መነሻ አንድ
ለማለት መዘጋጀታቸው ሲሰማ ወጣቱ ድምፃዊ ራሱን ለማጥፋት እስከመወሰንየዛሬ ሶስት ዓመት ሳሚ በየነ የተባለ ወጣት ድምፃዊ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የቅጂና የተዛማጅ መብቶች አዋጅን የዘነጋ አንድ አልበም አውጥቶ ነበር፡፡ አልበሙ መሉ ለሙሉ ድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩን ቀደምት ተወዳጅ ዘፈኖች መሀከል 12 ያህሉን መርጦ በድጋሚ በማቀንቀን ለህዝብ ሲያቀርብ ድምፁ ከኤፍሬም ታምሩ ጋር ከመመሳሰሉ ጋር በተያያዘ በብዙዎች ዘንድ ተደማጭነትን ያገኘው በአጭር ቀናት ነበር፡፡ በየመገናኛ ብዙሃኑ ብቻ ሳይሆን በየታክሲውና በየሆቴሉ መደመጥ የጀመረው የሳሚ በየነ አልበም ተቃውሞ የመጣበት ግን ብዙም ሳይቆይ ነው፡፡
ተቃውሞው የመጣው ቀደምት ስራዎቹን በአዲስ መልክ ለማውጣት እንቅስቃሴ በጀመረው በድምፃዊ ኤፍሬም ታምሩ ብቻ ሳይሆን ከግጥምና ዜማ ደራሲያኑ ፤አሳታሚው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤትና ከሙዚቃ አቀናባሪውም ጭምር ነበር፡፡ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ አስር ሺህ ያህል ሲዲዎችን ማሰራጨት የቻለው ሳሚ በየነ ብቻ ሳይሆን ዘፈኖቹን መርጦ እንዲያቀነቅነው ያደረገው አሳታሚውና ፕሮውዲውሰሩ ኢቫንጋዲ ሪከርድስም ከቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ጋር በተያያዘ ተቃውሞ የቀረበበት ወዲያውኑ ነበር፡፡ ያለ ምንም ፈቃድ ዘፈኖቹን ዘፍኖ ያወጣው ሳሚ በየነ በአዋጁ መሠረት በፍትሐብሔር ብቻ ሳይሆን በወንጀልም ከፍተኛ ሊባል የሚችል ቅጣት እንደሚጣልበት መነገር ሲጀምር ድምፃዊው ያልጠበቀው ችግር ውስጥ ገባ፡፡
ወጣቱ ድምፃዊ የኤፍሬም ዘፈኖችን አቀንቅኖ ካገኘው እውቅና የበለጠ ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ወደቀ፡፡ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጁ መሠረት የፈጠራ ስራዎቹ ባለቤቶች ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድና ‹አቤት›የሚደርስ ከባድ ወሳኔ ላይ መድረሱ ተነገረ፡፡ ከቀናት በኋላም ዘፈኖቹን ከገበያ ላይ እንዲሰበስብ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን ተከትሎ አሳታሚውና ድምጻዊው ታትመው ህዝብ እጅ ያልገቡ ሲዲዎችን ከከተማ ላይ በመኪና ተዘዋውረው መሰብሰብ ጀመሩ፡፡ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስም በግጥም ደራሲው ይልማ ገ/አብ፤ እንዲሁም በዜማ ደራሲው አበበ መለሰ ወኪልና በኤፍሬም ታምሩ ማናጀር፤በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤትና በሙዚቃ ቅንብሩ መሪ በነበረው ዳዊት ይፍሩ መኖሪያ ቤት ሳሚ በየነ አዛውንት እናቱንና ነፍሰ ጡር ባለቤቱን ይዞ በማለዳ በመገኘት ‹የይቅርታ› ምልጃ አቀረበ፡፡
