– ግርማ ካሳ
የሚቀጥለው ሳምንት ምርጫ ነው። ከምርጫው የሚጠበቅ ለዉጥ ባይኖርም መድረክ እና ሰማያዊ ( የአንድነት ሰዎች በብዛት በምርጫው እንቅስቃሴ ለማድረግ ስለገቡ) በጠበበው የፖለቲካ ምህዳር ዉስጥም ሆነ ሕዝቡን ለማንቀሳቀስ ጥረት እያደረጉ ነው። በተለይም መድረክ በኦሮሚያና በትግራይ ብዙ ድጋፍ እያገኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ።
መድረክን እና ሰማያዊ ወክለው ለፓርላማ ከሚወዳደሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን መካከል አንድ ሴት አለች። የዪኒቨርሲቲ ምሩቅ ናት። ሕወሃትን ከመሰረቱት መካከል። ሟቹ መለስ ዜናዊን መተኮስ ያስተማርቸው እርሷ እንደነበረች ይነገራል። ኢትዮጱያን የምትወድ፣ ህዝቧን የምትወድ ሴት።
ከባድመ ጦርነት በኋላ ህወሃት ሲከፋፈል፣ “አሰብ ለኢትዮጵያ ይገባታል” በሚል ከነ ስዬ አብርሃ ጋር በመሆን የመለስ ዜናዊ ተጻራሪ ሆነች። መለስ ዜናዊ የኦህደድና የብአዴኖችንን ድጋፍ ይዞ አሸናፊ ሆኖ ወጣ። ይች ሴትም ከሃላፊነቷ ተገፍታ ወጣች። ከጅምሩ ከመለስ ዜናዊ ጋር ሆና በስልጣን መቆይት ትችል ነበር። ከዚያም በኋላ ደግሞ አባይ ጸሃዬ እንዳደረገው ይቅርታ ጠይቃ ከመለስ ዜናዊ መታረቅ ትችል ነበር። ለሆዷ የቆመች ባለመሆኗ፣ ኢንቴግሪቲ ያላት በመሆኗ፣ ላመነችበት ነገር ጸናች። የሕዝብ ብሶት የወለደው ሕወሃት፣ ሕዝብን እና አገርን ከመጥቀም ይልቅ፣ ዳግማዊ ደርግ፣ እንደዉም ከደርግ የባሰ፣ አገርን የሚሸጥ መሆኑን በማወቋ፣ የሕወሃት ተቃዋሚ ሆነች። ከሌሎች ጋር በመሆን አረናን መሰረተች።
በ2002 ምርጫ በአድዋ አረና/መድረክን ወክላ ከመለስ ዜናዊ ጋር ተወዳደረች። “እንዴት ብትደፍሪኝ ነው” ብሎ መለስ ዜናዊ ፣በአድዋ፣ ጥይት መተኮስ ያስተማረችውን ታጋይ፣ እንድትደበደብ አደረገ። ሴት ናት፣ ሆኖም ሴትና አረግዊያንን መደብደብ ልማዳቸው የሆኑ የሕወሃት ጨካኝ ካድሬዎች በመልስ ትእዛዝ ቢደበድቧትም፣ እርሷ ግን አልተበግረችም። ብዙ ሕዝብ ደገፋት። መለስ ዜናው ግን ድምጽ ሰርቆ፣ ኮሮጆ ገልብጦ አሸነፍኩ አለ።
ይች ሴት አረጋሽ አዳነ ትባላለች። “ብዙዎች ደርግን ለመጣል ሕይወታቸውን የሰዉት ለመብት፣ ለሕግ የበለያነት፣ ለአገር አንድነት ነበር። ሆኖም በብዙዎች ደም የደርግ ስርዓት ቢወድቅም፣ ከሕወሃት ጥቂቶች ግን ድሉን ሃይጃክ አድርገዉታል” የምትለዋ አረጋሽ፣ የሕወሃት ስርዓት ተቀይሮ ለዉጥ እንዲመጣ መድረክ ወክላ በመቀሌ ትወዳደራለች።
ትግል ዉጣ ዉረድ አለው። ትግል መዉደቅ መነሳት አለው። ተስፋ የማትቆርጥ፣ ሕይወቷን ለትግሉ አሳልፋ የሰጠች፣ ለሕግ የበላይነት ለፍትህ፣ ለነጻነት፣ ለእኩልበት የቆመችዋን፣ አረጋሽ አዳነችን እንምረጥ !!!!! ሕወሃቶች ከአምስት አመታት በፊት እንዳደረጉት ድምጽ እንዳይሰርቁም፣ ድምጹ እስኪቆጠር ድረስ፣ ሕዝቡ በየምርጫ ጣቢያ ቁጭ ብሎ በመጠበቅ ራሱ ማስቆጠር አለበት። 3፣ 4 አጋዚ፣ ፌዴራልና ካድሬ ፣ ሺሆችን አስፈራርተው የሕዝብ ድምጽ እንዲሰርቁ ሊፈቅድላቸው አይገባም።
The post አረጋሽ አዳነ – ኢንቴግሪቲ ያላት ተወዳዳሪ appeared first on Zehabesha Amharic.