ከወረቀቱ አናት ላይ እንዲህ ተጽፏል፡፡‹‹ለመምረጥ በሚፈልጉት ፓርቲ ምልክት ፊት ለፊት የ ‹ኤክስ› ምልክት ያድርጉ፡፡››በወረቀቱላይ የተደረደሩ ፓርቲዎችን ስምና ምልክታቸውን በቀስታ ቃኘ፡፡በመጀመሪያው ረድፍ አመልካች ጣት፣ሁለት ጣት ፣አምስት ጣት ….በሌላኛውረድፍ ፈረስ፣ንብ፣አበባ …አየ፡፡
አገጩን ተደግፎ ፈገግ አለ፡፡ፊት ለፊት በሚተያዩት ምልክቶች መካከል ሳይቀር ፍጥጫያለ መሰለው፡፡አመልካቹ ጣት ሰጋሩን ፈረስ ቀጭን ትዕዛዝ ለመስጠት የተቀሰረ አይነት ነው፡፡ሁለት እግሮቹ አየር ላይ ሁለት እግሮቹምድር ላይ ያለው ፈረስ ደግሞ እንጃልህ እያለ እየጎፈላ ነው፡፡ ሁለቱ ጣቶች ንቧን ይዘው ሊያልዘምዟት የቋመጡ እንደሆኑ ያሳብቅባቸዋል፡፡ንቧ በሚጠጋ ጣት ላይ ነዝናዥ እሾኋን ለመቀብቀብ እንደ ቆረጠች አይነት ተነፋፍታለች፡፡አምስቱ ጣቶች አበባዋን ለመቀንጠስ የሆነ አጋጣሚ ብቻ የሚፈልጉ አይነት ናቸው፡፡የአበባዋ መዝመም በጣቶቹ ውስጥ ላለመግባት እንደመሸሽአይነት ሆነበት፡፡
‹‹ወንድሜ ቶሎ ምረጥና ቦታ ልቀቅ እንጂ ብዙ መራጮች እኮ እየጠበቁ ነው፡፡››የሚል ድምጽ በሚስጢር ድምጽ መስጫዋ ጠባብ ክፍል የጨርቅ ግድግዳ አልፎ ተሰማው፡፡ከያዘው የሃሳብ መዋለል ራሱን አነቃና እስኪርቢቶውንአቀባበለ፡፡
‹‹ማንን ልምረጥ?›› ለራሱ አንሾካሾከ፡፡እናቱ ትዝ አሉት፡፡የብዙ አማራጮች ንግስትየተለዩ ፍልስፍናዎች ግምጃ ቤት የሆኑት እናቱ ያወሩት መሰለው፡፡
‹‹እኔ በበኩሌ አባ ዮሴፍን ብትመርጣቸው ደስ ይለኛል፡፡››
‹ማናቸው አባ ዮሴፍ›
‹‹እኚህ ከዳቦ ቤቱ ጎን ባለው ቤት ውስጥ የሚኖሩት ሰውዬ ናቸዋ፡፡››
‹‹እንዴት ነው የትምህርት ደረጃቸው?››
‹‹መቸም ከአባዱላ አያንሱም››
‹‹ከህዝብ ጋር ለመጮህ ዝግጁ ናቸው?››
‹‹ሚሰማቸው ከተገኘ!››
‹‹ለምንድነው እሳቸውን እንድመርጥ የፈለግሽው?››
‹‹እንጃ እንዴው ሳያቸው አንጀቴን ይበሉኛል፡፡ጡሮታ ከወጡ በኃላ እንቅልፍ ያላቸውምአሉ፡፡››
‹‹እና ፓርላማ እንዲገቡ የምመርጣቸው እንዲንቀለፉ ነው?››
‹‹መቸም ከዚህ የተለየ ሲያደርግ ያየነው የፓርላማ አባል የለም፡፡››
አባዮሴፍን የማይመርጥበት ምክንያት ምልክታቸውን ሳላልወደደው ነው፡፡የአባ ዮሴፍየምርጫ ምልክት ሰባት ቁጥር ነው፡፡የመንግስት ደጋፊዎች ለምን ሰባት ቁጥርን ተጠቀምክ ሲሏቸው ‹‹ደደቢት በረሃ የገቡትን የመጀመሪያሰባት ታጋዮች ለማሰብ ነው ይላሉ፡፡የመንግስት ጠላቶችን በሚያገኙ ጊዜ ታሪኩን ይቀይሩታል ‹የጀግኖች ስብስብ የሆነውን ግንቦት7ን› ለማስታወስ ነው ብለው ይሸውዳሉ፡፡እንደ እማየ ያሉትን ከቤተመንግስት ይልቅ የቤተ ክርስቲየን ጉዳይ የሚመስጣቸውን ሰዎች ሲያገኙ ደግሞ‹ ወር በገባ በሰባት የሚውሉት ስላሶች ከጎኔ ናቸውለማለት ነው›› ብለው አንጀት ይበላሉ፡፡
እሱ ግን ሰባት ያለበት ነገር በጤና ተጠናቆ ስለማያውቅ አልራራላቸውም፡፡ማስረጃአቅርብ ቢባል 67ን ይጠቅሳል- ወጣት እንደ ስጦ አስፓልት የሸፈነበትንዓመት፡፡77ን ያነሳል- ርሃብ እንደ ቄጠማ ትውልድ የረመረመበት አመትን፡፡87ንያስታውሳል- አጎቱ ከነ መፈክሩ ስድስት ኪሎ በር ላይ የተደፋበትን፡፡97ን ይጠቅሳል – እሱና ወዳጆቹ ደዴሳ የከረሙበትን፡፡ዘንድሮደግሞ—-እንጃ እንግዲህ፡፡ብቻ ላይመርጣቸው ምሏል፡፡
አሁንም ወረቀቱ ላይ እንዳቀረቀረ ነው፡፡እስኪርቢቶውን በጣቶቹ መሃል ያሽከረክራል፡፡የምርጫአስተባባሪው ድምጽ በድጋሚ አባነነው፡፡
‹‹ኧረ ወንድሜ ፈጠን በልና ጨርስ፡፡ብዙ ሰው እኮ አንተን ነው የሚጠብቅ፡፡››
‹‹እሺ ትንሽ ታገሰኝ…››መልሶ የምርጫ ምልክቶችን ይመረምር ገባ፡፡
‹‹ማንን ልምረጥ ?›› የእናቱ ድምጽ በድጋሚ መጣበት፡፡
‹‹ኢህአዴግን ብትመርጥ ይሻላል፡፡››
‹አብደሻል?››
‹‹ባብድ በምን እድሌ ! ዘንድሮ እብድ እና ሰካራም ብቻ አይደል የልቡን እንዲናገርየተፈቀደለት›
‹‹ለምንድነው ኢህአዴግን የምመርጠው…?››
‹‹መረጥከውም አልመረጥከውም ጎረምሳው መንግስት ምርጫውን ማሸነፉ አይቀርም፡፡አንተባትመርጠው አንዳች ነገር አይጎድልበትም፡፡እንደሚባለው በየምርጫ ጣቢያው ስውር ካሜራ ካለው ደግሞ ይሄ ውሳኔህ ኮንደሚኒየም አልባ እና ምልምል ሽብርተኛ ያደርግሃል፡፡ለበለጠጦስ እራስን ከማመቻቸት ‹ደስ ይበላችሁ ያው መረጥኳችሁ ብሎ ማለፍ ይሻላል፡፡እነሱ እቴ ከስልጣን ወንበር ጋር አብረው ተሰፍተውእንኳን ህዝብ ቸሩ መድሃኒያለም ሰቅስቆ የሚያነሳቸውም አይመስሉም፡፡››
‹‹እማዬ ምርጫ ጣቢያ ውስጥ ካሜራ የለም፡፡››
‹‹አትሞኝ ልጄ፡፡በሁሉም ቦታ የስለላ መሳሪያ አላቸው ፡፡ሌላው ይቅር በስልክ ምትነጋገረውንሁሉ ጠልፈው ያዳምጣሉ፡፡ይሄን ያልኩት ካለ ማስረጃ አይደለም፡፡ባለፈው እንጀራ እየጋገርኩ ከማስረክበው ነጋዴ ጋር በስልክ እያወራሁነበር፡፡100 እንጀራ በ3 ብር ሂሳብ ስንት ይሆናል የሚለውን ለማስላት ያ እንከፍ ነጋዴ ግማሽ ሰዓት ፈጀበት፡፡በመሃል ሲያዳምጠንየነበረው ሰላይ ተናደደ መሰል ከየት ገባ ሳንለው በዝምታው መሃል ጥልቅ ብሎ ‹‹አንት ደነዝ ማባዛት ሳትችል ነውንዴ ብር የምትቆጥር›› ብሎ ልብሱ እንዳይቀርአድርጎ ሞለ ጨው፡፡››
