Quantcast
Channel: Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

ምርጫ ለይስሙላ –አክሎግ ቢራራ (ዶር)

$
0
0

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

electionበቅርቡ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን የዓለምን ሕዝብ በሚዘገንን ሁኔታ የቀሰቀሰው፤ ያስለቀሰውና ያስቆጣው የኢትዮጵያዊያን ክርስቲያኖች በሊቢያ በሚገኙ የአይሲስ ሽብርተኞች መታረድና በጥይት መርገፍ፤ ወደ አውሮፓ ሲጓዙ በጀልባ መሞት፤ በደቡብ አፍሪካ በሰላም ሲኖሩ በቤንዚን ተቃጥለው መሞት፤ በየመን የርስ በርስ ጦርነት በሳውዶዎች አየር ኃይል ተባራሪ ጥይት መሞት ወዘተ ብቻ አይደለም። በአወንታዊውም፤ የግብፅ መንግሥት ለሞት አደጋ የተዳረጉ ወገኖቻችን ከአደጋ ማትረፉ ሌላው ያልተጠበቀና የሚያበረታታ ዜና ነው። ኢትዮጵያዊያን በያሉበት ጎሳና ኃይማኖት፤ ሃብትና ሞያ፤ ጾታና እድሜ ሳይለዩ በሰብእነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው ተባብረው ድምጻቸውን ማሰማታቸውም የሚያበረታታ ክስተት ነው። አሁንም ተባብረን ከጩኸት ወደ ድርጊት እንድንራመድ አሳስባለሁ።

የኢትዮጵያዊያን የስደት ኑሮ አስከፊ ገፅታ ዲሞክራሳዊ በሆነችው ኢስራኤልም ሲካሄድ ቆይቶ ሰላማዊ ሰልፍና ግጭት አስከትሏል። የኢስራኤል መንግሥት ለሌሎች ኢስራኤላዊያን የሚያደርገውን እንክብካቤና የዜግነት መብት ለኢትዮ-ኢስራኤላዊያንም በማያሻማ ደረጃ መስጠትና ሰብአዊ መብታቸውን ማስከበር አለበት። ኢትዮጵያዊያን ጥቁሮች በመሆናቸው ራሱ ጋብዞና አባብሎ ካመጣ በኋላ ልክ እንደ አፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ ሁለተኛ ዜጋ ሊያደርጋቸው አይገባም። በሃገር ቤትም እንኑር በውጭ ተቃውሟችን በየቦታው ማሰማት ግዴታችን ነው። ይኼን በሚመለከት እኔንና ሌሎችን ተመልካቾች ያስገረመን የኢትዮጵያ ገዢ ፓርቲ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በኢስራኤል የሚገኙ፤ የሃገሪቱ ዜግነት ያላቸውን ትውልዳቸው ኢትዮጵያ፤ ዜግነታቸው ኢስራኤሊ የሆኑ ወገኖቻችን አስመልክቶ ለኢስራኤል መንግሥት ያቅረበው “አቤቱታ” ነው። ለመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችን ያፈነውና ለስደተኛነት ዋና ተጠያቂ የሆነው ገዢው ፓርቲ ከመቸ ወዲህ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሰብአዊ መብት ጠበቃ ሆነ?

ኢትዮጵያዊያን በገፍ ከሃገራቸው የሚሰደዱበት ምክንያቶች ሶስት ናቸው። አንድ፤ ሰብአዊ፤ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ስለታፈኑና መፈናፈኛና አቤቱታ የሚያቀርቡለት፤ ፍትህ የሚሰጥ፤ ከፖለቲካ ቁጥጥር ነጻ የሆነ የሚዳኝና ፍርድ የሚሰጥ ተቋም ስለሌላቸው ነው። ሁለት፤ የተማረ ሆነ ያልተማረ፤ የስራ ልምድ ያለው ሆነ ገና ልምድ የሌለው የስራ እድልና የግል ተቋም ለመመስረት ሁኔታው ጨለማ ስለሆነበት ነው። ሶስት፤ በአንዳንድ ክልሎች የርስ በርስ ግጭት፤ በዜግነት መብት ተማምኖ ለመኖርና ለመስራት አለመቻልና ሌሎች እርጋታ የሌለባቸው ሁኔታዎች እየተስፋፉ በመሄዳቸው ነው። ኢትዮጵያዊያን በገፍ ከሃገር ሲበረግጉ ምን አይነት የኢኮኖሚ መርህ አስበረገጋቸው ብሎ መመራመር አግባብ አለው። ሑሉን አሳታፊ፤ ሕዝብን ማእከል ያደረግና ለሕዝብ አገልጋይ የሆነ የእድገት መርህ ለአብዛኛው ሕዝብ እድል እንደሚከፍት የሌሎች ሃገሮች የእድገት ታሪክ ያስተምረናል።

ዛሬ ወጣት ሴትና ወንድ፤ ገጠሬና ከተሜ፤ መሃንዲስ፤ አውሮፕላን ነጅ፤ ሃኪም፤ መሃንዲስ፤ አስተማሪ፤ ኃብታም፤ ድሃ፤ የተለያዩ የኃይማንት መሪዎችና ተከታዮች፤ ኦሮሞ፤ አማራ፤ ትግሬ፤ ጉራጌ፤ ሶማሌ፤ ወላይታ፤ አኟክ ወዘተ ሳይለዩ በገፍ ይሰደዳሉ። ገዢው ፓርቲ ራሱ “የሰው ነጋዴ ነው”፤ የስራ እድል አለመኖርንና የፖለቲካ ተቃውሞን ችግሮች የሚፈታው በስደት ነው የሚሉ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። ከአራት መቶ በላይ ፈቃድ ተሰጥቷቸው ወገኖቻቸውን ለትርፍ የሚያስተናግዱ የሰው ነጋዴዎች (Human Traffickers) አሉ። ፈቃዱን የሰጠው መንግሥት መሆኑ ሊካድ አይችልም። ሊያቆመውም የሚችል መንግሥት ነው። አግባብ ያለው ጥያቄ ይኼን እንደ ዓባይ ወንዝ ጎርፍ የሆነ የሰው አስበርጋጊ ሁኔታ ምን አይነት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ስርዓት ፈጠረው? የሚለው ነው። “የሃገር አንበሳ” የሆነው አገዛዝ ለዚህ ግዙፍ መበርገግ (Exodus) መልስ የለውም። የኢትዮጵያ ችግሮች ሊቀረፉ የሚችሉት በሁሉም የፖለቲካ፤ የማህበረሰብና የኃይማኖት ተከታዮች ተባባሪነትና ተሳታፊነት ብቻ ነው። መበርገጉን ያመጡት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይደሉም። እርጋታ እንዳይኖር ያደረጉት “በሕገ መንግሥቱ መሰረት እንወዳደር” የሚሉት፤ ወይንም በእስር ቤት የታጎሩት፤ ወይንም ከሃገር የተሰደዱት ኢትዮጵያዊያን አይደሉም። ተቃዋሚው ኃይል የሚታገለው ለፍትህ፤ ለእኩልነት፤ አግባብ ላለው የእድል ክፍተት፤ ለዲሞክራሳዊ አገዛዝና ለሕግ የበላይነት ነው።

