Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

እሷ ያየችው ሰሙን እኔ የነገርኳት ወርቁን –ከተማ ዋቅጅራ

$
0
0

 

Ketemaሰም የሚገኘው ከማር ነው። ወርቅ የሚገኘው ከመሬት ነው። ማሩን ማር እንዲሆን ያደረገችው ከአበባ እና ከውሃ ቀምማ ንብ ናት። ወርቁን ወርቅ ያሰኘው ከአፈር ለይቶ  በእሳት አቅልጦ ሰው ነው። ታዲያ ሰምና ወርቅን ምን አገናኛቸው ቢሉ ፊደል። በምን ቢሉ በሰሌዳ።

አንዷ ወዳጄ በተደጋጋሚ ያየችውን ነገርና የገጠማትን ሁሉ ታወጋኝ ነበር። እኔም የምችለውን ያህል ሳይሰለቸኝ የሰማኋትን እንዳይሰለቻት አድርጌ እነግራት ነበረ። ታዲያ በእንደዚ ጨዋታ መሰላቻቸት በሌለበት መዝለቅ በተለይ በዘመነ ወያኔ መታደል ነው።

እናም ይቺ ወዳጄ እንዲ ብላ ያየችውን ጀመረችልኝ። ዛሬ ብታይ አለችኝ አፏን እየጠራረገች ዛሬ ብታይ በትልቅ ሙቀጫ ውስጥ ከቶኝ ሲሸከሽከኝ ነው ያደረው አለችኝ።

እኔም፡- ይኽውልሽ ምን መሰለሽ ለወገን የማያስብ መሪ ለህዝብ የማይጨነቅ ንጉስ ነግሶብን ኢትዮጵያ  የምትባል ትልቅ አገር መሃል ገብቶ በተለያየ አቅጣጫ እንደ ሙቀጫ ያለ እስርቤት አዘጋጅቶ ገሚሱን አንተ ኦነግ ነህ ሲለው ገሚሱን  አንተ ግንቦት 7 ነህ ሲለው ገሚሱን ደግሞ አንተ ኦብነግ ነህ እያለ ወዳዘጋጀው የእስር ሙቀጫ ይከታል። ጋዜጠኖችን እና የተለያየ ጽሁፎችን በመጻፍ የሚታወቁትን ጸሃፊዎችን ብቻ ምን አለፋሽ ለአገዛዙ  የማይመቹትን ከሆኑ የኛን ዓላማ ለማሰናከል ነው የሚንቀሳቀሱት በማለት  አሸባሪ የሚል  ታርጋ እየለጠፈ ስንቱ ያለ ሐጥያቱ ላገሩ በለፋ ለእውነተኛ ለውጥ ስለታገለ ሙቀጫ እስር ቤታቸው አስገብተው ስንቱን ንጹሃንን ሸከሸኩት መሰለሽ።

ሌላው ምን መሰለህ ብላ ቀጠለች….  ምጣድ ላይ ጥዶ ሲያምሰኝ ነው ያደረው አለችኝ

እኔም፡- አልኳት ፌድራል የሚባሉ ህዝብን ሊጠብቁ የተመረጡ ነገር ግን በተገላቢጦሽ ህዝብን ለሚጨቁኑ ባለስልጣን ተብዬዎች አገልጋይ የሆኑ ታሪክ የማይረሳው ስህተት እየሰሩ ያሉ አድርግ የተባሉትን ብቻ  የሚያደርጉ ከበላይ ትእዛዝ ከመጣላቸው ሴት ነሽ ህጻን ነሽ ትልቅ ነህ ትንሽ ነህ ሳይሉ በያዙት ዱላ ያገኙትን ሁሉ መቀጥቀጥ እንደ ስራ የቆጠሩት  ስንቱ ወገኔ በነዛ አረመኔ ተደበደበ  ወገኖቻችንን በየቦታው ስንቱን ያላመሱት አለ መሰለሽ አገር በየግዜው በነዚህ አረመኔዎች ስትታመስ አይደለ የምትውለው።

እንዲህ በማለት ቀጠለች የዛሬ ይገርማል ብላ ቀጠለች ትልቅ ብረት ምጣድ ላይ ጥዶ በትልቅ መቁያ ሲቆላኝ ሲቆላኝ ነው ያደረው አለችኝ

