- በጥያቄአቸው፣ በአስተዳደር ይኹን በልማት ሥራ ምንም ችግር የለም ብለዋል፤ በሌለ ልማት!
- ምእመናኑንም ‹‹ምንም ዓይነት ድርሻ የሌላቸውና ማንነታቸው የማይታወቅ›› ሲሉ ገልጸዋቸዋል
- የታሰሩት ምእመናን በፖሊስ ጣቢያ ‹‹ማዕተባችኹን በጥሱ መስቀላችኹን አውልቁ›› ተብለዋል
- የቀድሞው የደብሩ አለቃ ዘካርያስ ሓዲስና ኃይሌ ኣብርሃ ከውዝግቡ ለማትረፍ እያሰሉ ነው
የቤተ ክርስቲያን ይዞታ ከቤተ ክርስቲያን አቋም ጋር በሚስማማ እና ሀብቷን በሚያስጠብቅ አኳኋን እንዲለማ በመጠየቅ በቅንጅት የተንቀሳቀሱ የቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ደብር ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላትበሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥያቄ እየታሰሩ እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ለቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በክፍለ ከተማው ለወረዳ 12 ፖሊስ ጣቢያ በጻፉት ደብዳቤ፣ በምእመናኑ እና የሰንበት ት/ቤት አባላቱ ተበይዶ የታሸገው የደብሩ ቢሮዎች በፖሊስ ርምጃ እንዲከፈቱ ምእመናኑም በወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ አመልክተዋል፡፡
ጥያቄአቸውን ተከትሎ ባለፉት ኹለት ቀናት ከኻያ የማያንሱ ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት መታሰራቸው ታውቋል፡፡ ትላንት እና ከትላንት በስቲያ ታስረው ከተለቀቁት ውጭ እስከ አኹን በእስር የሚገኙ ስምንት ምእመናን (አራት ምእመናን እና አራት የሰንበት ት/ቤት አባላት) በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡ ተገልጧል፡፡ ከታሳሪዎቹ መካከል ደብሩን በስብከተ ወንጌል ሲያገልግሉ ቆይተው በጡረታ የተገለሉ የ70 ዓመት ሕመምተኛ አዛውንት ይገኙበታል፡፡ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ሲገቡ በአዛዡ ‹‹ማዕተባችኹን በጥሱ፤ መስቀላችኹን አውልቁ›› መባላቸውን ከእስር የተፈቱት ምእመናን ተናግረዋል፡፡
በደብሩ የልማት እና የመካነ መቃብር ይዞታዎች የሚገኙ የንግድ ቦታዎች እና ሱቆች ከቤተ ክርስቲያን ይልቅ ግለሰቦችን በሚጠቅም አኳኋን በከፍተኛ ዋጋ እየተከራዩ ባለበት ኹኔታ የደብሩ ገቢ እና ልማት እየተዳከመ መምጣቱ በምእመናን እየተገለጸ እና ይኸውም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የአስተዳደር ጉባኤ በተሠየመ አጥኚ ቡድን ተረጋግጦ እርምት እንዲደረግ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ በደብሩ የአስተዳደር ይኹን የልማት ሥራዎች ምንም ዐይነት ችግር እንደሌለ ነው በደብዳቤአቸው የጠቀሱት፡፡
በሌላ በኩል ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ችግር አለ ተብሎ የሚታሰብ ከኾነ ሊፈታ የሚችለው በሀገረ ስብከቱ ነው›› ቢሉም በትላንትናው ዕለት በጽ/ቤታቸው ላነጋገሯቸው 12 የምእመናን ተወካዮች፣ ‹‹አያገባኝም፤ የጻፍኹትም ደብዳቤ የለኝም፤ ሰንበት ተማሪ አድርግ የሚባለውን ከማድረግ በቀር ሌላ ሥልጣን የለውም›› ብለው እንደመለሷቸው ምእመናኑ በከፍተኛ ሐዘን ገልጸዋል፡፡
ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ማእምራን የማነ፣ በቤተ ክርስቲያን አስተዳደር የምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ሚና ‹‹አድርጉ የተባሉትን ብቻ ከማድረግ ያለፈ አይደለም፤ ልካቸውን ሊያውቁ ይገባል››በሚለው ንቀት የተመላበት ንግግራቸው ይታወቃሉ፡፡ በዚኽም ደብዳቤአቸው ምእመናኑን ‹‹በቤተ ክርስቲያኑ አስተዳደር ምንም ዐይነት የሥልጣን ድርሻ የሌላቸውና ማምነታቸው የማይታወቅ›› ሲሉ ነው የገለጧቸው፡፡ አካሔዱን አላርምም ባለው የደብሩ አስተዳደር ላይ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለማስጠበቅ እና ተጠቃሚነቷን ለማረጋገጥ በማስገዳጃነት የወሰዱትንም ርምጃ፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያንን መብት የሚጋፋ እና በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ በደል ነው››ብለውታል፡፡
