Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ሰማዕት መንግሥቱ ጋሼ – ከወለጋ እስከ ሊቢያ

$
0
0
 አይ እናት እስቲ ተመልከቷት ። እናት ምንጊዜም እናት ናት ። ፍቅሯ እስከመቃብር የሚዘልቀውን የእናት ብቻነው ።


አይ እናት እስቲ ተመልከቷት ። እናት ምንጊዜም እናት ናት ። ፍቅሯ እስከመቃብር የሚዘልቀውን የእናት ብቻነው ።

※ በእኔ በኩል በሊቢያ ሰማዕታት ጉዳይ ላይ የምጽፈው ማስታወሻዬ ላይ ሌላ ሰማዕት እስካልተገኘ ድረስ ይህ ታሪክ የመጨረሻዬ ነው ብዬ አስባለሁ ※

” ዘ ሐበሻ እና ድሬ ትዩብ የተባሉ ድረገጾችን ሳላመሰግን አላልፍም ። ምክንያቱም እግር በእግር እየተከታተሉ በፌስቡክ ፔጄ ላይ የምጽፈውን የሰማዕታቱን ታሪክ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አንባቢዎቻቸው መረጃ በማቅረብ የሰማዕታቱ ቤተሰቦች እንዲረዱ ስላደረጉ ከልብ አመሰግናለሁ” ።

መንግሥቱ ጋሼ ሩቅ አልሞ ቅርብ ያደረው ሰማዕት ።

መንግሥቱ ጋሼ ሩቅ አልሞ ቅርብ ያደረው ሰማዕት ።

” በተለይ በየክፍለ ሀገሩ ለማደርገው ጉዞዬ በስዊዘርላንድ በሚኖረው ወንድሜ ጴጥሮስ አሸናፊ አማካኝነት የተዋወቁኳቸው ኢትዮ ዙሪክ የእግር ኳስ አባላትና ደጋፊዎች ፣ በመጨረሻው ጉዞዬ ወንድሜ ዘማሪ ቀሲስ ወንድወሰን በቀለና የሚኒሶታዎቹ አንድነት የሙዚቃ ባንድ አባላት ሙሉ የሆቴልና የትራንስፖርት ፣ እንዲሁም የስልክ ካርድ መሙያ ይሆንሀል ብላችሁ የላካችሁልኝን በአግባቡ ተጠቅሜበታለሁ እናም ምስጋናዬ ካለሁበት ይድረሳችሁ ” ። ይህ ጉዳይ ያለ እናንተ ተሳትፎ የመሳካቱ ነገር አጠራጣሪነቱ ከፍ ያለም ነበር ። ምክንያቱም አሁን እኔ አሁን ባለሁበት ሆኔታ አቅም ኖሮኝ ሁሉንም እንዲህ በተሟላ መልኩ ማቅረብ እችላለሁ ብዬ ማሰቡ ስለሚከብደኝ ማለት ነው ።

ከዚህ በኋላ የሁሉንም የሰማዕታት ቤተሰቦች የመገኛ አድራሻና የባንክ ሒሳብ ጭምር ፖስት ስላደረግሁ ገንዘብንና ሌሎች ጉዳዮችን ከእኔ ጋር ጭምር በትነካኩ ይመረጣል ። አሁን የሰማዕት መንግሥቱ ጋሼን ታሪክ በእርጋታ እንዲያነቡ ልጋብዝዎት ። መልካም ንባብ ።

※※※★★★※※※★★★※※※

ሐሙስ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ራሴን አቶ ሙክታር ከድር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ቢሮ ውስጥ አገኘሁት ። በፕሬዘዳንቱ ቢሮ የመገኘቴ ምክንያቱ ደግሞ ወደ ወለጋ ለመሄድ መዘጋጀቴን የሰሙ አንድ አባት በትግራይ ክልል ወደ ሰማዕታቱ ቤት ስሄድ የአክሱምና የኢንቲጮ ከንቲባዎች እና አስተዳዳሪዎች ያደረጉልኝን ትብብር ከፌስቡክ ገጼ ላይ አንብበው ስለነበር አሁን ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ትብብር እንዲያደርግልኝ ለማድረግ በማሰብ ነበር እኔን መውሰዳቸው ።

