Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የማህሙድ አህመድ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎት ተከበረ * አላሙዲ 5 ሚሊዮን ብር ሸለሙት

$
0
0

 

(ዘ-ሐበሻ) የትዝታው ሙዚቃ ንጉሥ የሚል የክብር ስያሜን ከኢትዮጵያውያን የተጎናጸፈው ዝነኛው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎት ዘመኑ ተከበረ::

ማምሻውን በሸራተን አዲስ በተከናወነው በዚሁ የማህሙድ አህመድ የሙዚቃ ዘመን 50ኛ ዓመት ልደት ላይ ድምፃዊውን የሚዘክሩ የተለያዩ ፕሮግራሞች ከመቅረባቸውም በላይ ድምፃዊውም ሥራዎቹን ለሕዝቡ ማቅረቡን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ ጠቆሟል::

በዚሁ ምሽትም ለ50 ዓመት የሙዚቃ አገልግሎቱ ከሼህ መሃመድ አላሙዲ የ5 ሚሊዮን ብር ስጦታ እንደተበረከተለት ለማወቅ ተችሏል::

የማህሙድ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ ሕይወት በራሱ አንደበት እንደሚከተለው ዘ-ሐበሻ አሰናድታዋለች:: ይከታተሉት::
Mahamud Ahemed 2

ትውልድና ዕድገት
ቤተሰቦቼ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ነበሩ፡፡ አሁን በሕይወት የሉም፡፡ የተወለድኩት አሜሪካ ግቢ በ1933 ዓ.ም ነው፡፡ እስከ ሶስት ዓመቴ ድረስ አሜሪካ ግቢ ካደኩ በኋላ በሶስት ዓመቴ ወደ ጉለሌ አርበኞች ት/ቤት ፊትለፊት ያለው ኦሎምፒያ ኳስ የሚባል የግሪክ ክለብ ነበር እዚያ ውስጥ አባቴ ይሰሩ ነበር፡፡ በዚያ ስፖርት ክለብ ውስጥ እየሄድኩ የቅርጫት ኳስ፣ የእጅ ኳስ ሜዳ ስፖርተኞች ከተጫወቱበት በኋላ ሜዳውን ውሃ እያጠጣሁ እየደመጥኩ አስተካክል ነበር፡፡ አባቴ በሌሉበት ጊዜ የዚያ ስራ ሀላፊነት የኔ ነበር፡፡

ትምህርት ቤት

ትምህርት ቤትን በተመለከተ ብዙ ባይገባኝም መማር ጀምሬ ነበር፤ ትምህርት ቤት ስገባ ምናልባት 8 ዓመት 9 ዓመት ይሆነኝ ይሆናል፡፡ ቄስ ት/ቤትም ከጓደኞቼ ጋር ገብቼ ነበር፤ መጀመሪያ በእርግጥ ሙስሊም ት/ቤት ነበርኩ፡፡ ወደ 15 ዓመት ሲሆነኝ አባቴ የሚሰሩበት የግሪክ ክለብ ሲዘጋ ስራ ፈቱ፡፡ ከእናቴ ጋር ሆኜ የቤተሰቡን ህይወት ለማገዝ ከእናቴ ጋር ብታምኑም ባታምኑም ጉሊት ቁጭ ብዬ እንጀራ እሸጥ ነበር፡፡ ወደ ጫካ ሄጄ ጭራሮ ና ማገዶ ለቅሜ በማምጣት ለእናቴ እንጀራ መጋገሪያ አቀርብላት ነበር፡፡
በዚህ ሁኔታ ለ6 ዓመት ያህል ትምህርት ቤት እየሄድኩ ስመለስ ሊስትሮ ሆኜ ጫማ እጠርግ ነበር፡፡ ከጓደኞቼ መሀከል ሰነፉ ተማሪ እኔ ነበርኩ፡: ጥያቄ ሲቀርብ ግን የምመልሰው እኔ ነበርኩ፡፡ ግን ፈተና ላይ ስንቀመጥ ነርቨስ ስለምሆን መስራት አልችልም ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ መማር መቀጠል አልቻልኩም፡፡