ነጻ፤ ፍትሃዊ፤ ክፍትና አግባብ ያለው ምርጫ አብሮና ተባብሮ ብሄራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያስችል ነበር። የዚህ ትንተና ዋና መከራከሪያ ነጥብ ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት እንደሆነው አሁንም መንግሥትን በሕዝብ ድምጽ የመለወጥ እድሉ አይሳካም የሚል ነው። ምክንያቱም፤ ህወሓት/ኢህአዴግ እውነተኛ የሆነ፤ ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ ምህዳር ከልክሏል። ለሕዝብ አገልጋይና ጠበቃ የሆኑ የመገናኛ ብዙሃንንና የማህበረሰብ ድርጅቶችን አውድሟል። አግባብ ያላቸው የአገርና የውጭ ታዛቢዎች የሚሳተፉበት ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ አልፈቀደም። የአውሮፓ የጋራ ማህበር በምርጫው አልሳተፍም ያለበት ዋና ምክንያት ገዢው ፓርቲ በተከታታይ ያሳየው ማጭበርበርና አፈና የሚደገም መሆኑን ስላመነበት ነው። ገዢው ፓርቲ በተደጋጋሚ ያሳየው ልምድ፤ ምንም አፈና ለሌለበት የፖለቲካ ውድድርና የመንግሥት ለውጥ ተገዢ እንደማይሆን ነው። ይኼን ያልኩበትን ምክንያቶች ባጭሩ ላስቀምጥ።

በ1995 ዓም የጸደቀው ሕገ መንግሥት መግቢያ ዜግነትን መሰረት ያደረገ፤ ለመላው ሕዝብ ተጠሪነትና ሃላፊነት ያለው ሁኖ አልተቀረፀም። አገልጋይነቱ ለጎሳ ልሂቃንና ለአንድ ፓርቲ ስብስብ በሚሆን ብልሃት የተዋቀረ ነው። መግቢያውና አንቀፅ ስምንት “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሄረሰቦች፤ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች” ነን ይላል። የትግራይ፤ የኦሮሞ፤ የጉራጌ፤ የአማራ ወዘተ ሰፊ ሕዝብ ቀጥታ የሆነ “ሉዓላዊ ሥልጣን” ያለው ኃይል ነው የሚል፤ ወይንም ሕዝብ የሥልጣን መነሻና መድረሻ መሆኑን ህጋዊ መልክ ለመስጠት ነው። ሕዝብ የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት ለመሆን አልቻለም። ቢሆን ኑሮ ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ሰብአዊ መብቶች ይከበራሉ፤ ቀጥተኛ የሆነ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተሳትፎና ውድድር ይኖራል። ሕገ መንግሥቱ ያጠናከረው የአንድ ፓርቲን ፍፁም የሆነ ተከታታይነትና የጎሳ ልሂቃንን የበላይነት መሆኑን በጥቂት ምሳሌዎች ለማሳየት ይቻላል። አንቀጽ አስር (i) “ሰብዓዊ መብቶችና ነጻነቶች ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ የማይሰጡና የማይገፈፉ ናቸው” ይላል። በስራ ሲተረጎም፤ ማንኛውም ግለሰብ ወይንም ስብስብ መብቱን ተጠቅሞ ገዢውን ፓርቲ ለመተቸት፤ አማራጮችን ለማቅረብና ሰላማዊ ሰልፎችን ለማካሄድ መብቶቹ የተከበሩ ናቸው ማለት ነው። ይኼ በኢትዮጵያ አይታሰብም። Washington Post Editorial Comment, “In Ethiopia, a Chilling Message,” እንዲህ ሲል ደምድሟል። “Over the past decade, the Ethiopian government, which controls the country’s main media outlets, has displayed varying degrees of appetite for free political discourse” and mentions the 2005 contested election at which Ethiopians were massacred and that the ruling party annulled when it saw ominous signs of losing. ከአስር ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ የፖለቲካ፤ የኃይማኖትና የማህበረሰብ ሁኔታዎች ተባብሰዋል። የጋዜጠኞችንና የብሎገሮቹን አሰቃቂ ሁኔታ አስመልክቶ የፖስቱ ትችት እንዲህ ይላል። “The Ethiopian government has rejected criticism from Western governments and human rights groups about its handling of the case. It asserts the bloggers are on trial for attempting to sabotage the state.” ገዢው ፓርቲ ለሰብአዊ መብቶችና ለነጻነቶች መገፈፍ የሚሰጠው ምክንያት ተመሳሳይ ነው፤ “አመፀኛ፤ ሽብርተኛ፤ ፀረ-እርጋታ፤ ጸረ-ሰላምና ፀረ ልማት” የሚሉ።

የሰብአዊ ድርጅቶች የሚሉት ገዢው ፓርቲ ከሚለው የተለየ ነው። ለምሳሌ፤ ፍሪደም ሃውስ “ኢትዮጵያ ነጻ ካልሆኑ ሃገሮች መካከል አንዷ ናት” ይላል። The Committee to Protect Journalists (CPJ) በተደጋጋሚ ያወጣው ዘገባ “ኢትዮጵያና ኤርትራ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን ከሚያስሩና ከሚያሳድዱ መንግሥታት መካከል አንደኛና ሁለተኛ” መሆናቸውን አስምሮበታል። Human Rights Watch የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታን ለጎሳና ለፖለቲካ አድልወ፤ ለአፈናና ለሙስና እንደሚጠቀምና በፖሊሲ ደረጃ የኢትዮጵያ ልማት በማህበረሰብ አገልግሎት በዜጎች የኑሮ መሻሻል ያልተመሰረተ መሆኑን በማስረጃ አቅርቧል። The World Economic Forum ኢትዮጵያ በሕግ የበላይነት እንደማትተዳደር፤ የሕጉ አካል የገዢው ፓርቲ መቆጣጠሪይ በትር መሆኑን አመልክቷል “The independence of the judicial system was rated 2.9 out of a possible score of 7 in a recent report by the World Economic Forum.” በእነዚህና በሌሎች መስፈርቶች ሲገመገም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት የሚታወቀው በክህደቷን በስ ብአዊ መብቶች ገፈፋው እንጅ በሃቀኛነቱ፤ በግልፅነቱ፤ በፍትሃዊነቱና በሃላፊነቱ አይደለም።