ሁሉም ባለሙያዎች የነገሩን ከባድነት ባለመረዳት የተሰራ ስራ መሆኑንና የወጣቱን ድምጻዊ የወደፊት ህይወት ላለማበላሸት በሚል ሁሉም ይቅርታ አደረጉለት፡፡ እርግጥ ነው መኪናውን ሸጦ የተወሰነ ክፍያ ለደራሲያኑ መክፈሉ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡
መነሻ ሁለት
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በብስራት ኤፍ ኤም ላይ በሚቀርብው ‹ሁሉ አዲስ› በተሰኘው የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ በእንግድነት የቀረበው አንጋፋው ገጣሚ ይልማ ገ/አብ ከኤፍሬም ታምሩ ጋር ስለነበረው ጓደኝነትና ስለ ስራዎቹ ተጠይቆ ሰፊ ጊዜ ወስዶ ነበር ያብራራው፡፡ በድምፁ ከሚያደንቃቸው አርቲስቶች መሀከል አንዱ ኤፍሬም እንደሆነ የጠቀሰው ይልማ ገና በ23 ዓመቱ ሲያገባም ሚዜው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ‹ወንድሜ› ነው ሲል ነበር የገለፀው፡፡ ይህንን የይልማን ገለፃ የሰሙ አንዳንድ አርቲስቶች ግን የይልማ አባባል የዛሬ ዘጠኝ ዓመት በ1998 ዓ.ም ኤፍሬም ታምሩ ካወጣው ‹ኋላ እንዳይቆጭሽ› አልበም ጋር በተያያዘ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር የማይሄድ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በወቅቱ ኤፍሬም ታምሩ አዲሱን አልበም ለማውጣት የግጥምና ዜማ ስራዎችን ሲመርጥ እንደቀድሞ ብዙዎቹን የይልማ ገ/አብ ስራዎች አልመረጠም ነበር፡፡ ኤፍ
ሬም ካሴት ማውጣት ከጀመረበት ከ1974 ዓ.ም ጀምሮ በየካሴቶቹ ላይ አብዛኛዎቹን ግጥሞቹን የሰራለትና ለኤፍሬም እውቅናም መሠረት ከሆኑት ሰዎች መሀከል አንዱ የሆነው ይልማ በዚህ አልበም ላይ የተመረጠለት ግጥም አራት ብቻ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን ኤፍሬም ከይልማ ግጥሞች መሀከል የወሰደውን ‹ሰው ነው መሠረቱ› በተሰኘው ግጥም ሃሳብ በመመሰጡ በሲዲው ላይ በልዩ ሁኔታ ጠቅሶ ነበር በስራው እርካታ እንዳለው የፃፈው፡፡ ኤፍሬም የተለያዩ የግጥምና ዜማ ደራሲያን ስራዎችን መርጦ ካቀነቀነና ቅንብሩ ካለቀ በኋላ ፖስተር ታትሞ አልበሙ የሚወጣበት ቀን ተቆረጠ፡፡ ሚያዝያ 1998 ዓ.ም፡፡ ለዚሁ ስራ አሳታሚና አከፋፋዩ ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ሁሌም እንደሚያደርገው የኤፍሬም ካሴት አልበም በወጣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከገበያ ላይ የመጥፋት ልምድ ስላለ ይህንን ችግር ለመቅረፍ በአንድ ጊዜ በርከት አድርጎ በማሳተም እጥረቱን ለመቀነስ ደፋ ቀና በሚባልበት ሰዓት አልበሙ እንዳይወጣ የሚያደርግ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