ሊስትሮና ሙዚቃ

ማታ ማታ እናቴ ዘፈን ታንጎራጉር ስለነበር ስሜቴ ሁሉ ወደ ሙዚቃ ሆነ፤ በ1949 ዓ.ም የንጉሰ ነገስቱ የክብር ዘብ ግቢ ውስጥ የጠቅል ሬዲዮ የሚባል ነበረ፤ ማክሰኞና ሀሙስ ዘፈንና አንዳንድ ፕሮግራሞች ይለቀቁ ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ በሬዲዮ ቀርበው ይዘፍኑ የነበሩት እነ ካሳ ተሰማ፣ ተዘራ ሀ/ሚካኤል፣ መቶ አለቃ ኑር ወንዳፍራሽ (የብዙነሽ በቀለ የልጆቿ አባት የነበረው) ብዙነሽ በቀለ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ አየለ ማሞ፣ እሳቱ ተሰማ ወዘተ ነበሩ፡፡ የዚያን ጊዜ እነዚህ ድምፃውያን በሳምንት ሁለት ቀናት ሙዚቃቸውን እየመጡ ያሰሙ ስለነበር እኔ ቡና ቤት በር ላይ ሊስትሮ ሳጥኔ ላይ ቁጭ ብዬ ዘፈናቸውን አዳምጥ ነበር፡፡ የሚገርማችሁ ማታ የሰማኋቸውን ዘፈኖች ጠዋት ት/ቤት ከመግባታችን በፊት ለክፍል ጓደኞቼ እዘፍንላቸው ነበር፡፡

በወቅቱ ሞዴሌ አድርጌ የምቆጥረው ትልቁ ወንድሜን በአሁኑ ወቅት በዚህ ዓለም ላይ የሌለው ጥላሁን ገሠሠ ነው፡፡ ሌላ ደግሞ በወቅቱ ከውጪ ሀገር የሚመጡ ፊልሞችን እመለከት ስለነበር በተለይ የኤልቪስ ፕሪስሊንን ዘፈን አዳምጥ ነበር፡፡ ኤልቪስ ፕሪስሊን ሲዘፍን እግሩን እንዴት ያንቀጠቅጥ እንደነበር በፊልም ላይ እመለከት ስለነበር እኔም ወደፊት መድረክ ላይ ስወጣ እግሬን አንቀጠቅጣለሁ እል ነበር፤ የኤልቪስ ፕሪስሊንን ብቻ ሳይሆን የነ ሳምኩክን፣ የነ ጀምስ ብራውንን ዘፈኖች አዳምጥ ነበር፡፡
ወደ ሙዚቃው እየተሳብኩ ስመጣ የትምህርቱ ነገር እየቀረ መጣ፤ ከ8ኛ ክፍል በላይ ማለፍ አልቻልኩም፡፡ ጎረቤታችን ወ/ሮ የሺሀረግ ለእኛ የሰጡን አራት በአራት የምትሆን አንድ ክፍል ነበረችን፡፡ ጎረቤታችን አንድ ግብፃዊ ጠበቃ ነበር፤ ያ ጠበቃ ሹፌሮች ቡና ቤት ከሚባለው ቤት ባለቤት ጋር በመሆን ራስ ሀይሉ ቤት ውስጥ ናይት ክለብ ሊጀመር ነው የሚል ወሬ ስሰማ ለእናቴ ሄጄ ሥራ እንዲያስገባኝ ለምኚልኝ አልኳት፡፡ እሷም እሺ አለችና ሄዳ ስትጠይቀው ጥሩ ይምጣና ከአናፂዎች ጋር እመድበዋለሁ አለ፡፡ እሺ አልኩና ሄድኩ፡፡ ከአናፂዎች ጋር ሰርቻለሁ፡፡ ከቀለም ቀቢዎች ጋር ሠርቻለሁ፡፡ ቡና ቤቱ ለናይት ክለብ በሚሆን መልኩ ይሰራ ስለነበር ከነሱ ጋር ሰራሁ፤ በየግድግዳው ላይ ሰዎች ሲጨፍሩ ሁሉ የሚያሳይ ስዕል ተሰርቶ ተጠናቀቀ፡፡

ምሽት ክለብ

በ1954 ዓ.ም ገደማ የሚገርማችሁ ምሽት ክበቡ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ሲከፈት እኔ ወደ ወጥ ቤት ነበር የገባሁት፡፡ ወጥ ቤት ስገባም የወጥ ቤት ረዳት ተደርጌ ነበር የተመደብኩት፡፡ ረዳት ሆኜ እየሰራሁ ማታ ማታ ምሽት ክለቡ ውስጥ እየመጡ የሚዘፍኑትን እነ እሳቱ ተሰማ፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ ተፈራ ካሳ፣ ታምራት ሞላ፣ አባይ በለጠ (ነፍሳቸውን ይማረውና) እመለከት ነበር፡፡