ፕሬዚዳንቱ በስብሰባ ምክኒያት አልነበሩም ። ነገር ግን ስለ አላማው እኝህ አባት ለፕሬዚዳንቱ ጸሐፊ ሲያስረዱዋቸው ምክትል ፕሬዘዳንቱ በቢሮአቸው በመኖራቸው ወደ እሳቸው እንድንሄድ አደረጉን ። በዚያም ለምክትል ፕሬዘዳንቱ አቶ አብዱልአዚዝ የመጣንበትን ጉዳይ እኚሁ አባት አስረዱዋቸው ። ምክትል ፕሬዘዳንቱም እጅግ በሐሳቡ መደሰታቸውን ገልጸው ነገር ግን መኪኖች በሙሉ ለስብሰባ ናዝሬት በመሄዳቸው እንደምንም ብለን እስከ አርብ አምስት ሰዓት እንድንቆይ ጠየቁን ። እኔ በሁኔታው ብገረምም የማልደብቃችሁ ነገር በማግሥቱ የምፈጽመው የግል ጉዳይ ስለነበረኝ መቆየቱን አልጠላሁትም ።

ነገር ግን ምክትል ፕሬዘዳንቱ አስከምሽት ድረስ ከሥራ ሰዓት ውጪ ጭምር መኪና ቢፈልጉም ሊያገኙኝ አልቻሉም ። ይህንንም ጥረታቸውን በየሰዓቱ እየደወሉ ያሳውቁን ነበር ። እኔም ቅዳሜን መዋል ሰኞ ያለኝን የኤምባሲ ቀጠሮ ያዛባብኛል ብዬ ስላሰብኩ ማንንም ሳልጠብቅ ቅዳሜ በሌሊት ጉዞዬን ወደ ነቀምት አደረግሁ ። በመሃል ግን ምክትል ፕሬዘዳንቱ ነዳጅ የተሞላ V-8 መኪና ከነሹፌሩ አዘጋጅተው ለእኚያ አባት ይምጡና ጉዞአችሁን ጀምሩ ቢሏቸው እኔ ግን አምቦ ደርሼ የነቀምቴ መኪና ተሳፍሬ ነበር ። ከቡር አቶ አብዱልአዚዝ እግዚአብሔር ያክብርልኝ ። የእኔ ጊዜዬን ለመሻማት መቸኮል እንጂ እንዳደረጉልኝ ነው የምቆጥረው ።

ወሮ አለሚቱና የልጅ ልጆቻቸው ።

ወሮ አለሚቱና የልጅ ልጆቻቸው ።


ለማንኛውም በሰማዕታተ ሊቢያ ላይ ለጀመርኩት ጽሑፍ ይህ የወጣት መንግሥቱ ጋሼ ታሪክ የመጨረሻዬ ነው ብዬ እገምታለሁ ። ትናንት ከአዲስ አበባ ተነስቼ ነቀምት ገብቼ አዳሬን በነቀምት አደረግሁ ። በነቀምት የፌስቡክ ጓደኛዬና በወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህርት የሆነችው መምህርት ስርጉት እና በመንግሥቱ ጋሼ ሕይወት ዙሪያ ለሁለት ጊዜ ያህል ፕሮግራም የሠራው አሁን ደግሞ ወደ ሥፍራው የሚወስደኝ በነቀምት ፋና ኤፍኤም ራዲዮ ጋዜጠኛ የሆነው ጋዜጠኛ ኬነሳ አመንቴ አስቀድመን ተደዋውለን ስለነበር በግንባር ተገናችተን ሰለ ጉዞአችን ተወያይተን ወደ የማደሪያችን አመራን ።

በማግስቱ ትናንት ሰኔ 7/10/2007 ዓም እሁድ ከንጋቱ ሁለት ሰዓት ያረፍኩበት ሆቴል ድረስ የመጣው ጋዜጠኛ ኬነሳ ወደ አውቶብስ ተራ ይዞኝ ይሄዳል ብዬ ስጠብቅ ለካስ አስቀድሞ ተነጋግሮ ኖሮ በቀጥታ ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ ተፈሪ ጢያሮ ቢሮ ይዞኝ በመሄድ ለአስተዳዳሪው የመጣሁበትን ጉዳይ በማስረዳት የምንሄድበት ሥፍራም ያለ መኪና በእግር ሩቅ መሆኑን በመንገር አስተዳደሩ መልካም ፈቃዱ ሆኖ መኪና እንዲፈቅድልን በትህና ጠየቀ ።