በሊብያ መስዋእት የሆኑትን ወገኖቻችን በሚመለከት “ከጩኸት ባሻገር” በሚል ርእስ የሰጠሁትን ትችት እንደገና ላቅርብ። የግብጽ መንግሥት የሃገሩ ክርስቲያኖች በሊብያ አንገታቸው እንደ በግ ታርዶ ሲሞቱ ምንም ሳያመናታ በሽብርተኞች ላይ ዘምቷል። በቅርቡም ብዙ ኢትዮጵያዊያንን በጦር አውሮፕላኖች ተደግፎ ከሊቢይ መንጥቆ ከአደጋ አውጥቷቸዋል። እነዚህን ወገኖቻችን ፕሬዝደነት ሲሲ በካይሮ የአውሮፕላን ማረፊያ ሲቀበል ያየ ኢትዮጵያዊ “የእኛስ መንግሥት የት አለ” ብሎ ቢጠይቅና ለግብፅ መንግሥት አክብሮቱን ቢገልፅ አግባብ አለው። የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካይ ነኝ ባዩ ግለሰብ የወገኖቻችን አንገት እንደ በግ ሲቆረጥና በጥይት ተደብድበው ሲሞቱ “ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ገና በማጣራት ላይ ነን” ያለው ትውልድ የማይረሳው ከሃዲነት ነው። አንቀጽ ሰላሳ ሰባት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ “ፍትህ የማግኘት መብት” አለው የሚለው ለፖለቲካ ጥቅም አገልጋይ እንጅ በሃገርም ሆነ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መብት አስከባሪ አይደለም።

ገዢው ፓርቲና ደጋፊዎቹ ቢወዱም ባይወዱም፤ በሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረው አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ የኢትዮጵያ አፍራሽ መሳሪያ ሁኗል። ዛሬ ማንም ሃገር ወዳድ መንግሥት የሚገዛውን ሃገር ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ የበላይነት ትኩረት ሰጥቶ “የመገንጠል መብትን” አይደግፍም። ኢትዮጵያዊያንን ከሚያኮሩ እሴቶች መካከል የኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ፤ ነጻነትና ሉዓላዊነት መከበር አንዱና ዋናው ነው። የእንግሊዙ ጋዤጠኛና ደራሲ ሪቻርድ ዳውደን እንዲህ ሲል አስቀምጦታል። “Ethiopia has one rich asset that much of Sub-Saharan has lost or never developed. It has been a state for a very long time, longer than Britain and most of Europe…Ethiopian connections to the Semitic world go back thousands of years, through migration and trade. Its Coptic Christianity and ceremonies were established in the third Century, AD.” ይኼን የማይገኝና የማይተካ ጥሪት ነው ገዢው ፓርቲ ሆነ ብሎ ያፈረሰውና የሚያፈራርሰው። ዛሬ የሚታየው ክስተት የአዲስ ታሪክ ፈጠራ፤ የጎሳዎች መለያየት፤ የክልሎች አዲስ መሳፍንት አመራርና የወጣቱ ትውልድ በጎሪጥ እየተያዩ መተላለፍ ለሃገሪቱ ህልውናና ዳይቨርስ ለሆነው ሕዝቧ ጠንቅ የፈጠረ መሆኑ ነው። አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝ (አንድ) እንዲህ ይላል። “ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር፤ ብሔረሰብ፤ ሕዝብ የራሱን እድል በራሱ የመወሰን እስከ መገንጠል ያለው መብት በማናቸውም መልክ የተጠበቀ ነው።” ራሱን በራሱ ለመበታተን ፈቅዶ በሕገ መንግሥቱ ያስገባ ገዢ ፓርቲ ህወሓት/ኢህአዴግ ብቻ ነው። ከጎሳ ልሂቃን ውጭ አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኼን አንቀፅ አይቀበልም። ኢትዮጵያዊያን መስዋእት ሲሆኑ፤ የሃገሪቱ ዜጎች በገፍና በአንድ ላይ ያለቀሱትና የጮኹት፤ ገዢውን ፓርቲ የወቀሱትና የተቹት ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፤ ኢትዮጵያዊነትን እንደ ዜግነት መታወቂያና መለያቸው አድርገው ስለመረጡ ነው።

ገዢው ፓርቲ በልማትና በእድገት የሚከተለው መርህ ከፖለቲካው አይለይም።  አንቀጽ አርባ ሶስት (አንድ ሁለትና አራት) እንዲህ ይላል። “የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ በአጠቃላይም ሆነ በኢትዮጵያ ያሉ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦች፤ ሕዝቦች በተናጠል የኑሮ ሁኔታዎችን የማሻሻልና የማያቋርጥ እድገት የማግኘት እድላቸው የተጠበቀ ነው (ንኡስ አንድ)። ዜጎች በብሄራዊ ልማት የመሳተፍ በተለይ አባል የሆኑበትን ማህበረሰብ የሚመለከቱ ፖሊሲዎችና ፕሮጀክቶች ላይ ሃሳባቸውን እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት  አላቸው” (ንኡስ ሁለት)። ጠንካራና ተጠቃሚ የሆኑ የጎሳ ፖለቲካ መሪዎች ያሏቸው ክልሎች የተሻለ እድል ይኖራቸዋል ማለት ነው። እንደ ጋምቤላ፤ አዋሽ ሸለቆ፤ አፋር ወዘተ ያሉት ማን ይሟገትላቸዋል? የተዛባ የክልል ልማት ወይንም የተዛባ ገቢና ሃብት ቢከሰት ማን ይዳኛል፤ ማን ያስተካክላል? የተፈጥሮ ኃብት ባለባቸው፤ ለምሳሌ ለም መሬት፤ ወንዝ፤ መአድን ወዘተ ኋላ ቀር ክልሎች ሕዝብ መብትና ጥቅም ማን ይከራከራል? ንኡስ አራት እንዲህ ይላል። “የልማት እንቅስቃሤ ዋና ዓላማ የዜጎችን እድገትና መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ይሆናል።” ይኼ መርህ በስራ አልተተረጎመም። ለምሳሌ፤ የስራ እድል ከሌለ ገቢ ሊኖር አይችልም። የፍላጎት ምርት እያደገ ካልሄደ የኑሮ ውድነት የማይቀር ነው። ጉቦ፤ ጎሳዊ አድልው፤ ሙስና ተቋማዊ ከሆኑ ሃብት ከሃገር ማሸሽ የማይቀር ነው። ይኼን ሁኔታ ያባባሰው እያንዳንዱ የጎሳ አለቃ ወይንም አዲስ መሳፍንት የሚሰራው ለመላው የሃገሪቱ ሕዝብ አለመሆኑ ጭምር ነው። ሁሉም ለግሉና ለራሱ ቡድን ከሆነ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚያገለግል ኢኮኖሚ አልተመሰረተም ማለት ነው። ለልማት የሚውለው ካፒታል ለግዙፍ ስለላ ፈሰስ ከሆነ፤ ከተሰረቀና ለፖለቲካ ስልጣን ከዋለ ካፒታሉ ባከነ ማለት ነው። “የዜጎች እድገትንና መሰረታዊ ፍላጎቶች” ለማሟላት ቃል የገባና ቆርጦ የተነሳ መንግሥት የጥቂቶች አገልጋይ ሁኗል የምለው ለዚህ ነው።