እነሱ ዘፍነው ለእረፍት ሲቀመጡ እኔ ሳንድዊችና ሻይ አቅራቢ ነበርኩ፡፡ እነሱን ስር ስር ጉድ ጉድ እያልኩ ዘፈናቸውን በደንብ ነበር የማደምጠው፤ ታዲያ በአንድ አጋጣሚ እነ ጥላሁን ድሬዳዋ ለስራ ታዘው ሲሄዱ ሙዚቀኞች ብቻቸውን ቀሩ፡፡

ሙዚቀኞቹ የተፈራ ካሳን አልጠላሽም ከቶ ዘፈን መጫወት ሲጀምሩ ከወጥ ቤቴ ሹልክ ብዬ ወጥቼ ‹‹ይህቺን ዘፈን እሺ ልዝፈናት›› አልኳቸው፡፡ ቀጭን ስለነበርኩ አይተውኝ ‹‹ትችያዋለሽ እንዴ›› አሉኝ፡፡ እሞክራሁ አልኳቸውና መድረክ ላይ ወጥቼ ስጫወት እንደአጋጣሚ እዚያ ቤት ከምድር ጦርም ከጦር ሰራዊትም የኮንጎ ዘማቾች ነበሩና ሰምተው ተገረሙ ስጨርስ ቢስ ብለው አስደገሙኝ፤ ስጨርስ እንደገና ለሶስተኛ ጊዜ አስደገሙኝ፤ ‹ይህም አለ ለካ› የተሰኘውን የተዘራ ኃ/ሚካኤልን ስጫወትም ይደገም ተባለ፤ ደገምኩ፤ ያንን ዘፍኜ ከመድረክ ልወርድ ስል የምሽት ክለቡ ባለቤት ፊት ለፊቴ ቆሞ ‹‹ያ አላህ፤ ለመሆኑ መዝፈን ትችላለህ እንዴ?›› አለኝ ‹‹እሞክራለሁ›› ስለው ከነገ ጀምሮ ወደ ወጥ ቤት አትመለስም እነ ጥላሁን እስከሚመጡ ድረስ እዚሁ ትዘፍናለህ›› አለኝ፡፡ በማግስቱም መርካቶ ወሰደኝና ሙሉልብስ፣ ጫማና ሸሚዝ ከነልዋጩ ገዛልኝ፡፡ እነ ጥላሁን ከድሬዳዋ ሲመለሱ መድረኩ ላይ ቄብ ብዬ ጠበኳቸው፡፡ መድረክ ላይ ቆሜ ስዘፍን ሲያዩኝ ተገረሙ፡፡ ‹‹መዝፈን ትችያለሽ እንዴ›› እያሉ ሲጠይቁኝ ‹‹እሞክራሁ›› ነበር መልሴ፤ ከዚያ ብታምኑም ባታምኑም አንድ ሙሉ ግጥም የያዘ ደብተር አመጡልኝና አጥና አሉኝ፡፡ እየመረጥኩ የጥላሁንን፣ የእሳቱን፣ የተዘራን፣ የካሳን ዘፈኖች ግጥሞች ማጥናት ጀመርኩ፡፡

Mahamud Ahemed

ምሽት ክለቡ እየተሟሟቀ ብዙ ደንበኞች እየመጡ ሳለ በ1954 ዓ.ም እቴጌ መነን ያርፋሉ፡፡ በዚሁ ሰበብ ምሽት ክለቡ ተዘጋ፡፡ ግን ከሁለት ወራት በኋላ ሀዘኑ ይበቃል ብለው ግርማዊ ቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ ‹‹ህዝቤ ሀዘኔን ከኔ ጋር ተካፍለሀልና ከዚህ በኋላ ወደ ስራህ ግባ›› ባሉት መሠረት የሙዚቃ ሥራ ዳንስ ቤቱ ሁሉ ሲከፈት የእኛም ምሽት ክለብ ተከፈተ፡፡ የዚያን ጊዜ ያው የሰው ዘፈን እያጠናሁ ስለነበር የምዘፍነው የመጀመሪያዋን የራሴ ዘፈን፡-
‹‹ካንቺ በቀር ሌላ ብሞት አልመኝም
ግን እስካሁን ድረስ አላወቅሽልኝም››