በዕለተ ሰንበት ስብሰባ ሊገቡ በዝግጅት ላይ የነበሩት ባለሥልጣናት በሙሉ በሁኔታው በመደሰት መኪና ከነሹፌሩ ፣ እንዲሁም የዋዩ ቱቃ የወረዳዋን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ለቺሳ በቀለ ስብሰባውን አቋርጠው ከእኛ ጋር በመሄድ በመንገዳችን ሁሉ እንዲረዱን በመንገር ጉዞአችንን እኔ ፣ ኬነሳ ፣ ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ለቺሳ በቀለ መምህርት ስርጉት እና ጓደኛዋ መምህርት መአዛ ሆነን ከነቀምት ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ጉዞ ጀመርን ። አርብ ገበያ የምትባል ከተማ እንደደረስን በቀኝ በኩል ታጥፈን ወደ ደቡብ አቅጣጫ የጥርጊያ የገጠር መንገድ በመጓዝ “ጋረ ሁዳ ” የገጠር መንደር ከተባለ ቦታ ስንደርስ መኪናዋን አቁሙን እኛ መኪና የማይገባውን የእግር መንገድ ተያያዝነው ።

አካባቢው ለምለም ነው ። ግራናቀኙ ሰሞኑን በዘነበው ዝናብ አማካኝነት ምድር አረንጓዴ ምንጣፍ የተነጠፈባት መስላ ትታያለች ። የበቆሎ ቡቃያ ከመሬት ብቅ ብቅ ብሎ መታየት ጀምሯል ። በሚያምረው መስክና በገጠር መንደሮች እያቋረጥን ፣ መንገድ ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ” አሸም ፣ አሸም አከም ቡልተን ” እያልን ሰላምታ እየተለዋወጥን ከሰማዕቱ መንግሥቱ ጋሼ ቤተሰቦች ዘንድ ደረስን ።

የመምጣታችን ዜና አስቀድሞ ደርሶዋቸው ስለነበር ቤተዘመድና ጎረቤቶች ሁሉ ተሰብስበው ነበር የጠበቁን ። ወንበር ተደርድሮ ፣ አጎዛ ተነጥፎ ፣

ሁላችንም ቦታ ቦታችንን ያዝን ። የመንግሥቱ ጋሼ ወላጅ እናት አጠገቤ ተቀመጡ ። እንደ አስተርጓሚ ሆኖ ጊዜያዊ አገልግሎት ለመስጠትም ጋዜጠኛ ኬነሳ ተሰይሟል ። እኔም ቢሆን የዋዛ አይደለሁም ስናገረው ስብርብር ላድርገው እንጂ የሐረርጌ ልጅም በመሆኔ ኦሮምኛ ያደግሁበት ቋንቋዬ በመሆኑ ብዙም አልቸገርም ። እናም ቢያንስ ቱርጁማኑ ቢሳሳት እንኳን ለማረም እችላለሁ ማለት ነው ። አሁን ወደመጣንበት ጉዳይ ልንገባ ነው ። ወላጅ እናት ወሮ አለሚቱ ገለታ ስለሁሉም ነገር እንዲህ ይነግሩናል አድምጡዋቸው ።

ወሮ አለሚቱ ገለታና በሞት የተለዪዋቸው ባለቤታቸው አቶ ጋሼ ጉዲና በሕይወት በነበሩ ጊዜ 9 ወንዶችና 3 ሴቶች ልጆችን አፍርተዋል ። መንግሥቱ ጋሼ ደግሞ 6ተኛ ልጃቸው ነው ። የአባት በጊዜ ማረፍ 12 ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት በወሮ አለሚቱ ትከሻ ላይ ወደቀ ። ልጆች የጀመሩትን ትምህርት አቋረጡ ፣ ብዙዎቹ በላይ በላዩ በተከታታይ የተወለዱ በመሆናቸው የእድሜ ልዩነትም የላቸውም ።