ሕገ መንግሥቱ ለተዛባ ገቢ፤ ሃብትና እድገት የተቆራኙ የአገዛዝ መርሆዎችን ያስተጋባል። የተዛባውን የሚያስተካክል ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆነ ወይንም  የመንግሥት ሁኖ በሞያው ጥራትና በነጻነት የሚሰራ አካል የለም (The Constitution does not provide an independent oversight to ensure checks and balances in governance). አንቀጽ አምሳ (አንድ) እንዲህ ይላል። “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሳዊ ሪፐብሊክ በፌደራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው።” ልክ እንደ ኮሙኒስት ፓርቲዎች አንዱ ሌላውን የሚደግፍ ማእከላዊ የሆነ የአንድ ፓርቲን የበላይነትና የሚመሩትን ግለሰቦች የሚጠቅም አገዛዝ መሆኑ ነው። ምርጫውን ስንመለከት ሂደቱ ከላይ የቀረቡትን የአንድ ፓርቲ የበላይነት የሚያጠናክር ሁኖ እናገኘዋለን። አንቀጽ አምሳ ስድስት እንዲህ ይላል። “በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይንም ጣምራ ድርጅቶች የፌደራሉን መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል ያደራጃል/ያደራጃሉ/ይመጥጣል/ይመርጣሉ።” ይኼን በበለጠ የሚያጠናክረው አንቀጽ ሰባ ሁለት እንዲህ ይላል። “የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ከፍተኛ የአስፈጻሚነት ሥልጣን የተሰጠው ለጠቅላይ ሚኒስትሩና ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው” ይላል። ስለዚህ፤ ከዲሞክራሳዊ ባህሪው ይበልጥ ህገ መንግሥቱ የሚያደላው ጠንካራ፤ አንድ ወጥ ለሆነ፤ በመንግሥት ባጀት ለተደገፈ ፓርቲ ነው። በአሁኑ ምርጫ ከአርባ በላይ ከሆኑት “ተወዳዳሪ ፓርቲዎች መካከል ተቃዋሚ ሊባሉ የሚችሉት መድረክና ሰማያዊ” ናቸው። አብዛኛዎቹ ለህወሓት/ኢህአዴግ ታማኝ የሆኑ ተቀጥላዎች ወይንም ሕገ መንግሥቱ “ጣምራ ድርጅቶች” ናቸው። ይኼ የሆነበት ፈሊጥ “በምክር ቤቱ አብላጭ መቀመጫ” ለማግኘት ነው። ስለሆነም፤ ህወሓት/ኢህአዴግ አብላጭ መቀመጫ እንዲያገኝ ቀደም ብሎ ታስቦበት በስራ ላይ የዋለ የተለመደ ዘዴ ነው። ይኼ ሲሆን ከላይ የቀረቡትን የፖሊሲና የመዋቅር ችግሮች ለሕዝብ አቅርቦ ለመወያየት አይቻልም ማለት ነው። ምርጫው የሚካሄደው የገዢን ፓርቲ ስልጣን ለማራዘም ነው።

አደጋው ሰላምና እርጋታ እንዲኖር ሲባል ያለውን እንቀበል የሚለው ምክርና ሽምግልናም አብሮ የሚካካሄድ መሆኑ ነው። ፍትሃዊ የሆነ ለውጥ ከሌለ ችግሩ ይባባሳል፤ ወጣቱ ትውልድ ልክ አንበሳ እንዳየ የእንስሳ መንጋ እንደ ከብት እየበረገገ ከሃገሩ ይሰደዳል። “የነቃ ተሳትፎ ማድረግ” ይገባል የሚለው ምክር የሳታቸው ብዙ የፖሊሲ ጥያቄዎች አሉ፤ የኑሮ ውድነት፤ ሙስና፤ ከሃገር የሚሸሺ ሃብት፤ የወጣቱ ትውልድ ተስፋ መቁረጥ፤ የጎሳ ጥላቻ ወዘተ። “አዲስ አበባ ግንቦት 4/2007 መጪው ምርጫ በስኬት እንዲጠናቀቅ ኅብረተሰቡ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ የአገር ሽማግሌዎች ጠየቁ። የአገር ሽማግሌዎቹ ምርጫው ሠላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ በሚጠናቀቅበት ሁኔታ ዙሪያ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተወያይተዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ዜጎች የፈቀዱትን የፖለቲካ ፓርቲ በሠላም መርጠው እንዲገቡ ሽማግሌዎቹ የበኩላቸውን ያደርጋሉ።” ተናጋሪው “የፈቀዱትን የፖለቲካ ፓርቲ በሰላም መርጠው እንዲገቡ” ሲሉ ያልተናገሩት ከተናገሩት ይበልጣል፤ አንድነትና መኢአድ መፈራረሳቸው፤ ብዙ መቶ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች ጠበቃዎች አሁንም አለመፈታታቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በሃገር ቤትና በውጭ ለሚደርሰው የሰብ አዊ መብቶች መገፈፍ ሃላፊነትና ተጠያቂነት እንዳለበት አለማመኑ ወዘተ። “በሕዝብ የተመረጠው አካል ሥልጣኑን እንዲይዝና የተሳካ ምርጫ እንዲሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል። የአገር ሽማግሌዎቹ በፖለቲካ ፓርቲዎች የውይይትና የክርክር መድረኮች ላይ በመገኘት የሠላም ኃሳባቸውን እየገለጹ መሆኑን ነው የተናገሩት።የአገር ሽማግሌዎቹ ከተለያዩ የኃይማኖት ተቋማት፣ የሲቪክ ማኅበራትና ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተውጣጡ መሆናቸውንና ለኅብረተሰቡ ባላቸው ቅርበት ምርጫው በሠላም እንዲጠናቀቅ በማስተማር የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ገልጸዋል።

ከአገር ሽማግሌዎቹ መካከል ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም በአገሪቱ በርካታ ለውጦች እየመጡ መሆኑን በመግለጽ ይህንኑ ለማስቀጠል መጪው ምርጫ በሠላም ሊጠናቀቅ ይገባል ብለዋል።

