ወንድማችን ጆሲ የሰማዕታት ቤተሰቦች ጋር ሀዘን በመድረስ ለቤተሰቦች ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ባሰባሰበው ገንዘብ ሲረዳ ቆይቷል። ከማንም በፊት ለወገን ደራሽነቱን ያስመሰከረው ጆሲ የሱን ፈለግ ተከትለው በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የእርዳታ እጆቻቸውን ሲዘረጉ ቆይተዋል።
አሉን የምንላቸው ከበርቴ የሀገራችን ሚዲያዎች እንኳን መስራት ያልቻሉትን በራሱ ወጪ እያንዳንዱ ቤተሰብ ጋር በሞጓዝ የተቻለው ሲረዳ ቆይቷል ይህ ሳያንስ ትኩረት እንዲያገኙ አስችሏል።
ጆሲ ከአዲስ አበባ ጎንደር ከዛ ትግራይ ከትግራይ ደግሞ ወልቂጤ እየዞረ ያዘኑትን ሲያረጋጋ ሲረዳ የቆየ ብርቅዬ ልጃችን ነው። አሁንም በአዲስ አበባ ሰማዕት ብርሃኑ ጌታነህ ቤተሰቦች ጋር በመሄድ ታሪክ መስራቱን ቀጥሏል።
ከዚህ በታች የምትመለከቱት ፅሁፍ የጆሲ መልዕክት ነው።
የሁለት ልጆቿን አባት ፤የትዳር አጋሯን በሞት ከተጠነጠቀች፤ በሀዘን የተቆራመደችና ባዶ ቤት የታቀፈችን ሴት ማፅናናት በእርግጥ ከባድ ነው፡፡ ዛሬ ሁሉም ነገር ለእርሷና ለሁለት ልጆቿ ጨለማ ነው፡፡ ምክንያቱም የልጆቿን አባት ነውና በአይ ኤስ የግፍ ግድያ ያጣችው፡፡
ባለቤቷ ና እሷ ቋሚ ገቢ የሌላቸውና የግለሰብ ቤት ተከራይተው የሚኖሩ ሲሆን፤እሷ ኑሮአቸውን ለማሸነፍ በተለያየ ጊዜ ወደ አረብ ሀገራት ለስራ ሄዳ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላት ነበር የተመለሰችው፡፡እሷ ውጪ ሀገር በነበረችበት ወቅት ሁለቱን ህፃናት የማሳደግ ኃላፊነት የወደቀው አሁን በሕይወት በሌለው ብርሃኑ ጌታነህ ላይ ነበር፡፡
ብርሃኑ የባለቤቱን፤የሚወዳቸውንና የሚሳሳላቸውን የሁለት ህፃናት ልጆቹን ሕይወት ለመቀየር አስቦ፤ ከግለሰብ ለተከራየው ቤት የሁለት ወር ኪራይ ቅድሚያ ከፍሎ ለባለቤቱ፤ለቤት አከራዮቹና ለቅርብ ወዳጆቹ ድሬድዋ ለስራ እንደሚሄድ ተናግሮ ተሰናብቶ ወጣ ፡፡ ግን ያመራው ወደ ሊቢያ ነበር፡፡ ካሰበው ሳይደርስ፤ህልሙን ሳያሳካ ፍቅራቸውን ያልጠገበውን ሁለት ልጆቹንና ባለቤቱን ጥሎ በሊቢያ በረሃ ውስጥ በአይ ኤስ በግፍ ተሰዋ፡፡
ጆሲ መልቲሚዲያ ሀዘንተኞቹን በቅንነት ለመደገፍ ከተነሱት ያሬድ ሹመቴና መሐመድ ካሳ ጋር በመሆን አዲስ አበባ በተለምዶ አዋሬ ተብሎ በሚጠራውና ብርሃኑ ከግለሰብ ተከራይቶ ከባለቤቱና ከሁለት ህፃናት ልጆቹ ጋር ይኖርበት ወደነበረው ቤት ሄዶ የተሰማውን ሀዘን ገልፆ ፤ ለባለቤቱና ለቅርብ ወዳጆቹ መፅናናትን ተመኝቶ ABC የመኪና ኪራይ በእርዳታ የለገሰውን ብር 40.000(አርባ ሺ ብር) ለባለቤቱ አስረክቧል ፡፡
በአደጋው ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትንና እያደረጉ ያሉትን ግለሰቦችና ድርጅቶችን በመላው ኢትዮጽያውያን በተለይም ቤተሰቦቻቸውን በሞት በተነጠቁ ወገኖች ስም እናመሰግናለን ፡፡በነገራችን ላይ የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉትን ግለሰቦችና ድርጅቶች ስም የምንጠቅሰው ሌሎች ቅን አሳቢዎች አርያነታቸውን እንዲከተሉ በማሰብ እንደሆነ ለመግለፅ እንወዳለን ፡፡
ብርሃኑ ጌታነህ ጥሏቸው የሄደው ህፃናት የ 8 እና የ 4 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ናቸው፡፡ህፃናቱ መማር አለባቸው፡፡ለእዚህ ደግሞ የትምሕርት ቁሳ ቁስ ሊሞላላቸው ይገባል ፡፡ ቋሚ የሆነ መጠለያም ያስፈልጋቸዋል ፡፡ይህ ይሟላላቸው ዘንድ የሁላችንንም ድጋፍ ይሻሉ፡፡
አይ. ኤስ የተባለው ፅንፈኛ ቡድን በኢትዮጽያውያን ወገኖቻችን ላይ ጭካኔ የተሞላበት የግፍ ግድያ ሲፈፅም ዓላማው በልዩነት እንድንጋጭ ፤እርስ በእርስ እንድንናቆር ፤ፍቅራችን እንዲከስምና አንድነታችን እንዲላላ ወጥኖ ቢሆንም እኛ ግን ከልዩነታችን ይልቅ አንድነታችንን አፅንተንና ከመራራቅ ይልቅ ተቀራርበን ሀዘን ከጎዳቸው ወገኖቻችን በተለይም የቤታቸውን ምሶሶ ካጡት ከብርሃኑ ባለቤትና ከሁለቱ ህፃናት ጎን ልንሰለፍ ይገባል፡፡…ይህ የጆሲ መልቲሚዲያ መልዕክት ነው፡፡
ፈጣሪ ሁላችንንም ያፅናናን ፡፡
ጆሲ መልቲሚዲያ
The post “አይሲኤስ ወገኖቻችንን ሲገል እኛን ለማለያየት አስቦ ቢሆንም እኛ ግን አንድ ሆነን እየተረዳዳን ነው” – ጆሲ መልቲሚዲያ appeared first on Zehabesha Amharic.