እኔም፡- አዪዪ አልኩኝ የኢትዮጵያ ህዝብ መቆላት ከጀመረ እኮ ቆየ የምንስ ወገን ያልተቆላ አለ ብለሽ ነው ፈጁን እንጂ ነው የሚባለው። መንግስትንም ተቃውመው ሰልፍ ይውጡ በጥይት መቁላት ነው። የፖለቲካ ለውጥም ፈልገው ሰልፍ ይውጡ መቁላት ነው። ገበሬን አታፈናቅሉ መሬታችንንም ያለአግባባ መዝረፍ ይቁም ብለው ሰልፍ ይውጡ መቁላት ነው። የሐይማኖት ቦታችን ይከበርልን አትንኩብን ብለው ሰልፍ ይውጡ መቁላት ነው። ISISንም ተቃውመው ሰልፍ ይውጡ መቁላት ነው። ህዝባችን ተቆልቶ  አልቋል እኮ ምን ቀረ ብለሽ ነው ጋንቤላ ብትዪ ኡጋዴን ብትዪ ቤንሻጉል ብትዪ ባሕር ዳር ብትዪ አንቦ  ብትዪ አዲስ አበባ ብትዪ በወያኔ የግፍ ጥይት ማን ያልተቆላ አለ ብለሽ ነው እና …ብዬ ልቀጥል ስል አቋርጣኝ

አልተግባባንም እኔ የምልህን ምንም አላዳመጥከኝም አለችኝ

እኔም፡- ኽረ በድንብ አድምጬሻለው አልኳት

እሷም፡- እሺ ምንድነው ያልኩህ

እኔም፡- ያልሽኝን ነዋ  እኔ ደግሞ የሆነውንና የሚሆነውን ነገርኩሽ

እሷም፡- ጮክ ብላ አልነገርከኝም! አልሰማህኝም! እኔ ያልኩህ እንደሱ እንድትለኝ አይደለም!!!

እኔም፡- እና ምንድነው? ያልሽኝ አልኳት አይን አይኗን እያየኋት

እሷም፡- ሲሸከሽከኝ አየው ነው ያልኩህ

እኔም፡- እሺ የሸክሽክሽ

እሷም፡- ሲያምሰኝ አየው ነው ያልኩህ

እኔም፡- እሺ ያምስሽ

እሷም፡- ሲቆላኝ አየው ነው ያልኩህ

እኔም፡- እሺ ይቁላሽ

እሷም፡- ታዲያ የዚህን ፍቺ ነው ንገረኝ ያልኩህ እንጂ ሌላ አይደለም አለችኝ ቆጣ ብላ

እኔም፡- አይ አንቺ አልኳት በመገረም አኳኃን እያየኋት አንቺ የፈለግሽው ሰሙን እኔ የነገርኩሽ ወርቁን አልተግባባንም የገባው ወርቁን ይከተል ያልገባው በሰሙ ይቀጥል ምን እላለው ይኸው ነው ቃሌ አልኳት።

እሷም፡- በል ደህና ሁን ብላኝ ትታኝ ሄደች

እኔም፡- ይኸውልሽ እህቴ የምልሽን አድምጠሽኛል ወዳጅህ ሲታማ ለኔ ብለህ ስማ ይላል ያገረ  ሰው እናም በኢትዮጵያ  ውስጥ የሚደርሰው ግፍና በደል ሁላችንን ተሰምቶን ሊያስቆጣን እና በቆራጥነት አስነስቶን በህዝባችን ላይ ግፍ ፈጻሚዎችን በማስወገድ ህዝባችን በነጻነት፣ በሰላም፣ በፍቅር የሚኖርባትን አገር እንዲኖረን የማድረጉ  የሁላችንም ድርሻ  ነውና ይታሰብበት። በይ ደህና ሁኚ በድል ያገናኘን ብያት ተሰናበትኳት።

ከተማ ዋቅጅራ

13.06.2015

Email- waqjirak@yahoo.com

 

The post እሷ ያየችው ሰሙን እኔ የነገርኳት ወርቁን – ከተማ ዋቅጅራ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>