Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

አባቱን እንደናፈቀ ሳያገኘው ያለፈው ሰማዕት (ዳንኤል ሐዱሽ) “በዐይኔ አይቼ በጆሮዬም ሰምቼ ከሥፍራው በመገኘት ጻፍኩላችሁ”

$
0
0

ዘመድኩን በቀለ

ቅድስቲቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ከተማ ፣ ጥንታዊቷ የታላቋ ሐገር ኢትዮጵያችን የቀድሞ ዘመን ዋና መናገሻ ከተማ ፣ የታቦተ ጽዮን የዘለዓለም ማረፊያ ፣ የስልጣኔአችን ምንጭ ፣ የሥነ ዜማ ፣ የሥነ ፊደል ፣ የሥነ ጥበብ ፣ የሥነ ሕንፃ መገኛ ፣ የሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መፍለቂያ ዋነኛዋ ምንጭ በዘመነ ኦሪትም ኋላም በዘመነ ሐዲስ የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ማዕከል ወደ ሆነችው አክሱም ጽዮን ከተማ በትናንትናው ዕለት በሰላም መግባቴን ፣ በዚያም እንደደረስኩ እኔ ባልጠበኩት ሆኔታ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ካህሳይ እና አማካሪያቸው አቶ ሐጎስ አውሮፕላን ጣቢያ ድረስ በመምጣት ተቀብለውኝ ፣ የማረፊያ ሆቴልንና የምግብ አገልግሎትም ጭምር እንዲሰጠኝ አድርገውልኝ እንደነበር ነግሬያችሁ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ ይዘን የተለያየነው ።
የዛሬ ውሎዬን ደግሞ እነሆ ብያለሁ ።

hadush

hadush daniel
እንደ እኔ ሐሳብ ዛሬ ከአክሱም ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኘው ኢንቲጮ ከተማ በትራንስፖርት በመሄድ ከዚያም ጾረና ግንባር ወደሚገኘው ሰማዕት ቤትም ከዚያው ከኢንቲጮ ከተማ ትራንስፖርት ይዤ ለመሄድ ነበር እቅዴ ። እኔ እንዳሰብኩት መች ሆነና ብላችሁ እኔ ያላሰብኩት ሆነ እንጂ ።

የአክሱሙ ሲደንቀኝ የኢንቲጮው ከንቲባ አቶ ሰሎሞን በጠዋት መኪና እንደሚልኩልኝ ነግረውኝ ስለነበር በቃላቸው መሰረት ሾፌር ከነ መኪናው በጠዋት ልከውልኝ ረጅም ቀናት ይፈጅብኝ የነበረውን ጉዞዬን በአንድ ቀን እንዳጠናቅቅ ረድተውኛልና እባካችሁ ጓደኞቼ በሰማዕታቱ ስም አመስግኑልኝ ።

አሁን ሹፌሬ ክብሮም ቶዮታ ፒካፕ መኪናውን ይዞ ከአክሱም ወደ ምስራቅ አቅጣጫ በሚወስደው መንገድ ወደ ኢንቲጮ ከተማ ይዞኝ እየተጓዘ ነው ። በመንገዳችን ላይም ኢትዮጵያ ሃገራችን ነጻ ሆና እንድትኖር እነሱ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው የህይወት ዋጋ ከፍለው ነፃነት አግኝተን እንድንኖር ያደረጉበትን የአድዋን የጦርነት ሥፍራና እኒያን ሰማይ ጠቀስ የአደዋ ተራሮች እያየሁ ሥለ ቀደሙት ሰማዕታት እያሰብኩ በእኔ ዘመን ደግሞ አንገታቸውን ከነ ማዕተባቸው በመስጠት ለኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ እምነታቸው ያላቸውን ታማኝነት ወደገለፁት ብርቅዬ የዘመኑ ሰማዕታት ወንድሞቻችን ወላጆች ቤት ጉዞዬን ቀጥያለሁ ።