ወጣቱ ሠላምን በማረጋገጥ የአገሩን ልማት ለማስቀጠል የሚረዳውን ምርጫ በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ ያለውን ሚና ተገንዝቦ በኃላፊነት ሊንቀሳቀስ እንደሚገባም አስገነዝበዋል።” ኢትዮጵያ የአባቶች ምክር እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ። ምክር አቅራቢዎች ለህሊናቸው ብቻ የመገዛት ሃላፊነት አለባቸው። ምክሩ ጠቃሚና ሚዛናዊ የሚሆነው በገዢው ፓርቲ የሚካሄደው የሰብአዊ መብቶች ረገጣ እንዲቆም፤ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ፤ የሰላምና የእርቅ ድርድር በአስቸኳ እንዲካሄድና ሁሉን አሳታፊ የሆነ ብሄራዊ የሆነ የአንድነት መንግሥት ተቋቁሞ እውነተኛ ዲሞክራሳዊ ምርጭ እንዲካሄድ ቢጨመርበት የሕዝብ ተስፋን ይቀሰቅስ ነበር። በጎሳ ይሁን በጥቅም ወይንም ሌላ ምክንያት ምክሩ አድሏዊ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ይኼን ምክር ሲሰማ ለምርጫው ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በሽምግልና ስም ገዢውን ፓርቲ ደግፈው ድምፃቸውን ለሚያሰሙ አባቶችም ያላቸው አክብሮት ዝቅ እንደሚል መገመት አያስቸግርም። ወጣቱ ትውልድ ይኼን ሰምቶ “ነገ ስራ አገኛለሁ፤ ተስፋየ የጠነከረ ይሆናል” የሚል አይመስለኝም። በሌሎች ሃገሮች ዘጠና በመቶ የሚሆነውን የስራ እድል የሚፈጥረው የግል ክፍሉ ነው። በኢትዮጵያ የመቅጠር የበላይነት የያዘው ህወሓት፤ የሚቆጣጠረው መንግሥትና የፈጠራቸው ተቋሞች ናቸው።

ነጻ፤ ፍትሃዊና አግባብ ያለው ምርጫ እንዳይካሄድ ሆነ ተብሎ የሚደረገው ተንኮለኛነት መሠረታዊ ምክንያት አለው።  የግል ጥያቄየ ህወሓት/ኢህ አዴግ ለምን ራሱን ለአደጋና ለውርደት ያጋልጣል? የሚል ነው። የምርጫ ቦርዱን ለፖለቲካ የኳስ ጨዋታው የተጠቀመበት ምክንያት ግልጽ ነው። ህወሓት/ኢህአዴግ የውጭና የውስጥ ተመልካቾችን ለመሸንገል ሲል ያመቻቸውና የፈቀደው ለራሱ አጎብዳጅና ተገዢ ለሆኑ፤ በተለይ፤ በውስጣቸው ገብቶ፤ አባብሎ ወይንም አስፈራርቶ በኢትዮጵያ ሕዝብ ባጀት “ለገዛቸው” ተለጣፊ ቡድኖች፤ ተቀናቃኝ የሆኑትን አፍርሶ ላቋቋማቸው ታማኝ ድርጅቶች፤ ለፖሊሲ ለውጥ ሳይሆን ለወንበር ለተሰለፉትና፤ በአብዛኛው ለብሄር/ብሄረሰብና ሕዝቦች ፓርቲዎችን ተሳትፎ ነው። ማስፈራሪይ ዱላው ተተኪው መንግሥት “ያጠቃሃል፤ ያሳድድሃል፤ ያስርሃል፤ የዱሮ ጠላቶችህን ይመልስብሃል” የሚል የተለመደ ፕሮፓጋንዳ ነው። በሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት ላይ የሚደረገው ማሳደድ፤ መደብደብ ማሰርና “ተራ ወንጀል” ለዚህ ዋቢ ነው። የብሄር ሆኑ የህብረ ብሄር ድርጅቶች–

በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች–የመሳተፍ መብት እንዳላቸው አምናልሁ። በከፊልም ቢሆን፤ ቢያንስ ከገዢው ፓርቲ የሚለዩበትን መሰረታዊ ጉዳይ ለሕዝብ ለማቅረብ እየሞከሩ ነው። በቅርቡ የሚካሄደውን የቴሌቪዢን ውይይት ሳይ ልዩነቶቹ ከባድ መሆናቸውን እገነዘባለሁ። ለምሳሌ፤ አንድ ለአምሥት የሚለው የገዢው ፓርቲ የስለላ መረብ ማንን ለመቆጣጠር እንደተቋቋመ ለውይይት መቅረቡ። ምርጫው ዲሞክራሳዊ ነው አይደለም? የሚል ውይይት መካሄዱ። ይኼ እናዳለ ሁኖ፤ ውይይቱ ሕዝብ የሚፈልገውንና የሚመኘውን የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት አይችልም። በገፍ ለሚሰደዱ ወጣቶች አጥጋቢ እድል ከፋች መልስ አያመጣም። በኑሮ ውድነት ለሚሰቃየው ድሃና መካከለኛ ስርቶ አደር ሕዝብ በቀን ሶስት ምግብ አያቀርብም። ሙስናው እንዲቆምና በገፍ የተዘረርፈው ወደ ሃገር እንዲመለስ አያደርግም።

ፈልጎም ወይንም ተገዶ ሕዝብ ድምፁን ያሰማል። ሆኖም፤ ብሄራዊ ምርጫ አንድ ሶስተኛ፤ ወይንም ከዚያ በላይ በሆነ የሕዝብ ተሳትፎና በማስፈራራት ሊካሄድ አይችልም። አገሪቱ “ሰሜንና ደቡብ” በሚል የምርጫ ሂደት ብትጓዝ ተከታዩ በጣም አደገኛ ነው። ለመምረጥ አልፈልግም የሚለው ሕዝብ መብትስ ምን ሆነ፤ ለምን ታፈነ፤ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። የማይመርጡና በፍርሃት የሚመርጡ ቢኖሩም ህወሓት/ኢህአዴግ “በከፍተኛ የሕዝብ ድምፅ አሸነፍኩ” ለሚለው ስልት ይጠቅመዋል። ምን አልባት በ99.6 በመቶ ከማሸነፍ 90 በመቶ ወይንም ከዚህ በታች ቢያሸንፍ የፖሊሲ ለውጥ የማይታሰብ ነው።

ለዚህ የምርጫ ማጭበርበር ስልት የተካነበት የአደረጃጀት ዘዴ እንዳለው እናውቃለን። አስቀድሞ መገምገምና ታማኝና ታዛዢ የሆኑ ስብስቦችን ማደረጀትና አቅጣጫ ማስያዝ አገዛዙን ለማራዘም የተፈተነ ዘዴ ነው። ብዙ ማስረጃዎች የሚያመለክቱት፤ ህወሓት በውጭም ሆነ በውስጥ፤ በማንኛውም የኢትዮጵያ “ድርጅት ወይንም ስብስብ” ሰርስሮ ገብቷል። በኢትዮጵያ ሕዝብ ባጀት የፖለቲካ ደጋፊዎች በገፍ ሰብስቧል። በተለይ በወጣቶች ዙሪያ። አንድ ለአምስት ማለት ቁጥጥሩ ወደ ቤተሰብ ገብቷል ማለት ነው።፡ከምርጫ ዘጠና ሰባት በኋላ አንድ የዓለም ባንክ ጥናት ያሳየው የምርጫ ዘጠና ሰባት አይነት ጥቃትና ውርደት እንዳይከሰት፤ ህወሓት ሆነ ብሎ እቅድ አውጥቶ ብዙ ሚሊዮን ደጋፊዎችን ለኢህአዴግ አባልነት መልምሏል። በፈቃድ ሳይሆን በማባበል። በራሱ ወጭ ሳይሆን በሃገሪቱ ባጀት። ዛሬ ከክልል አንድ ውጭ የበላይነቱን የሚያካሂደው በክልሉ በተወለዱ፤ ባህሉን፤ ቋንቋውን ወዘተ በሚያውቁ፤ በተለይ ባለፉት ሃያ አምስትና ሰላሳ ዓመታት በተወለዱ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በቅጡ በማያውቁና እንዳያውቁ በተገደዱ ወጣቶች ተባባሪነትና ደሞዝተኛነት ነው።