በኦሮምኛ ረቢ ኢሲኒ ሀኬኑ ተብላችኋል ። እግዚአብሔር ይስጣችሁ ነው የሚሉት እማማ አለሚቱ ።

በኦሮምኛ ረቢ ኢሲኒ ሀኬኑ ተብላችኋል ። እግዚአብሔር ይስጣችሁ ነው የሚሉት እማማ አለሚቱ ።

ማብላት ፣ ማጠጣቱ ፣ ማልበስ ፣ ማስተማሩ ለወሮ አለሚቱ ጭንቅ ሆነ ። ነገር ግን ባይፈልጉትም ሳይወዱ በግዳቸው መንግሥቱ ጋሼን ጨምሮ 3 ልጆቻቸውን በእረኝነት ለተለያዩ ሰዎች በህፃንነታቸው ለእረኝነት አሳልፈው ሰጡ ። በዚህ የእረኝነት ሕይወት ግን መንግሥቱ አንድ አመት ብቻ ነው መቆየት የቻለው ። በአንድ በኩል የእናቱ ፍቅር በሌላ በኩል የሰው ቤት የሰው ነው ቢርብ መሶብ ተከፍቶ የማይበላበት ፣ ቢከፋ የልብን አውጥቶ ለመናገር አቅም የማይገኝበት ፤ ብቻ ብዙ ምክንያቶችን ይዞ ዓመት ሙሉ ፀሐይና ዝናብ ፣ ረሃብና ጥም ተፈራርቀውበት የሰራበትን ደምወዙን አንድ ፍየል ገዝቶበት ወደ እናቱ ተመለሰ ። አሁን መንግሥቱ እድሜው 11 ደርሷል ።

መንግሥቱ ትምህርቱን ከ3 ተኛ ክፍል እንዳቋረጠ አልተመለሰበትም ። ታላላቆቹ ትዳር መመስረት በመጀመራቸው የሰው ኃይል ጫና ለእናት መቀነስ ቢጀምርም እድሜያቸው እየገፋ በመምጣቱ ማረፍ ሲገባቸው የቤቱንም የውጪውም ሥራ የሚጠብቀው እሳቸውን ሆነ ። መሬቱ እኮ አለ ። ነገር ግን ማን ይረሰው ። ችግር ሆነ ። በዚህ ላይ ከመሬቷ ላይ ትዳር ለያዙት ድርሻቸውን እየሰጡ ሳሳ እያለ መጥቶባቸዋል ።

ለዚህ ደግሞ መንግሥቱ እናቱን ለማገዝ መሬት ያላቸው ነገር ግን በስንፍናም ቢሉ በጥጋብ ለማያርሱ ባለመሬቶች የእኩል በማረስ ምርት ሲደርስ በመካፈል በቀለብ በኩል እናቱን ማገዝ ጀመረ ። ይህም ቢሆን ባለመሬቶቹ በሚቀጥለው የምርት ዘመን እራሳቸው ያርሷታል እንጂ ለመንግሥቱ አያስደግሙትም ። እንደሚፈልገው እናቱን መርዳት ያለመቻሉ ያንገበግበው ጀመር ።

አዴ አለሚቱ ባለቤታቸው ከሞቱ በኋላ ሌላ ባል ለማግባት አልፈለጉም ። ዶሮ ከክንፎቿ በታች ጫጩቶቿን አቅፋ እንደምትኖር እሳቸውም መላ ዘመናቸውን እንደ አናትም እንደ አባትም ሁነው ልጆቻቸውን ለማሳደግ ሲሉ ዋጋ ከፍለዋል ።

እማማ አለሚቱ በተነጋገርነው መሠረት ጥቁር ልብሳቸውን አውልቀው ነቀምት በመምጣት የባንክ ሒሳብ ቡካቸውን ከባንኩ ሥራ አስኪያጅ ተቀብለዋል ።

እማማ አለሚቱ በተነጋገርነው መሠረት ጥቁር ልብሳቸውን አውልቀው ነቀምት በመምጣት የባንክ ሒሳብ ቡካቸውን ከባንኩ ሥራ አስኪያጅ ተቀብለዋል ።

መንግሥቱ አሁን እድሜው 14 ደርሷል ። ከአንድ ፍየል ተነስቶ 10 ከብቶችን ለማፍራትም በቅቷል ። ሆኖም ግን በመንደሯ ውስጥ በአንደኛው ግቢ ውስጥ የጎጆ ቤት ወደ ቆርቆሮ ቤት መለወጡ በመንደሯ ውስጥ መነጋገሪያ ሆኖአል ። ቆርቆሮ ቤቷ የተሰራችው በመጀመሪያ ሱዳን ከዚያ ሊቢያ በመቀጠል አውሮፓ ገባ የተባለ ልጅ በላከው ብር ነው መባሉ ደግሞ መንግሥቱና ጓደኞቹ ቅንአት ቢጤ ፈጥሮባቸዋል ። ነገር ግን እንዴት እንደሚኬድ ደግሞ ምንም የሚያውቁት ነገር የለም ።

