የተከበራችሁ እናቶቼና አባቶቼ፤ እህቶቼና ወንድሞቼ እንዲሁም ልጆቼ የምትሆኑ ወጣቶች!! አገራችን የምትገኝበትን አስጨናቂ ሁኔታ ሁላችንም እንረዳለን። የህወሓት/ኢሕአዴግ ፋሽስቶች ቡድን እየገረፈ፣ እያሰረና እየገደለ በካርዳችሁ መርጣችሁ የምርጫ ድግሴን ካላሞቃችሁልኝ እያለ ነው። እንኳንስ ዛሬ ታዛቢ በሌለበት፤ ታዛቢ እያለም እንኳን ወያኔ የሕዝብን ድምጽ በትክክል ቆጥሮ አያውቅም። ወያኔ ለህዝብ ድምጽ ምንም ደንታ የሌለው የኋላቀር ወሮበሎች ቡድን ነው::
ለስንት አስርት ዓመታት ለወያኔ ባርነት እንገብራለን? ለሀያ አስምስት ዓመታት ተገዛን፣ ተገደልን፣ ተቀጠቀጥን፣ ታሰርን፣ ተሰቃየን፣ ልጆቻችን በአገራቸው ተስፋ ቆርጠው ሲሰደዱ በበረሀ ንዳድ አለቁ፤ በባህር ሰጥመው ቀሩ፤ በባዕዳን አረመኔዎች እንደከብት ታረዱ፤ ቤንዚን ተርከፍክፎባቸው ተቃጠሉ። ሀይማኖታችን ተዋረደ፤ ባህላችን ረከሰ፤ ታሪካችን ተናቀ። በልማት ስም ወልደን ከከበድንበት ተፈናቀልን፤ አገራችን አደገች እያለ ሕዝብ በኑሮ ውድነት ተሰቃየ። በልቶ ማደር ብርቅ ነው። እንደሙጫ የሚያጣብቀንን ማህበረሰባዊ ትስስር በስልጣን ለመቆየትና ህብረተሰቡን ለመዝረፍ ሲል ሆን ብሎ እያፈራረሰው ነው:: ይኽ ሁሉ አይበቃንምን? ይኸ ሁሉ አይመረንምን?
ወላጆቼ፣ እህት ወንድሞቼ!ውርደት ይብቃን። የተረገጥንና የተገደልን አንሶን ፍጹም ማንንም ሊያሞኝ በማይችል የለበጣ ምርጫ ወደን የተረገጥን፤ ፈልገን የተገዛን ለማስመሰል ወያኔ የሚያደርገውን ሩጫ እናክሽፈው:: ከፊታችን ያለውን ምርጫ ባለመሳተፍ ምሬታችንን እንግለጽ።
ዛሬ በግሌ እና በአርበኞች ግንቦት 7፡ የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ስም ጥሪዬን አቀርባለሁ። በዚህ ምርጫ አትሳተፉ። የምርጫ ካርዳችሁን ቀዳችሁ ጣሉት። እናምርር። ካላመረርን ለውጥ ሊመጣ አይችልም። ይልቅስ ለማይቀረው የመጨረሻው ትግል ራሳችንን እናዘጋጅ::
አርበኞች ግንቦት 7፣ ከትግራይ፣ ከኦሮሞ፣ ከአፋር፣ ከኦጋዴን፣ ከጋምቤላ፣ ከቤሻንጉል ድርጅቶች ጋር ትብብር በመፍጠር የአገር አድን ኃይል በመገንባት ላይ ነው። እኛ ልጆችህ በብሔርም ሆነ በሀይማኖት አንከፋፈልም። ከትግራይ እስከ ኦጋዴን፤ ከአፋር እስከ ጋምቤላ ሁሉንም የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ያካተተ ስብስብ ፈጥረን በኅብረት አገዛዙን እየታገልን ነው። ይህ ትግል ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ ትግል ነው። የትግሉም ባለቤት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሙሉ ነው። ክርስቲያን ሙስሊም፤ ወንድ ሴት፤ ወጣት አረጋዊ ሳንል፤ በብሔርም ሆና በቋንቋ ሳንከፋፈል ሁላችንም ይህን አስከፊ ሥርዓት በቃህ እንበለው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! ይህንን የውሸት ምርጫ ባለመሳተፍ ለለውጥ ያለህን ዝግጁነት አሳይ! ደግሜ እለዋለሁ – የምርጫ ካርድህን ቅደድ!!!
የጦርና የፓሊስ ሠራዊት አባላት ሆይ!
እናንተ የሕዝብ አካላት ናችሁ። በወገኖቻችሁ ላይ አትተኩሱ። ይልቁንስ አፈሙዛችሁን አገራችንን ለውርደት በዳረገውና በሙስና በተጨማለቀው ዘራፊው የህወሓት አገዛዝ ላይ አዙሩት። ታሪካችሁን ከምታበላሹ፤ ታሪክ ሥሩ። ለራሳችሁ፣ ለቤተሰቦቻችሁ፣ ለልጆቻችሁ እና ለሕዝብ የሚጠቅም አገርና መንግሥት እንዲኖረን የእናንተ የግልም ሆነ የጋራ ተነሳሽነት ወሳኝ ነው። ወያኔ ህዝቡን የሚዘርፈው በእናንተ ትከሻ ላይ ቆሞ እንደሆነ ላንዳፍታም አትርሱት:: እንደመላው ህብረተሰብ እናንተም በነጻነትና በኩራት የምትኖሩበት ሀገር እንደምትሹ አልጠራጠርም:: ስለዚህም ይህን የህወሓት የውሸት ምርጫ ተቃወሙ። ዛሬውኑ ነፃነትና ፍትህ ከጠማው ወገናችሁ ጎን ቁሙ።
የኢትዮጵያ ወጣቶች፤ ትግላችን እስከ ነፃነት ድረስ ይቀጥላል። ነፃነታችንን በእርግጠኝነት በትግላችን እንቀዳጃለን። የምትወዷት፣ የምትኮሩባት አገር – ኢትዮጵያ – ትኖረናለች። ለዚህ ግን ዛሬ ተደራጅተን፣ ፀንተን መታገል የሁላችንም ኃላፊነት ነው። ዛሬ ሁላችንም በፍላጎትና በመንፈስ የተገናኘን ነንና ሁሉም በያለበት ትግሉን ያጧጡፍ። ውጤቱ ቀድሞ በታወቀው በዚህ ምርጫ አለመሳተፍ ለትግሉ ያለንን ቁርጠኝነት ማሳያ ነውና ለውሸት ምርጫ ያለን የመረረ ተቃውሞ በምርጫው ባለመሳተፍ እናሳይ።
ነፃ እንወጣለን!
የኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነቱ ባለቤት ይሆናል! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
The post “የምርጫውን ካርድ ቀዳችሁ ጣሉት” – ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ appeared first on Zehabesha Amharic.