–ግድያውን ፈጽሟል የተባለው ተጠርጣሪ እጁን ሰጥቷል
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመቀሌ ዲስትሪክት የማይፀብሪ ቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ፣ ስድስት የባንኩ ሠራተኞች ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በባንኩ የጥበቃ ሠራተኛ በጥይት ተገደሉ፡፡
ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. የተለመደ ሥራቸውን በማከናወን ላይ እያሉ፣ በባንኩ የጥበቃ ሠራተኛ በጥይት ተደብድበው የሞቱት የቅርንጫፉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ወልዳይ ገብሩ፣ የባንኩ ኮንትሮለር አቶ አትንኩት ደምሴና የደንበኞች አገልግሎት ኦፊሰሮች የነበሩት ወ/ሮ ለምለም ግደይና አቶ አስማማው ገብረ ማርያም መሆናቸውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮሙዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ንጉሤ ግርማና አቶ ጌትነት ባዩ የተባሉ በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካይነት የተቀጠሩ የባንኩ ሠራተኞችም መገደላቸውን አቶ ኤፍሬም አክለዋል፡፡
የባንኩ ሠራተኞችን በመግደል የተጠረጠረው የጥበቃ ሠራተኛ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ሆኖ፣ ግድያውን ሊፈጽም የቻለበት ምክንያት እየተጣራ መሆኑን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ግድያውን የፈጸመው ግለሰብ የሥራ አፈጻጸሙን በሚመለከት ምክር፣ ተግሳጽና ማስጠንቀቂያ ከተሰጠው ከደቂቃዎች በኋላ መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጥበቃና የፅዳት ሠራተኞችን የመቅጠርና የመቆጣጠር ሥራን ለኮሜርሻል ኖሚኒስ መስጠቱን የጠቆሙት አቶ ኤፍሬም፣ የባንኩን ሠራተኞች በመግደል የተጠረጠረው ግለሰብም የተቀጠረው ከዚያው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ተጠርጣሪው በሥራው ላይ ተገቢ ያልሆነ ባህሪያትን በማሳየቱ በባንኩ ኃላፊዎች ቢመከርም ሊስተካከል ባለመቻሉ፣ የቅርንጫፍ ዋና ሥራ አስኪያጁ መቐለ ለሚገኘው የኮሜርሻል ኖሚኒስ ጽሕፈት ቤት ደብዳቤ በመጻፍ፣ የጥበቃ ሠራተኛውን በሌላ እንዲተካላቸው ጠይቀው እንደነበር ገልጸዋል፡፡
የኮሜርሻል ኖሚኒስ ኃላፊዎች በሠራተኞቻቸው ላይ ቅሬታ ሲደርሳቸው በቦታው በመገኘትና ሠራተኞቹንና የተቋሙን ኃላፊዎች በማነጋገር፣ ሠራተኛው ተገስጾና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ሥራውን እንዲቀጥል ወይም እንዲባረር እንደሚያደርጉ የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ተጠርጣሪውም በዕለቱ ተመክሮ፣ ተገስጾና ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በዕለቱ ተረኛ ስለነበር መሣሪያውን ይዞ ወደ ሥራው መሰማራቱን ተናግረዋል፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ ግን ሁለት የፍተሻ ሠራተኞችን አቁስሎ ሌሎቹን መግደሉን አስረድተዋል፡፡
የተገደሉት የባንኩ ሠራተኞች የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈጸሙን ያስታወቁት አቶ ኤፍሬም፣ ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ወልዳይ ገብሩ ቤተሰቦቻቸው በሚኖሩበት በዓደዋ ልዩ ስሙ ወርኢ ዳጋብር ቀብራቸው እንደተፈጸመም አክለዋል፡፡ ኮንትሮለሩ አቶ አትንኩት ደምሴ በትውልድ ሥፍራቸው ባህር ዳር የቀብራቸው ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡ ወ/ሮ ለምለም ግደይና የኮሜርሻል ኖሚኒስ ሁለቱ ሠራተኞች አቶ ንጉሤና አቶ ጌትነት፣ በዚያው በማይፀብሪ ቀብራቸው ሲፈጸም፣ አቶ አስማማው ከማይፀብሪ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ዲማ በሚባለው አካባቢ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
ባንኩ በሠራተኞቹ ላይ በደረሰው ያልታሰበና ድንገተኛ አደጋ ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማው የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ ሠራተኞቹ መገደላቸው ከተሰማበት ግንቦት 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ቀብራቸው እስከተፈጸመበት ዕለት ድረስ፣ የመቀሌ ዲስትሪክት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሻግሬ አስመላሽ በሥፍራው ተገኝተው ያደረጉት አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ የንግድ ባንክ ጠቅላላ የጥበቃዎች ሥራ አስኪያጅም እዚያው ሆነው ጉዳዩን እየተከታተሉ መሆኑን አቶ ኤፍሬም አስታውቀዋል፡፡
Source:: Ethiopian Reporter
The post የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስድስት ሠራተኞች በጥይት ተገደሉ appeared first on Zehabesha Amharic.