Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

የደቡብ አፍሪካና የሊቢያው ጉዳይ ነግበ(እ) ኔን አሳደረ

$
0
0

በከበደ ኃይሌ

kbdeh2013@yahoo.com

ethiopiaመነሻ፡ ይህ ርዕሰ-ጉዳይ የሚያተኩረው በልዩ ልዩ ምክንያት ከአገራቸው ወጥተው በሳውዲ አረቢያ ገብተው እየደከሙ ይኖሩ በነበሩት ኢትዮጵያውያን ላይ የግፍ ግድያና ድብደባ ተፈጽሞባቸው የሞቱትን፤ የቆሰሉትንና የድካማቸው ዋጋ ሳይከፈላቸው ከአገሩ የተባረሩትን ወገኖች ለማስታወስ ያበቃንን የደቡብ አፍሪካና የሊቢያው ወንጀል ፍጻሜ ጉዳይ ቢሆንም፤ እገረመንገዱንም ኢትዮጵውያን በየደረሱበት ስለሚጠቁበት ምክንያት፤እንዲሁም ወገኖች በአሁኑ ጊዜ ከአገር ስለሚወጡበት፤ እንዳይወጡ ምንስ መደረግ ይኖርበታል ስለሚለውና፤የዓለም የድሞክራሲ ተምሳሊት በሆነቸው አሜሪካንና አውሮፓ አገሮች ውስጥ  የምንኖረው ዲያስፖራዎች የመኖር ዋስትናችን ቢጓደል ምን ዝግጅት ማድረግ ያስፈልገናል በሚሉት ነጥቦች ላይ ጸሐፊው ከወቅቱ የስደት ዘመን ጋር የተገናኙ የዛሬኛ፤የነገኛና የወደፊተኛ የግል አመለካከቱን ጽፎ ለአንባቢያን ለማጋራት ነው፡፡

የስደቱ ምክንያቶች፡ስለኢሰባዊ ድርጊታቸው ይህን ያህል ከጠቃቀስን በኋላ ወጣት የሆኑ ወገኖች ከአገር እንዳይወጡ በውጭው የሚኖረው ዲያስፖራ ምን የሥራ ድርሻ ወይም ኃላፊነት ይኖረዋል ለሚለው ጥያቅ ከፊል መልስ ሊሆን የሚችለውን ከመጠቆም በፊት ለመውጣት የሚያነሳሳቸውን ነገሮች በቅድሚያ እንመልከት፡፡ በአንደኛ ደረጃ አገር ቤት ያለው ወጣት ትክክለኛው የኑሮ ነጸብራቅ ቢነገራቸውም የውጭ አገር ኑሮ የዘመኑ ቴክኖሎጂ እንደሚያሳየው ቀላል እየመሰለው ምክር የሚቀበል ትውልድ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በተጨማሪም ውጭ ወጥቶ ለመኖር ዕድል ያገኙ ብዙ ወጣቶች በልዩ ልዩ ምክንያት ጠባያቸው ተበላሸቶና ያሰቡት ሳይሳካላቸው ወደ አገር ቤት እንዲሚመለሱ የተደረጉ ስደተኞች በአገር ውስጥ የሚኖሩ ወላጆች በመመልከትና ልጆቻቸው ውጭ ሄደው የማይማሩና በኑሮ የሚጨናነቁ ከሆነ ከአገር እንዲወጡ የሚፈቅዱ ወላጆች ፍላጎት ቢቀንስም ሁሉን አውቃለሁ የሚል ባህሪ ያላቸው ወጣቶች የወላጅ ምክር አይቀበሉም፡፡

