በአሜሪካ ዋሺንግተን ዲሲ ከተማ እና አካባቢዋ ያሉ አብያተ ክርስቲያንናት እንዲሁም የተለያዩ የሲቪል ድርጅቶች በቅርቡ በየመን፥ በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያዊያንን ለመዘከር እሁድ እለት በዚህ በዋሺንግተን ዲሲ ከተማ የመታሰቢያ ዝግጅቶችን አካሄዱ።
ነዋሪነታቸው በዋሺንግተን ዲሲ እና በአካባቢዋ በርካታ ኢትዮጵያዊን በታደሙበት በዚህ ዝግጅት፥ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ሟች ኢትዮጵያዊያንን አስመልክቶ ያስተላለፉት የሀዘን መልክት ተነቧል። ልዪ የጸሎትና የሻማ ማብራት ስነስርዓት በተከናወነበት በዚሁ ዝግጅት፥ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፥ ከኢትዮጲያ የሙስሊም እምነት ተወካዮች፥ ከመካነ-እየሱስ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን፥ እንዲሁም ከአለምአቀፍ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የተወከሉ የሀይማኖት አባቶች የሃዘን መግለጫ መልክት ማስተላለፋቸውን ከስፍራው የደረስን መረጃ አመልክቷል ።
ለግማሽ ቀን ያህል በተከናወነው በዚሁ የመታሰቢያ ዝግጅት ወቅት ከዋልድባ ገዳም ማህበር ፤ ከዲሲ ሜትሮ ግብረ-ሀይል እንዲሁም ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በሊቢያ በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያዊንን በማስመልከት የተሰማቸውን ሀዘን እንደገለጹ ታዉቋል።
በእለቱም ለሟች ቤተሰቦች ድጋፍ የሚውል የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ተካሂዶ ከ ፬ ሺህ ዶላር በላይ መሰብሰቡ ታውቋል።
በቅርቡ በሊቢያ፥ የመንና፥ ደቡብ አፍሪካ የተገደሉ ኢትዮጵያዊያንን በማስመልከት ነዋሪነታቸው በዚሁ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶችና የተለያዩ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ዝግጅቶችን ሲያከናውኑ መቆየታቸው ይታወሳል።
Source:: Ethsat
The post በሊቢያ በግፍ ለተገደሉ ኢትዮጵያዉያን የፀሎትና የሻማ ማብራት ስነስርዓት ተካሄደ appeared first on Zehabesha Amharic.