በአልበሙ ላይ አራት ዘፈን ብቻ በተመረጠለት በይልማ በኩል ይፋም ባይወጣ ‹ለምን› የሚል ጥያቄ መፈጠሩ አልቀረም ነበርና ቀደም ሲልም ‹ሰላም ልበለው አይንሽ› ከሚለው
አልበም ጀምሮ በ1988 እና በ1992 ዓ.ም ኤፍሬም ታምሩ ባወጣቸው አልበሞች ላይ ለሰራቸው ዘፈኖች የተከፈለው ክፍያ በአሜሪካ የታተመውንና የተሰራጨውን የሲዲ ክፍያ የማይጨምር ነበር፡፡ በመሆኑም ይህ አዲሱ አልበም ሊወጣና ሊሰራጭ የሚችለው የቀድሞዎቹ ስራዎቼ ክፍያ አንድ ላይ ከተከፈለኝ ብቻ ነው የሚል አቋም ያዘ ይልማ፡ ፡ ለዚሁም ብር ሁለት መቶ ሺ ጠየቀ፡፡ ጥያቄው የቀረበለት ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ጉዳዩን ወደ ኤፍሬም ታምሩ እንደመራው ጉዳዩን በቅርብ የሚያውቁ የቁም ነገር መፅሄት
ምንጮች ይናገራሉ፡፡ ኤፍሬም ለማውጣት የተዘጋጀበትን አልበም የግጥምና ዜማ ስራ የመረጠውና ያስቀረፀው አሜሪካ ሆኖ በመሆኑ ከይልማ ጋር በግጥም ስራው ዋጋ ላይ አልተነጋገረም ነበር፡፡ በመሆኑም አልበሙ አልቆ ተባዝቶ ለገበያ ሊቀርብ አፋፍ በደረሰበት ወቅትይልማየሁለትመቶሺብር የክፍያ ጥያቄ ማንሳቱ በኤፍሬም በኩል አልተዋጠለትም፡፡
ያም ሆኖ ኤፍሬም ማስታወቂያ ተነግሮ፤ ፖስተር ተለጥፎ፤ አድማጭ ከዛሬ ነገ ይወጣል እያለ የሚጠብቀው አዲሱ አልበሙ ላይ የተጋረጠውን የ ‹አይወጣም› ክልከላ ላይ አንድ ነገር ማድረግ ነበረበት፡፡ ያም ሆኖ ግን ‹ክፍያው ካልተፈፀመልኝ ግጥሜ በአልበሙ ውስጥ እንዳይካተት› የሚለውን ውሳኔ ለማስቀየር ከይልማ ጋር ተደራድሮ ከስምምነት ላይ መድረስ ኤፍሬም ‹ አልፈለገም› ይላሉ ምንጮች፡፡ ኤፍሬም የይልማ ሀሳብ ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት እንደደረሰው ያሰበው ነገር ቢኖር የይልማን ግጥም በሌላ ግጥም በመቀየር በዛው ዜማ መስራት ነበር፡፡የዚህ አይነት ፍላጎት እንዳለው በመግለፅም በአልበሙ ላይ ሌሎች የዘፈን ግጥሞችን ከፃፉለት ገጣሚያን መሀከል ሃብታሙ ቦጋለን በማስጠራት አዲስ ግጥም እንዲፅፍለት ለማድረግ ውሳኔ ላይ እንደደረሰ ይገልፃል፡፡ ሁኔታውን በቅርበት ይከታተሉ የነበሩ አርቲስቶች የኤፍሬምን ውሳኔ ለይልማ እንዲደርስ በማድረግ ጉዳዩን በሽምግልና ለመጨረስ በመሃል ይገባሉ፡፡ ጥረቱ ከቀናት በኋላ ተሳክቶ ይልማ ለዘፈኑ የሃያ ሺ ብር ክፍያውን ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ተቀብሎ ‹ኋላ እንዳይቆጭሽ› የተሰኘው አልበሙ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ ‹በወቅቱ የዚህ አይነት ውሳኔ ላይ የደረስኩት የገንዘብ ሰው አለመሆኔን ለማሳየት እንጂ የገንዘብ ጉዳይ ቢሆን ኖሮ የአራት አልበም የሲዲ ሽያጭ ዋጋ ሳይከፈለኝ ሥራዎቹ ለአድማጭ ሳይደርሱ እንዲቀሩ ማድረግ እችል ነበር› ይላል ይልማ ያንን ወቅት በማስታወሰ፡፡