በኢንቲጮ ከተማ መግቢያ ላይ ቆመው ይጠብቁኝ የነበሩትን የከቲማዋን ከንቲባ ክቡር አቶ ሰሎሞንን በመያዝ ወደ ሰማዕቱ ዳንኤል ሐዱሽ ቤት አመራን ።
በቤቷ ውስጥ ቀድሞ እኔ እንደምመጣ ታላቅ ወንድሙ ያውቅ ነበርና ጥቂት እንግዶችም ተገኝተው ነበር ። የእመቤታችን ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ ፣ የአቡነ አረጋዊ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪና የወረዳዋ ሰባኬ ወንጌልም በቦታው ነበሩ ።

የሰማዕቱ እናት ወሮ ዛፉ ገብረየሱስ ሐጎስም በሚያሳዝን ሁኔታ ከሁለት እናቶች መሐል ኩርምት ብለው ተቀምጠዋል ። ጥቂት አረፍ እንዳልን እናት ማልቀስ በመጀመራቸው ታላቅ ልጃቸው አቶ ጌታቸውም ፣ እንግዶቹም መገሰፅ መጀመራቸው እኔ ጥቂት ለመናገር በር ስለከፈተልኝ የሰማዕትነትን ጥቅም ፣ ልጃቸው ከቀደሙት ሰማዕታት ከነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስና ፣ ቅዱስ ቂርቆስ ጋር ያለውን ክብር በመጠኑ በመግለጽ ከእንግዲህ ማልቀስስ ለእኛ ነው እንጂ ፣ በምን እንደምንሞት ለማናውቀው ምስኪኖች ፤ በማለት ጥቂት ካጽናናሁ በኋላ ስለ ሰማዕቱ ዳንኤል ሐዱሽ እንዲነግሩኝ አግባባሁዋቸው ። እናት አማርኛ መስማት እንጂ ብዙም መናገር ባለመቻላቸው ልጃቸው ጌታቸው ሐዱሽ ስለ ሰማዕቱ ዳንኤል የነገረኝን እነሆ እናንተም ስሙት ብዬ በእንዲህ አይነት መልኩ አቅርቤላችኋለሁ እና ተከታተሉት ።

ጥቅምት 7 1982 ዓም ከምሽቱ ሦስት ሰአት ሲሆን የዛሬው ሰማዕት ዳንኤል ሐዱሽ አስመራ ከተማ እዳጋ አርቢ በተባለ ስፍራ ነው የተወለደው ። በ40ኛው ቀኑ ህዳር 12 ቀን በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት መሠረት እዚያው አስመራ ከተማ እንዳ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ውስጥ ስርዓተ ጥምቀትን በመፈጸም የክርስትና ስሙም ተስፋ ሚካኤል ተባለ ።

ይህ ኦርቶዶክሳዊ ህጻን ብዙም ሳይቆይ የመንግሥት ለወጥ በኤርትራ በመከሰቱ እንዳሊቁ በመባል ከሚታወቁ አባት ዘንድ የጀመረውን የቄስ ትምህርት በማቋረጥ በ1985 ዓም ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ይውጡ ሲባል ከቤተሰቦቹ ጋር ወደ ኢንትጮ ተመለሰ ።

የዳንኤል አባት ግን እንዴት በእድሜዬ ሁሉ የለፋሁበትን ሃብትና ንብረት እንዲሁ ከሜዳ ላይ በትኜው እቀራለሁ በማለት ተመልሰው ብቻቸውን ወደ አስመራ ያቀናሉ ። በዚያም በንብረታቸው ላይ ይገባኛል የሚል አካል ተነስቶባቸው ስለነበር በአስመራ ፍርድቤት እንደዋዛ የጀመሩት ክርክር መቋጫ በማጣቱ ከአስመራ ሳይወጡ የኢትዮ— ኤርትራው ጦርነት በመጀመሩ ይባስ ብለው ከቤተሰባቸው ተቆራርጠው ቀሩ ።

ዳንኤል ግን ምንም አባቱ ከአጠገቡ ባይኖሩም ከ1ኛ ክፍል እስከ 12ኛ ክፍል በዚሁ ባደገባት ኢንቲጮ በእናቱ አጋዥነት ተምሮ ባመጣው ከፍተኛ ነጥብ ወደ ጅማ ዩኒቨርስቲ በማምራት 4 ዓመት ሙሉ በትጋት ትምህርቱን በመከታተል በ2006 ዓም በኮምፒዩተር ሳይንስ ተመርቆ ትምህርቱን አጠናቅቋል ።