የተባለችው ዘፈን ተሰጥታኝ የጉሮሮዬ ማሟሻ ሆና ተጫወትኳት፡፡ ይህቺ ዘፈን አሁን ድረስ አብራኝ አለች፡፡

ጉዞ ወደ ክቡር ዘበኛ

ወደ ክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍል ከመግባቴ በፊት መጀመሪያ ፖሊስ ሠራዊት ሙዚቃ ክፍል ነበር ለመግባት የፈለግሁት፡፡ በዚህም መሠረት ለምን ሄጄ አልጠይቃቸውም ብዬ ሄጄ ስጠይቅ ‹‹የማንን ዘፈን ነው የምትዘፍነው?›› ሲሉኝ የነ ጥላሁን ገሠሠ፣ የነ እሳቱ ተሰማ ስላቸው ‹‹የሙዚቃ ትምህርት ተምረሃል ወይ›› አሉ፣ አልተማርኩም ስል ካላወቅህ አንፈልግም አሉኝና መለሱኝ፡፡ ከዚያ እንደገና ወደ ምድር ጦር ሙዚቃ ክፍል ሄድኩ፡፡ እዚያ ደግሞ ‹‹መጀመሪያ ደብረ ብርሃን ሄደህ ወታደርነት ተቀጥረህ ስትመጣ ነው ወደዚህ ክፍል የምትገባው›› አሉኝ፡፡ አይ እንግዲህ ዕድሌ አይደለም ብዬ ዝም ብዬ እዚያ ምሽት ክለብ ውስጥ ማታ ማታ ስሰራ ቆይቼ ለምን ክቡር ዘበኛ አልሄድም ብዬ ሻለቃ ግርማ ሀድጎ ስሄድ በዚያን ወቅት የፊደል ሠራዊት የሚባል ተቋቁሞ ለነሱ እርዳታ ማሰባሰቢያ የሙዚቃ ዝግጅት የክቡር ዘበኛ፣ የጦር ሠራዊት፣ የፖሊስ እና የቀዳማዊ ሀይለስላሴ የሙዚቃ ክፍሎች ባሉበት ዝግጅት ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ የቀዳማዊ ሀይለ ስላሴ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እነ ተሾመ ምትኩን ይዞ ተሳትፏል፡፡ በዚህ የሙዚቃ መድረክ ላይ ነው እንግዲህ ተፈትነህ ካለፍክ ትቀጠራለህ የተባልኩት፡፡ በዕለቱ ትዝ ይለኛል የመድረክ አስተዋዋቂ በዚያን ወቅት የ10 አለቃ ገዛኸኝ ደስታ ነበር፡፡ የተናገረው ነገር አሁን ድረስ አይረሳኝም፡፡ ‹‹አንድ አዲስ ልጅ ዛሬ እናቀርብላችኋለን፡፡ ልጁ ምናልባት የጥላሁን ገሠሠ ደቀመዝሙር ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡ ይሁን ካላችሁ ይቀጥላል›› ነበር ያለው፤ አስቦት ይሁን የተናገረው ታይቶት ይሁን አላውቅም፡፡ እንደዚህ አስተዋውቆኝ መድረክ ላይ ወጣሁ፡፡ ይዤ የነበረው የታምራት ሞላን፣ የገላን ተሰማን፣ የጥላሁን ገሠሠንና የራሴን የተሰጠችኝን ካንቺ በቀር ሌላን ተጫወትኩ፡፡ ከታምራት ዘፈን ቀጥሎ የራሴን ስዘፍን አቀባባሉ ልዩ ነበር፡፡ ስጨርስ ይደገም ተባለ፡፡ ደገምኩ፡፡ የሚገርማችሁ ሶስተኛውን ዘፈን ስጫወት ልክ ያኔ ኤልቪስ ፕሪስሊን እንደሚያደርገው እግሬን እያንቀጠቀጥኩ ነበር፡፡ ህዝቡም በልዩ አድናቆት አጀበኝ፡፡

ከመድረክ ስወርድ በክቡር ዘበኛ ውስጥ ልቀጠር እንደምችል አውቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም የህዝቡ አቀባበል ልዩ ነበር፡፡ ታዲያ ሻለቃ ግርማ ሀድጎ ምን አሉኝ ‹‹ስማ አንተ ልጅ በወታደርነት እንቅጠርህ ቢሉ እሺ እንዳትላቸው፤ በሲቪል ግን ካሉህ እሺ በላቸው፡፡›› አሉኝ፡፡ እሺ አልኳቸውና በወታደርነት እንቅጠርህ ሲሉኝ አልፈልግም በሲቪልነት ነው የምፈልገው አልኳቸው፡፡ ከዚያ የዚያን ጊዜ ደሞዝ 60 ብር ስለነበር በሲቪልነት በ60 ብር በወታደርነት ደግሞ በ60 ብር በድምሩ በ120 ብር እንቅጠርህ አሉኝ፡፡ አልፈልግ ስል በሲቪልነት በ60 ብር ደሞዝ ታህሳስ 15 ቀን 1955 ዓ.ም ክቡር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል ተቀጠርኩ፡፡