አዲሱ አልበም
ኤፍሬም ታምሩ እንደ ሌሎቹ አንጋፋ ድምፃውያን በርካታ ተወዳጅ ዜማዎችን ያቀነቀነ ድምፃዊ ይሁን እንጂ እንደ ሌሎቹ አርቲስቶች የጥንት ዘፈኖቹን በሲዲ አሰባስቦ አላሳተምም፡፡ በተለይም ከ1974 ዓ›ም እስከ 1988 ዓ.ም ድረስ የተጫወታቸው ዘፈኖች መሀከል የብዙዎችን ትዝታ የያዙት ዘፈኖቹ በካሴት ብቻ ያሉ በመሆናቸው ብዙዎች በሲዲ ተቀርፀው እንዲቀርቡ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ ኤፍሬም የጥንት ስራዎቹን ከመስራት ይልቅ አዳዲስ ዘፈኖችን በመስራት ላይ አተኩሮ በመቆየቱና የጥንት ስራዎቹን ችላ ማለቱ እንደ ሳሚ በየነ ላሉ መንታፊዎች ሊያጋልጠው እንደሚችል የጠረጠረ አይመስልም፡፡ በወዳጅ ዘመድ ጉትጎታ የድሮ ዘፈኖቹን በአዲስ መልክ መስራት የጀመረው ኤፍሬም አራት ዓመት ያህል የወሰደበት ሲሆን ዘንድሮ አልቆ ለህዝብ ለማድረስ ዝግጅቱ ተጠናቆ ነበር፡፡ ከሰራቸው ስራዎች መሀከል ›‹የድንገት እንግዳ› የተሰኘውን ነጠላ ዜማ ከተለቀቀ በኋላ ድጋሚ አልበሙ ለህዝብ ሊደርስ የሚችልበት ሂደት ላይ ችግር መፈጠሩ ተሰማ፡፡
ይልማ ገ/አብ በአዲስ መልክ ኤፍሬም ከሰራቸው 13 ዘፈኖች መሀከል አስሩ የይልማ ግጥሞች ናቸው፡፡ኤፍሬም በአጠቃላይ ከሰራቸው 130 ያህል ዘፈኖች መሀከል ምርጡን ሰብስቦ እንደገና ለመስራት ሲነሳ አስር ያህሉን ዘፈኖች የይልማ ስራዎችን ማድረጉ የይልማ ግጥሞች ምን ያህል በኤፍሬም ስራዎች ውስጥ ገዢ መሆናቸውን ያሳያል፡፡ ያም ሆኖ ኤፍሬም የድሮ ስራዎቹን ድጋሚ የመስራት ሀሳብ እንዳለው እንጂ የእሱን ስራዎች መርጦ ማቀንቀኑን ይልማ እንደማያውቅና ስራው ከተሰራ በኋላ እንደተነገረው ያስታውሳል፡ ፡ በመሆኑም ይልማ ቀደም ሲልም ያልተከፈለው የውጪ ሀገር የሲዲ ሽያጭ ክፍያ ዋጋ መኖሩን ከግምት በማስገባት አሁን ለመውጣት ከተዘጋጀው ሲዲላይለአንድዘፈንግጥም25ሺህብር በድምሩ 250 ሺህ ብር እንዲከፈለው ይጠይቃል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን አልበሙ እንዳይወጣ ማስጠንቀቂያ ለኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት መስጠቱን ምንጮች ገልፀዋል፡፡
ኤፍሬም ከሰራቸው 13 ዘፈኖች መሀከል ቀሪዎቹ ሁለቱ የፀጋዬ ደቦጭ ድርሰት ሲሆኑ አንድ ደግሞ በህይወት የሌለው የተስፋዬ ለሜሳ ድርሰት ነው፡፡ፀጋዬ ግን ከወራት በፊት ለሁለቱ ዘፈኖች ግጥም በድምሩ 14 ሺህ ብር ከኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት መውሰዱን ምንጮች አመልክተዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ አንዳንድ ወገኖች የይልማ ገ/አብን ውሳኔ ተገቢና በወቅቱ የቀረበ ሲሉ ሌሎች አስቀድሞ ባልተስማማበት ሁኔታ ስራው አልቆ ለህዝብ ሊደርስ ሲል የዚህ አይነት እንቅፋት መፍጠር ተገቢ አለመሆኑን ይተቻሉ፡፡