ወደ ዲያስፖራው ኃላነት ስንመለስ ደግሞ፤ኢትዮጵያውያን ከአገር  እንዲወጡ የዲያስፖራው ተሳትፎ ምን ያህል ነው ለሚለው ነገር ሲኒሳ ደግሞ በገንዘብ  ክፍያ፤ ስለውጭው አገር የኑሮ ነጸብራቅ እውነቱን ስለማይነገሯቸውና እኛ ከጎናችሁ እንቆማለን እያሉ ሞራል ስለሚሰጧቸው ነው የሚለው ሁለተኛ ደረጃውን ይይዛል ፡፡ በሦስተኛ ደረጃ ዲያስፖራው አገር ቤት ለጊዜውም ሆነ ለረጀም ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ሄዶ ሲዝናና በማይት የወጣቱን ቀልብ  ስለሚሰብ  እኛም እንደነሱ መሆን እንችላለን በማለት ከአገር ካልውጣን ሞቼ እገኛለሁ እያሉ ወላጆችን ስለሚያሰቸግሩ፤ ወላጆችም አጠገባቸው ሆነው ህግ-ወጥ ተግባር ፈጽመው ከሚታሰሩባቸው፤ ሥራ ፈት ሆነው ከሚመለከቷቸው፤ በመጠጥና በአደንዛዥ ዕጽ ነሁልለው ከምናያቸው ከአገር ወጥተው ዕድላቸውን ይሞክሩ በማለት ወደ አውሮፓ የማሸጋገር ጉዞ እናመቻቻለን የሚሉ ደላሎችና ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሚሰጧቸውን ያልተጨበጠ ተስፋ በማመንና በልጆቻቸው ጉዞ ወቅት የሚደርሰውን ስቃይና ሰቆቃ በግምት ውስጥ ባለማስገባት ተበድረውና ተለቅተው የመውጫ ወጪውን በመሸፈን ከአገር አስወጥተው ከአጠገባቸው ለማራቅ ሲሉ ነው፡፡ በአራተኛ ደረጃ በአገር ውስጥ የሥራ ዕድል ባለመኖሩና ቢወጡ በመንገድ ላይ ስለሚደርስባቸው እንግልትና ሕይወት ማጣት በማወቅም ሆነ ባለማወቅ በወኔ ከአገር እየኮበለሉ በየበረሃው የሚንከራተቱ፤ካለክፍያ እየሰሩ የሚገዙና ለሞት የሚዳረጉ ኢትዮጵያውያን ስደተኛ ቁጥር ብዙ እንደሆነ የዓለም ዜና አውታሮች በተደጋጋሚ በጽሁፍ ያወጡት እወጃ ለወጣቶችም ሆኑ ለወላጆች ጆሮ-ጠገብ ጉዳይ ሲሆን ቢሰሙትም ነገሩ እውነት ሳይመስላቸው ጉዳዩን አቅልለው ይመለከቱታል፡፡

በውጭው ዓለም  የኑሮ  ሁኔታ ውስጥ ተፈትነን ያለፍን ሰዎች ወጣት ወገኖቻችን ቢቀበሉትም ባይቀበሉትም በግልጽ በለማስረዳትና እንዲወጡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የምናደርገውን አስተዋጸዎ ብንቀንስም ባንቀንስም፤ሥራና በቂ የወር ደመወዝ የሚከፈለውና በተዘንናና ኑሮ ላይ ያለውም ሰው ቢሆን እንኳን ከኢትዮጵያና ከየትኛውም ክፍለ ዓለማት ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች በመግባት መኖር የማይፈልግ ሰው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ምክንያቱም የጥገኘነት ጥያቄያቸው ከተረጋገጠ በኋላ ካለቅድመ ሁኔታ የመኖሪያ ቪዛ ስለሚሰጡና ሰፊ የሥራ ዕድል ስለሚኖር ሰርተን ዲያስፖራው እንደሚሆን መሆን እንችላለን የሚል ብርቱ እምነት ስለሚያድርባቸው ነው፡፡

ድርጊቱ የተፈጸሙባቸው አገሮች፡በአረብ አገሮች ሰርተው በሚኖሩ ወገኖቻችን ላይ የደረሰው የበደል ድርጊት ትውስታው ከአዕምሮአችን ሳይጠፋ ኢትዮጵያ ስንት ውለታ አድርጋላት ከነጮች የግፍ አገዛዝ ቀንበር ስር ነጻ  የወጣችው ደቡብ አፍሪካ ጊዜው የፈቀደላቸው የዙሉ መሪ ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች ወደ ደቡብ አፍሪካ ገብተው የሚኖሩ ስደተኞች “ለደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ አስተዋጽዎ ለማድረግ ሳይሆን ለመቆያና ወደሌላ አገር ለመሽጋገሪያ፤ የአገሩን  ሰው የሥራ ዕድል  ለመሻማትና  የአገራቸውን የሠራተኛ ክፍያ መጠን  ለማራከስ ነው” ብለው ለሕዘባቸው ይፋ የሆነ ንግግር ባደረጉበት ወቅት የመሪያቸውን ንግግር ጨብጥ ላንድ አፍታ ያላገናዝቡ የአገሬው ቦዘኔ ሕዝብ ሰላማዊ ሰደተኞችን በያሉበት በማሳደድ በግፍ ገድለዋቸዋል፤ሠርተው ያተረፉትን ሃብት  ዘረፈዋል፡፡ ሸሽተው በመደበቅ ሕይወታቸው የተረፉት ደግሞ አንዴ ከአገር ወጥተናል የፈለገው ይሁን ብለው  በሕይወታቸው ቆርጠው ሳይወጡ በግል ቤታቸውና በቤተ-ዓምልኮ ድርጅቶች ውስጥ ተደብቀው በፍርሃት የሚኖሩት ስደተኞች አሁንም እየተሸማቀቁ ቢኖሩም የመኖር ዋስትናቸው የተረጋጋ አይደለም፡፡ ይህ በአፍሪካ ስደተኞች ላይ የደረሰው  አሰቃቂ በደል  በደቡብ አፍሪካ ነጮች ቢፈጸም ኖሮ አይቆጭም ነበር፡፡ ነገር ግን በጥቁር ዜጎቿ መፈጸሙ ግን በተለይ በአፍሪካውያን አዕምሮ ውስጥ የማይጠፋ ትውስታን ጥሏል፡፡

