Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

መነሻውን ከህውሃት ጉያ ውስጥ ያደረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ መፅሃፍና አነጋጋሪው ክህደት

$
0
0

በሰሜን አሜሪካና በተቀረው ዓለም የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ህብረትethiopian airforce

የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል በሃሰት ውንጀላ በጅምላ ወደ ህውሃት ማጐሪያ እንዲጋዝ ከተደረገና በኋላም በጨፍጫፊነት ተፈርጆ በአዋጅ ከስራ ውጪ እንዲሆን የፈረደበትን ግንቦት 1983 ዓ/ምን እሳቤ በማድረግ ከምስረታው እስከ አሳዛኝ ብተናው ድረስ የነበረውን ታሪክ በመፅሃፍ መልክ ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረት አስርተ ዓመታትን አስቆጥሯል።

በቅብብሎሽ አንዱ በፃፈው ላይ ሌላኛውም እያከለ የተቋሙን ታሪክ ወደ ሙሉዕነት ለመቀየር ከፍተኛ ድካም ተደክሞበታል ። መፅሃፉን አንድ ሰው ያሳተመው ይምሰል እንጂ ባለቤትነቱ በህብረት ነው ።

ከእዚህ ወደ እዚያ ሲንከባለል የቆየው የመፅሃፍ ዝግጅት መነሻ አየር ኃይሉ በደረሰበት ዕጣ ፈንታ በእጅጉ በመቆጨት –

1. የአገር አንድነትን ለማስከበር የተሰዋበትን
2. በአኩሪ ታጋድሎውም በህዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አክብሮት የተቸረበትን ፣
3. በአሳዛኝ መልኩ ስመጥር ታሪኩን በሬት በመለወስ በትውልድ እንደ ጨፍጫፊና ወንጀለኛ እንዲቆጠር የተደረገበት ሁኔታ ሌት ተቀን እንቅልፍ የነሳቸው የሰራዊቱ አዛውንት አባላት ተሰባስበውና ተማክረው እውነተኛውን ገፅታ ለማቅረብ ጊዜአቸውንና ሃብታቸውን መስዋዕት አድርገዋል ።

ይህንን በጐ ዓላማ ይዞ የተነሳው የታሪክ መፅሃፍ ታትሞ አደባባይ ከመውጣቱና በዚያ ታላቅ የሃገር ሃብት የሆነ የመከላከያ ተቋም ላይ የተወሰደው ፖለቲካዊ ብያኔ የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ስሜትና ቀልብ እንደሚስብ ፣ ሃላፊነት የጐደለውም ፍርደ ገምድላዊ ብያኔ ምን ያክል አገር የማፍረሱ አካል መሆኑን ቁልጭ አድርጐ በማሳየት በስልጣን ላይ ያለውን ዘረኛ ስርዓት ከማሳጣቱ በፊት ፖለቲካዊ ማድበስበስ ተደርጐ ለዳግም ክህደት ተዳርጓል ።

የተቃውሞው መነሻ –

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሙሉዕ ታሪክ ተፅፎ ለትውልድ ቢተላለፍ የሚጠላ አንድም ኢትዮጵያዊ እንደማይኖር ሁሉ ታሪኩ ጐዶሎና በፖለቲካዊ ደባ የተንሸዋረረ እንዲሆን ሲፈረድበት ዝም ብሎ መመልከት ደግሞ ለአገራቸው መስዋዕት የሆኑ ዛሬ ግን እራሳቸውን ሊከላከሉ የማይችሉትን ሰማዕታትንም አገርንም መክዳት ነው ።
የአየር ኃይል ታሪክ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ዘመነ መንግስት መመስረቱ ብቻ ሳይሆን በዘመነ ህውሃት/ኢህአደግ ዘመን በውርደት መፍረሱን ፣ በአባላቱም ላይ የደረሰው ወደር የለሽ ሰቆቃና እንግልት ፣ እስርና ረሃብን የማይገልፅ የታሪክ መፅሃፍ ሙሉዕነቱ የተጓደለ ብቻ ሳይሆን እውነትን ፈፅሞ ለመጋፈጥ የሸሸ አሳዛኝ አድርባይነት ይሆናል ።