ለ11 ዓመታት ያህል በክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ክፍል ውስጥ ሳገለግል የመጀመሪያው መምህሬ የአፍ አከፋፈትና የድምፁ አወጣጥ ያስተማረኝ ወንድሜ ጥላሁን ገሠሠ ነበር፡፡ ሌሎችም ጓደኞቼ የየራሳቸውን ምክር ሰጥተውኛል፡፡ እነ እሳቱ ተሰማ፣ ተዘራ ሀ/ሚካኤል፣ ብዙነሽ በቀለ ሁሉም መክረውኛል፡፡ እስከ ዛሬ ድረስ እጠቀምበታለሁ፡፡
በ1955 ዓ.ም ለ1956 ዓ.ም አዲስ ዓመት መግቢያ የምድር ጦር የንጉሰ ነገስቱ የክብር ዘብ ሙዚቀኛ፣ ፖሊስ ሠራዊትና ኪነ ጥበባት መምሪያ የሚባል ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ ያለው ልዩ ዓመታዊ የሙዚቃ ውድድር ያካሂድ ስለነበር ሁላችንም ተዘጋጅተን ነበር የምንሄደው፡፡ የዚያን ጊዜ እያንዳንዳችን አራት ወይም አምስት አዲስ ዘፈን ይዘን ነበር የምንቀርበው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለኔም ሌሎች አዳዲስ ዘፈኖች ተሰጡኝ፡፡ በደንብ መዝፈን ጀመርኩ፡፡ በ11 ዓመታት ቆይታዬ ብዙ ዘፈኖች ተጫውቻለሁ፡፡ ከዚያ ክቡር ዘበኛን ለቅቄ ወደ ናይት ክለብ ስራ ራስ ሆቴል ገባሁ፡፡

ወደ ናይት ክለብ ስራ ልገባ የቻልኩት ክቡር ዘበኛ የሚከፈለኝ 250 ብር እያነሰኝ መጣ፡፡ ቤታችን ውስጥም 3 ወንዶች ሶስት ሴቶች ስላለን ለማስተዳደር በቂ አልሆን አለ፡፡ አባቴም ስራ ስላቆመ እናቴም እንጀራ ጉልት ብቻ ስለነበር የምትሸጠው የኔ ደሞዝ እያነሰ ሲመጣ ለቅቄ በ1966 ዓ.ም ራስ ሆቴል አይቤክስ ጋር ናይት ክለብ ገባሁ፡፡ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ህይወቴም እየተሻሻለ መጣ፤ አሁን ለደረስኩበት ደረጃ መሠረት የሆኑኝን ዘፈኖች ሰራሁ፡፡

በኛ ዘመን ከነበረው አንፃር እናንተ በጣም እድለኞች ናችሁ፡፡ ምክንያቱም በኛ ጊዜ እግዚአብሔር ከሰጠን ድምፅ ፀጋ በቀር ሌላ እውቀት አልነበረንም፡፡ እናንተ ግን አሁን ሙዚቃን በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ነው እየተማራችሁ ያላችሁት፡፡ በዚህም ልትኮሩ ይገባል፡፡ ሙዚቃ በዓለም ላይ ትልቅ ደረጃ ደርሷል፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ የማድረስ ሀላፊነት እናንተ ላይ ነው የተጣለው፡፡ ለመጪው ትውልድ እናንተ መብራቶች ናችሁ ተጠቀሙበት፡፡
ስለ ፍራንሲስ ፋልሴቶ

በኔ በኩል የኢትዮጵያን ሙዚቃን ከራሴ አልፌ በዓለም እንዳስተዋውቅ ያደረገኝ አንድ ሰው አለ፡፡ ፈረንሳያዊው ፍራንሲስ ፋልሴቶ ይባላል፡፡ ይሄ ፈረንሳዊ ፕሮሞተር ነው፡፡ ፍራንሲስ ፋልሴቶ የኢትዮጵያ ሙዚቃን የሚወድ፣ ልቅም አድርጎ የሚያውቅ ሰው ነው፡፡

የኔን ዘፈን በሬዲዮ ሰምቶ ነው ከፈረንሳይ ወደ አዲስ አበባ የመጣውና ያገኘኝ፡፡ ራስ ሆቴል ድረስ መጥቶ ካንተ ጋር መስራት እፈልጋለሁ፤ አለኝ፡፡ የዚያን ጊዜ ያው እንደ ማንኛውም ሰው አይ ይሄ ፈረንጅ እውነቱን ነው ብዬ ነበር የተጠራጠርኩት፡፡ ከዚያ ከአይቤክስ ሙዚቀኞች ጋር ሆነን የመጀመሪያ ጉዟችን ወደ ፈረንሳይ ሄድን፡፡ የዚያን ጊዜ ትዝ የሚለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ ፓሪስ ውስጥ እኔ ስሰራ ከኛ አዳራሽ ፊት ለፊት ባለ ሌላ መድረክ ላይ ማይክል ጃክሰን ይዘፍን ነበር፡፡ የዚያን ጊዜ እኔ ስጫወት ሙላቱ አስታጥቄ ትልቁ ሙዚቀኛ አብሮን ነበር፡፡ ሙላቱ የኢትዮጵያ ሙዚቃን በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቀ ሰው ነው፡፡