የማውገዝ ዝግጅትና ሂደት፡በውጭና በአገር ውስጥ የሚኖረው ኢትዮጵያዊያንም ድርጊቱን በልዩ ልዩ መንገድ ለማውገዝ እንዲረዳ ማህበረሰቡን በአስቸካይ አሰባስቦ በማገናኘት ኃዘኑን እንዲወጣና ለሞትና ለጉዳት ሰለባ የሆኑ ወገኖችን በጋራ እንዲዘክር በየአካባቢያችን ባሉ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበራቶች አማካይነት ምቹ ሁኔታን በማቻቸታቸው ከተለያዩ ወገኖችና ድርጅቶች ምስጋና ተሰንዝሮላቸዋል።

አስተናባሪዎቹ በአፋጣኝ ባዘጋጁት ስፍራዎች ላይ የተሰባሰቡት በውጭው አገር ነዋሪ የሆኑት ትውልደ-ኢትዮጵያውያን (ዲያስፖራ) እራሱን እስላማዊ መንግስት(ISIS/ዳይሽ) እያለ በሚጠራው አሸባሪ  የስልምና ሃይማኖት ተከታይ ነን ባይ ቡድን ካለጉዙ ሠነድ ተጉዘው በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ቆይታ አድርገው የወደፊት የኑሮ ግባቸውን በማውጠንጠን ላይ እያሉ ያላሰቡት ገጥሟቸው ጥቃት ደርሶባቸው የተገደሉትንና በግፍ የተጨፈጨፉ፤ የተዘረፉና በፍራት ለመኖር የተዳረጉት ወገኖችን በሂሊና ጸሎት ለማስታውስ ቁጥሩ በዛ ያለ ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት በከፍተኛ ስሜት በመሪር ሀዘን፣ በቁጭትና የቁጣ ድባብ  አጥልቶበት ተዘክሮ  ታልፏል።

በረጅሙ ከተዘረጋ አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የኢትዮጵያ ባንዲራ ጀርባ ተደርድረው ሻማ ሲያበሩ ያመሹት በውጭ አገር ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ኃዘን በሰበረው ልብ፣ በቆሰለ ስሜትና አንገታቸውን ቆዝመው ትካዜ የተሞላው ዘለግ ያለ የፅሞና ጊዜ የወሰዱ ሲሆን፤ በዲሞክራሲ ስም “እኔ ባልበሰው ጭሬ ላበላሸው“ የሚል ድብቅ ካባ ለብሰው የሚንቀሳቀሱትን ቡድን ደጋፊ የሆኑ የፖለቲካ  ተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች/አባል ነን ባዮች አንገታቸው እንደከብት በካራ ታረዶ ሕይወታቸውን ላጡትና ለቆሰሉት ወገኖች ስም የተካሄደውን የጸሎት መድረክ በመጠቀም ‘ለዚህ ሁሉ መንግሥት ተጠያቂ ነው’ እያሉ ህሊናን ሞጋች የሆነ የፖለቲካ አጀንዳ አቋማቸውን በንግግር ሲያሰሙ ሌሎችም ይህ የብሄራዌ ጉዳያችን ነው እንጂ የፖለቲካ ጉዳይ ማስተጋቢያ አይደለም በማለት የቅሬታ ስሜታቸውን እየገልጹ ተካፍለውታል።