የአየር ኃይሉን አመሰራረትና የስልጠና ታሪክ ማሳየት ብቻ ሳይሆን አኩሪ ታሪክ የፈፀሙ ጀግኖች እኩሌታው በአሳዛኝ ሁኔታ ከአገር እንዲሰደዱ ተደርጐ ፣ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነው ደግሞ በፍርደ ገምድልነት የሞትና የእድሜ ይፍታህ ፍርደኛ ሆነው በመካከላችን ቆመው በሉበት ሁኔታ ፤ ከሁሉም በላይ ድሃዋ ኢትዮጵያ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የደከመችበትንና የሃገር ሃብት የፈሰሰበትን ፣ ሃላፊነት በጐደለው ስርዓት ገደል እንዲገባ የተደረገበትን እንዳላየና እንዳልሰማ በዳሰሳ ብቻ ማለፍ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው ።

ለመሆኑ በወንጀለኝነትና በጨፍጫፊነት ተወንጅሎ ለነጋሪ እንዳይተርፍ ሆኖ በጅምላ ታስሮ ፣ በሞትና በእድሜ ልክ እስረኝነት ፍርድ የተፈረደበት የአየር ኃይል ታሪክ መነሻውን ከህውሃት ቤተመንግስት እንዴት አደረገ ?

እንዲህ የሚከበርና ለአገርም አለኝታ እንደነበረ የሚተረክለት አየር ኃይል ስለምንስ ዛሬ ድረስ በጅምላ ወንጀለኛ የሚለውን ስም እንዲሸከም ተደረገ ? እንዴትስ አባላቱ የሞትና የእድሜ ልክ ፍርደኛ ሆነው ሊቀሩ ቻሉ ? በምንስ መመዘኛ አየር ኃይሉ በጅምላ ይህንን ያክል ፍዳና መከራ ሲሸከምና ሲከፍል ከዳር ሆነው የተመለከቱት የህውሃት/ኢህአዴግ ባለስልጣናት መፅሃፉ ሲመረቅ በክብር እንግድነት ተስተናገዱ ? ጥቂት ከዘረኛው ስርዓት ጋር የደም ትስስርና ዝምድ ካላቸው የቀድሞው ሰራዊት አባላት በስተቀረ ብዙሃኑ ተወንጃይ የአየር ኃይል አባላትስ የታሉ ? እንዴትስ የዚህ የተወነጀለው አየር ኃይል አባላትና የቀድሞው ስርዓት ጀነራል መኰንኖች የቤተ መንግስት ደጃፍ ያለከልካይ ክፍት ሆነላቸው ?

እነዚህን የመሳሰሉትን ሁሉ ያላገናዘበና ምላሽ ያልሰጠ ፣ ይልቁንም ዘረኛው ስርዓት በጐ እንደሚሰራ ለማስመሰል የሚደርግ ርካሽ የልወደድ ባይነት የተንፀባረቀበት ሆኖ አግኝተነዋል ።

አሁንም ታሪኩ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚደረገውን ጥረት እያደነቅን ነገር ግን ምስረታውንና እድገቱን ለመዘከር የደፈርነውን ያክል በአሳዛኝና ኃላፊነት በጐደለው መልኩም እንዲፈርስና እንዲወድም መደረጉንም ለመግለፅ ድፍረቱ ያስፈልገናል እያልን የህውሃትን ቡራኬ ለማግኘት ሲባል ብቻ ይህንን ታላቅ ዓላማና ስራ ወስዶ ህውሃት ጫማ ስር ማዝረክረኩን አጥብቀን እየተቃወምን ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የቀድሞውን የኢትዮጵያ አየር ኃይል አባላት ያላማከረና ያልወከለ ተግባር በመሆኑ አጥብቀን እናውግዛለን ።

በሰሜን አሜሪካና በተቀረው ዓለም የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ህብረት

The post መነሻውን ከህውሃት ጉያ ውስጥ ያደረገው የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር ኃይል ታሪክ መፅሃፍና አነጋጋሪው ክህደት appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>