የአርበኞች ግንቦት 7 በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮረ ጽሁፍ
የህወሓት አገዛዝ ፋሽስታዊ ባህርያት እያደር መረን እያጣ፤ ነውረኛ እየሆነ መጥቷል። በአሳለፍነው ሣምንት ብቻ እንኳን አስነዋሪ ይዘት ያላቸው ሁለት ፋሽስታዊ ክስተቶችን አስተውለናል።
አንዱ በምርመራ ስም በታሳሪዎች ላይ የሚደረገው አሳፋሪ ሰቆቃ ነው። በገላቸው በሚያፌዙና በሚሳለቁ ተቃራኒ ፆታ መርማሪዎች ፊት ለሰዓታት ተመርማሪዎች ራቁታቸውን እንዲሆኑ የሚደረግበት እና እየተፌዘባቸው የሚደበደቡበት ሥርዓት መኖሩ የጉዳቱ ሰለባዎች ይፋ ሲያወጡ እፍረቱ ለመርማሪዎቹ ብቻ ሳይሆን ይህንን ጉድ ተሸክመን ለኖርነው ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ነው። በተለይም ደግሞ እንዲህ ዓይነት ክብረነክ ሰቆቃ በሴቶች ላይ እየተፈፀመ መሆኑን ስንሰማ አገራዊ ውርደቱ ያሸማቅቀናል። እንዲህ ዓይነቶችን በሰው ስቃይና እፍረት የሚዝናኑ ጉዶችን ተሸክመን የምኖር መሆናችን ሁላችንን ያዋርደናል። ይህንን አስነዋሪ “የምርመራ ዘዴ” ያጋለጡት የዞን 9 ብሎገሮች፣ ጋዜጠኞችና ፓለቲከኞች ክብርና ሞገስ የሚገባቸው ጀግኖች ሲሆኑ የተዋረዱት እነሱ ሳይሆኑ እኛ ኢትዮጵያዊያን መሆናችን ሊሰማንና “ውርደት በቃ” ልንል ይገባናል።
ሁለተኛው አሳፋሪ ድርጊት ደግሞ ወገኖቻችንን በግፍ ባረደው አይሲስ በተሰኘው አሸባሪ ድርጅት ላይ የህወሓት አገዛዝ የተለሳለሰ አቋም ወስዷል ብለው ራሱ ህወሓት በጠራው ሰልፍ ላይ ተቃውሞዓቸውን ባሰሙ ወጣቶች ላይ አገዛዙ የወሰደው የኃይል እርምጃና ከዚያም ወዲህ እየተደረገ ያለው ነገር ነው። አገዛዙ ለፕሮፖጋንዳው ይጠቅመኛል ብሎ በጠራው ሰልፍ ወጥተው ተቃውሞዓቸውን የገለፁ ወጣቶች በአሰቃቂ ሁኔታ ተደብድበዋል፤ በጅምላ ወደ እስር ቤቶች ተግዘዋል። የአገዛዙ ካድሬዎች ወገኖቻችንን የፈጀውን አይሲስን በመቃወም ፋንታ የራሱ የህወሓትን ውል አልባ ህግ አክብረው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን ሰማያዊ ፓርቲ፣ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞችን እና አረና ፓርቲን እየወነጀሉ መሆኑ አጅግ አሳፋሪ ነገር ነው። የአይሲስን አረመኔአዊ ድርጊት ከኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የመብት ጥያቄ ጋር ለማገናኘት በህወሓት የደህንነት ቢሮ አማካይነት እንቅስቃሴ መጀመሩ እየተሰማ ነው። ለወጣቱ በብዛት መሰደድ በምክንያትነት የሚያቀርቡት ደላሎችን መሆኑ አላዋቂነት ሳይሆን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ቅራኔው በኢትዮጵያዊያን መካከል እርስ በርስ እንዲሆን ያለመ መሠሪነት ነው። ከዚህም አልፎ የትግራይ ወጣቶችን ነጥሎ በመሰብሰብ “ትምክህተኞች ሊበሉህ ነውና ታጥቀህ ሳይቀድሙህ ቅደም” እያሉ መቀስቀስ በመንግሥት ደረጃ የእርስ በርስ እልቂትን ከማደራጀት ተለይቶ አይታይም። የሥርዓቱ ይሉኝታ ቢስነት የደረሰበት ዝቅጠት ገላጭ ከሆኑ ነገሮች አንዱ “እስከምርጫ መጨረሻ ድረስ ልጆቻችሁን አስረን እናቆይላችሁ” እያሉ ወላጆችን እስከመጠየቅ መድፈራቸው ነው።