በዚህም መሰረት የተለያዩ ኢትዮጵያውያን የተሰማቸውን ጥልቅ ሀዘንና ቁጣ እንደ የዕይታቸው ለመግለጽ ዕድል አግኝተዋል። ሰለባዎቹን በመዘከርና ገዳዮቹን በመኮነን ሳይወሰኑ የችግሩን ምንጭ ለመመርመር የሞከሩም ግለሰቦች ነበሩ። በታሪካችን ባልታየ ደረጃ የኢትዮጵያ ልጆች እንዲሰደዱና ክብራችን በማንም የሚደፈር የተናቅን እንድንሆን ያበቃን ነገር ምን ይሆን የሚሉ ጉዳዮችን ያበጠልጥሉ አስተያየቶችም እንደተሰሙ የብዙሃን መድረኮች ዜናውን ለዓለም   ሕዝብ ጆሮ አድርሰዋል፡፡  የበተ-ዓምልኮ አባላትና የደብር አድባራት አለቆችም እንዲሁ በተለይ በሊቢያ ህይወታቸውን ባጡት ወገኖቻችን ላይ ያተኮረ የፍትሀተ ፀሎት እያደረጉ ከዕምነት አኳያ ለተሰዉት ሰማዕታት ክብር ሰጥተውና ፈጣሪ ኢትዮጵያውያንን ያስባል፣ ይህ የስደት ዘመን እንዲያበቃ ጸንተን እንጸልይ የሚሉ ጥሪዎችንም አስተላለፈው መጽናናትን መክረው ሕዝቡን በፀሎት  አሰናብተዋል።

ኢትዮጵያውያን ለምን ይጠቃሉ፤ በተለይ ኢትዮጵያውያን ሰደተኞች በየደረሱበት ለጥቃት ከሚዳረጉበት አንደኛው ምክንያት ኢትዮጵያና ኬንያ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍላጎታቸውን ለማጠናከር ከምዕራብያውያን አገሮች ያልተቆጠበ ዕርዳታ ለማግኘት ሲሉ በሃይማኖት ሳቢያ በግድያ ዓለምን ያተራመሰው አልቃይዳንና አካሉ የሆነውን የእስላማዊ አሸባሪ ኃይል በጋራ ለመዋጋት ከምዕራብ አገሮች ጋር በመተባበር የተቀናጀ የጥቃት ቃልኪዳን ፖሊስ ስለሚያራምዱ ሽፍቶቹም በአጸፋው በአገራቸው ውስጥና በስደት ላይ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን ዜጎቻቸውን ባገኙበት ቦታ እያሳደዱ በመግደል፤ንብረታቸውን በመዝረፍና በማቆሰል ያደረባቸውን የበቀል ስሜታቸውን  ስለሚወጡ ነው፡፡

መፍትሄ፡ወላጅዘመድ አዝማድና የቅርብ ጓደኛ የሆኑ ለመውጣት የሚጋበዙትን ወገኖች ለእነሱ ያለንን ፍቅርና ጊዜ በማፍሰስ አበክሮ ምክር መለገስ እንጂ ሕይወታቸውን እንዴት እንደሚመሩ ምርጫው የእነሱ ነው፡፡ ቢያምኑ ባያምኑበትም የውጭው አገር ኑሩ ምን እንደሚመስል፤በግላችን ላይ የደረሰ ነገር ካለ ካለሃፍረት በማረጋገጫ የተደገፈ ትክክለኛውን የኑሮ ነጸብራቅ በመግለጽ፤ በመንገድ ላይ ስለሚገጥማቸው ያልተጠበቀ ጥቃትና በአጠቃላይ ወጥተው ለሚደርስባቸው ከባድ ችግሮች በምንም መልኩ እንደማይጋሩላቸው አጠንክሮ በመንገር ኃላፊነትን ከእራሳችን ላይ በማውረድ ነው፡፡ሌላው አማራጭ የመርዳት ፍላጎቱና የገንዘብ አቅሙ ካለ ባሉበት ሠርተው መኖር የሚችሉበትን ሁናቴ በመፍጠር ብቻ ነው እንጂ ከአገር አትውጡ ብሎ ማሰገደድ የሚቻል ነገር አይመስልም፡፡