15 ኛ ዓመቱን ሲያከብር ግን እስካሁን አርብ ገበያ በምትባለው ከተማ ውስጥ የሚኖር አብዱ የተባለ ህገወጥ ደላላ እጅ ይወድቃል ። መንገዱም አልጋ በአልጋ እንደሆነ ይሰበካል ። ከአስሩ ከብቶችም ሰባቱን በመሸጥ ሦስቱን ደግሞ ለእናቱ በመስጠት 4 ሆነው እያንዳንዳቸው ለደላላው አስር አስር ሺ ብር በመስጠት ጉዞ ወደ ሱዳን ካርቱም ያደርጋሉ ።

መንግሥቱ በሱዳን ላለፉት አራት አመታት ተቀምጦ ለመሥራት ጥረት አድርጓል ። እንዳሰበው ለእናቱ የተመኘውን የቆርቆሮ ቤት ለመሥራት የሚያስችል ጥሪት መቋጠር ግን አልቻለም ። በመሃል ግን ከሱዳን ወደ ሊቢያ ከመሄዱ አስቀድሞ ለእናቱ 8 ሺህ ብር በመላክ የተመኘውን የቆርቆሮ ቤት ማሰራት ጀምሮ ነበር ። እንደውም ጠባብና ትንሽ እንዳይሆን ብሎ በሰፊው ነው ያስጀመራቸው ። ሳይጨርሰው ፍፃሜውንና የእናቱንም ደስታ ሳያይ ቀረ እንጂ ።

ከጓደኞቹ ሁለቱ ከሱዳን ወደ ሊቢያ ከዚያም ባህሩን ተሻግረው እድል ይቀናቸውና ጀርመን ይገባሉ ። ከጀርመንም ሱዳን ለቀሩት ለመንግሥቱና ጓደኛው እንዴት አድርገው ሊቢያ ከዚያም ባህር ተሻግረው አውሮፓ እንደሚመጡ ይነግሯቸዋል ። እነ መንግሥቱም ሐገር አማን ብለው በተነገራቸው መሰረት ከሱዳን ወደ ሊቢያ መንገድ ይጀምራሉ ። በመሃል ጉዞ እንደጀመሩ ከሌሎች ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ጋር ተቀላቅለው ጉዞ ወደፊት ወደ ትሪፖሊ ።

የሊቢያ ክልል እንደገቡ አሸባሪው ቡድን ተኩስ ከፍቶ ቁሙ ሲል መንግሥቱና ጓደኛው በተለያየ አቅጣጫ ለማምለጥ ሮጡ ። ጓደኛው የሄደበት መንገድ ሲያስመልጠው መንግሥቱ የሮጠበት መንገድ ግን ከጨካኞቹ እጅ ጣለው ። መንግሥቱ ከታረዱት ከእነ ዳንኤል ሐዱሽና ተስፎም ታረቀኝ ጋር ሳይሆን ጭንቅላታቸውን በጥይት ከፈረሰው ከሁለት ህፃናት አባቱ ብርሃኑና ከቂርቆሱ ባልቻ ጋር ሆነ ። ህልሙን እውን ሳያደርግ እናቱን ለማስደሰት እንደተመኘ በሰው ሐገር ቀባሪ እንኳን ሳያገኝ በምደረበዳ አሸዋ ውስጥ ከነህልሙ ተቀበረ ።

እኒህ የወሮ አለሚቱ ቀሪ ልጆች ናቸው ። ሦስቱ በቦታው ባለመኖራቸው ነው ።

እኒህ የወሮ አለሚቱ ቀሪ ልጆች ናቸው ። ሦስቱ በቦታው ባለመኖራቸው ነው ።

የመንግሥቱን መሞት ሸሽቶ ያመለጠው ጓደኛውና በኢንተርኔት አሰቃቂውን ድርጊት ያዩ የሚያውቁት ሰዎች መጥተው ለእናት አረዷቸው ። ያለ አባት 12 ልጆች ያሳደጉት የ60 ዓመቷ እናት ዛሬ ሀዘኑ ከልባቸው ባይወጣም ኢትዮጵያውያን በሙሉ በልጃቸው ሞት ማልቀሳቸው አፅናንቷቸዋል ።