ኤፍሬም በዚህ አልበም ከፍተኛ ክፍያ የሚያገኝበት ስለመሆኑ አያከራክርም፡፡ ቀደም ሲል እነ ይልማ እነዚህን ስራዎች ለካሴት ብቻ በሚል ሲሰሩ የተከፈላቸው ክፍያ ከአንድ ሺህ ብር እስከ ሶስት ሺህ ብር ብቻ ነበር፡፡ ኤፍሬምም በወቅቱ እነዚህን ስራዎች ሲሰራ ክፍያው ያን ያህል የተጋነነ አለመሆኑና ከአስር አስከ ሃያ ሺህ ብር ካሴቱን ይሸጥ እንደነበር ይነገራል፡፡
ከዛሬ ሃያና ሃያ አምስት ዓመታት በፊት የተሰሩት እነዚህ ተወዳጅ ስራዎችን በድጋሚ ኤፍሬም ሲሰራቸው ከፍያው ከ10 እጥፍ በላይ ስለመሄዱ ይነገራል፡፡ ኤፍሬም ይህንን የድሮ
ዘፈኖቹን በድጋሚ ሰርቶ ለማውጣት ከኤሌለክትራ ሙዚቃ ቤት ጋር አደረገ የተባለው ስምምንት በቃል የተደረገ ቢሆንም ኤፍሬም ሙሉ የባንዱን ወጪ ችሎ ዘፈኖቹን መርጦ ሰርቶ ማስተሩን ለማስረከብ ሲሆን ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ማስተሩን ሲረከብ ለግጥምና ዜማ ባለሙዎች ተገቢ የተባለውን ክፍያ እንዲከፍል ነበር፡፡ በዚሁ መሰረት ኤፍሬም ሙሉ የባንዱን ወጪ ችሎ ስራውን አጠናቆ ሲረከብ ለድምፁ ብር 800 ሺህ ብር ክፍያ እንደሚያገኝና ከሽያጩ ላይም የፕርሰንት ክፍያ እንዲያገኝ ለማድረግ ታስቦ ነበር ተብሏል ፡፡ እንደዛም ሆኖ ኤፍሬም የውጪ ሀገር የሲዲ ሽያጭ ገቢውን ለብቻው ያገኛል፡፡ ግን ይህ ስምምነት ወደ ወረቀት ተቀይሮ ውል ሳይፈረም ኤፍሬም አልበሙን ጨርሶ ማምጣቱ ነው የተገለፀው፡፡
አሁን አልበሙ ሊወጣና አድማጭ ዘንድ ሊደርስ የሚችለው ይልማ ያቀረበውን የገንዘብ መጠን በኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ወይም በኤፍሬም በኩል የሚሸፈን ከሆነ ብቻ ይሆናል፡፡ ያን ለማድረግ ደግሞ ለኤሌክትራ በኩል አስቸጋሪ ነው፡፡ የህትመት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ባለበትና የኮፒ ካሴቶች ሽያጭ ባልቆመበት ሁኔታ ይህን ያህል ወጪ ለአንድ ዘፈን መክፈል አዋጭነቱ አጠራጣሪ እንደሆነ ነው ስራውን የሚያውቁ የሙዚቃ ባለሙያዎች የሚናገሩት፡፡ በሌላ በኩል ይልማ አሁን ያቀረበውን ክፍያ መክፈል ቢቻል እንኳ ሌሎቹም ባለሙያዎች ተመሳሳይ የክፍያ ጥያቄ ማንሳታቸው ስለማይቀር በማናቸውም መልኩ የአልበሙን ወጪ ያንረዋል፡፡