ከዚያን ጊዜ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈረንሳይን ረግጨ ብዙ ስራዎችን አብረን ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር ሰርተናል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ አልበምን አሳትሟል፡፡ የኔ ብቻ ሳይሆን የጥላሁን ገሠሠ፣ ሙሉቀን መለሰ፣ አለማየሁ እሸቴን የሌሎችንም በልዩ ሁኔታ አስቀርፆ አውጥቷል፡፡

በነገራችን ላይ እኔ ይህ የመጀመሪያዬ ነው፡፡ ከተማሪዎች ፊት ቁጭ ብዬ የሕይወት ልምዴን ሳካፍል፤ ለናንተ ይህንን ነገር ከተናገርኩ በኋላ እኔ ዛሬ ማታ ብሞት ቅር አይለኝም፡፡
የአንጋፋው ድምፃዊ ማህሙድ አህመድ ገለፃ እንዳበቃ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ከተማሪዎች ቀርቦለታል፡፡ ከቀረቡት ጥያቄዎች መሀከልም የመጀመሪያ አልበምህ ያሳተምከው መቼ ነው? የሚለው ይገኝበታል፡፡ ማህሙድ ሲመልስ ‹‹በካሴት ደረጃ ያወጣሁት የመጀመሪያ ካሴት በ1972 ገደማ ነው፤ ከዚያ በፊት ሸክላ ነበር፤ በዚህ ካሴት ላይ አሽቃሩ የሚለው ዘፈን ያለበት ሲሆን ደራን ጨምሮ 10 ዘፈኖችን ይዟል፡፡ የሚገርማችሁ በዚያን ወቅት ጥላሁንም ካሴት አውጥቶ ነበር፡፡ የሱ በሎ የሚለውን የኦሮሞኛ ዘፈን የያዘ ሲሆን የኔ ደግሞ አሽቃሩ የሚለው የጉራጊኛ ዘፈንን የያዘ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ እሱ አሽቃሩ ሲለኝ እኔ በሎ በሎ ነበር የምለው፡፡››

በትዝታ ዘፈኖችህ ላይ ልዩ ድምፅ አለህ? ይህንን ችሎታህ እንዴት አዳበርከው ለተባለው ጥያቄ ደግሞ ‹‹እኔ ከሌሎች የተሻለ ድምፅ አለኝ ለማለት አልችልም፤ ከሌሎች ተሽዬ ሳይሆን ባለኝ አቅም እግዚአብሔር በሰጠኝ ፀጋ እዚህ ደርሻሁ፡፡ የድምፅ አወጣጥ ወይም ስለ ድምፅ የተሰጠኝ ትምህርት የለም፡፡ በተፈጥሮ ያለ ነገር ነው የምንዘፍነው ካንዳችን አንዳችን የምንማረው ነገር አለ፡፡ አሁን እናንተ እድለኞች ናችሁ የምለው በኖታ ተፅፎ እያነበባችሁ ነው ሙዚቃ የምትጫወቱት፡፡ በኮንዳክተር የሚዘፍኑ ድምፃውያን አሉ፤ ከኖታ ላይ የሚዘፍኑ አሉ፤ እኛ ግን የዚህ ዕድል ተጠቃሚዎች አልነበርንም፡፡ ለዚህ ነው እኔ ችሎታ አለን ብዬ የማልናገረው፡፡ ሀይል አለኝ አልልም፤ ሀይል የእግዚአብሔር ነው››
በሙዚቃ ህይወትህ ያጋጠሙህ ፈተናዎች ምን ይመስላሉ? እንዴትስ አለፍካቸው? ለወጣቶችስ ምን ትመክራህ? ‹‹በሙዚቃ ህይወቴ ብዙ ነገሮችን አሳልፌያለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ስቀጠር በሙዚቀኛ ደረጃ አልነበረም የምንጠራው፤ ያንን ጊዜ በትዕግስት አልፈናል፡፡ አዝማሪ ነበር የምንባለው፤ ግን በዚያን ወቅት አዝማሪ እንደስድብ የሚቆጠር ቢሆንም በኋላ ግን ክብር መሆኑን ነው ያወቅሁት፡፡ ምክንያቱም አዝማሪ ይዘምራል የሚል ነገር ስላለ ስድብ ሳይሆን ክብር መሆኑን ነው ያወቅሁት፡፡ ያንን ዘመን አሳልፈናል፤ ግን በፀጋ ነው ተቀብለን ያሳለፍነው፤ በውጪው ዓለም አሁን የሙዚቃ ሰው ያለውን ክብር እያያችሁ ነው፤ ይህንን ይዞ ወደፊት መሄድ ያስፈልጋል፡፡ እናንተ ናችሁ ሙያችሁን የምታስከብሩ፤ ተስፋ አትቁረጡ፡፡ እግዚአብሔር ይርዳችሁ ነው የምለው፤ ችግር ቢመጣም መቻል ነው ያለባችሁ፡፡ መሠረታችሁን ሳትለቁ የኢትዮጵያ ሙዚቃን ለማሳደግ ነው መጣር ያለባችሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ የውጪ ሀገር ሙዚቃዎችን ስታሰሙ እንዴት አድርገው ነው የሰሩት ልትሉት ትችላላችሁ፤ ግን በትምህርት የተሰራ በመሆኑ ትምህርታችሁን ጠንክራችሁ ልትማሩ ይገባል››