በዋና ሥራ አስኪያጁ ‹‹ማንነታቸው አይታወቅም›› የሚባሉት ምእመናን ግን የደብሩ አስተዳደር በየምክንያ የሚጠይቀውን ድጋፍ ከመስጠት የማይሰስቱ እና በበጎ አድራጎታቸው የሚታወቁ ናቸው፡፡ ልማት በሚል ለሦስተኛ ወገን እየተላለፈ በአስተዳደሩ የሚሰበስበው በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠር ወርኃዊ ገቢም ሓላፊዎቹንና ግለሰቦችን ከመጥቅም በቀር በተጨባጭ የሌለ ለመኾኑ ‹‹በደብሩ አካውንት ያለው ተቀማጭ ማሳያ ነው፤ ባዶ እጁን የመጣ መኪና ገዝቶ እየወጣ ነው››ይላሉ – ምእመናኑ፡፡
ምእመናኑን በመረዳት ችግሩን በትክክለኛ ገጽታው ተመልክቶ ከመፍታት ይልቅ ‹‹ልማቱን ለማስቀጠል›› በሚል እንዲታሰሩና በወንጀል ድርጊት እንዲጠየቁ ዋና ሥራ አስኪያጁ የወሰዱት ርምጃ ከአማሳኞች ጋር በተግባር ያልተፋቱ ለመኾናቸው ማረጋገጫ ነው፡፡ ለዚኽም ነው የቤተ ክርስቲያንን መብት ለማስጠበቅ ከተንቀሳቀሱት ምእመናን ይልቅ በእንቅስቃሴው ጥቅማቸውን ካጡ ተከራዮች ጋር ዳኝነት የተቀመጡትንና በውዝግቡ አጋጣሚ እንዴት እንደሚያትርፉ የሚያሰሉትን አማሳኝ ባለሟሎቻቸውን – የቀድሞው የደብሩ አስተዳዳሪ ዘካርያስ ሐዲስን እና ቀንደኛው ሌባ ኃይሌ ኣብርሃን እየሰሙ የሚገኙት፡፡
በሀ/ስብከቱ ሥር በሚገኙ 69 ገዳማት እና አድባራት የመሬት፣ የሕንፃ፣ የመካነ መቃብር ኪራይ እና የመኪና ሽልማት ጉዳዮችን አጥንቶ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲያቀርብ በጠቅላይ ቤተ ክህነት አስተዳደር ጉባኤ የተቋቋመው ኮሚቴ ጥር ፳፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ባቀረበው ሪፖርት፣ የደብሩ አስተዳደር ሱቆችንና ሰፊ ቦታዎችን በሕገ ወጥ መንገድ በማከራየት የቤተ ክርስቲያንን ጥቅም አሳልፎ መስጠቱን አረጋግጧል፡፡ የደብሩ አስተዳደር የቀሩትን ባዶ ይዞታዎች በማከራየት ሕገ ወጥ አካሔዱን ሊቀጥል እንደሚችል የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በሀገረ ስብከቱ በኩል ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጠው ጠይቆ ማሳሰቢያው እንደተላለፈ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
እንደ ቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ባሉ አድባራት ሰፊ ይዞታዎች ላይ ዐይናቸውን የጣሉት የዋና ሥራ አስኪያጁ የሙስና ባለሟሎች እነኃይሌ ኣብርሃ፣ ዘካርያስ ሐዲስ እና ተስፋ ፍሥሓ በልማት ስም በሚካሔዱ ግንባታዎች በየደብራቸው ያካበቱትን የዘረፋ ልምድ የሚያስፋፉበት ስልት ሲቀይሱ፣ ዋና ሥራ አስኪያጁም በልማት ስም በየአድባራቱ ጉብኝት እያካሔዱ እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነትን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ እና የዕቅበተ እምነት ንቅናቄ በተለያዩ ክሦች ለማዳፈን በመቶ ሺሕ ብሮች(እስከ ብር አምስት መቶ ሺሕ) መድበው የሚንቀሳቀሱትም ለዚኽ ነው፡፡
ይኹንና የአማሳኞች በደል እና የፍትሕ ዕጦት ያንገሸገሻቸው የአጥቢያው ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤቶች ግንቦት ፴ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. የጽ/ቤቱን ቢሮዎች በይደው በማሸግ፤ የአድባራቱን ሓላፊዎች በማባረር እና መኪኖቻቸውን በመቆጣጠር የያዙት አቋም ንቅናቄውን አንድ ርምጃ ወደፊት ያራመደ፤ ችግሩ በሚጠይቀው ልክ ለመሥዋዕትነት የተዘጋጁ፤ የታዘዙትን ብቻ የሚፈጽሙ ሳይኾኑ መልሰው እንደሚጠይቁም ያሳዩበት ኾኗል፡፡
* * *
The post በቦሌ ቡልቡላ መድኃኔዓለም ምእመናን እና የሰንበት ት/ቤት አባላት በዋና ሥራ አስኪያጅ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ ጥያቄ እየታሰሩ ነው appeared first on Zehabesha Amharic.