Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ለዚህ ሕዝብ መሰ-ዋት ይገባል – (ሔኖክ የሺጥላ)

$
0
0

እማዬ ለዚህ ሕዝብ መሰ-ዋት አይገባውም ትለኝ ነበር ! ( ያቺ የኔ እማዬ ካረፈች ቆየች ፣ ቀብሯ ደብረ ሊባኖስ ገዳም እንደነበር ዜና ዕረፍቷን ሲያረዱኝ ነግረውኛል ፣ አዎ ያቺ እማዬ ፣ በአይበሉባዋ ቂጣ ጠፍጥፋ ፣ በቅቤ እና በበርበሬ ቀብታ ትመግበኝ የነበረችው እማዬ ፣ ያቺ በፋሲካ እኩለ ሌሊት ፌጦ በእንጀራ አረስርሳ የጠዋቱ ዶሮ እንደ አባይ ግድብ በቦንድ እንጂ በዶሮነት አልወርድም እንዳይለኝ ወይም በፋሲካ ጾምና በሰፈራችን አቧራ ሉዓላዊ እና አንጀታዊ ቅባቱን ነጥፎ የከረመው ሆዴ ፣ ከዱለት ጋ በሚያደርገው ግብግብ ተረቶ በሸርተቴ እና በምግብ ፍንቀላ ዕለተ ፋሲካውን እንዳያሳልፍ ብእር ባልያዙ ፣ በፍቅር በተያዙ እጆቿ ትመግበኝ የነበረችው እማዬማ ከሞተች ሁለት ዓመት አለፋት ፣ የኢትዮጵያን ትንሣዔ እንደተመኘች !! አይ እማዬ ስላንቺ ሳስብ እንዴት ልቤን ሃዘን እንደሚያከው ፣ እንዴት ሁሌም በለቅሶና በእልህ መሃል እንደምናጥ ባየሽ !
ታዲያ አንዳንዴ ይገርመኛል ፣ እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ይሄን ሕዝብ ተነስ ሲሉ ! አንዳንዴ ግራ ይገባኛል እነ ሊቀ-ሊቃውንት ( ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ ) ለዚህ ሕዝብ ሲሉ መስዋት እንደሆኑ ሳስብ ፣ አንዳንዴ እጅግ በጣም ይገርመኛል እነ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድህንም እነ ሌንጮ ለታም ሁለቱም በአንዲት ኢትዮጵያ በተባለች ሀገር ላይ መፈጠራቸውን ሳስብ ። እንደው ረጋ ብላችሁ ካሰባችሁት እኮ ፣ ይሄ ሕዝብ ተራበ ፣ ተጠማ ፣ ተቸገረ ብሎ መጮህ እብደት አይመስላችሁም በእማዬ ሞት ?! አንዳንዴ የሰማያዊ ፓርቲ ልፋት ፣ የእስክንድር መከራ ፣ አንዷለም ላይ የሚደርሰው ግፍ ” ዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ፣ ወዘተ ወዘተርፈ ፣ ይሄ ሁሉ መከራን እና ስቃይን የሚቀበሉት ፣ ለምን ሲባል ይሆን ” ብዬ ራሴን እጠይቀዋለሁ ።
nega berehanu
ድሮ ድሮ ሰርግ ላይ ይዘፈን የነበረ ዘፈን ( እርግጠኛ አይደለሁም አሁንም ድረስ ይዘፈን ከሆነ ) የዚህን ሕዝብ ሁኔታ ( ስነ ልቦናዊ ቁምጥና እና አቀማመጥ ለማለት ነው ) የሚያሳይ ይመስለኛል ። እየበሉ እየጠጡ ዝም ! አዎ እያሳሰሩ ፣ እያስገደሉ ዝም ፣ ከተባለ የዚህ ሕዝብ ሁነኛ መገለጫ ነው !