አሁን እማማ አለሚቱ የሚያሳስባቸው ሌላ ነገር ነው ። እድሜዬ አልቋል ። አሁን ምንም ቀረኝ ብዬ አልጓጓም ። የሚያሳስበኝ ከአስራአንዱ ልጆቼ የሥስቱ ብቻ ነው ። አንዱ ወደ 11ኛ ክፍል አልፎ አንዴ ከእርሻው እናቱን በማገዝ አንዴ ከትምህርቱ ሲል ሲኦሲ ተፈትኖ ማለፍ አቅቶት ከቤት ውሏል ። አንደኛው ወንድ ልጃቸውና አንዷ ሴት ግን በትምህርት ላይ ናቸው ። የሚረዳቸው እና የሚያበረታታቸው ካገኙ ተስፋ የሚጣልባቸው ናቸው ።

እኔም የመጣሁበትን ምክንያት አስረድቼ ። ጆሲ ሄዶ ከረዳቸው በቀር ማንም እንዳልጎበኛቸው በነበረኝ መረጃ መሠረት የሚኒሶታ የአንድነት የሙዚቃ ቡድን አባላት በአቶ ሰሎሞን በኩል ይሰጥልን ያሉትን 50ሺህ ብር እና የኢትዮ ዙሪክ የእግር ኳስ ቡድን አባለት እንደተለመደው የላኩትን 8,520 ብር ጨምሮ ከሀገረ አሜሪካን እነ ሕይወት ፣ አቶ አማረ ፣ አቶ ሚናስ ፣ ባልና ሚስቶቹ ሔለን ነጋሽና ፈረደ ዓለሙ ዘማሪ ቀሲስ ወንደሰን በቀለ ፣ ቤተልሔም ከቱርክ ውቢት ከግሪክ እና ስሜ አይጠቀስ ያለች እህት ከሳዑዲ የላኩትን በአጠቃለይ 92500 ብር ያስረከብኩ ሲሆን ወንድሜ ዘማሪ ቀሲስ ወንድወሰን በቀለ ፣ ሚኒሶታዎች እንዲሁም ኢትዮ ዙሪክ የእግር ኳስ ቡድን አባላት ለመንገድና ይህን ጉዞ ስታደርግ ለምታወጣው ወጪ ይሁንህ ብለው ከላኩልኝ ሳንቲም ላይ በእኔ የማይታሰብ በሰጪዎቹ የሚደመርልኝ 2480 ብር በመጨመር በአጠቃላይ ለእማማ አለሚቱ 95000 ብር አስረክቤአለሁ ። የቀረውን ጥቂት ብር ለትርሓስ ፣ ለሮዚና ፣ ለደንኤል ሐዱሽ ፣ ለተስፎም እና ለዲያቆን እንዳልክ ቤተሰብ በየባንካቸው አስገባለሁ ።

እዚህ ላይ እንደተለመደው ቢሰሙኝም ባይሰሙኙም ወቀሳዬን የማቀርብባቸው አካላት አሉ ። እነሱም ።

የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት አመራሮች ✔ ሀዘኑ ብሔራዊ ነው ። ግን ደግሞ እንደ ክልል ምን አደረጋችሁ ? በተለይ ለገበሬ ልዩ ፍቅር እንዳላችሁ ትናገራላችሁ ሁሌም የምንሰማው ነው ። ታዲያ እኚህ ያለ ባል ብቻቸውን 12 ዜጋ ያሳደጉ አዛውንት ሴት ይህ ከባድ ሐዘን በደረሰባቸው ጊዜ ከምን ደረሳችሁ ? ሌላው ቢቀር እንኳን የሴቶች ጉዳይ ወዘተ ተብላችሁ የምትጠሩ ምነው ድምጻችሁ ጠፋሳ ! በእርግጥ የወረዳውና የዞኑ አስተዳደር ከሀዘኑ ቤት ተገኝተዋል ነገርግን ምን ያደርጋል መንግሥትን ያህል ትልቅ አካል ደሀ ቤት ያውም ከባድ ሐዘን የደረሰባቸው አዛውንት ቤት ገብቶ የቡና መግዣ እንኳን ሳይሰጥ መሄዱ ነውር ነው ። ባህላችንም አይደለም ። በዚህ በኩል የአዲስ አበባ መስተዳደር ለተጎጂዎቹ ቤተሰቦች ያደረገው ያስመሰግነዋል ።

