በሐዋርያዊት፣ ጥንታዊት እና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና እና ዕድገት ፊት ከተጋረጡትና አፋጣኝ እልባት ከሚሹት የዘመናችን የውስጥ ችግሮች እና የውጭ ተግዳሮቶች ውስጥ ሙስና እና ኑፋቄ ቀዳሚዎቹ ናቸው፡፡ አንዱ የሌላው መተላለፊያ፣ መንሥኤ እና ውጤት እየኾኑ ለቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ለውጥ የተደረጉ ጥረቶችን ሲያመክኑ፤ የመዋቅር እና የአደረጃጀት አቅሟን ሲያዳክሙ ቆይተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት የሚያዝያ ፳፯ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. መግለጫ እንደተመለከተው፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ተወግዘው ከተለዩ በኋላ በቅጥር ወደ አስተዳደራዊ እና የአገልግሎት መዋቅሯ የገቡ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን መኖራቸው ሙስና እና ኑፋቄ የተሳሰሩ እና የሚመጋገቡ ለመኾናቸው ግልጽ አስረጅ ነው፡፡
ከግንቦት ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. በጠቅላይ ቤተ ክህነት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ሲካሔድ ቆይቶ ለጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ አርዕድ አንቀጥቅጥ በኾኑ፤ መልካም አስተዳደር እና ፍትሐዊ ፍርድ በሚጠይቁ መዝሙሮች ትላንት ማምሻውን የተጠናቀቀው ፬ኛው ዓመታዊ ሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በጋራ አቋም መግለጫዎቹ በቀጥታ ይኹን በአማራጭ ያረጋገጠውም ይህንኑ እውነታ ነው፡፡
* * *
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ እና የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ እና የወላይታ ኮንታ እና ዳውሮ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ የበላይ ሓላፊ ሊቀ ጳጳስ፣ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፓትርያርኩ እንደራሴ ሊቀ ጳጳስ፣ የጉራጌ ስልጤ ከምባታ እና ሐዲያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት
የጠቅላይ ቤተ ክህነት የመምሪያ ሓላፊዎች
ከተለያዩ አካላት ጥሪ የተደረገላችኹ የክብር እንግዶች፤
እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤያትን ወክለን በ፬ኛው የሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አጠቃላይ ጉባኤ ላይ የተሳተፍን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ አባላት ከግንቦት ፳፩ – ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ላለፉት ሦስት ቀናት÷ የማደራጃ መምሪያው ዓመታዊ የአገልግሎት ዘገባ፤ ከ37 አህጉረ ስብከት የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት እና የሰንበት ት/ቤቶች ዋና ክፍሎች ሪፖርቶች፤ የሰንበት ት/ቤቶች አባላት በኾኑ ባለሞያዎች በቀረቡ ጥናታዊ ጽሑፎች ላይ ሰፊ ውይይት አድርገናል፡፡
በመምሪያው ዘገባም ኾነ ከ37 አህጉረ ስብከት የመጡ ተወካዮች ያቀረቡት ሪፖርት ሰንበት ት/ቤቶች እጅግ በርካታ ተግባራት እያከናወኑና የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማፋጠን እየተጉ መኾኑን አስገንዝቧል፡፡ ኾኖም ግን በየአህጉረ ስብከቱ የሚታዩ፡-
- የመናፍቃን እና የአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ተጽዕኖ፤
- በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እየደረሱ ያሉ የአስተዳደር በደሎች፤
- የበጀት እና የመምህራን እጥረት፣ የአዳራሽ እጥረት፤
- የአንዳንድ አህጉረ ስብከት ስፋት ለትራንስፖርት አመቺ አለመኾን፤
አገልግሎቱን እየተገዳደሩ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች ኾነው ተዘግበዋል፡፡
‹‹የሰው ኃይል አያያዝ በሰንበት ት/ቤት›› በሚለው ጥናታዊ ጽሑፍ መነሻነት በተደረገው ውይይትም ለቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ዕድገት ወሳኝ የኾነው የሰው ኃይል መኾኑን በማመን የቤተ ክርስቲያን አካላት በሙሉ በተለይም ሰንበት ት/ቤቶች ትኩረት ሰጥተን ልንሠራበት እንደሚገባ ተገንዝበናል፡፡ በማያያዝም ‹‹የኢኮኖሚ ግንባታ ለቤተ ክርስቲያን›› በሚለውም ጥናት፣ የኢኮኖሚ አቅም ማነስ÷ የመጠቀምን፣ የመደመጥን፣ የመወሰንን፣ የመተግበርን አቅም ያሳጣል፤ በሌላ በኩል እምነትን ይፈትናል፤ ሥጋዊውን ጥቅም ለማሳካት ሲባል ከቤተ ክርስቲያን መለየትን ያመጣል፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ምሏት ያለውን የእግዚአብሔር ቃል ያስጥሳል፤ ወጣቱንም ለስደት እና ለመከራ እየዳረገ ይገኛል፤ የቤተ ክርስቲያን ተልእኮም እንዳይፋጠን ያደርጋል፡፡
ስለዚኽ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም ኢኮኖሚያዊ አቅሟን ልታጠናክር፤ ተሰሚነቷን ልታስከበር ይገባታል፤ ሰንበት ት/ቤቶችም የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራት ሊሠሩ፤ የቤተ ክርስቲያን መምሪያዎችም ሊያግዟቸው እንደሚገባ ውይይቱ ትኩረት ሰጥቶበታል፡፡
በመጨረሻም በሪፖርቱም ኾነ በጥናታዊ ጽሑፎች የተጠቀሱትን ዋና ዋና ችግሮች በመለየት በተደረገ የቡድን ውይይት ሰንበት ት/ቤት በቀጣይነት በጋራ የምንሠራቸውን እና የምንስማማባቸውን የአቋም መግለጫዎች አውጥተናል፡፡
- የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ከ2006 – 2010 ዓ.ም. የታቀደውን የአምስት ዓመት መሪ ዕቅድ በቀሩት ጊዜያት ለመፈጸም እና ለማስፈጸም ቃል እንገባለን፤
- የሰንበት ት/ቤቶች አጠቃላይ መሪ ዕቅድ የኹሉም የአጥቢያ ሰበካ መንፈሳውን ጉባኤያት ዕቅድ አካል እንዲኾን እና የጠቅላይ ቤተ ክህነት መምሪያዎችም ኹሉ መሪ ዕቅዱን ከዕቅዳቸው ጋራ በማገናዘብ እንዲያካትቱ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤
- መልክአ ምድርን መሠረት ያደረገ የሰንበት ት/ቤቶች ትስስር በማጠናከር ሰንበት ት/ቤቶች ባልተቋቋሙባቸው አጥቢያዎች እንዲቋቋሙ፣ በተቋቋሙባቸው ደግሞ የተጠናከረ አገልግሎት እንዲሰጥባቸው ለማድረግ እንሠራለን፤
- የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ ችግሮችን ለማጋለጥ ያስችል ዘንድ ከሀገር አቀፍ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጀምሮ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት ት/ቤት የሚደርስ መረጃ የማሰባሰብ ሥርዐት በመዘርጋት የመረጃ ማሰባሰቡን አጠናክረን እንሠራለን፤
- በአኹኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ተልእኮ አፈጻጸም ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረ ያለው የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃንን እንቅሰቃሴ ለማስቆም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አፋጣኝ ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፤
- ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ስለ ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ መናፍቃን የቀረበው ማስረጃ ውሳኔ እንዲሰጠው፤ ውሳኔውም ተግባራዊ ይኾን ዘንድ ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ ያሉ የቤተ ክርስቲያን አካላት አስፈላጊውን ርምጃ እንዲወስዱ እንጠይቃለን፤
- በአኹኑ ጊዜ አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ሓላፊዎች በሰንበት ት/ቤት ወጣቶች እና አባላት ላይ በተሳሳተ አመክንዮ እያደረሱት ያለው እስር፣ እንግልት እና ወከባ እንዲቆምልን በአጽንዖት እንጠይቃለን፤
- ከዚኽ ጋር ተያይዞ የመንግሥት የፍትሕ አካላትም ከአጥፊዎች ጋር በመተባበር የሰንበት ት/ቤት አባላትን ከማሰር እና ከማንገላታት እንዲታቀቡ ይደረግ ዘንድ እንጠይቃለን፤
- በቃለ ዐዋዲው እና በ1986 ዓ.ም. ሕገ ደንቡ ላይ የተጠቀሰው የሰንበት ት/ቤቶች የዕድሜ ገደብ እንዲነሣልን በድጋሜ እንጠይቃለን፤
- ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ አንሥቶ እስከ አጥቢያ ሰንበት ት/ቤቶች የሚደርስ የፋይናንስ ትስስር እና አያያዝ ሥርዐት በመምሪያው በኩል ተጠንቶ እንዲጸድቅልን እንጠይቃለን፤
- የቤተ ክርስቲያንን ሀብት እና ንብረት ለግል ጥቅማቸው በማዋል የቤተ ክርስቲያንን አቅም የሚያዳክሙ አማሳኞች ማስረጃ ተጠናቅሮ በአገሪቱ ሕግ መሠረት እንዲጠየቁልን እንጠይቃለን፤
- የቤተ ክርስቲያን የፋይናንስ አሠራር ማእከላዊ እንዲኾን እና በባለሞያዎች የሚታገዝ የክትትል እና የቁጥጥር ሥርዐት እንዲኖረው እንጠይቃለን፤
- በዘመናችን ሚዲያ በወጣቱ እና በሕፃናት አስተዳደግ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠረ ስለሚገኝ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ በስፋት ለምእመናን ለማዳረስ እንዲቻል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚመራ እና የሚተዳደር፤ ቤተ ክርስቲያኒቷንም የሚወክል የቴሌቪዥን መርሐ ግብር እንዲጀመር በአጽንዖት እንጠይቃለን፤
- በአኹኑ ሰዓት በቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያንን የማይወክል ትምህርት እና መልእክት የሚያስተላልፉ የቴሌቪዥን መርሐ ግብሮች በተቻለ ፍጥነት እንዲዘጉ አልያም በቤተ ክርስቲያን ስም ከመጠራት እና ከመጠቀም እንዲከለከሉ እንጠይቃለን፤
- ለጠቅላላ ጉባኤው ተወካዮቻቸውን ያልላኩ አህጉረ ስብከት ተለይተው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የማያዳግም ርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን፤
- በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እና ልማታዊ ጉዳዮች ከአባቶቻችን ጋር በመኾን ያለንን አቅም አሟጠን በመጠቀም ለቤተ ክርስቲያን ዕድገት እና ልዕልና የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን፤
- የቤተ ክርስቲያናችንን ኹለንተናዊ ችግር ለመፍታት ከመንፈሳዊ ኰሌጅ ምሩቃን(ቴዎሎጅያን) ጋር ተባብረን የምንሠራ መኾናችንን እንገልጻለን፤
- የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ያቀረበው ጥያቄ የኹላችንም አቋም ስለኾነ አፋጣኝ መልስ እንዲሰጠው እንጠይቃለን፡፡
ግንቦት ፳፫ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.
Source:: haratewahido
The post ፬ኛው የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የጋራ አቋም መግለጫ appeared first on Zehabesha Amharic.