ጦሱ ያሳደረው ተጽዕኖ፡ይህንን ዓላማ በአዕምሯቸው የቋጠሩ ሰዎች አሜሪካ  ክፉኛ ኢኮኖሚ  ውድቀት እንደደረሰባትና በኑሩ ውድነት ሳቢያ የውጭ ሰው ወደ አገሯ እንዲገቡ የመቀነስ ፍላጎቷን ያልተረዱ ሰዎች  በጉዙዋቸው ተሳክቶላቸው ህይወታቸው  ከሞትና ከመታሰር ከተረፈ እግራቸው የረገጠበት የውጭው አገር ለመቆየት ሳይሆን ከአገር የወጡት አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ገብቶ ለመኖር ብቻ ነው የሚልውን  አስተሳሰብ ተግባራዊ ለማድረግ ወደ እነዚህ አገሮች ለመግባት የማያደርጉት ጥረት ባለመኖሩ በስደተኞቹ ላይ የደረሰው አደገኛ ጦስ በውጭና በአገር ቤት በሚኖረውም ወገን፤ዘመድና አዝማድ ላይ ያልታሰበ ጭንቀት/ተጽእኖን አሳድሯል፡፡

የስደተኛ አስተናጋጅ አገሮች ምን ይላሉ

እንደሚታወቀው ከተለያዩ አገሮች በጦርነት የሚፈናቀሉ፤ በኢኮኖሚ፤ በረሃብና በፖለቲካ ጥገኘነት ጠያቂዎችን በብዛት ተቀብለው የሚያስተናግዱ አገሮች በአብዛኛው ዩናትድ ስቴትስና የአውሮፓ አገሮች ነበሩ፡፡ ነገር ግን  የብሄራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ በጦርነትና ዘመኑ ያመጣባቸው የፖለቲካ፤የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሩ ሁኔታ የነበራቸው የኢኮኖሚ፤የፖለቲካና የውትድርና የበላይነት ጥንካሬያቸው ለመዳከም በቅቷል፡፡ እንዲሁም የስደተኞች ብዛት መጨመር፤ ዓለም አቀፋዊ የአሽብሪ ኃይልና ጸረ-ስደተኛ ቡድኖች በየአገሮቻቸው ውስጥ እየተጠናከረ መምጣት እንዲሁም የዓለም ጆዎፖለቲካ አካሄድና አቅጣጫ ስላሳሳባቸው ስደተኞችን ተቀብሎ የማደራጀትና የማኖሩን ጉዳይ በይታሰብበታል ይዘውታል፡፡

አሜሪካና ምዕራብ አገሮች ገብቶ ተግቶ ሰርቶ በማደር፤ በትምህርትና ንብረት በመያዝ መሰረታዊ ፍላጎትን በማሟላት እራስን ለማሻሻል ይቻል የነበረው የቀድሞ መልከ-ብዙ የብልጽግና ሕልማዊ አስተሳሰብ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሁኔታ ተለዋውጦ የአሜሪካና የአውሮፓ ባለሃብቶች ርካሽ የሰው ሓይል ጉልበት እንደልብ ወደሚገኝባቸው አገሮች ሃብታቸውን በማዞርና ዕውቀታቸውን በማፍሰስ ድርጅት ከፍተው  እየተጠቀሙ ለማትረፍ  እያሉ ወደ ደሃ አገሮች ፊታቸውን ስላዞሩ እንኳን ለውጭው መጤ ዜጋ ለእራሳቸውም ህዝብ  የሥራ ዕድል ተጣብቦ ለመንግሥት ድጎማ የተዳረገበት ጌዜ ሆኖባቸዋል፡፡

በዓለም የተንሰራፋው የኢኮኖሚ መንኮታኮት የሚያንሰራራበት ጊዜው አዝጋሚ በመሆኑ በደሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነት ሰፍቶ 1-99% ሆኗል፡፡ይህ ሁኔታ በመፈጠሩ ቀደም ብሎ ገብቶ የሚኖረው ስደተኛውና የአገሩ ተወላጅ ህዝባቸው የመበልጸግ ህልሙ የማይጨበጥ ስለሆነበት  እንኳን ስደተኛው የአገራቸው ሕዝብም  በቀላሉ ያገኝ የነበረውን ገቢ አሁን በጣም ደክሞ ሠርቶ እንዲያገኙ ለመብቃታቸው በአገራቸው የምንኖር ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራም ተቋዳሽ ስለሆንን የዓይን ምስክሮች ለመሆን በቅተናል፡፡ ስለሆነም ለሥራ አጡ  ህዝብ  የመንግስት እራዳታ እየሰጡ ከማስነፍ አዲስ የገበያና የህዝብ አስተዳደር ፖሊስ  ነድፈው በማውጣት ህዝባቸውን ለመርዳትና የሕዝብ ብሦት እንዲያቆም ለማድረግ ታጥቀው ተነስተዋል፡፡