እንደው በማዬ ሞት ለዚህ ሕዝብ መሰ-ዋ ይገባል ? ይሄ ሕዝብ እኮ አይደለም በ- አደባባይ ፣ በፌስ ቡክ ላይ የተጻፈ ፣ በልቡ የሚያምንበትን እውነተኛ ሃሳብ ፣ በኮምፒዩተር ስር ፣ ከቤቱ ቁጭ ብሎ ፣ ጋቢ ለብሶ ፣ ቡና እየጠጣ ፣ ቆሎ እየቆረጠመ ላይክ ( like ) የሚለውን ዶቃ መጫን የሚፈራ ሕዝብ ነው ፣ ” ፈርቼ ነው ጽሁፍህን ላይክ ያላደረኩት በርታ !”የሚል መልክት በሚስጥር ሳጥን የሚልክ ሕዝብ እኮ ነው ። በእማዬ ሞት አፉን ሞልቶ ” በርታ !” ሲል ምንም አይቀፈውም ! ። እባክህ አን-ፍሬንድ ( ኢ-ጏደኛ ) አድርገኝ ተሳስቼ ነው ጏደኛ ያረኩህ ፣ እኔ የልጆች አባት ነኝ ብሎ አፉን ሞልቶ የሚያወራ ሕዝብ እኮ ነው ። የልጆች እበት ማለቱ ይሆን አላለሁ ! ( ሳቁ እንጂ !)። ይሄ ሕዝብ እኮ የዶሮ ዘንቢል የሚመስል ቤት ውስጥ እየኖረ ፣ ፒያሳ ከዘመኑ ሰዎች ወርቅ ቤቶች ጋ እንድ ግድግዳ ተጋርቶ እያደረ ፣ ራበኝ የሚል ሕዝብ እኮ ነው ፣ እሱ ያመጣውን እሱ እስኪመልሰው ምን ይደረጋል ብሎ የሚኖር ሕዝብ እኮ ነው ። እንዴ! ይሄ ሕዝብ እኮ አማሪካን እየኖረ በኢትዮጵያ መንግስት ሕግ የሚተዳደር ነው ፣ ለሚያምንበት ነገር ሰልፍ ለመውጣት መፈክር ሳይሆን ጥቁር መነጽር ለመግዛት ከሰልፉ ቀደም ብሎ ሞል ( የገባያ አዳራሽ ) የሚሄድ ሕዝብ እኮ ነው ፣ ይሄ ሕዝብ እኮ መለስ ሲሞት ያለቀሰ ሕዝብ ነው (ገንዘብ ተከፍሎት ፣ ገለመኔ ፣ ገለመኔ ፣ ምንም ይሁን ምክንያቱ !) ፣ ይሄ ሕዝብ እኮ ከፌዴራል ፖሊስ ዱላ ለማምለጥ ፣ በኢትዮጵያ ከነገሰው ቸነፈር ለመሸሽ ፣ ወደ ቦንብ ቀጠናዋ የመን የሚተም ነው ፣ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያን ነቅለህ አሜሪካ ላይ ብትተክልለት ይሄ ሕዝብ ከአማሪካም ይሸሻል ። ሽሽቱ ከማንነቱ ይሁን ፣ ከፍርሃቱ ምንም አይገባኝም ። ታዲያ በእማዬ ሞት ይሄ ሕዝብ አሁን መስዋትነት ይገባዋል ።

እንዴ! ይሄ ሕዝብ እኮ መብቱን በአደባባይ በሳቅ እና በስላቅ ሲቀሙት ፣ ቦርሳውን እንደጣለ ሰው መሬት መሬት እያየ እኮ ነው ወደ ቤቱ የገባው ! ይሄ ሕዝብ እኮ ዘንድሮን ለማምለጥ ስለ ትናንትና የሚያወራ ነው ( አኖሌ አንዱ ምሳሌ ነው !)። ሌላ ብዙ ምሳሌዎች መጥቀስ እንችላለን ።

ይሄ ሕዝብ እኮ ከራሱ በላይ ፍርሃቱን የሚያምን ነው ። እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ” የምርጫ ካርድህን ቀደህ ጣል !” ሲሉት ደሞ ለመቅደድ ! ብሎ ራሱን በአደባባይ ቀዶ የጣለ ሕዝብ እኮ ነው ! ለዚህ ሕዝብ በትግል ፣ በነጻነት እና በሰይጣን መሃከል ያለው ልዩነት ፣ ሰይጣን ከገነት ሲባረር ነጻነት ግን ከኢትዮጵያ መባሩሩ ነው እንጂ ሁሉም ለሱ አንድ ነው ! ወገኖቼ ይሄ ሕዝብ እኮ ሽምብራ ዱቤ በቆርቂ አሰፍሮ ገዝቶ እየበላ፣ አድገሃል ሲሉት ፣ የጠዋት ጥላውን የሚያይ አይነት ቀበሮ ነው ። ከትግስት እና ፍርሃት ዛይት ቢጨመቅ ፣ ምናልባት ኢትዮጵያ ባለም አንደኛ የቅባት እህል አምራች ትሆን ነበር ። 90 ማንምን ሚሊዮን ቅባታም ! ይገርማል ወፍ እንኳ ሲርባት ትናከሳለች ! ውሃው የደረቀበት ወንዝ እኮ ፣ ቀየሜታውን በመገልማት ይገልጻል ፣ አረ ሬሳ እንኳ ይሸታል ! እንዴ ! መሚ ( የሬሳ ማድረቂያ ) ተቀብተን ነው እንዴ ቁመን የምንሄደው ?
ገንዳ ላይ ከውሻ ጋ ስጋ ተጋፍቶ የሚበላ ፣ ደሞ በዛ ላይ ፈሪሃ እግዚያብሄር ያለኝ ምናምን ይልሃል። እንዴት አይነት የምነት ሰው ነው ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሆነውን እያየ ዛሬም ስለ ” ግራህን ሲመቱ ቀኝህን ስጣቸው የሚሰብከው ?” ምን አይነት እውነት ነው “። የንጹሃን ሞትን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውጭ ( ያም ለስርዓቱ የሚስማማ ጥቅስ ) ፣ ሌላ ሊገልጥበት የሚችልበት ስሜት በሰብአዊ ማንነቱ ላይ አምላክ ያልፈጠረበት ቅዱስ አውሬ ማለት ይሄ “ሕዝብ” ነው!

ለዚህ ሕዝብ እንኳን ሕይወቴን እንቅልፌን አልሰዋም ነበር ያለው እንዳለ ጌታ ! ምርጥ ጸሐፊ !

አይ እማዬ ” ልጄ አትቃጠል ይሄ ሕዝብ በልጅነትህ የነገርኩህ ሕዝብ አይደለም እኔም ተሳስቼ አሳስቼህ ነው !” ነው ያልሽኝ አንድ ቀን ! አይ እማዬ !

The post ለዚህ ሕዝብ መሰ-ዋት ይገባል – (ሔኖክ የሺጥላ) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>