በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
መንግስት ሚያዝያ 14/2007 ዓ.ም ራሱ በጠራው ሰልፍ ላይ ‹‹ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳትና በማስተባበር›› ካሰራቸው ሰዎች መካከል እነ ወይንሸት ሞላ ላይ ክስ መሰረተ፡፡ በፌደራል አቃቤ ህግ ከሳሽነት ክሱ የተመሰረተባቸው አራት የሰማያዊ አባላትና አንዲት ሌላ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ተከሳሾች ዛሬ ግንቦት 4/2007 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ቄራ ምድብ ወንጀል ችሎት ቀርበዋል፡፡
በእነ ወይንሸት ሞላ የክስ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች ወይንሸት ሞላ፣ ዳንኤል ተስፋዬ፣ ኤርሚያስ ጸጋዬ፣ ማስተዋል ፈቃዱ እና ቤተልሄም አካለወርቅ ሲሆኑ፣ የክሱ ይዘትም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ህግ አንቀጽ 32(1)(ሀ) እና 490(3) የተመለከተውን በመተላለፍ መሆኑ በክሱ ላይ ተገልጹዋል፡፡
1ኛ ተከሳሽ መንግስት በጠራው ሰልፍ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃ/ማርያም ሲናገሩ፣ ስድብና ማንቋሸሽ እንደፈጸመችና ሌሎች ተከሳሾችን በማስተባበር ‹‹ናና ናና መንግስቱ ኃ/ማርያም ናና››፣ ‹‹ወያኔ አሳረደን፣ ወያኔ ሌባ›› እያሉ ህዝቡን ያነሳሱ እንደነበር ክሱ ላይ ተጠቅሷል፡፡
ሁሉም ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን እንዲያስጠብቅላቸው የጠየቁ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ባለመቀበል 20 ቀናት ቀጠሮ ሰጥቶባቸዋል፡፡ በዚህም ተከሳሾቹ ለግንቦት 24/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ተሰጥቶባቸዋል፣ ወደ ‹ማረፊያ ቤት› እንዲወርዱም ታዝዟል፡፡
አቃቤ ህግ አሉኝ ያላቸውን የሰው ምስክሮች ያሰማ ሲሆን፣ በምስክሮቹ ቃል ላይ ወጥነት የሌለውና ተደጋጋሚ መደነባበር ተስተውሎባቸዋል፡፡
(የክሱን ሙሉ ይዘትና የቀረቡ ምስክሮችን ዝርዝር ይመልከቱ!)
The post እነ ወይንሸት ዋስትና ተከልክለው ለግንቦት 24 ተቀጠሩ appeared first on Zehabesha Amharic.