ከኤፍሬም ታምሩ የድሮ ዘፈኖች በስተጀርባ የነበሩና ተወዳጅ ግጥምና ዜማዎችን ሲሰሩለት የነበሩት ይልማ ገ/አብና አበበ መለሰ የሙያቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልነበሩ ግልፅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ዓመታት በኩላሊት ህመም ሳቢያ ታሞ የነበረው አበበ መለሰ አስቀድሞ በስራዎቹ ጥሪቱን ለመያዝ ባለመቻሉ እጁን ለእርዳታ ለመዘርጋት መገደዱ ይታወሳል፡፡ በወቅቱም ለአበበ መለሰ ክብር ሲባል የተለያዩ ድምፃውያን የተሳተፉበት የሙዚቃ ኮንሰርት ሲዘጋጅ ኤፍሬም ታምሩ የኮንሰርቱ ተሳታፊ አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን አለኝታነቱን አለማሳየቱ በብዙዎች ዘንድ ግርምትን የፈጠረ ጉዳይ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ኤፍሬም ግን በእነዛ ዘፈኖች በየኮንሰርቱና በውጪ ሀገር በሚዘጋጁ የሙዚቃ ዝግጅቶች ላይ በመቅረብ ከፍተኛ ከሚባሉት የኮንሰርት ተከፋዮች መሀከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ አንዳንድ የሙዚቃ ባለሙያዎች እነ ይልማ በሙያቸው ተገቢውን ክፍያ ማግኘት ያለባቸው ሰዓት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ፡፡ ከስራዎቻቸው መሀከል በሲዲ ያልወጡትን ለብቻ መርጠው ከሚሰሩ ድምፃውያን ጋር በልዩ ድርድር የተሻለ ክፍያ በማግኘት ምናልባትም የመጀመሪያ ስራውን ሰርተው ሲሰጡ ያልተከፈላቸውን ክፍያ ሊያገኙ ይችላሉ ይላሉ፡፡
የትርፍና ኪሳራ ስሌት ኤፍሬም ታምሩ የአሁኑን የይልማ ገ/አብን የክፍያ ጥያቄ መነሻ በማድረግ እንደ ከዚህ ቀደሙ ግጥሙን በሌላ ገጣሚ ለመተካት የሚችልበት ዕድል ያለ አይመስልም፡፡ በመሆኑም ከይልማ ጋር ተደራድሮ ችግሩን መፍታት እስካልቻለ ጊዜ ድረስ አልበሙ ህዝብ ጆሮ የመድረስ ዕድሉ ጠባብ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይም ላለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከአንድ ነጠላ ዜማ በቀር /ከጎሳዬ ጋር የተሰራው ባላገሩ/ በቀር ከህዝብ ርቆ ለከረመው ኤፍሬም ይህንን አልበም በማናቸውም መልኩ ለአድማጭ ሳያደርስ መቅረት ሁኔታውን አስቸጋ ሪ ያደርግበታል፡ ፡ኤፍሬም አዲስ አልበም ለመስራት የጀመረ ቢሆንም አሁን ባለው ሁኔታ አዲስ አልበም ከሁለትና ከሶስት ዓመታት በፊት ለማውጣት ከባድ በመሆኑ ሁኔታው ለኤፍሬም ታምሩ አጣብቂኝ መሆኑን የሙዚቃ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የኤፍሬም አልበም በቀድሞ የሮሃ ባንድ አባላት በሀገር ቤት ተገናኝተው የሰሩት ሲሆን ከቀድሞው የባንዱ አባል ሰላም ስዩም ብቻ በሀገር ውስጥ ባለመኖሩ የተቀረፀው ድምፅ ተልኮለት በአሜሪካ ሀገር ለብቻው ሊድ ጊታሩን እንደተጫወተና በጥራት እንደተቀረፀ ታውቋል፡፡ የኤፍሬም አዲስ አልበም ከ70ሺ ኮፒ በላይ ይታተማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ህጉ ምን ይላል?