በ1968 እና 1968 ገደማ በነበረው የሀገራችን ሁኔታ ውስጥ የሰራሃቸው ስራዎች መሠረታዊ ለውጥ ያመጡ እንደሆኑ ይታወቃል፤ በተለይ የዕድገት በህብረት ዘመቻ ጊዜ የወጡት ስራዎች ማለት ነው፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ትችት የሰነዘሩባቸው ሥራዎች አሉ፤ ስለ እነዛ ሥራዎችና ስለወቅቱ እስኪ አንዳንድ ነገሮችን ንገረን? ተብሎም ተጠይቆ ነበር፡፡
‹‹ከ1963 ዓ.ም ጀምሮ ራስ ሆቴል ከአይቤክስ ባንድ ጋር እሰራ ነበር፤ በዚያን ወቅት እነ ኩሉን ማን ኳለሽ፣ እነአምባሰል፣ እነትዝታ፣ እነችቦ አይሞላም ወገቧ፣ አልማዝ ምንዕዳ ነው የሠራሁበት ወዘተ ነው፡፡ ክቡር ዘበኛ ሆኜ ነበር በራስ ሆቴል ማታ ማታ የምሠራው፡፡ ታዲያ በዚህ የተነሳ ምን አየሠራህ ነው ተብዬ ተጠይቄ ነበር፤ እነዛን ዘፈኖች የተቀረፀበት ብስራተ ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ነበር፡፡ታዲያ እነኩሉን ማንኩሎሻል ስጫወት ከፍተኛ ዝና ነበር ያገኘሁት፡፡ ጋዜጠኛ ግን ምንአለኝ ፍራሽ አዳሻ አለኝ፡፡ ‹‹ፍራሽ አዳሽ ስልህ ከፋህ ወይ›› ሲለኝ ለምን ይከፋኛል አልከፋኝም አልኩት፤ ፍራሽ አዳሽ የተበላሸ ፍራሽ ጥጥ እንደገና አስተካክሎ ሰው እንዲተኛበት የሚያደርግ ባለሙያ ነው፡፡ ፍራሹ ከመቆርቆር ወደ ምቾት ይቀይረዋል፡፡ እኔ ደግሞ የተረሱትን ዘፈኖች በማደሴና ፍራሽ አዳሽ በመባሌ ምንም ቅር አይለኝም ነው ያልኩት፡፡