የታፈነ ምርጫ ሙስናን ያንፀባርቃል

በጎሳዊ አድልዎ፤ በጉቦና በሙስና የተበከለ አገዛዝ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ሊፈቅድ አይችልም። እንዴት ራሱን ለአደጋ ያጋልጣል? የምርጫ ማጭበርበር ሙስና የተለያዩ ገጾች አሉት፤ የገንዘብ፤ የፍርሃት፤ የፖለቲካ፤ የስም ማጥፋትና ሌላ። በማባበል፤ ድጎማ በመስጠት፤ “ይኼን ካደረግህ ይኼን እስጥሃለሁ” በማለት። ለምሳሌ ብድር፤ ማዳበሪያ፤ መሬት፤ ፈቃድና ሌሎች ግብዓቶች በመስጠት አባላት መሰብሰብ የማጭበርበር ገፅታ ነው። (Fraud, deception and manipulation are forms of electoral corruption at a state level). “የመንግሥት ባጀት” ለፖለቲካ የበላይነት ውሏል። ሰርጎ ገብነት፤ ከፓርቲው ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ህብረ ብሄር ድርጅቶችን ማፈራረስ፤ እንዲካሰሱ ማድረግ፤ የግለሰቦችን ስም ማጥፋት፤ ፈቃዳቸውን መከልከል፤ ንብረታቸውን መቀማት ሙስና ነው። በጎጃም ገበሬዎች ላይ እንደሆነው “ምርጫው እስከሚያልቅ ድረስ የመሬት ጥቅም ይዞታ ፈቃዳችሁ ለጊዜው ተከልክሏል” ብሎ የፖለቲካ ውሳኔ ማዳረግ የማይረሳ ጭካኔና የስልጣን ብልግና ነው። በህብረ ብሄር ድርጅቶች ምትክ ጥገኛና ተለጣፊ ድርጅቶችን ፈጥሮ የሕግ እውቅና መስጠት ወዘተ “የሙስና አካል” ነው። እነዚህ አይነቶቹ ጫናዎች የተለመዱ የፖለቲካ የበላይነት መሳሪያዎች ሁነዋል። ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት አገልግለዋል። በዚህ አይነቱ የፖለቲካ ሁኔታ ነጻና ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ብሎ ማመን ራስን ማታለል ነው። የአሜሪካ የውጭ መስሪያ ቤት የፖለቲካ ክፍል ምክትል ሃላፌ ዌንዲ ሸርማን “ነጻ፤ ፍትሃዊ፤ ክፍትና አግባብ ያለው ምርጫ ይካሄዳል፤ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ናት” ብላ የተናገረችውን ሌላው ቀርቶ ብዙ የኢህአዴግ አባላት አይቀበሉትም። የኢትዮጵያን ሕዝብ አይቀበለውም፤ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ አላነጋገረችም። የኢትዮጵያንና የራሷን ሃገር ዘላቂ ጥቅም ጎድታለች።

ከፍተኛ ተስፋ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ሕዝብ የፖለቲካ ብስለት ያለው መሆኑ ነው። የፖለቲካ ጨዋታውን እየሳቀ ያልፈዋል። ማን ለምን እንደሚወዳደር ያውቃል። አንዳንድ ታዛቢዎች በምርጫው መሳተፍ የዲሞክራሲ ቀዳዳ ይከፍታል የሚል አመለካከት ይሰነዝራሉ። ይኼ አመለካከት ቢያንስ ባለፉት ሃያ አራት ዓመታት ሲነገር ቆይቷል። ጥቂት ወንበሮች መያዝ ይቻላል። ፖሊሲ ለመለወጥና ሙስናን ከስሩና ከጭንቅላቱ ነቅሎ ለመቅረፍ አይቻልም። በየትኛውም ዲሞክራሳዊ አገር የፓርላማ ውሳኔዎች የሚደረጉት በድምፅ ብልጫ ነው። ጥቂት ወንበሮች የድምፅ ብልጫ ሊያመጡ አይችሉም። ብቸኛ ተቃዋሚ የፓርላማ አባል ከመጮህ ውጭ ምንም ለማድረግ አይችልም/አትችልም። ችግሩ እንዳለ ለዓምስት አመታት፤ ለአስር አመታት ወዘተ ሊቆይ ይችላል። ገዢው ፓርቲ የሚፈልገው ይኼን ነው። የሰላሙ ትግል ዘዴዎች መቀየር አለባቸው የምለው ለዚህ ነው።

የመሳተፍ መብታቸው እንዳለ ሁኖ እውነተኛ በሆነ መንገድ ለሕዝብ መብቶች፤ ለፍትህና ለዲሞክራሳዊ ለውጥ የቆሙ ፓርቲዎች ይኼን “ምርጫ” ይካሄዳል የሚል የፖለቲካ ኪሳራ የሚያስከትል ፕሮፓጋንዳ መሸመትና መቀበል ያለባቸው አይመስለኝም። አስቀድሞ፤ “አናሸንፍም፤ ሆኖም የመሳተፍ መብታችን እንጠቀማለን” የሚል መልእክት ለሕዝብ ቢቀርብ ይጠቅም ይመሰለኛል።

ከለይ ያቀርብኩት የምከራከርብት ሃሳብ አንድ ነው። ይኼውም የፖለቲካ ለውጥ፤ ማለትም የመንግሥት አመራና የፖሊሲ ለውጥ ካስፈለገ “እምቢ፤ የገዢውን ፓርቲ ተንኮል ከአሁን በኋላ አንቀበልም” ብሎ ሕዝቡን ለመብቱ እንዲነሳ የማድረግ ግዴታ እንደሚታይ ነው። ይኼን ደጋግሜ የማመለክተው የምርጫው ውጤት አስቀድሞ የታወቀ ስለሆነ ነው። ያለፉት አራት ምርጫዎች የሚያሳዩት ልምድ፤ የምርጫው አሸናፊ ሁል ጊዜ ህወሓት/ኢህአዴግ እንደሚሆን ነው። የሚያሸንፍበት ምክንያት የፖለቲካ ለውጥ እንዳይመጣና ያካበተው ጥቅም እንዳይናጋ ጭምር ነው።

ታዲያ ምን ይደረግ?