ኢህአዴግን እንዳይመርጥ የወሰነበትን ምክንያት ብዙ ነው፡፡በዚህ ሰው ጭንቅላት ውስጥኢህአዴግ የሚለው ቃል ከታላላቅ ስድቦች ጋር ይመሳሰልበታል፡፡በአንድ ወቅት አንድ ጓደኛው ከስድቦች ሁሉ ትልቁ ‹ባለጌ› የሚለውነው ብሎት ነበር፡፡እንደ ጓደኛው አነጋገር ባለጌ የሚለው ቃል ውስጥ የማይወድቅ መጥፎ ድርጊት የለም፡፡ሌብነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ሰካራምነት‹ባለጌነት› ነው፡፡ነውረኝነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ሆዳምነት፣ጨካኝነት ፣አይረቤነት ባለጌነት ነው፡፡ታሪክ አዋራጅነት፣ትውልድ ሻጭነት፣ህልምአምካኝነት ‹ባለጌነት› ነው፡፡ከብዙ አመታት በኃላ ባለጌ የሚለውን ስድብ የሚበልጥ ስድብ እንደተፈጠረ ይሄ ሰው ያምናል፡፡ያም ስም‹ኢህአዴግ› የሚለው ቃል ነው፡፡
ኢህአዴግን ለመምረጥ የማይፈልገው ለዚሁ ነው፡፡ቢሆንም እናቱ ያሉትን ስጋት መርሳትአይቻልም፡፡ካቀረቀረበት ቀና ብሎ ዙሪያውን ቀኘ ከጠባቧ የድምጽ መስጃ ጣሪያ ላይ ካሜራ መኖር አለመኖሩን አረጋገጠ፡፡ካሜራ የለም፡፡ስለሆነምኢህአዴግን ባለመመረጥ ውሳኔው ጸንቶ ወደ ሌሎቹ ምልክቶች አቀረቀረ፡፡
የስኪርቢቶውን ክዳን እያኘከ በዝምታ ቆየ፡፡የቱን ፓርቲ እንደሚመርጥ ግራ ገባው፡፡የእናቱድምጽ ዳግም ተመለሰ፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ህዝቦች መጽናኛ ፓርቲን ምረጥ፡፡በምርጫ ቅስቀሳ ጊዜ ስልጣን ከያዝንየመጀመሪው ስራችን የቀድሞ ባለ ስልጣናትን ልብሳቸውን አስውቆ አርባ መግረፍ ነው ሲሉ ሰምቻለሁ፡፡››
‹‹እነሱን አልመርጣቸውም…››
‹‹ለምን?››
‹‹ ሬድዋን ሁሴንን ማን ራቁቱን ያያል፡፡ለብሶም ይዘገንነኛል፡፡››
‹‹እሺ የኢትዮጵያ ህዝቦች ምኞት ህብረትን ምረጥ፡፡የሀገሪቱ ችግር የጓድ መንግስቱአለመኖር ስለሆነ እሳቸው እንዲመለሱ እናደርጋለን ሲሉ ሰምቻቸዋለሁ፡፡››
‹‹እነሱንም አልመርጣቸውም፡፡››
‹‹ምን አጠፉ?››
‹‹መንግስቱ ሃ/ማሪያም እኮ አሁንም ስልጣን ላይ አለ፡፡ትንሽ ቁመትና ሞኝነት ጨመረእንጂ ››
‹‹ምን ደህና ደህና ሰዎችን ለቃቅሞ እስር ቤት ከትቶብን አኮ ነው ለምርጫ የተቸገርነው፡፡የዘንድሮውምርጫ እኮ መካሄድ የነበረበት ቃሊቲና ዝዋይ ነበር፡፡ባዶ የዕጣ ጥቅሎችን በትሪ ላይ እያንጓለሉ ‹‹በሉ አንዱን ምረጡ›› አይነትጨዋታ ሆነብን እኮ፡፡ለምን የሰገሌ ህዝቦች ነጻ አውጪ ፓርቲን አትመርጥም…››
‹‹ደግሞ እሱ የትኛው ፓርቲ ነው?››
‹‹ይሄ ካሸነፍኩ የሰገሌ ህዝቦችን ከመላ ሃገሪቱ እገነጥላለሁ ያለው ነዋ፡፡››
‹‹እሱን ታዲያ በቦክስ መገንጠል እንጂ የምናባቱ ድምጽ መስጠት ነው፡፡እስቲ ወንድየሆነ ይገነጠላታል፡፡ከሚስቱ የተኮራረፈ ሁሉ መኝታ ቤቴን ይዤ እገነጠላለሁ ሊል ምንም አልቀረውም እኮ፡፡ ሌሎች ነፍስ ያላቸው ፓርቲዎችየሉም?››