ዳንኤል ተመርቆ ሥራ ያለማግኘቱ ቢያስከፋውም እሱ ግን እንዲሁ ዝም ብሎም አልተቀመጠም ። መሆኒ ከተማ የምትገኘው እህቱ ዘንድም በመሄድ የእህቱ ባል እንዲያው ከፍ ወዳለ ሥራ እስክትሸጋገር ፎቶ ቤትም ቢሆን ልክፈትልህ ብሎትም እንደነበር ወንድሙ ጌታቸው ይናገራል ።

በመሃል ላይ ጆርጅ ከተባለ ስትሬት A ያመጣ ጎበዝ ተማሪ ጓደኛው ጋር ጠበቅ ያለ ጓደኝነት ከመመስረታቸውም በላይ መቐለ ላይ በማኅበር ተደራጅተው ሥራ ሊጀምሩ እንደሆነ እና ለዚህም እያንዳንዳቸው ከ10 ሺህ እስከ 12 ሺህ ብር እንደሚያስፈልጋቸው በመወሰኑ ለእርሱም ሠርቶ የሚከፍለው ብር እንዲያበድረው ታላቅ ወንድሙን ጌታቸውን ያግባባውና ያሳምነዋል ።

ለመጀመሪያ ጊዜ 2ሺህ ብር ይቀበለውና ወደ መቐለ ያመራል ። መቐለ እንደገባም ቀሪውን 10ሺ ብር ይልክለታል ። በቃ እፎይ ሥራ ጀመረ ብሎ ቤተሰቡም ተረጋግቶ ሳለ በመሃል ዳንኤል ሁመራ ነው ያለሁት ሥራው ሰፋ እያለ ስለመጣ ተጨማሪ 5 ሺህ ብር ያስፈልገኛል ብሎ ወንድሙን ይጠይቀውና ብሩን ወንድሙ ይልክለታል ።

በመሃል የዳንኤል ስልክ ዝም ጭጭ ይላል ። 2 ሳምንት ሙሉ በኔትወርክም እየተሳበበ ትንሽ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ድንገት ለጌታቸው ይደውልና ሱዳን ካርቱም መግባቱን ፣ ለእናቱ እንዳይነግር ፣ እሱም በቅርቡ አውሮፓ በመግባት የተበደረውን ገንዘብ ጭምር እጥፍ አድርጎ እንደሚከፍለው በመንገር በሰላም ካሰበበት እንዲገባ ጭምር እንዲጸልይለት ለወንድሙ በመንገር ተሰነባበቱ ። ወንድሙ ጌታቸው ምንም በሁኔታው ቢያዝንም ምንም ማድረግ የማይችለው ነገር በመሆኑ ዝም ከማለት ውጪ ምንም አማራጭ ስለሌለው ደንግጦ ይቀራል ።
ከቤት እናት ወሮ ዛፉ ገብረየሱስ ደግሞ ይህን ሁሉ የታላቅና የታናሽን ምስጢር ባይሰሙም ውስጣቸው እየተረበሸ ተቸግረዋል ። “ልጄ ምነው ድምፁ ጠፋ ” መቐለ ሆኖ ነው እንዲህ የጠፋው? ብለው ይጠይቃሉ እውነታውን የሚነግራቸው የለም እንጂ ። የእናት አንጀት አይደል የሚባል ። ወደ ኋላ ላይማ በግልፅ ” ህልም አይቻለሁ ። ልጄ ታስሯል ። አደጋም ደርሶበታል እያሉ ቢናገሩም ማን አድምጧቸው ።