ቢያንስ፤ ተወዳዳሪዎችን ዓለም የሚያከብራቸው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚቀበላቸው፤ ሊያቀርቧቸው የሚገባቸው ዲሞክራሳዊ ጥያቄዎች አሉ። “የህወሓት ገመና” በሚል፤ ከዚህ በፊት በድህረገጾች የቀረበ  በማስረጃ የተደገፈ ሃተታ የኢትዮጵያዊያን ሕዝብ ሰብአዊ መብቶች ፍፁም በሆነ ደረጃ እንደታፈኑ፤ ይኼ አፈና ለሃገሪቱ ህልውናና ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ህይወት አደጋዎችን እንደፈጠረ፤ የምእራብ ሃገሮች፤ በተለይ አሜሪካና እንግሊዝ ለህወሓት የሚሰጡት ግዙፍ እርዳታ፤ የመረጃና የዲፕሎማሲ ድጋፍ ለአደጋው መጋቢ እንደሆነና መለወጥ እንዳለበት አሳስባለሁ። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመተባበርና በመናበብ በጉዳዩ ሊረባረቡበት ይችላሉ፤ አዳማጭ ይኖራቸዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ የማህበረሰብ ክፍሎች፤ ልሂቃን፤ ለጋስ ድርጅቶችና መንግሥታት ደፍረው ማስተናገድ ያለባቸው አስኳል ጉዳዮች አሉ። ለምሳሌ፤ ሰላምና እርጋታ እየደፈረሰ መሄዱና የእርቅና ሰላም ድርድር አስፈላጊ መሆኑን በግልፅ መናገር፤ ሕዝቡ በኑሮ ውድነት መሰቃየቱ አደገኛ የማህበረሰብ ቀውስ (Social Crisis) እንደሚያስከትል ማሳሰብ፤ የምእራብ ሃገሮች ዘላቂ ጥቅም ዋስትና የሚኖረው ግፍ፤ በደል፤ ሙስና ወዘተ ሲጠፉ መሆኑን ማስረዳት። ወጣቱ ትውልድ በሃገሩ አማራጮች እንዲኖሩት ያልተቆጠበ ግፊትና ድጋፍ መስጠት። ተቃዋሚ ፓርቲዎች እነዚህን በግልፅ የሚታዩ ችግሮች መፍትሄዎች ችላ ካሏቸው አስፈላጊ የሆነውን የዲሞክራሲ ስርዓት ምስረታ ለብዙ አስርት ዓመታት ይገቱታል። የአሁኑን ጨቋኝ አገዛዝ ዲሞክራሳዊ በሆነ አገዛዝ ለመተካት ካልተቻለ ከፍተኛ ቀውስ መፈጠሩ አይቀርም።

አንዳንድ ተመልካቾች የሚሉት፤ ህወሓት የኢትዮጵያ የመፈራረስ አደጋ ከታየው ጠቅልሎ ወደ ምሽጉ ወደ ትግራይ ይገባል፤ የፈለገውን “ታላቋን ትግራይ” ይመሰርታል ነው። እንዲያውም፤ በቤኒ ሻንጉል የሚገኘውን የተሃድሶ ግድብ የሚገድበው ለራሱ ለህወሓት ጥቅም እንጅ ለነዋሪዎቹና ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቁሮ አይደለም የሚሉም አሉ። አንድ፤ ቢሆንስ፤ “ታላቋ ትግራይ” ታላቅ ኢትዮጵያ አትሆንም የሚል ግምት አለኝ። ህወሓት ኢትዮጵያዊያንን አናክሶ በሰላም ለመኖር አይቻልም። ሁለት፤ የትግራይ ሕዝብ አገር ወዳድ ስለሆነ እንዴት ይኼን ውጤት ይቀበላል፤ ራሱ መልሶ አንፈልጋችሁም የሚል ድምፅ አያሰማም ብለን ለመቀበል የምንችልበት ምን መረጃ አለ? መረጃ የለም እላለሁ። የጎንደር ሕዝብ፤ በሌላው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ተደግፎ፤ የተነጠቀውን መሬትና በአዲስ ለፖለቲካ የበላይነት የተመቻቹን ንዑስ ክልሎች ስኬታማ እንዳይሆኑ አድርጎ፤  የታወቀ ድንበሩን እስከ ተከዜ ወንዝ ሳያስመልስና ህወሓት በምስጢር ለሱዳን የሰጠውን መሬት ሳያስመልስ “ለታላቋ” የህወሓት ትግራይ ሰላም የሚሰጥ አይመስለኝም። “የተኛ” የሚመስል ሕዝብ ጉዳቱ እየበዛበት ሲሄድ መነሳቱ የማይቀር ነው። ቢያንስ ለራሱ ህልውና ይታገላል የሚል ግምት አለኝ። የጎንደርም ሆነ የሌላው ሕዝቡ ትእግስት ማለቁን የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶች አሉ። በመከላከያ ኃይሉ ውስጥ ልዩነቶች መነሳታቸው አይቀርም። የኃይማናት አባቶች በቅርቡ ያወጧቸው መግለጫዎችና አደራዎች የኢትዮጵያ የመከላከያ ኃይል መወከል ያለበት አምባገነኑን አገዛዝ መሆን የለበትም የሚል ነው። የሕዝቡን አደራ አክብሮና ተቀብሎ ፊቱን ወደ ራሱ ሕዝብ መብትና ክብር እንዲያዞር አደራ ብለዋል። ትግል በተናጠል ስኬታማ አይሆንም። ኢትዮጵያዊያን ተባብረውና ቆርጠው በአንድ ድምጽ ከተነሱ አዲስ ታሪክ የመስራት ብቃትና አቅም አላቸው።

በውጭም ሆነ በሃገር ቤት የምንኖር አገር ወዳዶች ማጤን ያለብን በግልጽ የሚታዩ ሁለት አደጋዎች አሉ። አንድ የኢትዮጵያ ሉዐላዊነት መበረዙና ሃገሪቱ በየቦታው እየተናጋች መሆኗ፤ ሁለት ገዢው ፓርቲ ሆነ ብሎ የቀረፀው የጎሳ ልዩነት ሊቆም የማይችል የሚመስል የጎሳ ጥላቻ  መፍጠሩ። ቀውስ የማይቀር ነው የሚሉ የሃገር ውስጥ ታዛቢዎች ብዙ ናቸው። እኔ የምከራከረው ሁለቱንም አደጋዎች ለመከላከል መተባበር አስፈላጊ ሁኗል በሚል ነው። ትእቢተኛውና ጠባብ ጎሰኛው ህወሓት አላወቀበትም እንጅ፤ ቀውስ ለማንም አይበጅም። አስከፊ የሆነ የርስ በርስ ጦርነት ሊነሳ ይችላል። የቀረችው ኢትዮጵያ የመከፋፈል እድሏ የተባባሰ እንደሚሆን አስቀድሞ መገመት አስፈላጊ ነው። አንዳንድ ታዛቢዎች የሚሉት በትጥቅ ትግል ለመገንጠል የሚታገል ኃይል ለህወሓት ህልውናና የበላይነት አደገኛ ከሆነና በፖለቲካውና በዲፕሎማሲው የሚያዋጣው ከሆነ የህወሓት አመራር አንቀጽ ሰላሳ ዘጠኝን ተጠቅሞ ኤርትራን እንዳስገነጠለ ሁሉ፤ ሌላ ክልል እንዲገነጠል ቢያደርግ አያስገርምም። ኢትዮጵያን ዘላቂነትና ፍትሃዊነት ወዳለው የእድገት ጎዳና ለማመቻቸት የሚቻለው ለሁሉም አሳታፊ የሆነ በሕግ የበላይነት የተመሰረተ እውነተኛ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ ሲመሰረት ብቻ ነው። ገዢው ፓርቲ በራሱ አቅምና ብርታት ዘላቂና ፍትሃዊ እድገት ለማራመድ አይችልም። እስካሁን የቆየው ተቃዋሚው ኃይልና ሌሎቻችን ተከፋፍለን ደካማና ፈሪ መሆናችንን ስለተረዳውና በውጭና በሃገር ቤት ያለው “ተቃዋሚ” ጥበበኛ አመራር ስለሌለው ነው። ይኼ ሁሉ እናዳይደጋገም ከተፈለገ አፋኙን አገዛዝ የሚተካ፤ ሁሉን የሚያስተናግድ ዲሞክራሳዊ አማራጭ አስፈላጊ ነው። ለዚህ መደራጀትና አብሮ መስራት ወሳኝ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳስቢያለሁ።