‹‹የሥነ ጽሑፍ የኪነጥበብ እና ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች የአንድ ሀገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን በማፋጠን ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው፤ የሚበረታቱበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፤ የሥነ ፅሁፍ የኪነጥበብና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ስራዎች ላይ ተዛማጅ መብቶችን በህግ እውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ የኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀጽ 55/01 መሰረት የሚከተለው ታውጇል፡፡ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዐዋጅ አንድ የሙዚቃ ስራ ተሰርቶ ታትሞ ለአድማጭ ሲቀርብ የፈጠራ ስራ ባለቤቶቹ እነማን እንደሆኑ የሚያከራክርበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ክርክሩ የሚመነጨው የፈጠራ ስራው አብዛኛውን ጊዜ በድምፃውያኑ ስም ሲጠራ ስለሚሰማ ነው፡፡ በሀገራችን ፀድቆ ስራ ላይ ያለው የቅጂና የተዛማጅ መብቶች አዋጅ ግን የአንድ የሙዚቃ ስራ የፈጠራ ባለሙያዎች እነማን እንደሆኑና የጥቅም ተጋሪነታቸውም እስከምን ድረስ እንደሚሆን በግልፅ ደንግጓል፡፡ በአዋጁ መሠረት የአንድ ዘፈን ዋና ባለመብቶች የግጥምና ዜማ ደራሲያኑና ሙዚቃውን ያቀናበረው ባለሙያ ነው፡፡ድምፃውያኑና አሳታሚው ወይም ፕሮውዲሰውሰሩ የተዛማጅ መብት ተጋሪ መሆናቸውን ህጉ በግልፅ አስቀምጦታል፡፡
ቴሌቪዥን ጣቢያዎቹ እንዲሁም ከየሆቴሎቹና ከህዝብ ማመላለሻ አውቶብሶችና ባቡሮች ላይ ያገኛሉ፡፡ እነሱ ቢያልፉ እንኳ ወራሾቻቸው ክፍያውን ይቀበላሉ፡፡
የሌሎች ሀገሮች ልምድ
የኪነጥበብ ባለሙያዎችን የፈጠራ ሥራ መዝግቦ በመያዝ ለሙያተኞች ተገቢ የሆነ ክፍያ በማበጀት በር ከፋች ተደርጋ የምትወስደው አሜሪካ ነች፡፡ በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ጀምሮ እያደገ የመጣውን የፖፑላር ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ፈር ለማስያዝ የተለያዩ ህጎችን በማውጣት ትታወቃለች፡፡ በአሜሪካ የመጀመሪያ የፌዴራል መንግስት የኮፒራይት copy right Act of 1790 የተባለው የረቀቀና የፀደቀው እ.ኤ.አ በ1790 ነው፡፡
ከዚህ ጊዜ በኋላም በአሜሪካ ጃዝ ሙዚቃ ራሱን ከቤተክርስቲያን መዝሙር በመለየት የተሻለ ተደማጭ መሆን ችሏል፡፡ የአሜሪካ የኮፒራይት ህግ በየጊዜው እየተቀያየሩ ከሚወጡት የቴክኖሎጂ ውጤቶች አንፃር የመብት ጥበቃ እየተሻሻለ የሄደ ሲሆን በዋናነት የኮፒራይትና ሮያሊቲ ክፍያው የሚመለከታቸው ወገኖች በግልጽ ተለይተው የተቀመጡበት ነው፡፡
የሙዚቃ ደራሲያን ሮያሊቲ ማንኛውም የሙዚቃ ስራ ከተቀረፀ በኋላ ለአድማጭ በመድረክ ሲቀርብ ወይም በመገናኛ ብዙሃን አማካይነት ሲሰራጭ ክፍያ ለባለቤቶቹ ይከፈላል፤ በዚህ ረገድ ዘፈኑን በተለያየ መልኩ የሚጠቀሙ ወገኖች ይኖራሉ፡፡ የመጀመሪዎቹ ዘፈኑን መድረክ ላይ ደግመው የሚጫወቱ ሲሆኑ የመድረክ ክፍያ (performing right) መክፈል ይጠበቅባቸዋል- በተጫወቱት ቁጥር፡፡