በዚህ ሳቢያ ወደ አሜሪካና አውሮፓ ለመግባት የሚጓጓዘው የውጭ አገር ዜጋ ከአገሩ ሳይወጣ  አገራቸው ገብቶ ሊጨብጥ የሚፈልገውን ህልሙን በአገሩ ማሳካት እንደችልና ስደተኛ አልተቀበሉም ተብለው እንዳይወቀሱ አሜሪካና አውሮፓ የበለጸጉበትን የአሰራር ባህላቸውንና የገንዘብ ማግኛ ስልታቸውን የወዳጅ አገሮቿቸው ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑላቸው በቴክኖሎጂ፤ በሲኒማ፤ በቴሌቪዥን ድራማ፤በሙዚቃና በተለያዩ የምርትና የግልጋሎት  ውጤቶችንና የህዝባቸውን አኗኗር ዘዴዎቿቻውን የሰው ኃይል ርካሽ ወደሆነባቸው አገሮች ስለላኩ ወደ አሜሪካ እየተሰደዱ ማግኘት የሚችሉትን በአገራቸው እንዲያገኙት በማድረጋቸው እበለጽጋለሁ የሚለው ሰርዓተ-ህልም በአሜሪካና በምዕረቡ አገሮች ለማግኘት አይቻልም የሚለው መልዕክታቸው ያልደረሳቸው ግለሰቦች ናቸው ከአገር ለመውጣት በየበረሃውና በየስደተኞች መጠለያ ጣቢያ የሚጉላሉት ብለዋል፡፡ የዓለም የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄ አለኝ የሚሉ የውጭ አገር ዜጎች ካሉም አሳማኝ ጉዳያቸውን በአገራቸው ውስጥ ባሉት ኤምባሲዎቿቸው አማካይነት ከጨረሱ በኋላ ወደ አሜሪካና አውሮፓ አገሮች ለመግባት እንደሚችሉ አመቻችተናል ይላሉ፡፡

ይህን በማድረጋቸው ሞያውና ዕውቀት ያላቸው የአሜሪካና የአውሮፓ አገሮች  ህዝብም ንብረትነቱ የአሜሪካና የምዕራብ አውሮፓ አገር ዜጋ ሥር በሚተዳደሩ ድርጅቶች ውስጥ ሄዶ ለመሥራት ፈቃደኛ ከሆኑና ካመለከቱ ሰርቶ የመኖር ሕልማቸውን እውን ለማድረግ ቅድሚያ እንደሚሰጡዋቸው ይፋ ስላደረጉ ሥራ ፈላጊው ህዝባቸው ተጠቃሚ በማድረግ ላይ በመሆቸው ከአገሩ ወጭ እሄደ የሚሰራው የአሜሪካና የአውሮፓ ዜጋ ቁጥሩ በርካታ እንደሆነ በየጊዜው እየወጣ የሚሰራጨውን አሃዝ በቀላሉ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ በመሆኑም የአሜሪካና የአውሮፓ ባለሃብቶች በውጭው አገር በርካሽ ጉልበት የሚያስመርቱትን የምርት ውጤታቸውን  ወደ አገሮቻቸው ውስጥ እያስገቡ ወገናቸውን ለመጥቀምና ገቢያ እንዲያገኙበት በምርታቸው ላይ የየአገራቸውን ሰም ወይም ሰንደቅዓላማ ምልክቶች እያስለጠፉ የምርት ውጤቶችን በውጭ ቀርቶ በአገራቸው ገበያ ላይ በማዋል መቸርቸር ከጀመሩ ከርማዋል፡፡