በዕድገት በህብረቱ ዘመቻ ወቅት ተማሪው በሙሉ ወደ ገጠር ዘመቻ ሲሄዱ እኔ አታውሩልኝ ሌላ፣ ነይ ደኑን ጥሰሽ፣ መላ መላን፣ አባይ ማዶን ነበር የዘፈንኩት፤ እንደውም የአባይ ማዶን ግጥም የገጠመልኝ ሰው እዚህ መሀከላችሁ ይገኛል፡፡ ሸርፈዲን ሙሳ ይባላል፡፡ አባይ ማዶን ብቻ ሳይሆን ሌላም ዘፈን ፅፎልኛል፡፡ በቅርቡ ትሰማላችሁ ‹‹አብራኝ ናት›› የተባለ ግጥም ፅፎልኛል፡፡ አብራኝ ናት የሚለው አሁን አብራኝ ላለችው ባለቤቴን ነው፡፡ ድሮም ነበረች፤ አልማዜ ብዬም ዘፍኜላት አውቃለሁ፡፡ አብራኝ ናት ያልኩት ለምንድንነው? ከልጅነት እስከ እውቀት አብራኝ ናት፣ በሞራል አብራኝ ናት፣ በስራዬ አብራኝ ናት፣ የምታማክረኝ ናት፣ የኑሮ ደረጃዬ ከፍ እንዲል እየሠራች እዚህ ደረጃ ያደረሰችኝ እሷ ናት፡፡ አልማዝ አልማዝዬ ብዬ ዘፋኜላታለሁ፡፡ አሁን ደግሞ አብራኝ ናትን እዘፍንላታለሁ፡፡ አልማዝ አልዝዬ ግጥምና ዜማ የሰጠኝ ነፍሱን ይማረውና ፍሬው ሀይሉ ነበር ዛሬ ልጁ ደግሞ ፍሬው እዚሁ ት/ቤት ተምሮ ራሱን ለትልቅ ደረጃ ያበቃ የራሱን ካሴት ያወጣ ልጅ አፍርቷል፡፡ እናንተንም ለዚህ ደረጃ ያብቃችሁ ነው የምለው ፡፡
ታዲያ እነዛን ዘፈኖች በዕድገት በህብረት ዘመን ወቅት በመዝፈኔ በፖለቲካ ጉዳይ ውስጥ ባልገባም ብሔራዊ ቴአትር የነበሩ ሠራተኞችና ሙዚቀኞች አድማ አድርገው ታፍሰው ነበር፡፡ በአድማው በታሰሩበት አንድ ካድሬ መጥቶ ሊያስፈታቸው ሲል ‹‹እኛ ትግል እየታገልን እንደገና አንዳንዱ አታውሩልኝ ሌላ ከሷ ዜና በቀር አያለ ይዘፍናል፡፡ እኛ ትግል እየታገልን ነይ ደኑን ጥሰሽን ይዘፍናል›› ብለው ወደሌላ ነገረ ቀይረው ሊያስመቱኝ ነበር፡፡ በወቅቱ ብዙ ችግሮችን አልፌያለሁ፤ ግን እግዚአብሔር ይመስገን ያንን ሁሉ አልፌ ለዚህ ደረጃ በቅቻለሁ፡፡

የት የት ሀገራት የሙዚቃ ስራዎችህን አቅርበሃል? በሚል ለተጠየቀው ጥያቄ ‹‹መጀመሪያ ጊዜ ከፍራንሲስ ፋልሴቶ ጋር ፈረንሳይ ላይ ሙዚቃዎቼን ካቀረብኩ በኋላ ያልሄድኩበት ቦታ የለም ልል እችላለሁ፤ እንግዲህ በአሁኑ ሰዓት በትክክል የማላውቃቸው ሀገሮች ጃፓንና ብራዚል ብቻ ናቸው ልል እችላለሁ፤ ከዚህ ውጪ ያሉ ሀገሮችን አይቻለሁ፡፡ በእንግሊዝ ሀገርም የቢቢሲ ሚውዚክ አዋርድ ተሸልሜያለሁ፡፡ በመላው ዓለም ዛሬ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሼ ሀገሬን አስተዋውቄያለሁ ብል የዋሸሁ አይመስለኝም፡፡››
የህይወት ታሪክህን የተመለከተ መፅሐፍ እየተዘጋጀ እንደሆነም ይነገራልና መቼ ለአንባብያን የሚደርስ ይመስልሃል? በሚል ለቀረበለት የመጨረሻ ጥያቄም‹‹ታሪኩ በረድፍ በረድፉ እየተሠራ ነው፤ ግን ማነው በጥሩ ሁኔታ የሚፅፈው የሚለውን እያፈላለግሁ ነው፡፡ የራሴን ገጠመኞች እኔ ነኝ የምፅፈው ወይስ ለሌላ ሰው ተናግሬ ነው የማፅፈው የሚለው ገና ነው፡፡ ግን በህይወት እያለሁ መፅሐፌ ታትሞ ባየው ደስ ይለኛል፡፡ እኔ ላልፍ እችላለሁ፤ ግን ታሪኬን በመፅሐፍ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ምኞት አለኝ፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያሳካው እምነት አለኝ፤ ኢትዮጵያ በነፃነት ለዘለዓለም ትኑር አመሠግናለሁ፡፡››

The post የማህሙድ አህመድ 50ኛ ዓመት የሙዚቃ አገልግሎት ተከበረ * አላሙዲ 5 ሚሊዮን ብር ሸለሙት appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>