በመጨረሻም የዳንኤል የመጨረሻ ወንድሙ ሃኒ ኢንተርኔት ሲጎረጉር የወንድሙን የግፍ አገዳደል አይቶ ደነገጠ ። ለማን እንደሚነግር ቢጨንቀው ወንድሙ ጌታቸውን በመጥራት ዳንኤል ታርዷል ብሎ ምስሉን ያሳየዋል ። ከዚያ በኋላ የሆነውን ጌታቸው ማስታወስ አይፈልግም ። እስካሁን ድረስ ምነው ያን ገንዘብ ባልሰጠሁት እያለ ይንገበገባል ። የእናቱን ፊት እንኳን በሙሉ አይኑ ለማየት አይደፍርም ። ጥቁር ልብሱን እንኳን ዛሬ ነው እንዲያወልቅ በካህናቱ አስመክሬ እሺ ያሰኘሁት።

ምናልባት ተሳስቼ ወይም ተመሳስሎብኝ እንደሆነ ብሎ ደብረዘይት በኢንጅነሪንግ ተመርቆ በማስተማር ላይ ወዳለው ታናሽ ወንድሙ ጋር ቢደውል ወንድሙ ጣዕመ ሐዱሽ ለካ ቀድሞ በኢንተርኔት አይቶ ኑሮ ትኬት እንደቆረጠና በበነጋው እንደሚመጣ ፣ እናታቸውንም እንደሚያረዱ ተነጋግረው በማግሥቱ እናት በህልማቸው ያዩትን የልጃቸውን አደጋ በገሐድ አረጋገጡላቸው ።

አባት አቶ ሐዱሽ ገብረ ኪዳን አሁንም አስመራ ናቸው በቅርብ ርቀት ድንበር የሚሉት ጣጣ አይሻገሩት ነገር ችግር ሆኖባቸው የወለዱትን ልጅ አድጎ ዩኒቨርስቲ ገብቶ ተመርቆ እስኪወጣ እንደናፈቃቸው ዓይኑን ለማየት እንደጓጉ በሊብያ በረሃ በጨካኞች እጅ ወድቆ ሰማዕትነትን ተቀበለ ። ባለፈው ዓመት ጅማ ዩኒቨርስቲ ዳንኤል ሲመረቅ በባህርም በየብስም ብዬ እንደምንም ብዬ መጥቼ የልጄ የምርቃት ፕሮግራሙ ላይ እገኛለሁ ቢሉም አልተቻለም ።

ልጅ ዳንኤል ከኢትዮጵያ አባቴን እንዳለ ፣ አቶ ሐዱሽም ከአስመራ ልጄ እንዳሉ ፣ ላይገናኙ እንደተነፋፈቁ ተላለፉ አባትና ልጅ ። ወይ ነዶ አለ ያገሬ ሰው ።
አቶ ሐዱሽ እንደምንም ብለው አሁን መውጫ ቀዳዳ አግኝተው ከኤርትራ ምድር ወጥተው ጎረቤት ሐገር ገብተዋል ። እግዚአብሔር ካለ ሰሞኑን ኢትዮጵያ ይገባሉ ። ዳንኤልን በሕይወት ባያገኙትም ቀሪ ዘመናቸውን ከተቀሩት ልጆቻቸው ጋር ለማሳለፍ ሃገራቸው ለመግባት ቀናት እየቆጠሩ ይገኛሉ ።

ዳንኤል በክርስትና ህይወቱ የተመሰከረለት ፣ ለሃይማኖቱ እጅግ ልዩ ቅንአት ያለው ልጅ እንደነበረ አሁን በሕይወት የሚገኙት ጓደኞቹ ጭምር ይናገራሉ ። ISIS እጅ ከወደቀበት ጊዜ ጀምሮ በረሃብና በጥም ጭምር ብዙ የተሰቃዩ ቢሆንም እንኳ ከፊቱ ላይ ወዙ እንዳለ እንደነበር ሁላችን ያየነው ነው ። አንገቱን ከአካሉ ቆርጠው ወገቡ ላይ አስቀምጠውት እንኳ የተቆረጠው ፊቱ ላይ ፈገግታና ወዙ እንዳለ ነበር የሚታየው ።

