(ዘ-ሐበሻ) “አንድነት” በሚል በሊቢያ በአይሲኤስ የተሰውቱን ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች በገንዘብ ለማገዝ ሜይ 23 2015 የተጠራው ኮንሰርት ትርፍ ባይገኝበትም አዘጋጆቹ ከኪሳቸው አዋጥተው ገንዘቡን ለመ/ር ዘመድኩን በቀለ ላኩ:: የሟች ቤተሰቦችን በየከተማው እየዞረ ከውጭ የተላኩትን ገንዘቦች እያደረሰ የሚገኘው መ/ር ዘመድኩን ገንዘቡን መረከቡን እና ወለጋ ውስጥ ለሚገኙ የአይሲኤል ሰለባው መንግስቱ ጋሼ ቤተሰቦች እንደሚያደርስ አስታውቋል::
መንግስቱ ጋሼ የተባለው የአይሲኤል ሰለባ ቤተሰቦቹ እስካሁን እርዳታ አለማግታቸው ሲታወቅ መምህር ዘመድኩንም በሁለት ቀናት ውስጥ ከሚኒሶታ የተዋጣውን ገንዘቡን ይዞ ወደ ወለጋ እንደሚሄድና ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያጽናና ለዘ-ሐበሻ ገልጾአል::
የአንድነት የሙዚቃ ኮንሰርት አዘጋጆችች መካከል ዲጂ ሶሎ ለዘ-ሐበሻ እንደገለጸው 100% ትርፉ በሊቢያ ለተሰዉት ወገኖች መርጃ ይውላል ተብሎ በተዘጋጀው አንድነት ኮንሰርት ከትኬት $21, 876.00 ገቢ ተገኝቷል:: ሆኖም ግን ወጪው $22,709.30 በመሆኑ ኮንሰርቱ ላይ ምንም ትርፍ አልተገኘም:: ወጪውም ለአርቲስት ተመስገን ደሳለኝ; ለምነው ሸዋ ኢንተርቴይመንት; ለአብዱ ኪያር, ለንጉሱ ታምራት እና ለሃፍቶም የተከፈለ $10.500; ለራስ ባንድ $2,500; ለ11 ሰዎች ዓየር ትኬት ወጪ $3,884.40; ለሆቴል $636.90; ኮንሰርቱ ለተዘጋጀበት አዳራሽ ኪራይ $3,500; ለኮንሰርት ኢንሹራንስ $413; ለሳውንድ ቴክኒሻን $945 በአጠቃላይ $22,709.30 ወጪ መውጣቱን ዲጄ ሶሎ ለዘ-ሐበሻ ገልጿል::
ይህን ኮንሰርት ያስተባበሩት ሶሎ ኤቨንትስ $500; አርቲስት ደሳለኝ ተሻለ $500; አቶ ማሙሽ አማረ $500; ፋሲል ዱባለ $500 እንዲሁም ከማስታወቂያ በተገኘ $450 በአጠቃላይ $2,400 ወለጋ ለሚገኙት የመንግስቱ ጋሼ ቤተሰቦች እንዲደርስ ለመ/ር ዘመድኩን ገንዘቡ ተልኳል:: ይህን ኮንሰርት በማስተዋወቅም ዘ-ሐበሻ ሰፊ ድርሻ ነበራት::
አቶ ሰለሞን በኮንሰርቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮችንና መልካም ነገሮችን ሲገልጹ “አርቲስት ተመስገን ገብረ እግዚአብሄር (ተሙ) እኩለ ለሊት ላይ ገንዘቤን ካልሰጣችሁኝ መድረክ ላይ አልወጣም በማለቱና በድቅድቅ ጨለማ ካሽ ገንዘብ ለመፈለግ ሲሯሯጡ ዘፋኙ ዘይግቶ ሥራውን እንዲጀምርና ተመልካቹም ተመስገን ወደ መድረክ እስኪወጣ አላስፈላጊ መቆየት ውስጥ እንደገባ” ጠቅሰዋል:: “ከዚህ በፊት በርካታ ዘፋኞችን አምጥተናል – ሁሉም ሥራ ካለቀ በኋላ በፖስታ ገንዘባቸውን ሰጥተን አመስግነን ነው የምንልካቸው” ያሉት አቶ ሰለሞን ተመስገን በፈጠረው የገንዘቤን ካልሰጣችሁኝ መድረክ ላይ አልወጣም ግብግብ ሕዝቡ የሚገባውን ያህል በዘፋኙ ሊዝናና ባይችልም አብዱ ኪያር; ንጉሱ ታምራትና ሃብቶም መድረኩን ይዘው ቆይተዋል::
አቶ ስለሞን መልካሙን ነገር ሲገልጽ “ይህ ኮንሰርት ኪሳራው ከ$6 ሺህ ዶላር በላይ ይሆን ነበር:: በሚኒሶታ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲን ፈቃድ (ላይሰንስ) በመጠቀማችን ከትርፍ ነፃ የሆነ ኮንሰርት በመሆኑ ታክስ ከመክፈል ድነናል:: ለኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ ምስጋናችንን እናቀርባለን:: ብሏል::
The post በሚኒሶታ የተደረገው ኮንሰርት ትርፍ ባይገኝበትም አዘጋጆቹ ከኪሳቸው ያዋጡት ገንዘብ ለመ/ር ዘመድኩን በቀለ ተላከ * ወለጋ ለሚገኙት የአይሲኤስ ሰለባ ቤተሰቦች ይሰጣል appeared first on Zehabesha Amharic.