በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም መስቀል አደባባይ ህዝቡን ከጠራው ሰልፍ ጋር በተያያዘ በትናንትናው ዕለት ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል ናትናኤል ያለምዘውድ ዛሬ ግንቦት 5/2007 ዓ.ም ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ የተሰማበት ሲሆን ለግንቦት 11/2007 ዓ.ም ለብይን ተቀጥሯል፡፡
በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ ወንጀል ችሎት የቀረበው ናትናኤል ቀደም ብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው የፓርቲው አባላት በተመሳሳይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 490(3) ስር የተመለከተውን በመተላለፍ ሰላማዊ ሰልፍ እንዲረበሽ አድርጓል የሚል ክስ ቀርቦበታል፡፡
በዕለቱ ተከሳሹ ‹‹ከሌሎች ግብረ አበሮቹ ጋር›› በመሆን ወያኔ አሳረደን፣ ኢቲቪ ሌባ፣ መንግስቱ ናና እያሉ በመናገር ፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ሁከት እንዲፈጠር አድርገዋል መባሉ በክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡ አቃቤ ህግ አሉኝ ካላቸው 5 የሰው ምስክሮች መካከል ሁለቱን ያሰማ ሲሆን ቀሪዎቹን የተለየ አያስረዱልኝም በሚል ሳያሰማ ቀርቷል፤ ናትናኤል በበኩሉ ምንም መከላከል አልፈልግም ብሏል፡፡ ምስክሮቹ ተከሳሹ ‹‹ወያኔ አሳረደን፣ እናት ኢትዮጵያ ያስደፈረሽ ይውደም፣ እኛን ከምትደበድብ አይ.ኤስ.አይ.ኤስን ደብድብ…›› በማለት ሰልፉን ረብሹዋል ሲሉ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለግንቦት 11/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በሌላ ዜና ናትናኤል ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት በስፍራው ከተገኙት ጓደኞቹ መካከል ዮናስ መኮነን የተባለ ወጣት ፎቶ አንስተሃል በሚል መታሰሩ ታውቋል፡፡
(ሙሉ የክሱን ይዘት ይመልከቱ)
The post ትናኤል ያለምዘውድ ለብይን ተቀጠረ appeared first on Zehabesha Amharic.