የኦሮሚያ ቴሌቪዥን ✔ ጣቢያችሁ ምርጥ ምርጥ የተባሉ ድራማዎችን እና ፕሮግራሞችን እንደሚያቀርብ ብዙዎች ያዩዋችሁ ይናገራሉ ። በዚህ ሐዘን ላይ ግን አለመገኘታችሁ ያስወቅሳችኋል ። እርግጥ ኦሮሚያ ሰፊ ናት ። ነገር ግን ምንም ሰፊ ብትሆንም ነቀምቴ ሩቅ አይደለችም ። ፕሮግራም ብትሰሩ አዛውንቷ ይረዳሉ ፣ እግረመንገዳችሁንም የስደትን አስከፊነትና እስከአሁን በአርብ ገበያ የድለላ ሥራውን እየሰራ ያለውን አቶ አብዱንም ታነጋግሩት ነበር ። ምናልባትም ማን ያውቃል ይህ ደላላ ጌታውን የተማመነና ላቱን ከደጅ የሚያሳድር እንደሆነም ትነግሩን ነበረ ።

የኦሮሚያ አርቲስቶች ✔ አፈርኩባችሁ የሙያ አጋራችሁና ጓደኛችሁ ጆሲ ከአዲስ አበባ ፣ አራት አርቲስቶች ከሚኒሶታ ለእኚህ አዛውንት ሲደርሱ እናንተ በሐገር ውስጥ ያላችሁ ምን ነካችሁ ? አደራ ነገ ደግሞ ያ መከረኛ ጋዜጠኛ መጥቶ ሲጠይቃችሁ እኛ ቀሪ ሃብታችን ሕዝባችን ነው እያላችሁ በሳቅ ፍርድ አድርጋችሁ እንዳትገድሉን ብቻ ።

ባለሃብቶቻቸው ✔ ምን አለበት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር እንኳን ባትሰጡ ጥቂት መቶ ብሮችን ብትወረውሩላቸው ብዬ ልጠይቃችሁ አሰብኩና ተውኩት ። ምክንያቱም የሞቱት ለካስ ዘፋኞች አይደሉም ። አፉ በሉኝ አለ የአፋር ሰው ። እናም ይቅርበሉኝ ወይ አለማወቅ ። አንዳንዴ ሳስበው ግን ብር ወረቀት ነው ያልቃል ። የማያለቅው ፍቅርና ለሰማዕታቱ የተሰጠውን ክብር ሳስበው ከሚያልቀው ብር የሚበልጥ የማያልቅ የአምላክ ፀጋ ነው በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለሰማዕታቱ ቤተሰቦች የሰጡዋቸው ። እናም ይቅር በሉኝ ። ከተቻላችሁ ግን ሦስቱን ልጆች ሥራ ብታገኙላቸው መልካም ነው ። አይይይይ የእኔ ነገር ደግሜ አስቸገርኳችሁ አይደል ምን ላድርግ ብላችሁ ነው ቢጨንቀኝ ያየሁትም እረፍት ቢነሳኝ ነው ።

የፕሮቴስታንት ቸርች አመራሮች ✔ ሟች መንግሥቱ ጋሼን ጨምሮ ቢያንስ ፎቶው ላይ የምታዩዋቸውን የእምነታችሁ ተከታዮች አድርጋችኋቸዋል ። ታዲያ እንዲህ በሆኑ ጊዜ ቢያንስ ሌላው ቢቀር የሚለበስ እንኳን አታጡምና እስቲ ጎብኟቸው ።
ፍጻሜው ይመር እንጂ አብረውኝ የሄዱትን የወረዳዋን ምክትል አስተዳዳሪ ገንዘቡ ዝም ብሎ ከሚቀመጥና ከሚጠፋ በከተማዋ ላይ ትንሽ መሬት ብትሰጡዋቸው እና ልጆቻቸውም ሥራ የሚያገኙበት በዚያውም አዛውንቷም የሚጦሩበት ወፍጮ ቤት ብንከፍት ብዬ ጥያቄ አቅርቤላቸው ነበር ። እሳቸውም በቅርቡ እናደርገዋለን ካቢኔው እንዲወስንበት ጥያቄ አቀርባለሁ ። መልሱንም እነግርሃለሁ ብለውኛል ። እንጠብቃለን ኦቦ ለቺሳ ።

በመጨረሻም ዛሬም ነቀምት መዋሌ ነው ። የቸኮልኩበት የኤምባሲ ቀጠሮም ቀለጠ ፣ ውኃ በላው ማለት ነው ። ምክንያቱም እማማ አለሚቱ ከገጠር መጥተው የባንክ አካውንት መክፈት አለባቸው ። ጆሲ የሰጣቸው 40 ሺ ብር እንኳን እስከአሁን በቃጫ አስረው ከቤት ነው ያስቀመጡት ። ይሄ ደግሞ አደጋ አለው ። እሱም ባንክ መግባት አለበት ። እኔ ይዤው የሄድኩ በባንክ ያለ ነው እሳቸው የባንክ አካውንት ሲያወጡ ጠብቄ የግድ ማዘዋወር አለብኝ ።