ለዚሁም ተብሎ ከመድረክ ላይ የሚጫወቱ ሰዎችንና ኮንሰርት የሚያዘጋጁ ድርጅቶችን የሚቆጣጠር የመድረክ ክወና ማህበር (the performing Right Society) የሚባል ማህበር አላቸው፡፡ ማህበሩ ከየኮንሰርቶቹ ላይ ለሚቀርቡ ዘፈኖች ፈቃድ በመስጠት፤ ለቀረበው ዘፈን ክፍያ በመሰብሰብ ለሚመለከታቸው ባለቤቶች ክፍያ ይፈፅማል፡፡ ማህበሩ በዋናነት ከሚከታተላቸው የመድረክ ስራ ማቅረቢያ ቦታዎች መካከል የሙዚቃ አዳራሾች፣ የምሽት ክለቦች፣ ሲኒማ ቤቶች፣ ስታዲየሞች ማንኛውም የመድረክ ሥራ የሚቀርብባቸውን ቦታዎች ይከታተላሉ፡፡
የሬዲዮና የቴሌቪዢን ጣቢያዎችም በቀጥታ የሙዚቃ ስርጭት በሚያቀርቡበት ወቅት ለማህበሩ የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ ማህበሩ አስቀድመው የኮንሰርቱ አዘጋጆች ለመጫወት ፈቃድ የጠየቀባቸውን ሙዚቃ ዝርዝር መሰረት ማቅረባቸውን ከሬዲዮ ወይም ከቴሌቪዢን ላይ በመቅዳት ይከታተላቸዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፊልምና የቪዲዮ ካምፓኒዎችም ዘፈኖችን በፊልማቸው ውስጥ መጠቀም ከፈለጉ ከማህበሩ ፈቃድ የማግኘት ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ በፊልም ውስጥ የሙዚቃ ሥራን የማቅረብ መብት የጥምረት መብት (Synchronisation right) ተብሎ ይታወቃል፡፡’
ሁለተኛው የመብት አይነት የቀረፃ መብትን (Mechanical right) ይባላል፡፡ ምንግዜም ሙዚቃ ተደማጭ ሊሆን የሚችለው በቀረፃ ባለሙያዎች አማካይነት ተገቢውን ጥራት ጠብቆ ሲቀርብ በመሆኑ ይህንኑ ሥራ በሚሰሩና በማብዛት ሙያ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች የሚሰበሰብ ክፍያ አለ፡፡ ይህንን ክፍያ የሚሰበስበው ደግሞ የቀረፃ መብት ጥበቃ ማህበር (The Mechanical Copy right Protection Socity) ነው፡፡
ይህ ማህበር አንድን ወጥ የሙዚቃ ስራ በተለያዩ መንገዶች በማብዛት ለህብረተሰቡ ከሚያደርሱ ድርጅቶች ላይ ተሰብስቦ ለአሳታሚዎች የሚከፋፈል ነው፡፡ ይህ የፈጠራ ስራዎችም የመጠቀም መብት ተግባራዊ ለማድረግ የቴክኖሎጂው በየጊዜው መቀያየር አፈፃፀሙን አስቸጋሪና ውስብስብ አድርጎታል፡፡ በተለይም የሶፍትዌሮች መበራከትና ለቁጥጥር እጅግ አስቸጋሪ ሆነው መውጣት ጋር በተያያዘ ብዙ የአውሮፓ ሀገራት የአርቲስቶቻቸው ዘፈኖች መብት ለማስጠበቅ እየተቸገሩ እንደሆነ ይታያል፡፡
በተለያዩ ድረገፆች ላይ ሙዚቃዎችን የሚሞሉና ለአድማጭ ኮፒ እንዲያደርገው ሁሉ የሚፈቅድ የኢንተርኔት መረቦች የቁጥጥር ስራውን ፈታኝ አድርጎታል፡፡ እንግሊዝ ከዛሬ 10 ዓመት በፊት ከድረ ገፆች ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶችን ለመቆጣጠር European copyright Directive የተሰኘ ማንዋል ያፀደቀች ቢሆንም አሁንም ድረስ በተለይ በእጅ ስልኮች ላይ የተለያዩ ሙዚቃዎችን ከማባዛት ማቆም አልተቻለም፡ ፡ ይሄ የቴክኖሎጂ ውስብስብነት በአፍሪካምለቁጥጥር አስቸጋሪ መሆኑ እየታየ ነው፡፡
The post የኤፍሬም ታምሩ አልበምና ውዝግቡ – ያልተሰሙ አንዳንድ አዳዲስ መረጃዎች appeared first on Zehabesha Amharic.