ይህን የሥራ ዕቅድ የተጠቀሙ የአሜሪካና የአውሮፓ ባለሃብቶች በኢነቨስትሜንት ስም በአገር ውስጥ ያላቸውን ጥሬ ገንዘብ አሸሹ ተብለው ታክስ አልከፈሉም በሚል ምክንያት ባለሃብቶችንና ከእነሱ ጋር ውለታ የፈጸሙ በውጭ አገር ያሉ ባንኮች ሃብታቸውን ያዞሩ ግልሰቦች ስም ዝርዝር አቅርበዋል፡፡ ይህ የሚጠቁመው የገበያ ፍክክር መሰፋቱንና በጋርዮሽ ኢኮኖሚ መኖር የዘመኑ ቴክኖሎጂ ስለሚያግልጥ ነው፡፡ እንደ አሁኑ ጊዜ ዓለም ሳይሰለጠጥና የዓለም ሕዝብ የትም ብንሄድ አገሬ ነው የሚለው አመለካከት ያደረባቸው ስደተኞች ዓላማ ሳይጠናከር ብቻቸውን ባካበቱት የግልዮሽ ሃብት ጥርቅም ሳቢያ ሃብታም ያሰኛቸው መዋለ-ነዋይ በማህበር የተደራጀው ሰራተኛ የኑሮ ውድነት ለመቋቋም የደመውዝ ዕድገት ጥያቄ ግፊት መሳሪያ ሆኖላቸው መንግስትንና ቀጣሪ ድርጅቶችን ሲያሰገድዱ መንግስታትም በአጻፋው ቀጣሪ ደርጅቶች የሥራ ሰዓታቸውን ለቀነሱባቸው ሠራተኞች የኑሮ ድጎማ በመስጠት፤አሰሪዎች የሰራተኛውን ደመወዝ መጠን እንደ እየአካባቢው የኑሮ ሁናቴ ከፍ እንዲያደርጉና የሕዝቡን ጤንነት ለመንከባከብ የኢንሽራንስ ድርጅቶች ወርሃዊ የክፍያ መጠናቸውን ዝቅ እንዲያደርጉ በመዋዋል ሳይወዱ በግድ ፊታቸውን ወደ  ህዝባቸው ጉዳይ ለማዞር ተገድደዋል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በአገሩ ውስጥ በደረሰው የሥራ አጥነትና ተጧሪው ሕዝቧ ቁጥር መበራከት ከአገራቸው ኢኮኖሚ  አቅም በላይ  ስለሆነባቸው እንጀራ ፈላጊ ስደተኛ መጤው ወደ አገር ውስጥ እየገባ የስራ ዕድሉን እንዳያጣብብ ብሎም የክፍያ መጠኑን እንዳያርክሰው የመጤውን ህጋዊ መግቢያ በር ለማጥበብ ድርጅቶች ካለፈቃድ ሰራተኛ ቀጥረው ቢገኙ ከፈተኛ ቅጣት ጥለዋል፡፡ በተጨማሪም ቀደም ሲል በአገር ውስጥ ገብተው የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ለሚኖሩት ስደተኞች፤ለአቅመ ዓዳም ላልለደረሱ ልጆች፤ኢንቨስትሜንት ለማድረግ ለሚፈልጉ ከበርቴዎችና ልዩ ሞያ አለኝ ለሚሉ ስደተኞች ብቻ ፈቃድ እንስጣለን ብለው የውጭ ሰው ወደ ምድረ-አሚሪካና አውሮፓ አገሮች እንዳይገቡ አዲስ የእምግሬሽን ሕግ አውጥተው በሥራ ላይ ለማዋል የሚጥሩና ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች አሉ፡፡ ፀረ-ስደጸኛ/አገር ወዳዱ ህዝባቸውም በበኩሉ በሳውዲና በደቡብ አፍሪካ አገሮች ውስጥ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ ዓይነት አይብዛ እንጂ የመኖሪያና የንግድ ቤታቸውን በማቃጠል አገራችን ውስጥ ያላችሁ ስደተኞች ውጡልን፤ ለመምጣት የምትፈልጉም አትምጡብን ለማለት ቅሪታቸውን ለመግለጽ ደክሞ አዳሪ ስደተኛ ላይ አልፎ አልፎ ህገወጥ ድርጊቶች በመፈጽም ተቃውሟቸውን በየመልኩ እያሳዩ ስንቱ ስደተኛ በሥራ ላይ እያሉ ተገድለው ህይወታቸውን፤ አካላቸውንና ንብረታቸውን ለማጥታ እንደበቁ ሁላችንም የምናውቀውና ተሰምቶ የታለፈ ታሪክ በመሆኑ አምሻሻቶ በሚሰራባቸው የንግድ ድርጅቶች ውስጥ ተቀጥሮ የሚሰሩ ስደተኞች ቁጥር ጥቂት እንዲሆን ምክንያት ሆኗል፡፡

የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም የደረሰባቸውን የኢኪኖሚ ችግር ለመቋቋም ሰለተቸገሩና ሥራ አጡ ህዝባቸው ቁጥር እየበዛ ስለመጣባቸው ቀድሞ ይገዟቸው ከነበሩና በኢኮኖሚ ካላደጉ አገሮች ወደ አገራች በጦርነት የሚፈናቀሉትን የተሻለ ኑሮ ፍለጋ በስደተኛነት ወደ አገራቸው ለመግባት በጀልባ የሚያጓጓዙትን ስደተኞች ተቀብሎ ለማስተናገድ ኮታው ስለሞላና በሰርጎ ገብ አሸባሪዎች ጸጥታ መደፍረስ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየለወጠና ወንጀሉ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ለመቆጣጣር ከአቅማቸው በላይ እንደሚሆን ከወዲሁ ስለተገነዘቡ የሰው ንግድ ዝውርውር ምንጩን ማድረቅ ብቸኛ አማራጭ ነው የሚለውን አቋም ይዘው ስደተኞች ከሚወጡባቸው አገሮች ጋር በመተባበር መመሪያ አርቅቀው በሥራ ላይ ለማዋል የተባበሩት መንግሥታት ደርጅትን አባላት ሙሉ ድጋፍ በመጠየቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

መድረሻ፡በውጭው ዓለም በጥገኝነት የምንኖረው ዲያስፖራ የመኖር ዋስትናችን ባላታወቀ ምክንያት ተጓድሎ ውጡልኝ ብንባል ምን ማድረግ ይኖርብናል ለሚለው አርቆ የማሰብ ጥያቄ መልስ ይሆናል ተብሎ በግምት ውስጥ ልናስገባ የሚገቡ የቅድመ-ዝግጅት ጉዳዮች ቢኖሩ የሚከተሉትን ይመስላል፡፡ በተግባር እንደታየው ከሆነ አሜሪካና አውሮፓ ተሰድደን የምንኖረው ሙሉ ጤና ካለንና አኗኗሩን ካወቅንበት ፍላጎታችንን ለማሟላት ችግር ስለማይገጥመን፤አይሆንንም ትተን ይሆናልን በማሰቀደም አንድም ቀጥ ብሎ በመሥራትና በቁጠባ እየኖርን ገንዘብ መቋጠር፤ አሊያም ቀጥ ብለን በመማር ዕውቀት በመገብየት የመጣንበትን ዓላማችንን አሳክተን በመዘጋጀት ሁናቴዎች አስተገድደውን እስከምንወጣ ድረስ መቆየት እንችላለን፡፡

ከችግር ነጻ የሆነ ምንም ነገር ባይኖርም፤ ከሚያጋጥሙ የኑሮ ሁኔታዎች አኳያ ሲታይ ከአገር ወጥቶ መኖሩ ብቻ ብዙ ችግሮች እንዳሉት በተሞክሮ ከሞላ ጎደል ለማረጋገጥ ችለናል፡፡በመሆኑም በየምክንያቱ ክፍፍሉንና ሽኩቻውን ትተን በተናጥልም ሆነ በጋራ ትከሻ ለተከሻ ገጥመን ካልቆምንና ኃላፊነታችንን በተገቢው መንገድ ካላተወጣን በቀር ችግሮች አፍጥጠው ሲመጡ ወዲያው ልንወጣው የማንችለው ጉዳይ እንደሚሆን የዓለም ኢኮኖሚው ሁናቴ ፍንጭ እየፈነጠቀ  በመሆኑ ወገኖቻችን በጥቁር አፍረካውን በግፍ ተገድለውና ቆስለው ማየታችን የሰው አገር ምን ጊዜም የሰው አገር መሆኑን  በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ይኖሩ በነበሩ ኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው በደል ነግ()በኔ ሁኔታን በዲያስፖራው አንደበት አሳድሮ ለማለፍ ምክንያት እንደሆነ የተገነዘብ እንኖራለን፡፡ የየትኛውም አገር ስደተኛ ወደ አሜሪካ ለመኖር ቆርጦ የመጣው የትምህርትና የኢኮኖሚ ዕድል ለማግኘት ስለሆነ፤ እኛም ከእነኝህ ዕድሎች ውስጥ አንዱን መርጠንና ዓላማ አድርገን ካልተንቀሳቀስን በቀር ተሰድደንና ተቸግረን እየኖርን ነው የሚል ምክንያት እየሰጡ በሊቢያ፤በሳውዲ አረቢያና በደቡብ አፍርቃ ለጊዜው መኖር እንደማያዋጣ ከወዲሁ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ ድርጊት ይመስላል፡፡

ጸሐፊው ነጻ ጸሐፊና መጽሐፍትን አሳትሞ አስነብቧል፡፡

 

 

 

 

 

 

The post የደቡብ አፍሪካና የሊቢያው ጉዳይ ነግበ(እ) ኔን አሳደረ appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>