እፎይ ሁሉንም ጨርስኩ ። የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የንግድ ባንክ ሰራተኞች ሥራ አስኪያጁን ጨምሮ መላው የባንኩ ሰራተኞች በሚገባ አስተናግደውናል ። ለሟች እናትም ክብር ሰጥተው አስተናግደውኛል ። በእጃቸው ያለውን ገንዘብና እኔ ያመጣሁትንም ገንዘብ በመጨረሻ ከባንክ ገብቶላቸዋል ።

ይኸው ሁሉንም በእግዚአብሔር ቸርነት በእመቤታችን አማላጅነት በቅዱሳን ተራዳኢነት በእናንተ በጓደኞቼ ጸሎት እንደዋዛ የጀመርኩት ነገር አልለቅህ ብሎኝ በመጨረሻ ወለጋ ላይ ፍጻሜውን አግኝቷል ።

ነጋቲ ጋ አዴ አለሚቱ !! ጀባዳ !!

ነጋቲ ጋ አዴ አለሚቱ !! ጀባዳ !!

በቀጣይ በዚህ ዙሪያ አጠቃላይ የእርዳታችሁን መጠንና ቀሪ ሥራዎችን እጠቁማችኋለሁ ።

የሚቀረኝ ነገር ቢኖር የሰማዕቱ ባልቻ እህት የነገረችኝና በአሜሪካ ከምትገኙ ሰዎች መካከል አንድ ሰው ሊፈጽመው የሚችለው ቀላል ነገር ማስቸገር ብቻ ነው ጉዳዩ ገንዘብ ነክ አይደለም ።

ሌላው የሰማዕቱ የኢያሱ ሚስት የሮዚና ጉዳይ ነው ። ሮዚና ወጣት ናት ። በዚህ ዕድሜዋ የወጣት ተጧሪ መሆን አለባት ብዬም አላምንም ። ይህን እድሜዋን በመስራት ማሳለፍ አለባት ። በዚህ መሰረት ጀርመን የሚገኙት የአቢሲኒያ የጉዞ ወኪል ባለቤት ወሮ መሠረት አዲስ አበባ የሚገኝ የአንድ ካምፓኒ ባለቤት እንዳነጋግር በነገሩኝ መሠረት የካምፓኒውን ባለቤት አነጋግሬ ፍጹም ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸውልኛል ።

ስለዚህ ከነቀምት መልስ ሮዚና ሥራ ይኖራታል ማለት ነው ። የሚቀረው ከሽንት ቤት ላይ ያለውን የመኖሪያ ቤቷን የክልሉን መስተዳደር ጠይቆ ቤት የምታገኝበትን መንገድ መፈለግ ነው ። ይሄም እንደ አዋሬዋ ብርቱኳን ይሳካል ብዬ አምናለሁ ። የትርሓስ ጉዳይም መቋጫ ይፈልጋል ። ለዛሬ አበቃሁ ።

ወሮ አለሚቱ ገለታ ጂራታን መርዳት የምትፈልጉ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ነቀምቴ ቅርንጫፍ
የባንክ ሒሳብ ቁጥር
1000129744147 ነው ። ካላችሁበት አገር ሆናችሁ ባለችሁበት ሐገር ባንክ በኩል ከማናችንም ጋር ንክኪ ሳትፈጥሩ በ Swift Coode : CBETETAA መላክም ትችላላችሁ ።

ወይም ታሪኩ ጋሼ ብላችሁ በስልክ ቁጥር +251921199718 በተለይ ኦሮምኛ የምትችሉ ሰዎች ደውላቭጉጥ አፅናኑዋቸው ።

በተረፈ ውድ ጓደኞቼ በዚህ ጉዳይ የምትጠይቁኝ እና እንድመልስላችሁ የምትፈልጉት ነገር ካለ ። ያው እንደተለመደው በእጅ ስልኬ +251911608054 ላይ ደውሉልኝ ። ሰላም ሁኑልኝ ። አክባሪ ወንድማችሁ ።

ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ሰኔ 8/10/2007 ዓም
ከነቀምት ወደ አዲስ አበባ በጉዞ ላይ ።

The post ሰማዕት መንግሥቱ ጋሼ – ከወለጋ እስከ ሊቢያ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>