የዲሞክራሲ መንግሥት አማራጭ እንዲሁ በምኞት አይገነባም። ሕዝቡ፤ በተለይ ወጣቱ ትውልድ ለራሱ ህይወት መሻሻል ሲል እውቀቱንና አቅሙን ማጎልመስ፤ እንደ እንሰሳ ከመበርገግ ይልቅ ሳይሰለች መታገል፤ ለፍትህ መስዋእት ለመሆን መድፈር፤ አቤቱታውን በተባበር ድምፅ ማሰማት ወዘተ ግዴታው ነው። በሊብያ አንገትን ተቆርጥና በጥይት ተደብድቦ ከመሞት፤ በየመንና በደቡብ አፊሪካ ተሰዶ ከመዋረድ በሃገር ውስጥ ሁኖ ለመብቶች መታገል ዘላቂ ፍትህ ያመጣል። ይኼን ማንም የውጭ ኃይል ሊያደርግልን አይችልም። ከሁሉም በላይ በየደረጃውና በየአካባቢው ድርጅት ማቋቋም፤ አዲስ መሪዎች እንዲወጡ ማበረታታት፤ በሰሰከነ አእምሮ ብልሃት ያለው ብሄራዊ የፖለቲካ አመራር እንዲኖር መጎትጎት፤ አብሮና ተባብሮ የመስራት የፖለቲክና የማህበረሰብ አደረጃጀት ልምድ እንዲስፋፋና ጥልቀት እንዲኖረው ጠንክሮ መስራት፤ ወጣቱ ትውልድ ከህወሓት/ኢህአዴግ የጎሳ ጥላቻ መርዝና መንጋጋ ነጻ እንዲወጣ ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ፤ በውጭ የሚኖረው ስደተኛ አፋኙን መንግሥት እንዳይደግፍ፤ ማንኛውንም ዓይነት እገባ እንዲያደርግ ጥሪ ማድረግና ለጋስ ድርጅቶች፤ መንግሥታትና ኢንቬስተሮች ለሰብአዊ መብቶች መከበር ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጡ ሳይሰለቹ መጎትጎት  ይገኙበታል። ልዩ በሆነ መንገድ መደራጀትና ማደረጀት ተቀዳሚነት አለው። እኛ ካልደፈርንና አብረን ለመስራት ከፍተኛ ጥረት ካላደረግን ማንም መንግሥት አይደግፈንም። እንዲያውም እንደ ተናቅ እንቆያለን። መቃወም ብቻ አማራጭ አይደለም።

ይኼን የተቀነባበረ ትግል ለማካሄድ ለአብዛኛው ሕዝብ ህይወት አለመሻሻል ማነቆ የሆኑ ስርዓት ወለድ ማነቆዎች እንዳሉ መገንዘብና መፍትሄ መፈለግ ተገቢ ነው። የፖለቲካው ምህዳር ፍፁም በሆነ ደረጃ መዘጋቱ፤ የሰብአዊ መብቶች በሚያሰቅቅ ደረጅ መገፈፋቸው ከችግሮቹ መካከል የመጀመሪያውን ደረጃ ይዘዋል። ይኼን ችግር ነጥለን ብናየው (መነጠል ባይቻልም)፤ በሃገር ቤት የተቃዋሚ ፓርቶዎች ድርጅታዊ ህልውና ጠፍቷል። ጥሩው ነገር መሪዎቹና አባላቱ አሉ። አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ይደግፋቸዋል። ሊያንሰራሩ ይችላሉ። በውጭ ያለው ግዙፍ ኃይል በጋራ ራእይና የዓላማ አንድነት ተስማምቶ የተበታተነውን ተቃዋሚ ለማስተባበር ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ ግዴታው ነው። ወገኖቻችን ሲሞቱ ማልቀሱና መቅበሩ ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም። አንዱ በሌላው ማመካኘቱ መቆም አለበት። በሃገርና በውጭ ያለው አለመግባባትና አብሮ ለመስራት አለመድፈር የሕብረተሰቡን አሰቃቂ የኑሮ ሁኔታ እንዳባባሰው ስለምናውቅ ከመወቃቀስ ባህል ወደ መተባበርና መስማማት ባህል እንሸጋገር።

ወደ ተሻሻለ ዲሞክራሳዊ አገዛዝ አማራጭ ሊይወስድ የሚያስችል፤ የተዋሃደም ባይሆን የተባበረ፤ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጭ የሚንቀሳቀሱ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን፤ የማህበረሰብ ክፍሎችንና ግለሰቦችን ያካተተ አማራጭ መስርቶ በእውቀትና በጥበብ የተቀናጀ፤ የማይበገርና የሃገሪቱን የሕዝብ ስርጭት የሚያንፀባርቅ ድርጅትና አመራር መፍጠር የወቅቱ ታሪካዊ ጥያቄና ግዴታ ሁኗል። ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፤ ኢትዮጵያዊያንን እንደ ሕዝብ የምንቀበልና የምናከብር ሁሉ ደፍረንና ተባብረን ከተነሳን የሚያቆመን ኃይል አይኖርም። ለአንድ ለሚያልፍ ህይወት፤ ለሚያልፍ ዝናና ጥቅም ከመረባረብ ይልቅ ተከታታይ ትውልድ ለሚጠቅሰው ቁም ነገር የራሳችን የግል አስተዋፅኦ ብናደርግ ራሳችን አስከብረን ሃገራችንም እናስከብራለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

The post ምርጫ ለይስሙላ – አክሎግ ቢራራ (ዶር) appeared first on Zehabesha Amharic.


Viewing all articles
Browse latest Browse all 15006

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>