ዳንኤል ሐዱሽ ማዕተቡን ከአንገቱ ሳይበጥስ ከነማዕተቡ አንገቱን የሰጠ ጀግና ሰማዕት ነው ። ቁም ነገር የላችሁም ለምንባል ለእኛ ፣ አዬ የ8ተኛው ሺህ ልጆች ለምንባል ለእኛ ኩራት የሆነን ። ቀና ብለን እንድንሄድ ያደረገን ምርጥና ብርቅዬ የተዋህዶ ልጅ ፣ የ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመንም ሰማዕት ነው ።

በ ስዊዘርላንድ የሚገኙት የኢትዮ ዙሪክ የእግር ኳስ ቡድን አባላት የላኩትን 8520 ብር አቶ አምሀ ከአሜሪካን እነ ህይወትም እንዲሁ ከአሜሪካን ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሐገረ ስብከት ሊቀጳጳስ በሀገረ ስብከታቸው ከሚገኘው የካናዳ ቫንኮቨር ሆህተ ሰማይ ቅድስት ማርያም ምእመናን ልጆቻቸው ተቀብለው እንዳደርስ የሰጡኝን 4100 ብር በአጠቃላይ 25177. 95 ብር በኢንቲጮ ከተማ አስተዳሩ በአቶ ሰሎሞን እጅ አስረክቤላችኋለሁ ። ለሰጣችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ይስጣችሁ ።

የሰማዕቱ ዳንኤል እናት ያቀረቡልኝን ነጭ ወተት የመሰለ ማር በአንባሻ ከተቀበልኩ በኋላ ክቡር ከንቲባው በረሃው ሳይበረታባችሁ በጊዜ ወደ ጾረና ግንባር ወደሚገኘው ሰማዕቱ ተስፎም ታረቀኝ በስመ ጥምቀቱ ተስፋማርያም ቤተሰቦች ዘንድ እንድንሄድ መኪናዋን ከነ ሹፌሩ ስለፈቀዱልኝ ከአባቶች ቡራኬ ተቀብዬ የሰማዕቱ ዳንኤል ወንድም ጌታቸውም አብሬህ ነው የምሄድ ብሎኝ ጉዞ ወደ ገርሁ ስርናይ አድርጌያለሁ ።

ኦ አምላኬ ምን አይነት ምስቅልቅሉ የወጣና የሚያሳዝን ቤተሰብ በዚያ እንደገጠመኝ ሰሞኑን አወጋችኋለሁ ። በትእግስት ጠብቁኝ ።

አሁን ከሌሊቱ 5 ሰዓት ሆኗል ። ነገ ሰንበት ስለሆነ አክሱም ጽዮን የማስቀደስ እድሉን አግኝቻለሁ ። በረራዬ ከምሽቱ 11 ሰዓት ላይ መሆኑ አክሱም እቆያለሁ ።
የሰማዕቱን ዳንኤል ሐዱሽን ቤተሰቦች ለመርዳት የምትፈልጉ በእናትየው ስም በተከፈተው የባንክ አካውንት ካላችሁበት ሆናችሁ አስገቡላቸው ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አኒቲጮ ቅርንጫፍ
የባንክ ሂሳብ ቁጥር
Z 21 S 010007346
ሞባይል +251917872705 አቶ ጌታቸው ሐዱሽ ብላችሁ ደውላችሁ አጽናኗቸው ።

ይህን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ ሼር ቢያደርጉት ከበረከቱ መካፈል ለሚፈልግ ሰው እድል እንደመስጠት ይቆጠራልና ላልሰማ ሼር በማድረግ እናሰማ ።
ማንኛውንም አስተያየታችሁን እቀበላለሁ ። በዚህ ዙሪያ ለምትጠይቁኝ ሁሉ መልስ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ ። የእጅ ስልኬ +251 911608054 ነው ።

ከሁሉ የማንስ እኔ አክባሪ ወንድማችሁ
ዘመድኩን በቀለ ነኝ
ግንቦት 29/9/2007 ዓም
አክሱም — ኢትዮጵያ

The post አባቱን እንደናፈቀ ሳያገኘው ያለፈው ሰማዕት (ዳንኤል ሐዱሽ) “በዐይኔ አይቼ በጆሮዬም ሰምቼ ከሥፍራው በመገኘት ጻፍኩላችሁ” appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>