድ ስህተት ነው ባይ ነኝ፡፡
እንግዲህ በገበያ ላይ የሚገኙ የአፍ መጎመጥመጫዎች ሊጠቅሙ ቢችሉም መጥፎ የአፍ ጠረንን በመከላከል ረገድ ሙሉ በሙሉ ልትተማመንባቸው እንደማትችል በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንዲያውም ብዙውን ጊዜ አልኮል ባለባቸው መጉመጥመጫዎች መጠቀም የአፍ ድርቀት ሊያስከትል ይችላል፡፡ አንዳንድ በጣም ውጤታማ ናቸው የሚባሉ የአፍ መጉመጥመጫዎች በጥርስ ላይ የሚላከኩ ቆሻሻዎችን መቀነስ የሚችሉት 28 በመቶ ብቻ ነው፡፡
ስለዚህ የምትመርጠውን የአፍ መጉመጥመጪያ ከተጠቀምክ በኋላም ቢሆን በአፍህ ውስጥ ከነበሩት ባክቴሪያዎች ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑቱ ላይጠፉ ይችላሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ሙከራዎች መሰረት በአፍ መጉመጥመጪያ ተጠቅሞ ጥርስንም ካፀዱ ከ10 ደቂቃ እስከ አንድ ሰዓት ባሉት ጊዜያት ውስጥ መጥፎ የአፍ ጠረን እንደሚያገረሽ ነው፡፡
በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መጥፎ የአፍ ጠረንን በመከላከል ረገድ ግዴለሽ መሆን አያስፈልግም፡፡ ከዚህ ይልቅ አፍህንና ጥርስህን ዘወትር እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው ውድ መሳሪያዎች አድርገህ መያዝ ይኖርብሃል፡፡ ስለዚህ የሚገባቸውን እንክብካና ጥንቃቄ አድርግላቸው፡፡ እንደህ ካደረግህ መጥፎ የአፍ ጠረንንና በዚሁ ሳቢያ የሚመጣውን ጭንቀትና ሐፍረት ትቀንሳለህ፡፡ ከዚህም በላይ አፍህ ንፁህና ጤነኛ ይሆናል፡፡
ጥያቄ፡- አመሰግናለሁ፡፡
ዶ/ር፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
The post Health: ለአፍ ጠረን መንስኤ የሆኑ 16 ክስተቶችና ህመሞች -የዶክተሩ ትንታኔ appeared first on Zehabesha Amharic.