ሐራ ዘተዋሕዶ
- የሰንበት ት/ቤቶቹን አንድነት ለማገድ እና አመራሩን ለመበተን መታቀዱን ተቃውመዋል
- በአጥቢያዎች የተቀናጀ ፀረ ሙስና እና ፀረ ኑፋቄ እንቅስቃሴ እንደሚካሔድ ተጠቁሟል
- ‹‹የቤተ ክርስቲያን ተረካቢ እንጂ የበዓላት ማድመቂያ ብቻ ቄጤማ አይደለንም››/ወጣቶቹ/
(ሰንደቅ፤ ፲ኛ ዓመት ቁጥር ፭፻፮፤ ግንቦት ፲፪ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም.)
በምዝበራ ላይ የተሰማሩ አማሳኝ የገዳማት እና የአድባራት ሓላፊዎች የሀብት ምንጭ እንዲመረመር፣ ማስረጃ በቀረበባቸው የተሐድሶ መናፍቃን፣በሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ላይ ርምጃ እንዲወሰድ እንዲኹም ሕገ ቤተ ክርስቲያንን የሚጥሱ አካሔዶች እንዲታረሙና የቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔዎች ተፈጻሚ እንዲኾኑ ያቀረቧቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ እስኪያገኙ ድረስ እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች ገለጹ፡፡
የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ የመክፈቻ ጸሎት ሥነ ሥርዐት በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በተካሔደበት ዕለት፣ ዕቅበተ እምነትንና መልካም አስተዳደርን የተመለከቱ አምስት ዐበይት ጥያቄዎችን ለፓትርያርኩ እና ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ማቅረባቸውን ሰንበት ት/ቤቶቹ አስታውሰዋል፡፡
ከ160 በላይ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ሰንበት ት/ቤቶች የተውጣጡ ሦስት፣ ሦስት ሊቃነ መናብርት የተሳተፉበት የግማሽ ቀን ውይይት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በሀገረ ስብከቱ ሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መሪነት የተካሔደ ሲኾን ጥያቄዎቹ የተስተናገዱበትን ኹኔታ በመገምገም ቀጣይ የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች መቀመጣቸው ተገልጧል፡፡
ከተለመደው በተለየ በአራት ቀናት በተጠናቀቀው የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ ጥያቄዎቻቸው እንደተጠበቀው በአጀንዳ ተይዘው ውሳኔ አለማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው በውይይታቸው የገለጹት ሰንበት ት/ቤቶቹ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱን ቅድስና እና ሀብት የማስጠበቅ ትውልዳዊ ግዴታቸውን አስፈላጊ እና ሕጋዊ ርምጃዎችን በሙሉ በመጠቀም እንደሚቀጥሉበት አስታውቀዋል፡፡
ጥያቄዎቻቸው፣ በቃለ ዐዋዲው እና በሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መተዳደርያ ደንብ አግባብ መቅረባቸውን ሰንበት ት/ቤቶቹ አረጋግጠው÷በመደጋገፍ እና በመተባበር ላይ በተመሠረተው የሀገረ ስብከቱ የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት መርሕ መሠረት በሰባት ክፍላተ ከተማ(ወረዳዎች) የተዋቀረው 69 አባላት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ እና 11 አባላት ያሉት የሀገረ ስብከቱ አመራር ከሚመለከታቸው የቤተ ክህነት፣ የመንግሥት እንዲኹም ኅብረተሰብ አካላት ጋራ እየተገናኘ ተከታትሎ እንዲያስፈጽም መስማማታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ሰንበት ት/ቤቶቹ÷ በቅዱስ ሲኖዶሱ የምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ መክፈቻ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች እና ወጣቱ ባሳየው ፀረ ኑፋቄ እና ፀረ ሙስና መነሣሣት ተደናግጧል ያሉት ‹‹አማሳኝ ቡድን››፣ ከአንዳንድ የሀገረ ስብከቱ እና የቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ጋራ በማበር የሀገረ ስብከቱን የሰንበት ት/ቤቶች አንድነት አመራር አባላት ለማስፈራራት እና ለማሳሰር ሙከራ ማድረጉን ጠቅሰዋል፤ ከዚኽም አልፎ ከመጪው ጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በፊት የሀገረ ስብከቱንና የክፍላተ ከተማ አመራሩን ከሓላፊነቱ ለማገድና በሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት የሚገኘውን ቢሮውን ለማሸግ መታቀዱ የሰንበት ት/ቤቶቹ ከፍተኛ ቁጣ እና ተቃውሞ የተገለጸበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት፣ ሥርዐት እና ትውፊት ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ እና የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያዎችን የማስፈጸም ጥያቄዎቻቸው፣ ደንባዊ ብቻ ሳይኾኑ ፓትርያርኩ በቃለ ምዕዳኖቻቸው ያወጁት የብዙኃኑ አገልጋይ እና ምእመን ሮሮዎች መኾናቸውን ሰንበት ት/ቤቶቹ ይናገራሉ፡፡ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ለማቅረብ የተገደዱትም ‹‹በየደረጃው ያሉ ሓላፊዎችም መፍትሔ ለመስጠት የሚቸገሩ መኾናቸውን በየጊዜው ባደረግናቸው ጥረቶች ያረጋገጥን በመኾኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ሰንበት ት/ቤቶች፣ ‹‹የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደራዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎት የሚረከብ በሥነ ምግባር የታነፀ ብቁ ትውልድ የሚፈሩበት የትምህርት እና የልማት ማእከላት እንጂ የበዓላት ማድመቂያ ቄጤማ ብቻ ተደርገን መታየት የለብንም፤››ያሉት ተወያዮቹ፣ ፓትርያርኩ የብዙኃን አባት እንደመኾናቸው በልጅነታችን ጠርተው ሊያወያዩን ይገባ ነበር በሚል የተሰማቸውን ቅሬታ ገልጸዋል፡፡
እንደሰንበት ት/ቤቶቹ ገለጻ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አጥፊው የሚሾምበት፣ መልካም ሠሪው የሚታገድበት የጎጠኝነትና የጥቅመኝነት አሠራሮች መንሰራፋታቸው ለአገልግሎት ትልቅ ዕንቅፋት ፈጥሮአል፡፡ አኗኗራቸው ከደመወዛቸው የማይመጣጠን ጥቂት የማይባሉ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ከግብር አበሮቻቸው ጋራ በመኾን ቤተ ክርስቲያኗን ሰላም እየነሱ ነው፡፡ በምትኩ በየአጥቢያው ሙስናንና ኑፋቄን የሚያጋልጡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች ‹‹ሽብርተኞች ናቸው፤ መንግሥትን ለመገልበጥ አሲረዋል›› በሚሉ ሰንካላ ምክንያቶች እየተዋከቡ ነው፡፡
የሀብታም ልጆችና የድኻ ልጆች ብለው ከፋፍለው ትምህርተ ሃይማኖት እናስተምራለን የሚሉ ግለሰቦችና ሓላፊዎች እንዲታረሙ የቀረቡት አቤቱታዎች ሰሚ ጆሮ አላገኙም፡፡ ኹኔታው የቤተ ክርስቲያኗን አስተምህሮ የሚፃረሩና ማስረጃ ቀርቦባቸው ጉዳያቸው በእንጥልጥል የተያዘ ግለሰቦች ሳይቀር ስማቸውን ቀይረው በመዋቅሯ ውስጥ በመስረግ በጥፋት ተልእኳቸው ለመግፋት ምቹ ኹኔታ ፈጥሮላቸዋል፡፡ በአጠቃላይ ፓትርያርኩ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን ከቤተ ክርስቲያን በማጥፋት ቅድስናዋን፣ ልዕልናዋንና ክብርዋን እንደሚያስመልሱ በተደጋጋሚ የገለጡ ቢኾንም እስከ አኹን ምንም የታየ ለውጥ ባለመኖሩ ችግሩ እየከፋ አቤቱታዎች ተጠራቅመው አቅጣጫቸውን እንዳይስቱ ምላሽ እንዲሰጣቸው ሰንበት ት/ቤቶቹ ድምፃቸውን አሰምተው ይጠይቃሉ፡፡
‹‹ለቤተ ክርስቲያን ተልእኮ የማይመጥኑና ቅድስናዋን የሚፃረሩ አሳፋሪ ድርጊቶች አንገታችንን እያስደፉና እያሳፈሩን አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን ለማለፍ ሃይማኖታችንም ኾነ ሕሊናችን ስለማይፈቅድ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ ስለሚያስጠይቁንና በታሪክም ስለሚያስወቅሱን ጩኸታችን ሰሚ እስኪያገኝና የሚታረምበት አሠራር እስኪዘረጋ ድረስ አማሳኞችን ከቢሮ ለማስወጣት፣ መናፍቃንን ከዐውደ ምሕረት ለማውረድ በየአጥቢያው መንቀሳቀሳችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፤ በዚኽም የሚመጣውን መሥዋዕትነት እንቀበላለን እንጂ ቤተ ክርስቲያናችንን ለአማሳኞች እና ለተሐድሶ መናፍቃን አሳልፈን አንሰጥም፤›› ይላሉ፡፡
The post የአ/አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ለቅ/ሲኖዶሱ ባቀረቧቸው ጥያቄዎች እንቅስቃሴያቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል appeared first on Zehabesha Amharic.