ከላይ በአጭሩ የተዘረዘሩት ኩነቶች የሚያረጋግጡት ህወሓት የተማከለ አመራር አጥተው መንገድ የጠፋቸው፤ ሆኖም ግን እጃቸው ውስጥ የገባው ስልጣንና ሀብት ላለማጣት ምንም ነገር ከማድረግ የማይመለሱ አውሬዎች ስብስብ መሆኑ ነው። እንዲህ ዓይነቱን የአውሬዎች ስብስብ የሚገዛው የህግም ሆነ የሥነ-ምግባር ገደብ የለም። ህወሓት እስር በርሳችንን አባልቶ አገራችንንና ሕዝቧን ወደ ማንወጣው አዘቅት ከመክተቱ በፊት ራሱ ህወሓትን ማስወገድ እና በምትኩት ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን መገንባት የዚህ ትውልድ ኃላፊነት ነው። ይህ ካላደረግን አሁን በወህኒ ቤቶች የሚደረገው ዜጎችን ልብስን አስወልቆ የማዋረድ አስነዋሪ ተግባር ነገ በአደባባዮች የማይደረግ ስለመሆኑ ምንም ማረጋገጫ የለንም። ይህ ትውልድ ኃላፊነቱ ካልተወጣ ህግን አክብረው ከአገዛዙ የተለየ ሀሳብ እናራምዳለን የሚሉ ወገኖቻችን በሙሉ አደጋ ውስጥ ናቸው። በህወሓት መሠሪ ተግባራት ሳቢያ በክርስትናና እስልምና እምነት ተከታይ ኢትዮጵያዊያን መካከል ያለው መግባባት እንዲሻክር እየተደረገ ነው። ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም። ይህንን ማስቆም ያለብን እኛ ሁላንችንም ነን። በአደባባይ መደራጀት ሲከለከል በምስጢር መደራጀትን መልመድ የኛ ኃላፊነት ነው። የኢትዮጵያ አርበኞች ድል መታሰቢያ በዓልን ስናከብር ከቀደምቶቻችን ልንወርስ ከሚገቡን እሴቶች አንዱ ለክብራችን ዋጋ መክፈል ያለብን መሆኑን ጭምር ነው። የኢትዮጵያዊያን ክብር በወያኔ ሲዋረድ እያየን ዝምታን ከመረጥን ከዚህም የባሰ እንዲመጣ መፍቀዳችንን እንወቀው።
አርበኞች ግንቦት 7:የአንድነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የዜጎችና የአገር ውርደት ይብቃ! በተባበረ ክንድ ህወሓት ይወገድ፤ በምትኩም ፍትህ፣ ነፃነት፣ ዲሞክራሲና እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለመመሥረት መሠረት እንጣል፤ ይህንን ታላቅ ኃላፊነት ለመወጣት በኅብረት እንነሳ ይላል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!
The post “ዜጎችን በማዋረድ የሚደሰት አገዛዝና ለመዋረድ የፈቀደ ሕዝብ እስካለ ድረስ የቁልቁለቱ ጉዞ መጨረሻ የለውም” – አርበኞች ግንቦት 7 appeared first on Zehabesha Amharic.