የእናቱ መልስ አይጠፋውም -አሉ፡፡ግን ቢያሸንፉም አያሸንፉም፡፡ እንቅልፋሙን ፓርላማእንቅልፍ የሚነሱ ጥሩ ምሁራን ነበሩ፡፡የተናገሩት አድማጭን ሚያሳድግ የሚሰነዝሩት ተመልካችን የሚያነቃ ጎበዝ ሊቆች ነበሩ፡፡ህዝብበጅምላ እንዳልመከነ የሚያሳዩ ናሙናዎች አሉ፡፡ሁለት አይነት ሰዎች አሉ፡፡አንደኞቹ ከሚበልጣቸው ሊቆች ጋር እየዋሉ እራሳቸውን ለመስተካከል የሚጥሩ፡፡ሁለተኞቹ የሚበልጣቸውን ሊቅአሰድደው ‹እኔ ነኝ የቀረኋችሁ ሊቅ !›የሚሉ፡፡መንግስት ከሁለተኛው ይመደባል፡፡ባለው ሃቅም ልሂቃኑ ከአጠገቡ እንዳይቀመጡ ይተጋል፡፡የምርጫወቅት ይሄ የመንግስት ኢያጎአዊ ጠባይ የሚገለጥበት ነው፡፡ሚሊየን ሰው ልሂቃኑን ይምረጥ ቢሊየን አውጥቶ ድምጻቸውን ይዘርፋል፡፡
‹‹እንደዚህ ከሆነ ለምን እመርጣለሁ!›› አለ በድንገት፡፡
‹‹ድምጼ የማይቆጠር -ሃሳቤ የማይከበር ከሆነ ለምን እመርጣለሁ?››
‹‹ለአለም በሚያሳዩት የሳውቅዮሽ አውጫጭኝ መሃል ለምን እዳክራለሁ?››
‹‹በባሩድና በሚታጠን በድንጋይ በሚከበብ ወር መሃል ስለምን እቆማለሁ?››
የድምጽ መስጫ ወረቀቱን አጣጥፎ በኪሱ ከተተ፡፡እስኪርቢቶውን በደረት ኪሱ ውስጥአስገባ፡፡ከተከለለው ጠባብ የድንኳን ክፍል ሊወጣ ተሰናዳ፡፡
የእናቱ ድምጽ መጣበት
‹‹ሊቢያ ላይ የተሰውት ወጣቶች ገዳዮቻቸውን አሳፍረው ሞሞታቸውን ሰማሁ ልበል?››
‹‹አዎ እማዬ አለም እያወራበት ነው፡፡በሞት አፋፍ ላይ ሆነው ሁሉ ጠላቶቻቸው ይፈልጉትየነበረውን ፍርሃት እና ለቅሶ እና መሰበር ሳያሳዩ ማለፋቸው ብዙ ሰውን አስገርሟል፡፡››
‹‹ አየህ ቶሎ አልተገለጠልንም እንጂ – ጀግንነት ጠላትህ ከሚፈልገው ተቃራኒ ቆሞበማሳየትም ይገለጣል፡፡አቀርቅር በሚባልበት ሰዓት ቀና ማለት ጀግንነት ነው፡፡ዝምበል በተባልክበት ሰዓት መናገር ጀግንነት ነው፡፡ቁምበተባልክበት ሰዓት መራመድ ጀግንነት ነው፡፡እርምህን አውጣ በተባልክበት ሰዓት ተስፋህን ማሳደግ ጀግንነት ነው፡፡ትልቁ ሞት ሳይሞክሩመሞት ነው፡፡››
የድምጽ መስጫ ወረቀቱን ከኪሱ አወጣ፡፡እስኪርቢቶውን ከደረት ኪሱ መዘዘ፡፡በምልክቶቹላይ አይኑን አበረረ፡፡ከሆነ ምልክት ፊት ለፊት ባለው ሳጥን ውስጥ የኤክስ ምልክት አደረገ፡፡
ምልክቱን ከገዥው ፓርቲ ምልክት ፊት ለፊት አለማድረጉን ያውቃል፡፡
ባለጉም ሃሳቦች ከመሰረቷቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፊት ለፊት አለማድረጉን ያውቃል፡፡
ሲረገጡ መሬት ይዘው የሚነሱ ሊሂቃን እና ተስፋዎች የተሰባጠረው ፓርቲ ፊትለፊትምልክት ማድረጉን ብቻ አረጋጧል፡፡የድምጽ ወረቀቱን አጣጥፎ ፈንጠር ብሎ በሚገኘው ሳጥን ውስጥ ጨመረው፡፡በር ላይ ከምርጫ አስተባባሪዎችአንዱ ‹በሰላም ነው ብዙ ጊዜ ፈጀብህ እኮ ….›› ሲል ስሞታ አቀረበበት፡፡
‹‹አንዳንዴ ለመጀገን ጊዜ ይፈጃል›› ብሎት ከምርጫ ጣቢያው ራቀ፡፡
The post መጀገን – በምርጫ ቀን appeared first on Zehabesha Amharic.